Friday, 12 April 2024

በብልጽግና ወንጌል የተለከፈ …

 Please read in PDF

በእግዚአብሔር ጸጋ ፍጹም አምናለሁ፤ ዳሩ ግን በ”ብልጽግና” ወንጌል አንዴ የተለከፉትን፤ እነርሱን በንስሐ ማደስ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርቱ፣ የቀደሙትን ሰዎች አዳምና ሔዋንን እንዳሳተው አሳች፣ አንተን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስተካክል አጋንንታዊ ትምህርት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ዶክተር ተካልኝ “የጸሎት-ንግድ ቤት” በሚለው መጽሐፉ እንዲህ በማለት የሚጠይቀውና የሚመልሰው፣

“… በእግዚአብሔር ማመንን ወደ “እንደ እግዚአብሔር ማመን” ቀይሮ ክርስትና የሚባል እምነት ይኖራልን? ፈጽሞ፤ … የትምህርቱ ኹሉ ነገር እምነት በሚባል አስገዳጅ ኃይል እግዚአብሔርን ጨምሮ ነገሮችን ኹሉ ለሰው ጥቅም ማስገዛት እና ማስገበር ነው፡፡” (ገጽ 60) ይላል፡፡



በትምህርቱ ኖረው፤ ኖረው ወጡ የሚባሉ ሰዎች ራሳቸውን ወደ እግዚአብሔር ሊያሳድጉ ሲጋጋጡና እንደ እግዚአብሔር ለመኾን ሲራኮቱ የነበሩ ናቸው፣ “ከተመለሱ” ወይም ተመልሰናል ካሉ በኋላ፣ ራሳቸውን እንደ ፍጡርና ከእግዚአብሔር ውጭ ባዶና ምንም መኾናቸውን ተረድተው፣ ወደ እግዚአብሔር አምላክ ለመጸለይ እጅግ ይፈተናሉ፡፡ ለዚህም ቀንደኛ የዶክትሪኑን አማኝና አስተማሪ የነበሩትን በምሳሌነት ልጥቀስ፦

"I was wrong" በሚለው መጽሐፉ የሚታወቀው ጂም ቤከር፣ ከዚህ አደገኛና መርዘኛ ትምህርት “ተሳስቼ ነበር፤ አኹን ግን ተመልሻለኹ” ከማለቱ በፊት፣ የግል “ቤተ ክርስቲያኑን አማኞች” ገንዘብ፣ ወደ ግል የሂሳብ ደብተሩ በማዘዋወርና ለግሉ በመጠቀሙ፣ በዝሙት፣ በግብር ማጭበርበርና በሌሎችም ክሶች ተከስሶ 48 ዓመታት ተፈርዶበት፣ ጤናው በመቃወሱና በሌሎችም ምክንያት “በአመክሮ” ከስምንት ዓመታት እስር በኋላ ተፈታ፡፡

ይህ ሰው ግን “ተመልሻለሁ” ብሎ ኑዛዜውን በመጽሐፍ ካሳረፈ በኋላ፣

  1. ብዙም ሳይቆይ “ብርማው መፍትሔ” ብሎ በሰየመው “መድኃኒት” በብርማ ጠርሙስ የተሞሉ ፈሳሾችን ኮሮናን ብቻ ሳይኾን ሳርስ፣ ኤድስን እና ኢቦላን ሁሉ ድምጥማጣቸውን ያጠፋላችኋል" በማለት በ80 ዶላር “ቤከር ሾው” በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያው ለገበያ አቅርቧል።
  2. ሌላው ደግሞ በገዛ የቴሌቭዥን ጣቢያው ላይ የሚያስተዋውቀውና በ135 ዶላር የሚሸጠው 154 ምግቦችን የያዘ የ50 ቀን "ሰርቫይቫል ምግብ" አዘጋጅቶ ይቸበችባል። ምግቡ ሊመጣ ባለው “በመከራ ዘመን” ምግብ ስለማይገኝ፣ የመከራ ዘመንን መሻገሪያ ምግብ ነው የሚል ማስታወቂያም አለው።

ጂም ቤከር ብቻ ሳይኾን ቤን ሂንም ከዚህ መርዘኛ ትምህርት ተመልሰናል ቢሉም፣ ነገር ግን ኹለቱም "ከተመልሰናል ንስሐቸው" በኋላ እዚያው ስህተታቸው ላይ ይንደባለላሉ። ለምን? መመለስ ተግባራዊ የንስሐ ፍሬ ከሌለው ከንቱ ነው፤ በተለይ ከብልጽግና ወንጌል! መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ነው፣ የእግዚአብሔርን ጸጋ ተለማምደው የሚክዱትን ለመመለስ አዳጋችነቱን ሲናገር፣

አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።” (ዕብ. 6፥4-6)

“በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።” (2ጴጥ. 3፥20-22)

እናም፣ “ከብልጽግና” ወንጌል ኑፋቄ የተመለሱትን፣ “ተመልሰናል” ስላሉ ብቻ፣ ቤተ ክርስቲያን “ሾላ በድፍኑ” ብላ ብትቀበላቸው ከፊተኛው ስህተቷ በኋለኛው ተግባርዋ የባሰ ስህተት እንዳትሠራ እፈራለሁ፡፡ ዛሬ ላይ በአገራችንም “ተመልሰናል” በሚሊት በመመለሳቸው ደስ ይለናል፤ መመለሳቸው ግን እውነተኛ የንስሐ ፍሬ እስኪያሳይ ድረስ መታገሥ፣ ፈጥኖ ለአገልግሎትና ለምስክርነት ማስቸኮል ተገቢ አይደለም!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment