Thursday 13 October 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል አምስት)

መጽሕፍ ቅዱስና ዘረኝነት
መጽሐፍ ቅዱስ ዘረኛነትን በግልጥ ይቃወማል፡፡ ምክንያቱም ፦
1.    ሁላችን ከጥንት አንድና እኩል ነበርን ፤ ነንም!
    እግዚአብሔር ከጥንት የሰው ልጆችን ያየው በአንዱ ሰው በአዳም በኩል ነው፤ የሰው ልጅ በኃጢአቱ የወደቀውና የተበላሸው በአንዱ በአዳም በኩል ነው፤ (ሮሜ.5፥12)፡፡ እንዲሁ ወደአዲስ ኪዳንም ብንመጣ እግዚአብሔር አለምን ሁሉ በምህረት አይኑ ያየው በአንድ ልጁ በኩል ነው ፤ ማለትም እንደአንድ ቤተ ሰብ የቆጠረን በደሙ በተጠራነው ጥሪ ነው፡፡
    በክርስቶስ አንድ ወደሆንነበት ቅድስት ሕብረት ለመሰባሰብ መስፈርቱም ማንነትና ዘር ሳይሆን አብርሃማዊ እምነት መያዝ በቂ እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ “እምነት የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፤ ከመንፈስ ቅዱስም ይገኛል፤ (ገላ.5፥23 ፤ ኤፌ.2፥8 ፤ 2ተሰ.2፥13)፡፡ ሰው በእምነት ይጸድቃል፤ (ሮሜ.3፥28 ፤ ገላ.2፥16) ነገር ግን በእምነት ከክርስቶስ ጋር ስለሚተባበር፥ እግዚአብሔርን ሥራ መሥራት ይጀምራል (ኤፌ.2፥8-10) ስለዚህ ሰው እውነተኛ አማኝ መሆኑ የሚጣወቀው በሥራው ነው”፡፡ [1]

    የክርስቶስ ቤተ ሰብ ለመሆን እምነት ብቻ ከእኛ ከተጠየቀ፥ አብርሃማዊ ልጅነትን ማግኛው መንገድ ከዚህ በቀር የለም ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ጋር ቅዱስና ሕያው ግንኙነት ስላለን ማናቸውንም ልዩነት በመካከላችን ልናደርግ አይገባንም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ብሔር ተኮር ብቻ ሳይሆን ጾታዊ ልዩነት ልናደርግም አይገባንም፤ (ገላ.3፥28)፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሁላችን የሕይወትን ጸጋ (1ጴጥ.3፥7)፤ የመንፈስን ተስፋ (ገላ.3፥14)፤ የመለኮቱ ባሕርይ ተካፋዮችና እርሱን መምሰል (ቈላ.3፥10 ፤ 2ጴጥ.1፥4) ፤የዘላለም ሕይወት፤ ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው የሚጻፍ (ራእ.21፥27) ቅዱሳን ልጆቹ ነን፡፡
   ስለዚህ በምንም አይነት መልኩ ልዩነት ላይ በመቆም መለያየትን ልናመጣ አይገባንም፡፡ ሁሉን ባልንጀራችንን እንደራሳችን ልንወድ ይገባናል እንጂ፥ እኛ የተሻልን እንደሆን ልናስብ መጀመር ክርስቶስ ኖሮ ካስተማረን ቅዱስ ሕይወት በተቃራኒ መቆም ነው፡፡ ቅዱስ ቃሉ፦ “… እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር ፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን” (ፊልጵ.2፥3-5)ብሏልና፡፡
2.   ንድ እረኛና መጋቢ ያለን አንድ መንጋ ነን!
   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝብም ለአህዛብም ታማኝ እረኛ ነው፡፡“…መልካም እረኛ እኔ ነኝ” (ዮሐ.10፥11) ያለው ጌታ፥ “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ.5፥45) እርሱ የፍጥረት ሁሉ አባት ነው፡፡ እግዚአብሔር ማንንም ከማንም አስበልጦ አያይም፤ አያይም ብቻ አይደለም እንዲህ ያለ ሃሳብ በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፡፡የምድር ሁሉ ጌታና የምድርም ነገሥታት ሁሉ አምላክ  የሆነው እግዚአብሔር (ኢያ.3፥11 ፤ 1ነገ.19፥15) እርሱ በልዩነት አይን አያየንም፡፡ ለእግዚአብሔር ዓይኖች ምድር ሁሉ አንድ ናት፡፡
    ከምንም በላይ ደግሞ በልጁ ሞት የተጠራን አማኝ ክርስቲያኖች፥ የእርሱን እረኝነት የምናምነው ያለስስት ለበጐቹ እኩል ነፍሱን በመስጠቱ ነው፡፡ ለጳጳስም፣ ለቄስም፣ ለፓትርያርክም፣ ለድኃውም፣ ለሃብታሙም፣ ለጤነኛውም ለእብዱም፣ ፊደል ለቆጠረውም ላልቆጠረውም … እኩል ስለመዳናችን የፈሰሰው የክርስቶስ ደም አንድ ነው፡፡በክርስቶስ ለምናምን እግዚአብሔር አንዱን ብሔር ከሌላው አስበልጦ እንደሚያይ ማሰብ እጅግ አስነዋሪ ነገር ፤ ርኩሰትም ነው፡፡
3.   ቤተ ክርስቲያን አንዲትና ሁሉን አቀፍ ናት!
    ሐዋርያት የሰበሰቧት ቤተ ክርስቲያን አንዲትና ቅደስት ናት፤ በዘር፣ በሃብት፣ በማንነት፣ በዕውቀትና በሌሎችም ነገሮች በመካከሏ ፈጽሞ አንዳች ልዩነት አልነበረም፤ (ሐዋ.2፥44-45)፡፡ የክርስቶስም ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን ለዘወትር በአንድ ሃሳብና ልብ ትሆን ዘንድ ነው፤ (ማቴ.18፥20)፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድ ልብ ከመሆን በቀር ማናቸውም መለያየትና መከፋፈል በመካከሏ ሊሰማ አይገባም፤ (1ቆሮ.1፥11-15) ምክንያቱም ክርስቶስ አልተከፈለምና፡፡
    ከቤተ ክርስቲያን ባሕርያት አንዱ ቅድስት ሲሆን ሌላው ሁሉን አቀፍ መሆኗ ነው፡፡ አንድ ስለሆነች መከፋፈል የለባትም ፤ ሁሉን አቀፍ ናትና ደግሞ ሁሉን የመቀበል እጅ ይኖራታል ወይም ከመቀበል የተለየ ምክንያት አይኖራትም፡፡
4.   ከዚህም ተዋጅተናል!!!
“ … በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው ፤ … ” (ራእ.5፥10)

   ለሰው ልጆች በተደረገው ድንቅ ውጅት ቅዱሳን መላዕክት ያሰሙት ዝማሬ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሞቱ ዐቢይ ሥፍራ የተሰጠው እኛን ከቋንቋ ፣ ከወገን ፣ ከሕዝብ ሁሉ በመዋጀቱ ነው፡፡ ስለተዋጀንም ነው፥ “ … አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”(ገላ.3፥28) በማለት ሐዋርያው ግልጥ መልዕክት የጻፈልን፡፡ አዎን! ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ያለን ፍጹም አንድነት በዘርም፤ በጾታም አንዳች ገደብና ልዩነት አይደረግበትም፡፡
   በእርግጥም፥ እኛ የአብርሃም ዘር ነን ፤ ቀድሞ አብርሃም ፣ በሥጋም በመንፈስም ለአይሁድ ሕዝብ አባት ነው፤ (ዮሐ.8፥31 ፤፤ 33 ፤ 39 ፤ 53 ፤ ሐዋ.7፥2 ፤ ሮሜ.4፥12) ለእኛም ደግሞ፦ “ … እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፥ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።” እንደተባለ አብርሃም በእምነት አባታችን ነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን ከቤተ አይሁድም ከቤተ አህዛብም የሆኑ አማኞችም ሁሉ የአብርሃም መንፈሳውያን ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህም የአብርሃም ዘር ተብለው ይጠራሉ፤ (ዕብ.2፥16)፡፡
    እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ካመንን፥ ከአብርሃም ዘር ውጪ የሌላ ዘር ፈጽሞ መሆን አይቻለንም፤ ቤተ ክርስቲያን ከዘረኛነት መርገም በአብርሃም ዘር አንድነትን ገንዘብ አድርጋ፤ ተዋጅታ፤ ነጻ ከወጣች በኋላ ዳግም የዘረኛነትን ነውር ልታነሳው፤ አንስታም በልጆቿ መካከል ልዩነትን ልታደርግበት አይገባትም፡፡ ይህን የምታደርግ ከሆነ ሊዋጀን ደሙን ያፈሰሰውን ፦ “ … የእግዚአብሔርን ልጅ ትረግጠዋለች ፤ የኪዳኑንም ደም እንርኩስ ትቆጥረዋለች ፤ የጸጋውን መንፈስ ታክፋፋለች” (ዕብ.10፥29) በክርስቶሰ ደም ነጻ ከወጣን በኋላ፥ ነጻነታችንን ትተን ዘርና ነገድ መቁጠር ብንጀምር በእርግጥም የተደረገልንን ክደናል፤ አክፋፍተነዋልም፡፡ እንድናስተውል የደሙ ጉልበት ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...



   [1] የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ የመጸሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፤ 2002 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ. 178

No comments:

Post a Comment