Please read ion PDF
ዛሬ ካነበብኩት መጽሐፍ እናንተም እንድትካፈሉ ወደድሁ፤ እናም ታነብቡት ዘንድ ይኸው ጋበዝኳችሁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ዛሬ ካነበብኩት መጽሐፍ እናንተም እንድትካፈሉ ወደድሁ፤ እናም ታነብቡት ዘንድ ይኸው ጋበዝኳችሁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
መሪ
አንባቢ ሆይ! በዚህ መጽሐፍ ከመጀመርያ እስከመጨረሻ ወደ ምሥራቅ ሔድሁ፤ ወደምዕራብ ተመለስሁ፤ ወደሰሜን ሔድሁ፤ ወደደቡብ ተመለስሁ እያለ
ተጽፎ ይገኛል፡፡ ምሥራቅ ሲል መጻሕፍተ ሐዲሳት ማለቱ ነው፡፡ ምዕራብ ሲል መጻሕፍተ ብሉያት ማለቱ ነው፡፡ ሰሜን ሲል የሊቃውንት
መጻሕፍት ማለቱ ነው፡፡ ደቡብ ሲል አዋልድ መጻሕፍት ማለቱ ነው፡፡ ዓለም ያለ እንደሆመ ግን መጻሕፍትን ሁሉ ማለቱ ነው፡፡ ይህንም
ካስታወቅሁ በኋላ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ የሚለው ሀገር እንዳይመስላችሁ፡፡ እግዚአብሔር የልጁን የክርስቶስን ብርሃን በልባችሁ
ውስጥ ያብራላችሁ፡፡ አሜን፡፡ ፪ጴጥ.፩፥ ፲፱፡፡
ምዕራፍ ፪
ስለሁለተኛው
ዛፍ
ከዚህም በኋላ ወደምሥራቅ ሀገር ዞርሁ፡፡ በዚህም ሀገር፤ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣
ሉቃስ፣ ዮሐንስ፣ የሚባሉ ሰዎች ጌቶች ሆነው ይኖራሉ፡፡ ወደእነርሱም ደጅ የማይደርስ ሰው የለም፡፡
እኔም ወደ እነርሱ ቤት ስሔድ በመንገድ ዳር አንድ ዛፍ አገኘሁ፡፡ ይህም
ዛፍ በቁመትም፣ በመልክም፣ በፍሬም ያንን በመጀመርያ ያየሁትን ዛፍ ይመስላል፡፡ ዮሐ.፲፬፥፱፡፡
በጥላውም ውስጥ ጥቂት አረፍሁ፡፡
ከዚህም በኋላ ለመሔድ ተነሣሁ፡፡ ጥቂትም እንደ ሔድሁ፤ ዘወር ብዬ ብመለከት
ያ ዛፍ ፍጹም ሰው መስሎ ታየኝ፡፡ ዕብ.፪፥፱፣፲፬፡፡
እስኪ ባላገሮችን ልጠይቃቸው፤ ከቶ ይህ ዛፍ እንደምን ይሆን ብዬ ወደመንደር መሮጥ ጀመርሁ፡፡ ወደመንደርም
ሳልደርስ ዳግመኛ ዘወር ብዬ ብመለከተው ፍጹም ዛፍ መስሎ ታየኝ፡፡ ዮሐ.፲፥፴
ከዚህ በኋላ ግን ያየኝ ሰው ይስቅብኛል ብዬ መንገዴን ሔድሁ፡፡ ያ የመንገድ
መሪ የሆነኝ ሰው ከኔ ቀድሞ ሔዶ ነበርና ቶሎ ብዬ ደረስሁበት፡፡ የዛፉንም ስም ያውቀው እንደሆነ ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም የዛፉ
ስም ብዙ ነው፡፡ አማኑኤል ክርስቶስ ኢየሱ ይባላል አለኝ፡፡ ማቴ.፩፥ ፳፫-፳፭፡፡
ያፈራልን? አልሁት፡፡ እንዴታ፤ ፍሬው ስንኳ እጅግ ጣፋጭ ነው፡፡ የሚያፈራውም
ካመት ዓመት ነው፡፤ የዚህም አገር ሰዎች ከዚህ በቀር ሌላ ምግብ የላቸውም፡፡ ከእርሱም የሚበላ ለዘላለም አይራብም አለኝ፡፡ ዮሐ.፮፥፴፭
እኔም እጅግ አደነቅሁ፡፡ ማድነቄም ምግብነቱ ከሀገሬ ምግብ ልዩ ስለሆነ
ነው፡፡ ዮሐ.፮፥፶፰፡፡
የሀገሬ ምግብ እንጀራና የከብት ሥጋ ነው፡፡ ያውም ማታ በልተውት ለጧት
አይገኝም፡፡ እንዲህም እየተደነቅሁ ስሔድ ሐራ ጥቃ የሚባሉ ሰዎች አገኘሁ፡፡ ስለዛፉም ጠየቅኋቸው፡፡ እነርሱም በውነት ዛፍ ነበረ፡፡
አሁን ግን ዛፍነቱ ቀርቶ ሰው ሆኗል አሉኝ፡፡ እኔ ግን ስቄባቸው ሔድሁ፡፡ ጥቂትም ከሔድሁ በኋላ አውጣኪን አገኘሁት፡፡ ስለዛፉም
ጠየቅሁት፡፡ እርሱ ግን ወደኔ ዘወር ብሎ ጤና የለህምን፤ ሰው መምሰሉ ከቀረ በስንት ዓመቱ፡፡ ዛሬማ ፍጹም ዛፍ ሆኖ የለምን አለኝ፡፡
እኔም ስቄበት መንገዴን ሔድሁ፡፡
ከዚህ በኋላ ሳላስበው በድንገት ወደ ሰሜን ዞርሁ፡፡ በሰሜን ያሉ ሰዎች የዛፉን
ነገር ጠንቅቀን እናውቃለን ይላሉ፡፡ እኔም ወደእነርሱ ሔጄ ጠየቅኋቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ነው፤ ሁለት ነው በማለት ክርክር ይዘው
ነበሩና እኔን ከቁም ነገር ስላልቆጠሩኝ የእነርሱ ክርክር መጨረሻ ሳይኖረው ጊዜ በዚህ ቆሜ ልቀር ነውን፤ ብዬ ወደምሥራቅ ዞርሁ፡፡
በምሥራቅም ያሉ ሰዎች አንድ መሆኑን ዘወትርም ዛፍና ሰው መስሎ መታየቱን አስረዱኝና እጅግ ደስ አለኝ፡፡ ማቴ.፫፥፲፯፤ ፩ቆሮ.፰፥፮፤
ዮሐ.፱፥፴፮ - ፴፰፡፡
ምዕራፍ ፫
ስለሦስተኛው ዛፍ
በዚሁ በምሥራቅ ሀገር ከወዲያ ወዲህ ስመላለስ በነፋሻ ስፍራ የበቀለ አንድ
ዛፍ አገኘሁ፡፤
ይህም ዛፍ በልምላሜው በቅጠልም በርዝመትም አስቀድሞ ያየኋቸውን ሁለቱን
ዛፎች ይመስላል፡፡ የበቀለበት ሥፍራ ተራራማ ስለሆነ ይወዘውዘው ነበር፡፡
የዚህንም ነገር እየመረመርሁ ስሄድ መቅዶንዮስን አገኘሁት፡፡ የዛፉንም ነገር
ያውቀው እንደሆነ ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም እንዲህ የሚያስደንቅህ የዚህ የዛፍ ነገር ነውን፤ ከዚህ የሚበልጡትን ሁለቱን ዛፎች አይተህ
በሆነ ምንኛ ባደነቅህ ኖሯል፡፡
ይህ ዛፍ በሁለቱ ዛፎች ዘንድ የቁጥቋጦ ያህል ነው አለኝ፡፡ እኔ ግን
ስቄበት ሔድሁ፡፡ ጥቂትም እንዳለፍሁ ዘወር ብዬ ብመለከት ያ ያየሁት ዛፍ እንደ ርግብ ክንፍ አውጥቶ ሲበር አየሁት፡፡ ከዚህም በኋላ
እያደነቅሁ መንገዴን ሔድሁ፡፡ ያ ወዳጄ ልቤም ካማርኛ ይልቅ የግዕዝ ቋንቋ ያውቅ ነበርና ወመንፈስከ ቅዱስ ኢታውፅእ እምላዕሌየ፡፡
ወበመንፈስ አዚዝ አጽንዓኒ፡፡ አይቴኑ አሐውር እመንፈስከ እያለ ዳዊት መዝሙር ይዘምር ጀመረ፡፡ መዝ.፶፩፥፲፩ ፣ ፻፴፱፥፯፡፡
(ምንጭ፦ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፤ ወዳጄ ልቤና ሌሎችም፤ 2002 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤
አሳታሚ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ፤ ገጽ.2-5)
No comments:
Post a Comment