Sunday, 30 August 2020

የልጁን መልክ መምሰል (ክፍል ፩)

Please read in PDF

    “ሁላችን በሃይማኖትና የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ፍጻሜ ልክ የአካል መጠን እንዲደርስ ፍጹም ሰው እንሁን” (ኤፌ.4፥13)

መግቢያ

    በዘመናችን ሰዎች ክርስቶስን በትክክል መኾን እንደሚቻላቸው አያሌ የስህተት ትምህርቶችን መስማት ከጀመርን ሰነባብተናል። አንዳንዴ ክርስቶስን የፍጥረቱ አካል በማድረግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እኛ ራሱ ክርስቶስን ልንኾን እንደምንችል በአደባባይ ታውጆአል፤ በተለያየ መንገድ ይህን ትምህርት ፊት ለፊት በመቃወም፣ የትምህርቱን ስሑትነትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተቀዳ መኾኑን ተናግረናል፤ አስተምረናል። ዛሬም ክርስቶስ የፍጥረት አካል እንዳይደለ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩንን፣ ፍጹም አምላክነቱና ፍጹም ሰውነቱን  ደፍረን እንናገራለን።

   ትምህርቱን በምንቃወምበት ትይዩ ደግሞ እውነተኛውን ትምህርት ማስተማር ይገባናል፤ ስለዚህም፣ ከዚህ በኋላ “ወደ ክርስቶስ ማድግ” በሚል ርእስ፣ በተከታታይነት ወደ ክርስቶስ ከምን ተነስተን እንዴት ወደ ክርስቶስ እንደምናድግ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ያገኘነውን እናስተምራለን። በግልጥ ቃልም ወደ ክርስቶስ ማደግ ማለት፣ ክርስቶስ ራሱን አለመኾንና የእርሱ ገንዘብ መኾን እንደ ኾነ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ደፍረን እንመሰክራለን፤ እንናገራለን።

የትመጣችን!

     እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ እኛን በእርሱ መልክና አምሳል ፈጠረን (ዘፍ. 1፥26)። እግዚአብሔር ሰው በራሱ መልክና አምሳል መፍጠሩ በእኛ ላይ ትልቅ ዓላማ እንዳለው ማስተዋል ይቻላል፤ ከዚህም ባሻገር፣ እኛ የፈጠረበት ዓላማው ክብሩና ከሌላ ፍጥረት ልዩትነት ባለው መንገድ፣ ከእርሱ ጋር ቀጥታ ሕብረትን እንድናደርግ፣ እንድንነጋገርና ምላሽን በመስጠት እንመስለው ዘንድ ጽድቅን፣ ፍቅርን፣ ክብርን፣ ሞገስን፣ ዕውቀትን፣ ቅድስናን … ከፍሎ በመስጠት እንደ ኾነ ቅዱስ መጽሐፍ በምልአት ያስተምረናል፤ (ዘፍ. 3፥8፤ ኤፌ .4፥24፤ ቈላ. 3፥10)። ፍጹማንና ኃጢአት የሌለብን ቅዱሳን ስለ ነበርንም፣ በኹለንተናችን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ተጎናጽፈን በዕርቃን ሳንተፋፈር በአንድነት ታይተን፤ ተመላልሰንም ነበር፤ (ዘፍ. 2፥25)።

  ነገር ግን የገዛ መንገዳችንንና ፈቃዳችንን በመከተል፣ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ኀጢአትን ሠርተን ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላን፤ የሰይጣንን የአታላይነት ድምጽ በመስማታችን፣ በእግዚአብሔር ፊት የምንንጓደድበትን መልክና አምሳል፤ ግርማና ሞገስ፤ ጽድቅና ቅድስና፤ ዕውቀት ማስተዋል አጣን ወይም በእግዚአብሔር ፊት የማያቆም አዳፋ፣ ርኩስ፣ ጥዩፍ፣ ፍጹምነት የጐደለው ኾነ። እግዚአብሔርን የሚመስልበት መልኩን በገዛ እጁ አሳደፈ።

 ስለዚህም፥ “አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ” (ዘፍ. 5፥3) እንዲል፣ እግዚአብሔር ፍጹም በኾነው በራሱ መልክና አምሳል የፈጠረው ሰው ባለመታዘዙ ምክንያት በተበላሸውና ባደፈው በራሱ መልክ አዳም ወንድ ልጅን ወለደ። ስለዚህም፣ “በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤” (ሮሜ. 5፥14)። በዚህ ብቻ ሳያበቃ፣ “አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤” እንዲል (ሮሜ 3፥9) መላለሙ ከኀጢአት በታች የተገዛና የተከሰሰ ኾነ፡፡

  እንግዲህ እንዲህ የኾንነውን፣ እግዚአብሔር ያድነንና ወደ ልጁ መልክ እናድግ ወይም የልጁን መልክ እንመስል ዘንድ፣ እንደገና ጸጋ አበዛልን፤ አትረፈረፈልን፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል … 

3 comments:

  1. ይብዛላችሁ! ይጨምርላችሁ! ክፉ አይንካችሁ። ለምልሙልን።

    ReplyDelete
  2. የእግዚአብሔርን እውነት እናውቅ አግዘከናልና ፀጋ ይብዛልህ ወንድሜ

    ReplyDelete
  3. You are blessed

    ReplyDelete