Tuesday 28 March 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሰባት)

                                                         Please read in PDF

7.   አገልጋይ ለጌታው በፍጹም ፈቃዱና በፍጹም ሃሳቡ መታዘዝ ይገባዋል፦ ከሕጉ ትዕዛዛት አንዱ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” (ዘጸ.20፥3) የሚል ነው፤ ይህ ቃል የምሥራቅ ዓለሙን ሁሉ አምላኪነት የሚቃወም ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል እግዚአብሔርን በመፍራትና በማክበር ልታመልከው እንደሚገባ ፍጹም አመልካች ሕግ ነው፡፡ ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ሌሎችንም ሃሳቦች በውስጡ ይዟል፡፡ ይኸውም (1) አማኞች ቅዱስ ለሆነው እግዚአብሔር ከአማልክትና ከርኩሳን አጋንንት ራሳቸውን በመለየት መቀደስ አለባቸው፡፡ ከከንቱ አማልክትም መራቅ ይገባቸዋል፡፡ ይህ የቆሙትንና የሚሰገድላቸውን አማልክት ብቻ ይይደለ፣ ከእግዚአብሔር ያስበለጥነውን ወይም ያስተካከልነውን ማናቸውንም ነገራችንን ይመለከታል፡፡ (2) አማኞች እግዚአብሔር በጎውን ነገር ብቻ እንደሚሰጣቸው  በማመን በፍጹም ኃይላቸውና ፈቃዳቸው፤ ሃሳባቸውም ሊያምኑትና ሊታዘዙለት ይገባል፤ (ዘዳግ.6፥5 ፤ ፊልጵ.3፥8)፡፡

Sunday 19 March 2017

“እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” (ማቴ.24፥25)

                                          Please read in PDF

   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃሎች መካከል፣ በደብረ ዘይት ለደቀ መዛሙርቱ ስለዳግመኛ መምጣቱ ምልክቶች የተናገረው አንዱና ሠፊውን ክፍል የያዘ ነው፡፡ በውስጡ ብዙ ነገር መናገሩን ወንጌላዊው ጽፎልናል፡፡ በመካከሉም ቅዱስ ማቴዎስ፣ ጌታችን “እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” ብሎ መናገሩን ከጻፈልን የወንጌል ቃል ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ጭብጦችን ማውጣት እንችላለን፤ ይኸውም፦
1.      ጌታችን ሁሉንም ነገር የነገረን  በግልጥ ነው፦ ጌታ ለእኛ ከሚያስፈልገን  ቀድሞ ያልተናገረን ምንም ነገር የለም፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ሊሆንና ሊመጣ ያለው ነገር ሁሉ ተነግሮናል፡፡ በዚህ ምድር ሕይወት ስላለው ብርቱ ሰልፍነት፣ ታ ኢየሱስንም አምነን በመከተላችንም ሆነ ሳናምን በመከተላችን ስለሚገጥመን ሕይወትና ሞት፣ ስሙን አምነን በመከተላችንና በመመስከራችን ስለሚያገኘን ነቀፋ፣ ስድብ፣ ግርፋት፣ ስደት፣ ስም ማጥፋት፣ ርስትና ጉልት ማጣት፣ በቤተሰብ ሁሉ ዘንድ ከበሬታና ቦታ መነፈግ፣ መጠላትና መገለል፣ መገደል፣  ... እኒህ ሁሉ አስቀድመው የተነገሩ ናቸው፤ (ማቴ.10፥16 ፤ 24፥9 ፤ ዮሐ.15፥19)፡፡

Monday 13 March 2017

አትተወን

የትዳር አልጋችን ረከሰ ከየሰ
የኪዳን ቃላችን ሳይውል ፈራረሰ
ከባልንጀራ ጋር በሐሜት ተራኩተን
አንድ ነን እያልን አለቅን ተበላልተን፡፡

Wednesday 8 March 2017

“የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ”

  
    ልክ ዛሬ፣ የዲያቆን አቤንኤዘር ተክሉ ገጽ በሚለው የጡመራ መድረክና(Blog) በፊት ገጽ(Facebook) መጻፍ ከጀመርኩ አራት ዓመታትን አስቆጠርኩ፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በጌታ ጉልበትና ቸርነት፤ በመንፈስ ቅዱስም እርዳታ ሃሳብን በማስፈር ቀስ ብዬ እየዳኽኩ፤  እያደግሁ መጥቻለሁ፤ ገና ወደፊትም ጌታ እንደረዳኝ ብዙ እንደምሠራ መሻቴ ነው፤ ግና ጌታ ብቻ እንደፈቀደ ይሁን፤ አሜን፡፡ ምኞቴና መሻቴ አንዱንና የሞተልኝን ጌታ ኢየሱስን በዘመኔ ሁሉ አክብሬ ማገልገልና ማረፍ ነው፤ ለእርሱ ኖሮ መሞት መታደል፤ እጅግ ወደር የለሽ ክብር ነው!

Sunday 5 March 2017

ምኩራቡን ለምኩራቡ ጌታ አገልግሎት!

    
Please read in PDf
  የእስራኤል ልጆች በስደት ምድር በባቢሎን ሳሉ፣ በኢየሩሳሌም የነበረው ዋናው ቤተ መቅደስ  ስለፈረሰና በምርኮ ምድር ደግሞ ቤተ መቅደስ መሥራት ስላልተቻላቸው ለጸሎት፣ ቃሉን ለማንበብና ለማጥናት እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ለማሳደግ ምኩራብን በየአቅራቢያቸው ሠሩ፡፡ በምኩራቡ ውስጥም በየቀኑ የሚነበቡ የተለያዩ የሕግና የነቢያት የብራና ጥቅልሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎችን አስቀመጡ፡፡
   የእግዚአብሔር እውነተኛ ሕዝብ በየትኛውም ሥፍራና ሁኔታ ሊያስቀድመውና ሊጠነቀቅለት የሚገባው ነገር ከአምላኩ ጋር ያለው ዝምድና፣ ትስስሩና ግንኙነቱ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ግንኙነት ሊያሳስበው፤ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በምቹና የተደላደለ ትርፍ ሰዓት ባለው ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁን በስደት፤ ፈጽሞ ምንም ዓይነት ዕድል ላይገኝ በሚችልበት መንገዱ፣ የጌታ ነገር ቀዳሚና ትኩረቱን ሳቢ ሊሆን፤ በሕይወቱም ጭምር ሊሰጥለት ይገባል፡፡