Monday 5 December 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና - (የመጨረሻ ክፍል)

2. ሕበረ - ሰበ መስቀሉን ማብዛት፤
    ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀሉ ሞት መልካሙን ያደርጉ ዘንድ አዲስ ማሕበረሰብን ፈጥሯል፡፡ ይህን ማሕበረሰብ ያዋቀረው ደግሞ “… ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቆ ነው (ኤፌ.2፥10 ፤ 16)፡፡ “ሁለታቸው” የተባሉት “በሥጋ አሕዛብ የነበሩት፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባሉትና” (ኤፌ.2፥11)፤ ቤተ እስራኤል ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱም አንዳች የዘርና ቀለም፤ የቋንቋና የነገድ ልዩነት ሳይኖር ነው፡፡
“ … አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል”
(1ቆሮ.12፥13)
እንደተባለ ክርስቶስ ኢየሱስ ልዩነትን ሽሮልናል ብቻ ሳይሆን ፍጹም አንድነትን እንኖርበት ዘንድ ሰጥቶናል፡፡

    ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ጉዳይ እጅግ በጣም በአድናቆት ያነሳዋል፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ፤ ከትልቅ ዘር መወለዱንም ሁሉ ለክርስቶስ ሲል እጅግ አድርጎ ይንቀዋል፡፡ በሥጋ ማስመካት የሚያስችል ነገር ቢሆንም፥ መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት ግ አንዳች አይጠቅምም፡፡ ስለዚህም እንዲህ አለ፦
“ … በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ”
    የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ከገጠሙት አስከፊ ተግዳሮቶቹ አንዱ፥ “በብሔርህ ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና እንዴት ትረሳለህ? … ብሔርህን ባትወድ፤ ወገንህን ባታከብር ነው” የሚል ነው፡፡ [1]በእርግጥም ከቅዱስ ጳውሎስ የተሻለ መልስ የለኝም፤ አይኖረኝምም፡፡ ለጥላቻስ መልሱ ጥላቻ ነውን? አይን ላጠፋ ምላሽ አይንን መቦጥቦጥ ነውን? ከፍቅር የሚያንስ ኃይልን ሰው ለሚባለው ሰው መጠቀማችን እንዴት ምስኪን መሆናችንን ያሳብቅብናል፡፡ አዎን! ሁላችን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ነን፤ (2ቆሮ.5፥17) ዳግም የአሮጌውን ሰው ልብስ ልናስወግደው እንጂ ልንለብሰው አይገባንም፤ (ኤፌ.4፥22)፡፡
    ትላንት አይሁድና አህዛብ፤ አይሁድና ሳምራውያን (ዮሐ.4፥9) ጨርሶ ሊቀራረቡበት የሚያስችል አንዳች መስመር አልነበረም፤ የክርስቶስ ሞት ግን ይህን የልዩነት ድልድይ ሰብሮታል፡፡ አህዛብም፤ ሳምራውያንም ወደወይን ግንዱ ተጨምረዋል፡፡ መጨመር ብቻ አይደለም፤ ሐዋርያ እስከይሁዳ ብቻ ሳይሆን እስከሰማርያና እስከአሕዛብ ምድር ድረስ ሄደው እንዲያስተምሩም ታዘዋል፤ (ማቴ.28፥19 ፤ ሐዋ.1፥8)፡፡ ስለዚህም የቀደመውን የልዩነትና የጥላቻ ድርጊትን እያነሳን የዛሬውን መልካምና በክርስቶስ ሞት የተሰጠንን የአንድነት ክብራችንን መናቅም የለብንም፡፡
3. መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መገዛት
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ … ይነሣልና” (ማቴ.24፥7)
     በዘመን ፍጻሜ ሊሆኑ ካሉ ታላላቅ የጌታ ትንቢቶች መካከል አንዱ፥ ከላይ ያለው የትንቢት ቃል ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚነሳው አንዱና ዋናው መንፈስ የዘረኛነት መንፈስ ነው፡፡ አለም በቴክኖሎጂው አንድ መንደር ሆናለች ቢባልም፥ የዚያኑ ያህል የሰፋ ልዩነትና አለመቻቻልም ነግሦባታል፤ በዕውቀት ያልተዳሰሰው ርዕስና ንዑስ ርዕስ የለም ቢባልም፥ ዘረኝነትን ግን ማጥፋት ቀርቶ “ባለበት ማቆም” ካለመቻሉም አልፎ ብዙዎችን ወጥመዱ ጠልፎ እየጣለ ነው፡፡
  አንዱ ሕዝብ በሌላው ሕዝብ ላይ ሊነሣ፣ ሌላውን ሕዝብ ሊጨቁን፣ ሊበድልና ሊያግፍ መንፈሱ በትዕቢት ሲታጀልና ሌላውን እንደአናሳ ወይም የበታች አድርጎ መቁጠር ሲጀምር ነው፡፡ ይህ በዓለም ታሪክ በተደጋጋሚ የተፈጸመመ አስነዋሪ ትዝታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ዓመጽ ሲበዛ ይህ ሊሆን እንዳለ በግልጥ ይናገራል፡፡ 
    “ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” (ማቴ.24፥12) ፍቅር ሁለት አክናፍ አለው፤ እርሱም “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” (ሉቃ.10፥27) የሚል ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሲቀዘቅዝ፤ ሲጠፋ ሰው፤ ሰው ብቻ እንደሆነ ያስባል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በስንፍናና በሥጋ ጠባይ ይወረሳል፡፡ የዚያኔ “በልቡ እግዚአብሔር የለም ያለው ሰነፍ” (መዝ.14፥1 ፤ 53፥1) እግዚአብሔርን ከመሳደብ(ኢዮ.2፥9) በገዛ ወገኑም ላይ ግፍን ከመሥራት ስለማይመለስ ምድር ከእርሱ የተነሳ ትጨነቃለች፡፡
ተፈጸመ፡፡

ዋቢ መጻሕፍት
o   የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት  9ኛ እትምየኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ 2002 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
o   ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
o   ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ 1962 ዓ.ም፤ አሳታሚ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
o   ማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፤ 1978 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፡፡
o   ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
o   መስፍን ወልደ ማርያም፤ መክሸፍ እንደኢትዮጲያ ታሪክ፤ 2005 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚው ያልተጠቀሰ፡፡
o   ምኒልክ አስፋው፤ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ርእሰ ጉዳዮችና ተግዳሮቶች፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ራእይ አሳታሚ፡፡
o   ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፡፡ አሳታሚው አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
o   አባ(ጳጳስ) ጐርጐርዮስ ፤ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ  ሁለተኛ እትም፤ 1986 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡
o   ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ፤ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ሐረግ ምንጭ፤  ሐምሌ 2008 ዓ.ም፤ ቫሌሆ፣ ካሊፎርኒያ፤ አሳታሚ ኔባዳን ኃላ. የተ. የግል ማኅበር፡፡
o   አዘጋጅ ያልተጠቀሰ፤ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፡፡ 1982 ዓ.ም፤ ኣሳታሚ ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት፡፡
o   የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም፡፡
o   ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን)፤ ስማችሁ የለምና ሌሎችም፤ 2006 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ አግዮስ ኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላ.የተ. የግል ማኅበር፡፡
o   ተስፋዬ ገብረአብ ፤ የደራሲው ማስታወሻ፤ 2002 ዓ.ም፤ ዋሽንግተን ዲሲ፤ ነጻነት አሳታሚ፡፡
o   ተስፋዬ ገብረአብ፤ የጀሚላ እናት፤ 2014 ዓ.ም፤ ምጽዋ - አሥመራ፤ አሳታሚው ያልተጠቀሰ፡፡
o   መልአከ ብርሃን ብርሃኑ ብሥራት ፤ ኑሮና ክርስትና በአሜሪካ ፤ 2001 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ኤች ዋይ የኅትመት ሥራ ድርጅት ኃላ. የተወ. የግል ማኅበር፡፡
o   አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጲያ፤ 1901 ዓ.ም ፤ ሮም፡፡
o   በላይ ግደይ፤ የኢትዮጲያ ሥልጣኔ፤ 1983 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ፡፡
o   Rawlinsons , Ancient Monarchies, vol 1






    [1] ይህን ሙግት የሚያነሱ ሰዎች፥ የገዛ ብሔርን መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ትርጉም የላቸውም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በግል በሥራ አለም ብዙ የማውቃቸው እንዲህ ያሉ ወገኖች ለገዛ ወገናቸው ለቤተሰባቸውና በቢሮ ደረጃ ለሚያስተናግዷቸው ባለ ጉዳዮች እንኳ አግባብነት ያለውን ምላሽ በቅንነት ሲሰጡ አላይም፡፡ በቅንነት ብንተረጉመው እንኳ፥ ወገንን መውደድ ማለት ባለንበት የሥራ ኃላፊነት ተገቢውን አገልግሎት “ወገን ለሚሉት” እንደሕጉ መስጠት ብንችል ቢቻላቸውና፥ ለቤተሰባቸውም የሚገባውን ክብር በመስጠት ቢኖሩ እንደሰብዓዊ ማንነት እጅግ የተሻለ ነው፡፡ መቼም በቅርብ ያለውን ሳይወዱና ሳያከብሩ ባዕድ ምድርን እየናፈቁ፥ የሩቁን ሰውና ማንነትን መውደድ ጤናማነት ማለት እጅጉን ይከብዳል፡፡
     በተለይም በአሁን ሰዓት በአገር ቤት ያሉት የባዕዱን እየናፈቁ፥ በውጭው ዓለም ያሉት ደግሞ በርቀት ካሉበት ከዚያ የሚዘሩት የዘረኝነት እንክርዳድ ራሳችንን “የት ነው ያለነው?” ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ በአንድ ጎጥና ብሔር ተሰንጎና ተጎንፎ ለአገር፣ ለአኅጉርና ለዓለም ሰላምና አንድነት ለቤተ ክርስቲያን ልማትና መለምለም ማሰብ ከቅዠት በቀር ምንም ልንለው አይቻለንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዝታ የተባዛችው በሞቱና በትንሣኤው ኃይል ብቻ ሲሆን፥ አገርና አኅጉርም እንደወንዝ በማያቋርጥ ሰላምና አንድነት ውስጥ ተዘልለው ሊኖሩ የሚችሉት ከዘርና ከወንዝ በዘለለ ሰብዓዊ አንድነት ውስጥ በአንድነት ሊጣመሩ ይገባቸዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment