Sunday 25 December 2016

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ“አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አንድ)

   Please read in PDF
     የዚህ ጽሁፍ ዋና ጭብጥ፥
1.      ዋናችን ጌታ ኢየሱስን በክርስትና ሕይወታችን ሁሉ ትኩር ብለን እንድንመለከት፤
2.     ዋናችን የሆነውን ጌታ ኢየሱስን ትተን በእርሱ “ሎሌዎች” ላይ ዓይናችንን የተከልን፥ በንስሐ እይታችንን እንድናጠራ፥ ከሰባኪ አድናቂነትና ተከታይነት ወደጸጋ አደላዳዩና ሠጪው ጌታ እንድናተኩር፤
3.     አገልጋዮች የሆንንም፥ “የሚከተሉንን” ምዕመናንና ምዕመናት የተሰጠንን “ስጦታ” ሳይሆን፥ ሰጪውንና ሁሉን አድራጊውን እንዲመለከቱ፥ በሁላችንም ላይ የሚፈርደውንና የሁላችንን ሥራ ለሚያየው ጌታ ሕይወታቸውንና መንገዳቸውን አሳልፈው በማስጨከን እንዲሰጡ በማሰብ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምልከታ ነው፡፡
መንደርደርያ
    ለብዙ ዘመናት ሰይጣን ሰዎች ዋናውን ጌታ እንዳይመለከቱና “ሥጦታውን መመልከት ሠጪውን የመመልከት ያህል ነው” ወደሚል ከንቱ ማታለል ብዙዎችን ሲመራ አይተናል፡፡ በተለይም በዘመናችን ይህ እውነታ ጎልቶና ደምቆ በመካከላችን በሚገባ ይስተዋላል፡፡ ሰዎች ሰባኪ[ሎሌውን] ብቻ መስማትን ልክ እግዚአብሔርን እንደመስማት ሲቆጥሩት፥ ቅዱሱን ወንጌል ከመመርመርና ጌታ ኢየሱስን በትክክል በመመልከት የክርስትና ሕይወት ሩጫቸውን ከመሮጥ ተዘናግተዋል፤ [ይህ በወንጌሉ ፍጹም እውነትነት ላይ የቆሙትንና ለቃሉ ፍጹም በመታመን በማገልገል ያሉትን የጌታ ታማኝና እውነተኛ አገልጋዮችን አይመለከትም]፡፡

Tuesday 20 December 2016

ከመናገር ለሚያልፈው ለሶርያ ልጆች እባካችሁ አልቅሱ!

    ከመናገር ለሚያልፈውና ደም መፍሰሱ ቅጥ ላጣው ለሶርያ ልጆችና ለምድሯ ሁሉ ሰቆቃ እባካችሁ አልቅሱ፣ እዘኑ፣ ራሩ፣ ጹሙና ጸልዩ! 

Friday 16 December 2016

የወዳጅ ሕመም

ደድሯል አካሌ፣ አመርቅዞ ውስጤ ፤
ነፍሴ ተኮራምታ፣ ተራቁታብኝ አቅሌ፤
ያጎረስሁት ያው እጅ፣ ይሸረክተኛል፤

Monday 12 December 2016

ጸሎትና ጾም ለኢትዮጲያ(የመጨረሻ ክፍል)


2.     “እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ መቅበዝበዝን ወድደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፥ በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፡፡ እግዚአብሔርም፦ ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው፡፡ በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ፤” (ኤር.14፥10-12)
     በኤርምያስ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች ወደእግዚአብሔር በፍጹም ንስሐ ከመመለስ ይልቅ በክፋታቸው በመጨከናቸው ምክንት ሊመጣ ያለውን ቅጣት ነቢዩ ይናገራል፡፡ በልባቸው ወደጣዖት አምልኮ አዘንብለውና በእግራቸው ወደዚ እየቸኮሉ ነገር ግን ጾምን ቢጾሙ፣ መሥዋዕትን ቢያቀርቡ እግዚአብሔር በዚህ ፈጽሞ አይረካም፡፡ ኤርምያስ እንዲህ ላለ ሕዝብ ፈጽሞ እንዳይማልድ በተደጋጋሚ ተክልክሏል፤ በክፋቱ የጸና ሕዝብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይተዋል እንጂ ምንም አይነት እርዳታ አይደረግለትም፡፡

Thursday 8 December 2016

ጸሎትና ጾም ለኢትዮጲያ



  ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስለረሃብ እንዲህ “ተቀኝቶ” ነበር፥

Monday 5 December 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና - (የመጨረሻ ክፍል)

2. ሕበረ - ሰበ መስቀሉን ማብዛት፤
    ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀሉ ሞት መልካሙን ያደርጉ ዘንድ አዲስ ማሕበረሰብን ፈጥሯል፡፡ ይህን ማሕበረሰብ ያዋቀረው ደግሞ “… ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቆ ነው (ኤፌ.2፥10 ፤ 16)፡፡ “ሁለታቸው” የተባሉት “በሥጋ አሕዛብ የነበሩት፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባሉትና” (ኤፌ.2፥11)፤ ቤተ እስራኤል ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱም አንዳች የዘርና ቀለም፤ የቋንቋና የነገድ ልዩነት ሳይኖር ነው፡፡
“ … አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል”
(1ቆሮ.12፥13)
እንደተባለ ክርስቶስ ኢየሱስ ልዩነትን ሽሮልናል ብቻ ሳይሆን ፍጹም አንድነትን እንኖርበት ዘንድ ሰጥቶናል፡፡

Monday 28 November 2016

Tuesday 22 November 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ስምንት)

ታዲያ ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ምንድር ነው?
   የብሔርተኝነትን ትርጉም ይዘን ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነትን ስንተረጉመው፥ “ለአንድ ተመሳሳይ ወይም በአንድ ውስን ሥፍራ ወይም በአንድ መልክአ ምድራዊ  ክልል ውስጥ ለሚኖሩ፥ በሃይማኖታዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፥ በአንድ ቋንቋ መጠቀም[በሃይማኖት ጥላ መሰባበሰብ]፥ በጋራ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የወል ሥነ ልቦናዊ ገጽታዎችና በሃይማኖታዊ አመለካከቶች መያያዝን ያመለክታል ... ”  ብለን በአጭሩ መተርጐም ይቻለናል፡፡
    ምናልባትም ለሃይማኖታዊ “ብሔርተኝነት” ከዚህ የተሻለ ትርጉምን ልናመጣለትም አንችልም፡፡ [1] እንግዲህ የብሔርተኝነትን ትርጉም አንስተን ከሃይማኖት ጋር ለማሻረክ መሞከር፥ በራሱ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገሮችን እንድንፎርሽ ያደርገናል፡፡ በክርስቶስ የተመሠረተው ክርስትናችን ለጠቅላላው ዓለም[ሰው] መፍትሔ እንጂ “በሃይማኖት ወገንተኝነት” ላይ በማነጣጠር ወይም እንዲህ ባለው ነገር ላይ መሠረት በመጣል ፈጽሞ አይደለም፡፡

Wednesday 16 November 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሰባት)

Please read in PDF
ለመሆኑ፦
ሃይማኖታዊ “ብሔርተኝነት” ምንድር ነው?
  “ ... የሃይማኖት ብሔርተኝነት መነሻው አገራችን በሰማይ፤ ኑሮዐችን በዓለመ ነፍስ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት ሲባልም ሃይማኖትን በሃይማኖት እናት፣ አባትና ብሔር አድርጐ መውሰድ ወይም በአጭሩ የሃይማኖት ወገንተኛ ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ወንዝ- ጐጥና ዘውግ ዘለል መሆኑን ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በቤተ ክርስቲያናችን የነበረና የቆየ ማእከለ አንድነት እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ [1]
   ... የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እያጸጸ መምጣቱንና ውስጡ ጥቅመኝነት ሆኖ ሽፋኑ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ የሆነ ብሔርተኝነት መሠረት እየያዘ መሆኑን ነው፡፡ እናም መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለና በጐ ከማድረግ አኳያ የጊዜውን አበው፣ ሊቃውንትና ምእመን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ዋጅቶ ከወንዛዊ- ጐጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት ደዌ መፈወስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡
   ... ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ከባድ ግን ልትወጣው የምትችለው ፈተና አለባት፡፡ በቃላት የሚፈታና የሚነገር ሳይሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚፈተነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣዩ ጉዞ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እጅ ለእጅ መያያዝንና  ጠንካራ አንድነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለምን አልተጣሉም? ለምን አልተከፋፈሉም? የሚሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አርፈው የሚቀመጡበትም ሁኔታ እንደሌለ መገንዝብ ይቻላል፡፡ ... ብፁዓን አበውም፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ምእመናንም ይህን አውቀው በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ጠንክሮ መጓዝ ይጠበቅባቸዋለን እንላለን፡፡” [2]

Friday 11 November 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ስድስት)

አማኞች፦ ከእኛ ምን ይጠበቃል?
    “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”፤ (ገላ.3፥28) የሚለው ቃል ከክርስቶስ ጋር አንድነት በዘር፣ በማኅበራዊ ኑሮ ደረጃና በጾታ ልዩነት ገደብ የሌለበት መሆኑን በግልጥ ያሳያል፡፡ ክርስቶስ የመሠረታት አዲስ ኪዳናዊት ሕብረት ልዩ የሚያደርጋት ይህ ነው፤ ምንም ምን ልዩነት በሰው ልጆች መካከል ፈጽሞ አያደርግም፡፡ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና”፤ (ሮሜ.10፥12)፥ የሚለው ቃል ደግሞ፥ ጌታን ለማመንና በእርሱ ለመዳን ምንም የዘር ቅድመ ሁኔታ አለመቀመጡን እናያለን፤ (1ቆሮ.12፥13 ፤ ኤፌ.2፥15 ይመልከቱ)፡፡

Thursday 3 November 2016

ወዳንተ ቃል ቀዬ


የፍቅር እንጎቻ የእምነት እንጀራ፥
የቸርነት ዳቦ የምሕረት መና፥
ጨለማ ʻማይነካው የዘላለም ጸዳል፤

Tuesday 1 November 2016

“ … የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ”(ኤፌ.4፥3)

ከአንድነት ወደመንፈስ አንድነት እንመለስ!
      ቤተ ክርስቲያን የአይሁድና የሳምራውያን፤ የአሕዛብም ድምር ውጤት ናት፡፡ ይህ ፍጹም የመንፈስ አንድነት የተገኘው እንዲያው ዝም ብሎ ሳይሆን የወልደ አምላክ የክርስቶስ ኢየሱስን ሞትና የደም ዋጋ የጠየቀ፥ በእርሱም የደም ቤዛነት በተደረገ ዕርቅ የተገኘ ነው፡፡ አንድነቱ ተራ ወጥነት ያለው አንድነት ወይም ተመሳሳይነት ማለት አይደለም፡፡ አንድ የመሆን አንድነት በራሱ ከውጫዊ ተጽዕኖ የሚመጣ የጫናና የፍጹም ውጥረት ዳርቻ ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ አንድ ያልሆኑ ልቦች ብዙ ናቸው፡፡
    የመንፈስ አንድነት ግን ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነና ከአንድነት የተለየ መልካም ነገር ነው፡፡ የብዙዎች አንድነት ቅድመ መርኅን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህም አብረው ያሉ፣ የተስማሙ፣ የማይለያዩ፣ የማይከዳዱ፣ የማይነጣጠሉ … ይመስላሉ እንጂ፥ ፈጽመው አንድ አይደሉም፡፡ ትልልቅና የማይፈርሱ የሚመስሉ አንድነቶች እንዴት እንደፈረሱ እስኪደንቀን ድረስ ፈጽመው ስም አጠራራቸው እስኪጠፋ ፈርሰዋል፡፡

Wednesday 26 October 2016

ስለሁለተኛው ዛፍ

Please read ion PDF

ዛሬ ካነበብኩት መጽሐፍ እናንተም እንድትካፈሉ ወደድሁ፤ እናም ታነብቡት ዘንድ ይኸው ጋበዝኳችሁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
መሪ
     አንባቢ ሆይ! በዚህ መጽሐፍ ከመጀመርያ እስከመጨረሻ ወደ ምሥራቅ  ሔድሁ፤ ወደምዕራብ ተመለስሁ፤ ወደሰሜን ሔድሁ፤ ወደደቡብ ተመለስሁ እያለ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ምሥራቅ ሲል መጻሕፍተ ሐዲሳት ማለቱ ነው፡፡ ምዕራብ ሲል መጻሕፍተ ብሉያት ማለቱ ነው፡፡ ሰሜን ሲል የሊቃውንት መጻሕፍት ማለቱ ነው፡፡ ደቡብ ሲል አዋልድ መጻሕፍት ማለቱ ነው፡፡ ዓለም ያለ እንደሆመ ግን መጻሕፍትን ሁሉ ማለቱ ነው፡፡ ይህንም ካስታወቅሁ በኋላ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ የሚለው ሀገር እንዳይመስላችሁ፡፡ እግዚአብሔር የልጁን የክርስቶስን ብርሃን በልባችሁ ውስጥ ያብራላችሁ፡፡ አሜን፡፡ ፪ጴጥ.፩፥ ፲፱፡፡
ዕራፍ ፪
ስለሁለተኛው ዛፍ
    ከዚህም በኋላ ወደምሥራቅ ሀገር ዞርሁ፡፡ በዚህም ሀገር፤ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ፣ የሚባሉ ሰዎች ጌቶች ሆነው ይኖራሉ፡፡ ወደእነርሱም ደጅ የማይደርስ ሰው የለም፡፡
    እኔም ወደ እነርሱ ቤት ስሔድ በመንገድ ዳር አንድ ዛፍ አገኘሁ፡፡ ይህም ዛፍ በቁመትም፣ በመልክም፣ በፍሬም ያንን በመጀመርያ ያየሁትን ዛፍ ይመስላል፡፡ ዮሐ.፲፬፥፱፡፡

Wednesday 19 October 2016

Thursday 13 October 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል አምስት)

መጽሕፍ ቅዱስና ዘረኝነት
መጽሐፍ ቅዱስ ዘረኛነትን በግልጥ ይቃወማል፡፡ ምክንያቱም ፦
1.    ሁላችን ከጥንት አንድና እኩል ነበርን ፤ ነንም!
    እግዚአብሔር ከጥንት የሰው ልጆችን ያየው በአንዱ ሰው በአዳም በኩል ነው፤ የሰው ልጅ በኃጢአቱ የወደቀውና የተበላሸው በአንዱ በአዳም በኩል ነው፤ (ሮሜ.5፥12)፡፡ እንዲሁ ወደአዲስ ኪዳንም ብንመጣ እግዚአብሔር አለምን ሁሉ በምህረት አይኑ ያየው በአንድ ልጁ በኩል ነው ፤ ማለትም እንደአንድ ቤተ ሰብ የቆጠረን በደሙ በተጠራነው ጥሪ ነው፡፡
    በክርስቶስ አንድ ወደሆንነበት ቅድስት ሕብረት ለመሰባሰብ መስፈርቱም ማንነትና ዘር ሳይሆን አብርሃማዊ እምነት መያዝ በቂ እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ “እምነት የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፤ ከመንፈስ ቅዱስም ይገኛል፤ (ገላ.5፥23 ፤ ኤፌ.2፥8 ፤ 2ተሰ.2፥13)፡፡ ሰው በእምነት ይጸድቃል፤ (ሮሜ.3፥28 ፤ ገላ.2፥16) ነገር ግን በእምነት ከክርስቶስ ጋር ስለሚተባበር፥ እግዚአብሔርን ሥራ መሥራት ይጀምራል (ኤፌ.2፥8-10) ስለዚህ ሰው እውነተኛ አማኝ መሆኑ የሚጣወቀው በሥራው ነው”፡፡ [1]

Saturday 8 October 2016

ኢትዮጲያ ሆይ! ላሁኑ ብቻ ያይደለ፥ ላለፈውም ጥፋትሽ ማቅ ለብሰሽ ንስሐ ግቢ!!!


   Please read in PDF

  አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው።” (ነህ.1፥5-11)


      ልብ የሚሰብር ጸሎት የጸለየው የእግዚአብሔር ሰው ቅዱስ ነህምያ ነው፡፡ ነህምያ የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ያጽናናል” ማለት ነው፡፡ በእውነትም ሕይወቱና ንግግሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሊያጽናናበት የተጠቀመበት ምርጥ ሰው ነው፤ ነህምያ፡፡  ይህ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እጅግ የተወደደ፥ ለእኛም ብዙ ምሳሌና ልንማርበት የሚያስችል የቅድስና ሕይወት የነበረው ነው፡፡

Wednesday 5 October 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል አራት)

Please read in PDF
የዘረኛ ሰዎች ባሕርያት
1.    ላውን የሚንቁ
      ዘረኛነት ባህርይው ራሱ “የእኔ ነገር ትልቅ ነው” የሚል ነገር በውስጡ አለበት፡፡ ንቀት ”እኔ ከሌላው እሻለለሁ ወይም እበልጣለሁ” የሚል ክፉ ሃሳብን ያዘለ ነው፡፡ ጀርመናውያን በይሁዲዎች ላይ ከመነሳታቸው በፊት ሲመለከቷቸው የነበረው በንቀት ነበር፡፡ በአገራችንም ያለውን እውነት ብናይ አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር ሲንቅ ያየንበት፤ የምናይበትም ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ለሥራ ጉዳይ ወደአንድ ክልል ሄዶ ነበር፤ በዚያም መኪናችን ቆሽሻ ነበርና ልናሳጥብ ወደአንድ መኪና ማሳጠቢያ ገባን፤ የመኪናችንን ታርጋ ብቻ አይተው በሚጠየፍ ማንነት ነበር አጣቢዎቹ የተመለከቱን፤ ሊያጥቡልንም ፈቃደኞች ስላልነበሩ ትተን ሄድን፡፡ በጥቆማ ግን ወደሌላ ሥፍራ ሄደን አሳጥበናል፡፡ ያጠበልን ልጅም ግን “የታርጋው አከባቢ ነዋሪ” እንደነበር በኋላ ላይ ሰማን፡፡

Wednesday 28 September 2016

የጳጳሱና የሰባክያኑ ቤተ ክርስቲያንን “መለካዊ” የማድረግ ሃሳባቸው እስከምን ድረስ ነው?!

Please read in PDF      

          ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ “አልቃሻው ነቢይ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ዋናው ምክንያት፥ ሕዝቡ በኃጢአትና በነውር ምድሪቱን እጅግ በማርከሳቸውና ፊታቸውን ወደንስሐ ዘወር እንዲያደርጉ፥ ከእነርሱ ጋር እየተራበና እየተጠማ በመካከላቸው ሆኖ አዘውትሮ ቢናገራቸውም፥ እስራኤል ሊሰሙት ካለመውደዳቸው ባሻገር አጥብቀው ስለተቃወሙትና ሊቀበሉት ፈጽመው ስላልወደዱት ነው፡፡
    በዚህም ምክንያት በጥልቅ ሐዘን መዋጡን፥
    “አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም፡፡ … ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም፡፡”፤ (ኤር.4፥19-22)፤ “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ፡፡ ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ፡፡”(9፥1-5)፤ “እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል፡፡”(10፥21)፤ “ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ፡፡ ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ ማሰማርያ ደርቆአል፤ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም፡፡ ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (23፥9-11)
የሚለው የነቢዩ ንግግር የሚያየው የእስራኤል ክፋት ምን ያህል እንዳቆሰለውና እንዳሳዘነው በትክክል ይገልጠዋል፡፡

Tuesday 20 September 2016

በዘመን መለወጫ የተቀማጠለው ንጉሥ (የመጨረሻ ክፍል)

  please read in PDF

ልንመርጥ የምንችለው አንድ መንገድ ብቻ ነው፤ ከኃጢአትና ከጽድቅ መንገድ አንዱን፡፡ ከሁለቱ አንዱን እንጂ ለሁለቱም ማመቻመች አንችልም፡፡ “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤” (ዕብ.12፥4) የሚለው ቃል በእውነት ላይ እስከመጨረሻ አለመጽናትንና አለመጨከንን የሚያሳይ ነው፡፡ ለእውነት ከቆምን እስከሞት ድረስ እንጂ ሁለቱን ለማደላደል መሞከር ከውርደት አያድነንም፡፡
    የሳሙኤልን መጽሐፍ የጻፈው ጸሐፊ፥ በንጉሥ ዳዊት ሕይወት የሆነውን ውድቀት ሁሉ ምንም ሳያዛንፍ ነው፡፡ አስቡ! የነቢዩ ሳሙኤልን ሕይወት፥ “እነሆኝ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ፡፡ እነርሱም፦ አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ፤” (1ሳሙ.12፥3-4) በማለት ገልጦታል፡፡ እንዲሁ የዳዊትን ደካማና ኃጢአተኛ ሕይወት ሳያቅማማ ነው የገለጠው፡፡

Wednesday 14 September 2016

... አዲስ ዘመን የለም



ቢግተለተል ዕድሜ፥ ምን ቢረዝም ዘመን፤
ተቆጥሮ ተሰልቶ፥ ቢሰጠን ብዙ ቀን፤

Friday 9 September 2016

በዘመን መለወጫ የተቀማጠለው ንጉሥ (ክፍል አንድ)


Please read in PDF

እንኳን ለንስሐ የሚሆን ዘመን  ተጨመረላችሁ!!!
     ቅምጥልነትን፥ ቅዱስ ጳውሎስ “ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት” (1ጢሞ.5፥6) በማለት ይገልጠዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት መሞትን በሕይወት ቆሞ መሄድ አይተካውም፡፡ መንፈሳዊ ሞት ወደር የለሽ እጅግ አስጨናቂ ሞት ነው፡፡ ቆሞ በመሄድ ማማር የለም፤ በቁም “በውጭ አምረው የሚታዩ” ሁሉ ደመ ግቡዎች አይደሉም፤ ውስጣቸው “ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ሊመስሉ ይችላሉና”፤ (ማቴ.23፥27)፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች በሕይወት የሞቱና ሕያውና የሚያድን ድምጽ መስማት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
     ጌታችን “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” (ሉቃ.9፥60) በማለት የተናገረው፥ በመንፈስ ሙት የሆኑ በሥጋ ሙት የሆኑትን ሊቀብሩ እንዳሉና በመንፈስ ሕያው የሆነ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት በብርታት ማገልገልና መስበክ እንዳለበት አጽንቶ ሊናገር ወዶ ነው፡፡ አስተውሉ! ጥቂት ቅምጥልነት ለምን አይነት መንፈሳዊ ሞት አሳልፎ ሊሰጠን እንደሚችል፡፡
   ንጉሥ ዳዊት ሁሉንም “ጠላቶቹን” ቢያሸንፍም፥ አሞናውያንን [1] ግን ገና አላሸነፈም ነበር፤ (2ሳሙ.10፥19)፡፡ እኒህ የቀሩ ጠላቶች ቢኖሩትም ግን፥ “እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ወደጦርነቱ ሰድዶ ለራሱ ግን በኢየሩሳሌም ቆየ፤” (2ሳሙ.11፥1) አመሻሽ ላይ በዚያ ምቹና ተስማሚ ሰገነት ላይ (1ሳሙ.9፥25) ዳዊት ይመላለስ ነበር፡፡ በሌላ ንግግር ወደዳዊት ሕይወት ቅምጥልነት ሰተት ብሎ ገባ ማለት ነው፡፡ “በልክ መዝናናት” አንድ ነገር ነው፤ ለሥጋዊ ተድላና ለቅምጥልነት ተዘልሎ መቀመጥ ግን ራስን በወጥመድ ውስጥ የማስገባት ያህል እጅግ አደገኛ ነው፡፡

Sunday 4 September 2016

የኢትዮጲያ “መካከለኞች” ወዴት ናቸው?

Please read in PDF     

       ቺቸሮ “አለመግባባት መፍትሄ የሚያገኘው በሁለት መንገዶች በውይይት ወይም በኃይል ነው፡፡ የመጀመርያው የሰው ባሕርይ ሲሆን ሁለተኛው የአራዊት ነው” ይላል፡፡ ባለመታደል ሁላችንም ሁለተኛውን መረጥን፡፡ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍን ያለመቀበል እንደባህል አድርገን በመያዛችንና በሃገሪቱ የፖለቲካ ልምድ ካለመኖር ጋር ተዳምሮ የኢትዮጲያ ተራማጆች ኃይልን መርጠው በመንቀሳቀሳቸው የደም መፋሰሱንና የጥፋቱን መጠን በማባባስ ለሃገር ግንባታ ይውል የነበረ ወጣት ለቅስፈት ተዳርጓል፡፡ (ሌ/ኰሎኔል ፍሥሐ ደስታ፤ አብዮቱና ትዝታዬ ፤ 2008 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት)

       ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም “እርምጃ እንዲወሰድ ከማዘዛቸው” በፊትም ሆነ በኋላ፥ የሕዝብ ኩርፊያ አሁንም ጋብ ያለ አይመስልም፡፡ ሕዝብ እንደሚናጠቅ የአንበሳ ደቦል “በገዛ ወገኑ” [እርስ በራሱ] ላይ ያደባ ይመስላል፤ “መንግሥት ሆይ!  ችግር አለብህ፤ ተስተካከል” ለማለት እየሄደበት ያለው አቅጣጫና አንዳንዶች እንደሚሉት ሕዝቡን የሚመራው “ሦስተኛው አካል” ዓላማና ግቡ ምንም እንደሆነ በትክክል አለመታወቁ ነገሮች የበለጠ እንዲወሳሰቡ ያደረገ ይመስላል፡፡
     እርግጥ ነው፥ የአብዛኛው ሰው ስሜት ሲደመጥ፥ “ይኼ መንግሥት በቃው፤ ይውረድ” ይመስላል፡፡  ይህ አካሄዱ ግን ፍጹም ኢ መንፈሳዊነት ብቻ ሳይሆን ኢ ሰብዓዊነት፣ ኢ ሥነ ምግባራዊነትና ኢ ሞራዊነት የሰፈነበት መሆኑ ነገሩን አስጨናቂና እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ምንድር ነው አስጨናቂና አሳሳቢ የሚያደርገው? ብንል፦
1.     ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ምን ሆነው? በማን ላይ ነው እርምጃ እንዲወሰድ አዝዣለሁ ያሉት? ከእርምጃው በፊት ማወያየትና ማነጋገር አይቀድምም ወይ? ምክር አይፈለግም ወይ? እርምጃ የመጀመርያ ደረጃ መቀራረቢያና መግባቢያ መንገድ ነው ወይ? ሕዝብን ማድመጥና ፍላጐቱን መጠየቅ አይገባም ወይ? በደፈናው ከመፈረጅ ጥንተ ምክንያቱን ማጥናት፤ መረዳት አይገባም ወይ? ወይም ለምንድነዉ መንግስት በፖለቲካ አቅጠጫ ማሸነፍ የተሳነው? የሚሉና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን መምዘዝ ይቻላል፡፡

Saturday 27 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሦስት)

በእኛ መካከልስ ምን ይመስል ነበር?
   ዘረኛነትን በተመለከተ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብንነሳ፥ ኢትዮጲያ ከሰማንያ አራት በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባትና በተለያየ ብዙ ቋንቋዎችም የሚነጋገሩ ሕዝቦች ያሉባት አገር ናት፡፡ አንዱ አንዱን ለመብለጥ ምክንያት የሚመስሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሰዎች ከአንድነት ይልቅ በየራሳቸው ነገር ላይ ትኩረት ሲያድርጉ ሳያውቁት ሌላውን በመጻረር የሚቆሙበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ ሰዎችን ወደሌላ የክህደት መንገድ ለመምራት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ በዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ሆነው የቀሩ ሰዎች ያሉትን ያህል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠግተው ለራሳቸው ምስክርነት እየፈለጉ በዘረኛነት ክፉ ኃጢአት የተያዙ ብዙ ናቸው፡፡
    መጽሐፍ ቅዱስን ተገን ተደርጐ የሚሠራ ኃጢአት እጅግ አስከፊ ኃጢአት ነው፤ በእኛ መካከል ያለው የዘረኛነት መንፈስ እንዲህ ያለ ነው ብንል ማጋነን አለበት አያስብልም፡፡ አንድ ሃይማኖት የተወሰኑ ወይም የአንድ ብሔር እስኪመስል ወይም እስኪባል ድረስ በመካከላችን የሚታየው ነገር አስነዋሪ ነው፡፡ ይህንን በአንድ ጽሑፍ፦
“ … አሁን አሁን ነገራችን እንደዖዝያን ለምጽ ሊሸፈንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ራሱ ችግሩም “አለሁ፣ አለሁ” ብሏል፡፡  የለህም ብንለውም ራሱን በራሱ ያስመሰክራል፡፡ ሙስናው ፣ የዘመድ አሠራሩ …ወዘተ አግጥተው ወጥተዋል፡፡” [1]

Monday 22 August 2016

በአዲስ አበባ፥ ምነው በሰበበ “ሰላማዊ ሰልፍ” ሁከት አልተቀሰቀሰም?!

Please read in Pdf 
የኢዮአታምን ምክር የማይሰማ ሕዝብና መሪ መጨረሻው ጥፋት ነው!!!
     ትላንት ማምሻውን ስልኬ ከወደብዙ ቦታ በተደረገላት ጥሪዎች ስትንጫረር ነበር፡፡ ከ“ክፍለ አገር” እና ከውጪው ዓለም፡፡ “አዲስ አበባ ሰላም ዋለችን? ከመገናኛ ብዙኃን ምንም መረጃ አጣን? ምንም ሁከት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ አልነበረም? ... ምንም ምን አልነበረም? ... ” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ወንድሞችና እህቶች፡፡
     ከዚህ የጥያቄ ግርፍ በኋላ ለረጅም ሰዓት ቆም ብዬ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ሰው ከሰላም ይልቅ “ሰላማዊ ሰልፍ” ለምን ተጠማ? ከጸጥታ ይልቅ ግርግርና ሁከት ለምን መረጠ? የማያስማማ፣ የማያነጋግር፣ የማያወያይ፣ ጅምር ላይ ሆነን ፍጻሜ መተለም የማያስችል ክፉ መንፈስ ከወዴት ይሆን የተጣባን? የቀደመው ዘመን ታሪክ ስለምን መማርያ አልሆነንም? ከዚህ ቀደም የ“ንጉሠ ነገሥቱን” ሥርዓት ሰለቸን ብለን፥ ከአርባ ዓመት በላይ “የመራንን” ንጉሥ አዋርደን፣ ከሰውነት ተራ አውጥተን፣ “ለባዕድ” የማይነፈገውን የቀብር ቦታ እንኳ ለ“ንጉሠ ነገሥቱ” ነስተን፣ ስም አጠራሩን አጥፍተን ... ወታደራዊውን መንግሥት “በእልልታ በሆታ” በራሳችን ላይ ሾምን፡፡
እርሱም የዘራነውን አሳጨደን፡፡

Thursday 18 August 2016

በዓይናችን አይተን!

Please read in PDF


ተረት መች ሆነና ብልሐታዊ ንግርት፣
የምሰብከውና የምንዘምርለት፣
አጉል ፍልስፍና ጥበብ መሰል ነገር፣

Tuesday 16 August 2016

የኢትዮጲያ የ“ማስተዋል” ጸሐይ ምነው አዘቀዘቀ?



Please read in PDF


መንግሥት ሆይ! እባክህ ከማሰር ፤ ከማጐር ይልቅ፥ ራራ! ይቅር በል! ማር!!!
     በምዕራቡ ዓለም በተደላደለ መኖሪያ ቤታቸው ተቀምጠው እንደሰበኩን፥ “ጨካኝ ፣ እብሪተኛ ፣ አምባገነን ፣ አረመኔ ፣ ጉበኛ ፣ ዘረኛ ፣ ሴሰኛ ፣ አድርባይ ፣ አፋኝ …” ያሉት ይህ የአገር ቤቱ መንግሥት ወረደ እንበል፤ ግን እኒህ ዲያስፖራ ፖለቲከኞችና ፈሪሳውያን ሃይማኖተኞች ያልመለሱልን ጥያቄ፥ “ማን እንዲመራን ነው ያቀዱት? ፣ ማንን ይሆን ያዘጋጁልን? እነርሱ ራሳቸው ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሊመጡና ሊመሩን? ፣ ወይስ ከዚሁ አገር ቤት የሚያሰናዱልን ነገር ኖሮ ይሆን?”
     አንድ ሌላ ጥያቄ አለኝ? እኒህ “ዲያስፖራውያን የፖለቲካና የሃይማኖት ዲስኩረኞች” ለመሆኑ ስለአንድነትና ስለመንፈስ አንድነት ለማውራት በእውኑ ሞራሉና ብቃቱ አላቸው? በአንድ ነገር አምናለሁ ፤ የአገር ቤቱ መንግሥት ብዙ ነውር ፣ ዕድፍ ፣ ርኩሰት ፣ ልክፍት ፣ በደል … አለበት ፤ ይህን አምናለሁ፥ አልጠራጠርም፡፡ አንድ ብርቱ መከራከርያ ግን አለኝ፡፡ ከአገር ቤቱ መንግሥት ይልቅ “የአሁኑን የነውጥ እንቅስቃሴ እየመራ ያለው የዲያስፖራው ጐልማሳ” ግን ነውሩና ርኩሰቱ ከአገር ቤት መንግሥት ይበልጣል ባይ ነኝ፡፡

Monday 8 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሁለት)

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
    Please read in PDF

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
     ይህ አለም አቀፍ አዋጅ በዘረኛ ጠባይና ድርጊት በሚከተሉ ሰዎች በግልጽ ከመሻሩና ከመጣሱም በላይ፥ በአለም ላይ ዘረኛነት በግልጥ የታየበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በሥልጣኔ ከመጠቁት እስከ በሥልጣኔ ወደኋላ በቀሩት ሕዝቦች መካከል ከሚታይ ጥላቻ እስከትውልድ መደምሰስ የሚያደርስ የዘረኝነት ተክል በአለም ሁሉ ፊት  በቅሏል ፤ አብቧል ፤ ፍሬውም ሆምጣጤ ሆኖ በክፉ ምሳሌነቱ ታይቷል ፤ አሁንም ድረስ እየታየ ነው፡፡ ዘረኛነት ድንበር ሳይከለክለው በጸሐፍት፣ በባዕለ ሥልጣናት፣ በምሁራን [1] ፣ በጳጳሳት ፣ “ለምድር የከበዱ በሚባሉ ብዙ ሕዝቦች” ዘንድ ተገልጧል፡፡
       ሄሮዶተስ (Herodotus) [2] በሊብያ በረሃ ደቡብ ምዕራብ ጠረፍ ስለሚኖሩ ሕዝቦች ማንነት ሲናገር፥ “… ከአደገኛ አውሬዎችና ልዩና አስገራሚ ፍጥረታት ጋር የሚኖሩ ፣ ጭንቅላት የሌላቸው ፣ ዓይናቸው በደረታቸው ላይ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ናቸው” [3] በማለት ለአፍሪካና አፍሪካዊ ማንነት የሰጠው ተፈጥሮን ተቃራኒ ንግር ነበር፡፡ [4] ጥቁር በመሆን ብቻ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ፥ ሌሎች የእስያና የሌሎችም አህጉራት ሕዝቦች እጅግ ከባድ ውርደትና አጸያፊ ጥላቻን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ምናልባት ይህ እጅግ በራቀው ክፍለ ዘመን ፤ ሥልጣኔና አመለካከት ባልዳበረበት ዘመን ነው ብለን ብንሞግት እንኳ፥ አሻራው ሳይደበዝዝ በዚህ በዛሬው ጊዜ ፍንትው ብሎ ፤ በመካከላችንም ጭምር እናስተውለዋለን፡፡

Tuesday 2 August 2016

“27 አባቴ” የሚባል አባት የለንም!

Read in PDF

    አባት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው ሲፈቱት፥ “የግብርና የክብር የማዕረግ ስም፡፡ አባት መባል በብዙ ወገን ስለኾነ ከግዜር ዠምሮ ያባትነት ሥራ ለሚሠሩ ለመንፈሳውያን አባቶች ለቄስ ለመነኵሴ ለአእሩግና ለሊቃውንት ለመምህራን ኹሉ ይነገራል፡፡ … (ሐተታ) አብ በጥሬነቱ ዘርፍ ይዞ ሲቀጸል ምስጢሩ ካባትነትና ከጌትነት ከባለቤትነት አይወጣም፡፡” [1] በማለት በግልጥ አስቀምጠውታል፡፡
     የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም፥ “ የወለደ፥ በሥርዓት ኮትኩቶ ያሳደገ፥ በሥጋና በመንፈስ የአባትነትን የፈጸ ሁሉ አባት ይባላል፡፡ … ምእመናን ከእርሱ በመንፈስ ቅዱስ ስለተወለዱ “አባ አባት” ብለው ይጠሩታል ፤ ማቴ.6፥9 ፤ ዮሐ.1፥12 ፡ 13 ፤ ገላ.4፥6” በሌላ ሥፍራም፥ “አብ ፤ አባት ማለት ነው፡፡ ይህ ስም ከዘለዓለም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር አብ የሕላዌ(የአንዋንዋር) ስሙ ነው(ማቴ.28፥19 ፤ 1ጴጥ.1፥1-2)፡፡ ኢየሱስ ስለሰማያዊ አባት ሲናገር ብዙ ጊዜ አብ ብሎ ጠራው፡፡” በማለት ቄስ ኮሊን ይገልጡታል፡፡ [2]

     በሌላ ትርጉምም “አባት ፤ (አብ) ወላጅ አስገኝ ፤ አሳዳጊ ፤ ሞግዚት ፤ መነኵሴ፡፡ (የነገር አባት) ፣ ጠበቃ ነገረ ፈጅ፡፡ (ያገር አባት) ፤ ሽማግሌ መካር ዛሬ አንዱ ቤት ነገ እሌላ ቤት እያደረ የሚጦር፡፡ … (የድኻ አባት) ድኻ ሰብሳቢ፡፡ (የንጀራ አባት) ፤ የናት ባል እንጀራ እያበላ ያሳደገ፡፡ … ” [3] በማለትም አስፍተው መተርጉማን ያስቀምጡታል፡፡
    ከእነዚህ የፍቺ መዝገበ ቃላት የምናስተውለው ትልቅ ቁም ነገር አባትነት ከጽንሰት እስከ ልደት ፤ ከልደት እስከእውቀት በሁለንተናው ከተወላጅ ልጅ ጋር ፍጹም ሥጋዊ ፣ ነፍሳዊ ፣ ዕውቀታዊ … ትስስርን የሚያሳይ ትልቅ ምስጢርን ያዘለ ትርጉም መሆኑን ነው፡፡ 

Thursday 28 July 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል አንድ)

Please read in PDF
ያለነው እንደሸማኔ መወርወርያ በሚፈጥነውና በሚቸኩለው ዘመን ፤ ኃጢአትም ከተመሸገበትና ካደባበት ሥፍራው ላይ መገለጥና “እነሆ አለሁ” በሚለው አካላዊ ማንነቱን ማሳያ ዘመን ላይ ነን፡፡ ከቀደመው ዘመን ይልቅ የኃጢአት ጽዋ በዓለም መካከል ብቻ ሳይሆን “የእግዚአብሔር ነን” በሚሉትም መካከል እየሞላና እየፈሰሰ መሆኑን እያስተዋልን ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ፦ “ … ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” (2ጴጥ.3፥9) እንዲል እየሆነ ያለው እግዚአብሔር ስለሌለ አይደለም፡፡

Friday 22 July 2016

ትልቅ ነው አምላኬ

Please read in PDF

ከፍ ከፍ በል ጉላና ድመቅ
ወገብህን አጽና ዝናርህን ታጠቅ
መስባትንም ስባ
ለድልደህም ወፍር
ሙሉ ብረት ለብሰህ ሸልልና ፎክር
በል በልብህ ጀምር ከ’ኔ ማን ሊወደር?

Thursday 14 July 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
ምን እናድርግ?
1.     በእኒህ ማኅበራዊ የመረጃ መረቦች ላይ የሚጠቅመንንና መንፈሳዊ ነገሮቻችንን ብቻ ልናስተላልፍበት ፤ እንዲሁም የምናየውን ፣ የምናደምጠውን ፣ የምናነበውን ... ከእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ጋር የሚያቃርነን ነገር እንዳይሆን በብርቱ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የተጠራነው በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ነው ፤ እርሱ የጠራን ቅዱስ ነውና(1ጴጥ.1፥14-16)፡፡
    “አባታችን ሆይ”፥ ብለን እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠራን፥ እንደእግዚአብሔር ልጆች ለፈቃዱ ብቻ ልንታዘዝ ይገባል፡፡ እርሱ ፈቃዱ ቅድስና ነው፡፡ ቅድስና ከኃጢአት ከርኩሰት ተለይቶ ፤ ለእግዚአብሔር ብቻ መሆንን የሚፈልግ ዓቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችን በየትኛውም ጉዟችን “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ኢየሱስ ገብተናል፥ ለዚህ ኪዳናችን ታማኞች በመሆን ሁሉን እንደቃሉ ልንመረምር ይገባናል፡፡

Tuesday 5 July 2016

“VOA”ና ባልንጀሮቹ ከኃጢአት በቀር “ሥርየት”ን መች ይሆን የሚዘግቡት?

   በኃጢአት ውድቀታችን የሰይጣን ልጆች ስንሆን፥ በትንሣኤ ልቡና በምናደርገው የንስሐ መመለስ ደግሞ ከክርስቶስ ሞትና ከትንሣኤው ኃይል የተነሣ የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን፡፡ ማደፍ ፣ መርከስ ፣ መውደቅ የሥጋ ባሕርይ ነውና ሁላችን በዚህ በኩል፥ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ... አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ ...” (ሮሜ.3፥11-14) የሚለው ፍርድ የአዳምን ልጆች ሁሉ አጊኝቷቸዋል፡፡
    እናምናለን፤ ሁላችንም ያለክርስቶስ የሚታይ ምንም መልካምነት የሌለን ከንቱዎች ፤ የእግዚአብሔር ክብር የጐደለን እርባና ቢስ ነን፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ ከነበርንበት ጨለማነት ፣ ጠላትነት ፣ የቁጣና ያለመታዘዝ ልጅነት ፣ የኃጢአት ባርያ (ሮሜ.6፥20) የኃጢአተኝነት ሕይወት ፍጹም በማውጣት ወደሚደነቅ ብርሃን ፣ ወዳጅነት ፣ የመታዘዝና የእግዚአብሔር ልጅ ወደመሆን በደሙ አጽድቆ ፣ ቀድሶ ያፈለሰንና ወደአባቱም ንጹሐንና ነውር የሌለባቸው አድርጐ ያቀረበን፡፡

Thursday 30 June 2016

ከእረኛህ ጋር ጽና!


ሰርጐ ገቢው ፤
ተመሳስሎ በቀስ አድቢው ፤
የበግ ለምዱን አለስልሶ -
                  አለሳልሶ ፤
የዝማሬ ድምጸት ገርቶ ፤
የስብከቱን ቃና ለምዶ ፤
የጽሑፉን ዝፍቱን ቀብቶ ፤  
በበግ መሐል አንገት ደፍቶ ፤
ተኩላ ክፉ በዚህ ብቻ መቼ ረክቶ?

Sunday 26 June 2016

ቢረፍድም፥ ለወንጌሉ ደወል ለመደወልና ትውልዱን ለማንቃት አሁንም ዕድል አለን!!!

Please read in PDF


 የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስምዋ በባለቤትነት የምትመራውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሰሞኑ ከፍታልናለች፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩም፦
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” (ዮሐ.5፥24)፡፡
የሚለውን ቅዱስ ቃል በማንበብ መክፈቻዊ ንግግር በማድረግ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ወደር የለሽነትና የበላይነት ፍንትው አድርገው ሲናገሩ፥ ፍጥረታት ያለቅዱስ ቃሉ ሕያዋንና ነዋሪዎች መሆን እንደማይቻላቸው በአጽንዖት አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ለዛ ባለው ውብ ንግግራቸውም የቴሌቭዥን ሥርጭቱ መከፈቱን በመባረክ አብሥረዋል፡፡
     በመቀጠል ሊቃነ ጳጳሳትም አጫጭር ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ንግግር ካደረጉት መካከል ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ለዚህ ትልቅ ሥራ “ማርፈዳችንን” ምንም በማይሸነግል ንግግር ተናግረዋል፡፡ እውነታውን ላስተዋለው ካለን አማኝ ቁጥር ብዛትና ካለን አቅም አንጻር እጅግ በጣም ቢረፍድም፥ “ዘግይቶ መከፈቱ በራሱ” እጅግ ደስ የሚያሰኝና ለወንጌሉ ሥርጭት መልካም እድል እንደሆነ እናምናለን፡፡ 

Friday 24 June 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (ክፍል ሁለት)

3. ስድብና ስም ማጥፋት
    ተሰምተው የማታውቋቸውን ስድቦች ወደፊት ገጽና(Facebook) ሌሎችም ድኅረ ገጻት  ስትመጡ ነፍሳችሁ እስክትጠግብ ልትሰሙ ፣ ልታዩ ትችላላችሁ፡፡ አጅግ የምታከብሩት ሽማግሌ ፣ ባልቴት ፣ ወጣት ፣ ልጅ … ድንገት የስድብ ናዳ ሲወርድበት ታያላችሁ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የሃይማኖት መልክ ያላቸው በዚህ ነገር የተጠመዱና የተለከፉ መሆናቸው ነው፡፡
   ስድብ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ ዲያብሎስ ተሳዳቢ ነው፡፡ ልጆቹም እንዲሁ(ራእ.13፥6)፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ ግን ክፉ ከአንደበቱ አይወጣም (ማቴ.15፥11)፡፡ ከአንደበት የሚወጣ ክፉ ነገር መላ ብልትን ያረክሰዋልና፥ የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ስለሚናገረው ይጠነቀቃል፡፡ ይልቁን እንዴት መናገር እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” (መክ.10፥1) እንዲል፥ ቃላችን በስንፍና የተመላ እንዳይሆን “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን” (ቈላ.4፥6) የሚለው ቃል ሊገዛን ይገባል፡፡

Sunday 19 June 2016

ጰራቅሊጦስ - ሌላ አጽናኛችን


Please read in PDF

     “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” (ዮሐ.14፥15-16)
     መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጆች የሚሰጥ የአብ ውብና ድንቅ ስጦታ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመርያ ጊዜ የምንመለከትበት ክፍል ይህ ከላይ ያየነው ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የመሰጠቱ ተስፋ ከኢየሱስ መሔድ ወይም ማረግ በኋላና እርሱም በዚያ ሆኖ በሚለምነው ልመና እንደሆነ፥ “እኔም አብን እለምናለሁ ... ” የሚለውን የጌታ ቃል አብነት በማድረግ ቅዱስ ያሬድ በድጓው፥ “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የእኔ ስለሆኑት ምሕረትን ወደምለምንበት ወደአባቴ ወደሰማይ ዐርጋለሁ አላቸው” በማለት በገጽ.113 ሲያሰፍር፥ እንዲሁም “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደአባቴ ዐርጋለሁ ስለእናንተ እለምነዋለሁ አላቸው” (ድጓ ገጽ 291) በማለት በግልጥ ይደግመዋል፡፡

Friday 17 June 2016

ቤተ ክርስቲያን ሆይ! መንፈስ ቅዱስ ያጽናናሽ ፤ ኢትዮጲያንና ኤርትራን ደግሞ ጌታ ይማራችሁ!!!


ሰውን በማረድ ፣ በማዋረድ ፣ በመስደብ ፣ በማንጓጠጥ ፣ በማሰቃየት ፣ በማረድ … የሚረኩና የሚደሰቱ ከሥነ ምግባር የወረዱ “ሃይማኖት ለበስ” የሰይጣን ደቀ መዛሙርት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በግ ሳለች በተኩላ መካከል የተላከች ታማኝ መልእክተኛ ናትና እኒህን ልትታገሳቸው ፤ ወንጌልን ተግታ ልትመሰክርላቸው ይገባታል፡፡ አሠማሪው ጌታ በክፋትና በነውር በሚጨክነው ተኩላና የተኩላ ዓለም ላይ ቤተ ክርስቲያን ለእውነትና ለዘለዓለም ሕይወት እንድትጨክን የኃይልን መንፈስ ሰጥቷታል (ኢሳ.11፥3)
     “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” እንደሚለው፥ እግዚአብሔር የታመኑና የጽድቅ ምስከር የሆኑ ልጆቹን ከሞት በማዳን ፤ ከአንበሳ መንጋጋ በማላቀቅ ፤ ከሰይፍ ስለት በማስመለጥ ፤ በወኅኒ ከመጋዝ በመታደግ … ብቻ አይከብርም፡፡ እንዲሞቱ ፣ በአንበሳ እንዲበሉ ፣ በሰይፍ ስለት እንዲቀሉ ፣ በወኅኒ እንዲጋዙም በመፍቀድና በመውደድ ክብሩን ይገልጣል፡፡ ክርስትና መስቀል የመሸከም መንገድ እንደመሆኑ መጠን ለእውነተኛው የጌታ ወንጌል ፈጽሞ እንድንጨክን ተጠርተናል፡፡

Friday 10 June 2016

ባታርግ ኖሮ … (እንኳን አረግህ!)

Please read in PDF


ሞትን ድል ነስተህ
ሲዖልን ረግጠህ
የገሃነምን፥ ደጆች አፍርሰህ
ላመኑህ ልጆች፥ ተስፋውን ሰጥተህ …
ባታርግ ኖሮ …

Monday 6 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (የመጨረሻው ክፍል)


  

 “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። … በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? … ” (ያዕ.3፥16 ፤ 4፥1-2)

     እንደማንኛውም ሰው ስናስብ፥ በአስተዳደር ጉዳይ መጣላት ሊኖር ይችላል፡፡ መጋጨት ስላለም ሁከት ፣ ጦርና ጠብ ውጭ ለሚያየው መገለጫ ሆነው ይታያሉ፡፡ ለመንፈሳዊ ሰው ግን የጦርና ጠብ መነሾ ዋና ምክንያቱን ቅዱስ ያዕቆብ እንደነገረን ስናስተውል፥ በብልቶቻችን ውስጥ ከሚዋጉ ምቾቶቻችን እንደሆነ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ምቾት ብርቱ ስሜት ፤ ጠንካራ ውጊያ ፤ አደገኛ ምኞት ፤ ክፉ ቅንአትንም ጭምር ያሳያል፡፡ የዚህም መነሾው ሥፍራው ልብ ነው እንጂ የትም አይደለም፡፡ በልብ ብርቱ ሰልፍ አለ ፤ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ ሮሜ.7
   በዚህ ሳምንት በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀለል አድርጐ ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን ያለ ምስክር አይተውምና (ሐዋ.14፥17)፥ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ እውነታውን በማንሳት መምከርና መገሰጽ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ልብንና የመንገድን ቅንነት እንጂ ዕድሜን ወይም ታላቅ መሆንን ብቻ እንደማያይ ታላቁ ባለበት አቤልን ፣ ዮሴፍን ፣ ኤፍሬምን መምረጡን ፤ በእድሜ የሸመገሉቱ ዔሊና ሌሎች ካህናት ባሉበት ሕጻኑን ሳሙኤልን ፣ እንዲሁም [ወጣቱን] ሕጻኑን ኤርምያስን እንደመረጠው መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ይነግረናል፡፡ 

Thursday 2 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (ክፍል አንድ)


Please read in PDF
   የፍጥረትን አፈጣጠር የሚነግረን ቅዱስ ሙሴ የኦሪቱን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፍ ሲጀምር፥ “…ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ …” (ዘፍ.1፥2) ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን እስኪል ድረስ፥ ጨለማው በምድር ሁሉ ላይ ሰልጥኗል ፤ ማለትም፥ ምድር ለሥራ የማትመችና የማትታይ ፣ ቅርጽ አልባና ባዶ ፣ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ የተወረሰች ነበረ ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ ግን፥ ለሥራ የማትመቸዋ ምድር ታየች ፣ ተገለጠች ፣ ሕልውናዋ ታወቀ ፤ ቅርጽ አልባና ባዶ የነበረችው አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ልታበቅል ዝግጁ ሆነች ፤ አስደሳችና ውብ ውበትን ለበሰች ማለት ነው፡፡ ጨለማዋን የእግዚአብሔር ብርሃን ገልጦላታልና፡፡
    ለተፈጠረችው ምድር ጨለማ ቀድሞ ሰልጥኖባት እንደነበረው እንዲሁ፥ ዋናው ብርሃን ዘእምብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሊሰለጥንና በሕይወታችን ብርሃንን ከማብራቱ በፊት የኃጢአት ጨለማ በልባችን ለዘመናት ሰልጥኖ ነበር፡፡ ምድር ስትፈጠር ብርሃን ይሁን ያለው እግዚአብሔር ወልድ፥ አሁንም በአዲስ ኪዳን ልደት፥ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” (2ቆሮ.4፥6) በማለት፥ በዚህ ቃል ቀድሞ ምድር ሕልውናዋ እንደተገለጠ፥ አሁንም ለእኛ በጽድቅ መኖርና መገለጥ ክርስቶስ መሠረትና ዋናችን ሆኖልናል፡፡ እርሱ በደሙ ቤዛነት ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን አውጥቶናልና፡፡

Sunday 29 May 2016

ለካ በተጣዱበት የሚሞቁ ምርጥ አርቲስቶች አሉን?¡¡¡


    አውቃለሁ ፤ ክርስትና የመገለጥ ጉዳይ እንጂ የእውቀት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህን የምለውም በግኖስቲካዊ አቋም ዕውቀትን ከሚያመልኩ ጐን በመሰለፍ ወይም አምርረው ከሚጠሉትም ጐራ ራሴን በመደመር አይደለም፡፡ ክርስትና በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሆነውን ቤዛነትና ውጅት ማመንና ይህንንም መንፈስ ቅዱስ በፍጹም መገለጥ የሚያስተምረን ሕያው እውነት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ላመኑትና ለተቀበሉት ብቻ ነው (ዮሐ.1፥12)፡፡

  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ መቀበል ማለት፥ በሕይወታችን ፣ በትዳራችን ፣ በሥራችን ፣ በሁለንተናችን እርሱን ማመንና በተገለጠ ቅዱስ ሕይወት እርሱን ጌታችንን በኑሮአችን መመስከር ማለት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስን ለማመንና ለመቀበልም ሆነ ለማገልገል ፍጹም መሞት ያስፈልጋል፡፡ በትክክል ሳንሞት በትክክል መኖር አንችልም ፤ በትክክል ሳንኖርም በትክክል መሞት አንችልም፡፡ መስቀል ባልፈተነው ጉብዝና እንደመኖር ባዶ ክርስትና የለም፡፡

Monday 23 May 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (ክፍል አንድ)

please read in PDF

    

 ማኅበራዊ ድኅረ ገጾች ለብዙ ዓመታት የተለያዩትን ቤተሰቦች ፣ ዘመዶች ፣ ወገኖች የመገናኘት ምክንያት ሆነው፤ ለንግዱ ማኅበረሰብ ሥራዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያስተዋውቁና እንዲያሻሽጡ ፤ ለተጠቃሚውም ዝቅተኛ የገበያ ዋጋ ፣ በጥራትና በዋጋ የተሻለውን ለመምረጥ ፤ በማኅበረሰቡና በአገራት መካከል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ፤ የአንዱን ማኅበረሰብ መልካም እሴት ለሌላው ለማስተላለፍ ፣ ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ፣ ስለተለያዩ ነገሮች የተለጠፉ “አስፈላጊ” የሆኑ መረጃዎችን “ለመጠቀም” ፤  “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥” (ማቴ.24፥14) ተብሎ እንደተነገረ፥ ወንጌልን “ለዓለሙ ሁሉ” ለማሰራጨትና ለሌሎችንም ፋይዳዎች ያስገኙትን ያህል የዚያኑ ያህል (ምናልባትም በሚበልጥና በከፋ ሁኔታ) አሉታዊ ጎናቸውም እጅግ ሰፊና አሳሳቢ ነው፡፡

Saturday 14 May 2016

ብርሃን ትሆኑ ዘንድ


ያ አሮጌው አዳም ፍጥረትን አስረጀ
በልዞ ቸክኮ  ፤ በኃጢአት ሸለቆ ዘመናትን ፈጀ
አልታዘዝንምና፦ እኛንም አገኘ ፤

Tuesday 10 May 2016

“ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” (ሐዋ.2፥32)

   
   ደቀ መዛሙርት የተጠሩለት ዋና ዓላማ አንድና ግልጥ ነው፡፡ “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥” (1ቆሮ.15፥3-4) የሚለውን ሕያው እውነት ለዓለሙ ሁሉ ማወጅና መመስከር ነው፡፡
   
          በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ገና ከጽንሰቱ ጀምሮ አብሮ ነበር (ሉቃ.1፥35) ፤ በአገልግሎቱ ጅማሬም መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አልተለየውም (ሉቃ.4፥17) ፤ ሲጠመቅም እንደርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ታይቷል (ማቴ.3፥16) ፤ በትንሣኤውም እግዚአብሔር የሞትን ጣር አጥፍቶለት (ሐዋ.2፥24) እንደቅድስና መንፈስ (ሮሜ.1፥4) ከሙታን መካከል ተነስቷል ፡፡

Thursday 5 May 2016

እውን ከጾምን ምንን ይሆን የተራብነው?


ጌታ ኢየሱስ ከጾመም በኋላ እንደሰውነቱ ተርቧል፡፡ “አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ” (ሉቃ.4፥2) እንዲል፡፡ ጾም የዝግጅት ጊዜ ነው ፤ የዝግጅት ጊዜም ስለሆነ ጌታ ወደአደባባይ አገልግሎት ከመውጣቱ በፊት ጾምን ጾመ፡፡ ከጾመ በኋላ ደግሞ መራቡን እናስተውላለን፡፡ በዓውዱ ያስተዋልን እንደሆን የተራበው መብልን ይመስላል፡፡ ዋናውና ትልቁ የጌታችን ረሃብና ጥም  ምግብና መጠጥ እንዳልሆነ ግን ቅዱስ ወንጌልን ስናጠና እናስተውላለን፡፡
   በአንድ ወቅት በሰማርያ፥ ደቀ መዛሙርቱ ምሳን ሊገዙ ወደከተማ ሄደው ቆይተው፥ ምሳን ገዝተው ሲመለሱ ጌታ ኢየሱስ ከአንዲት ውኃ ልትቀዳ ከመጣች ሴት ጋር ሲያወራ አገኙት፡፡ በአይሁድ ልማድ አንድ ረቢ (ወንድም ቢሆን) ከሴት ጋር (ሚስቱንም ቢሆን) በመንገድ ላይ አያናግርምና እርሷን ያውም ሳምራዊትን ሴት በማናገሩ ደቀ መዛሙርቱ ተደነቁ፡፡ ምሳ እንዲበላ በለመኑት ጊዜ “እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው” (ዮሐ.4፥32)፡፡ እነርሱ ከመምጣታቸው በፊት ከሴቲቱ ጋር የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መሠረታዊ ትምህርትን ሲያስተምራትና መሲሕነቱን እየነገራት ነበር፡፡ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳቸውም ስለምን ከሴቲቱ ጋር እንደሚያወሩ ጌታንም ሆነ ሳምራዊቷን ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም፡፡

Friday 29 April 2016

“ፋሲካ”ውን በኃጢአት ልንፈስከው ቀን ቀጥረን ይሆን?


እንኳን ለብርሐነ ትንሣኤው መታሰቢያ በዓል በሠላም አደረሳችሁ፡፡
      የእስራኤል ልጆች የብሉይ ኪዳኑን ፋሲካ በተለያየ ዘመን እንዴት እንዳከበሩት ስናስተውል እንዲህ የሚመስሉ ቁም ነገሮችን እናገኝበታለን፦
ü በሙሴ ዘመን፦ የመጀመርያው ፋሲካ እንዲፈጸም የተሰጠው ለሙሴ ሲሆን ይህም በፈርዖን ቤት የበኵር ልጅ ሲገደል፥ በቤተ እስራኤል ይህ መቅሰፍት እንዳይደርስና እንዲያልፋቸው (ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነውና) ይህም የዘለዓለም ሥርዓት እንዲሆናቸው ተሰጣቸው፡፡ (ዘጸ.12፥14) ለፋሲካው የሚቀርበው ጠቦት በግ “ነውር የሌለበት”(ዘጸ.12፥5) ነው፡፡ ይህ በግ የሚበላው በመራራ ቅጠል እርሾ ከሌለበት ቂጣ እንዲሆን ታዘዋል፡፡ በእነዚህ የበዓል ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የሚበላ፦ “ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ” (ቁ.15) የሚል ግልጥ ማስጠንቀቂያ አለ፡፡ ስለዚህም ከዚህና ከሌሎችም ማስጠንቀቂያዎች የእስራኤል ልጆች ራሳቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ (ዘኍል.9፥6)

Thursday 28 April 2016

ትዝታዬ ሁነኝ


                                         Please read in PDF

ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት መታሰቢያ በዓል እንኳን አደረሳችሁ፡፡


ሁሌ እራገማለሁ የአይሁድን ጥላቻ
ጌታ ኢየሱስን …
ለምን ጠሉት? ብዬ ሙግት ማንሳት ብቻ
ለምን ነው ይሁዳ? ለምን ነው ጲላጦስ?

Sunday 24 April 2016

ሆሳዕና - ንጉሥ ያለቀሰላት ከተማ (ሉቃ.19፥41)

Please read in PDF

“... ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ሉቃ.19፥41-44)


    መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል እንደመንፈስ ቅዱስ ተማሪ ቁጭ ብለን ስናጠና፥ ነቢዩ ኤርምያስ አልቃሻው ነቢይ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ኤርምያስን አልቃሻ ያሰኘው፥ የእስራኤልን መጥፋትና መማረክ ፤ የቤተ መቅደሱን መፍረስና የጐበዛዝቱን መውደቅ በተናገረ ጊዜ ሰሚ ማጣቱ ፤ የሕዝቡ አንገተ ደንዳናነት እጅግ ያበሳጨውና ያስለቅሰው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እጅግ ረጅም ጊዜ በማልቀሱ አልቃሻው ነቢይ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ነቢይ ሕዝብን ከእግዚአብሔር በአደራ ተቀብሏልና ሕዝቡ በነፍሱ ሳያርፍ፥ ሲቅበዘበዝ ፣ ሲንከራተት ... ሲያይ አብሮ መባዘኑ መንከራተቱ አይቀርም፡፡ እስኪመለሱም እጅግ በማዘን ይተጋላቸዋል ፤ በተመለሱም ጊዜ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ የነቢይ የዘወትር ደስታው የሕዝቡ በአምላኩ መንገድ መሆን ብቻ ነው፡፡