3. ስድብና ስም ማጥፋት
ተሰምተው የማታውቋቸውን ስድቦች ወደፊት ገጽና(Facebook) ሌሎችም
ድኅረ ገጻት ስትመጡ ነፍሳችሁ እስክትጠግብ ልትሰሙ ፣ ልታዩ ትችላላችሁ፡፡
አጅግ የምታከብሩት ሽማግሌ ፣ ባልቴት ፣ ወጣት ፣ ልጅ … ድንገት የስድብ ናዳ ሲወርድበት ታያላችሁ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው
የሃይማኖት መልክ ያላቸው በዚህ ነገር የተጠመዱና የተለከፉ መሆናቸው ነው፡፡
ስድብ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ ዲያብሎስ ተሳዳቢ ነው፡፡ ልጆቹም እንዲሁ(ራእ.13፥6)፡፡
ከእግዚአብሔር የሆነ ግን ክፉ ከአንደበቱ አይወጣም (ማቴ.15፥11)፡፡ ከአንደበት የሚወጣ ክፉ ነገር መላ ብልትን ያረክሰዋልና፥
የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ስለሚናገረው ይጠነቀቃል፡፡ ይልቁን እንዴት መናገር እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሞቱ ዝንቦች
የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” (መክ.10፥1) እንዲል፥ ቃላችን በስንፍና
የተመላ እንዳይሆን “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ
ይሁን” (ቈላ.4፥6) የሚለው ቃል ሊገዛን ይገባል፡፡
አንድ አማኝ ንግግሩ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ፣ ውበት ያለው ፣ በጐ የሆነና
ፍጹም በሆነ በቅዱሱ በእግዚአብሔር ቃል የተቀመመ መሆን አለበት፡፡
ለዚህም ለእግዚአብሔር ቃል እውነት ጥናት የበዛ ጊዜ ሊኖረንና በልባችንም እስኪበዛ መትጋት እጅግ አስተዋይነት ነው፡፡ የዚያኔ በቃሉ
እንደቅመም የተሟሸው ቃላችን ያመንነውንና የምናምነውን እንዲሁም ለሌሎች የምንናረውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት በፍቅር መግለጥ
ወይማ መናገር ይቻለናል፡፡
በጨው የተቀመመ ቅመም ንጹህ ፣ ከተዋኃስያን የጸዳ ፣ በቶሎም የማይጠቃ ነው፡፡
“የምድር ጨው ናችሁ” (ማቴ.5፥13) የሚለው ቃል፥ አልጫ ለሆነው ለዓለማዊነት ጠባይ የማይመች ማንነትን የሚገልጥ ነው፡፡ ጨው
ማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን መድኃኒትነትም እንዳለው፥ “ … ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም …” (ሕዝ.16፥4)
የሚለው ቃል ያስረዳናል፡፡ በጨው የተቀመመ መሆንም ከኃጢአት መራቅንና ፍጹም መንጻትን ፤ እንዲሁም ከእድፈትና ከነውር ጋር አለመስማማትን
የሚያሳይ ነው፡፡
ደግሜ እላለሁ፦
ስድብ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ ተሳዳቢ ሁልጊዜ ተሸናፊ ነው፡፡ ስለተሸነፈም የውርደትን ቃል ይናገራል፡፡ ዲያብሎስ ለምን የሚሳደብ
ይመስላችኋል? በሥራው ስለተዋረደና ፍጹም ስለተሸነፈ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ግን ክፉን እንኳ በክፉ ማሸነፍ አልተባለልንም
(ሮሜ.12፥17) ፤ በተለይም ስድብን በተመለከተ በግልጥ ቃል፥ “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ
ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና” (1ጴጥ.3፥9) ተብለናል፡፡ ክፋትን በክፋት መመለስ ፤ ስድብን በስድብ
መመከት ሰይጣናዊ ቀኖና ነውና፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፎቶ ለጥፈው ፣ አዲስ ታሪክ ፈብርከው ፣ አቀናጅተውና አደራጅተው የሰዎችን
ስም የሚያጠፉ “ወገኖችን” ምን ማለት ትችላላችሁ? ፈጽሞ ክርስቲያኖች ሊሆኑ አይችሉም ፤ አይሆኑምም ከማለት ውጪ፡፡
አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አዳዲስ ታሪኮችንና የስም ማጥፋት ድርሰቶችን የሚያዘጋጁ
ሰዎች፥ ልባቸው ቢቀና የጌታን ወንጌል እንዴት እንደሚሰብኩ አስብና … ጌታ ግን አፈ ቀላጤውንና መለኛውን ሳይሆን በዓለም ሁሉ ፊት
እንደጉድፍ የተጣለውን ሰው መምረጡን አስቤ፥ “እግዚአብሔር ሆይ ትክክል ነህ” ብዬ እደመማለሁ፡፡ አዎ! የሐሰት ታሪክ አንብበን
እውነት ብለን የተሟገትንና ከሰዎች ጋር የተቀያየምን ፤ ስማቸው “ከጠፋባቸውም” ሰዎች ሳናረጋግጥ የተቆራረጥንም እጅግ የሚታክት
ቁጥር ነን፡፡ ይህ ነገር ይበልጥ የሚያሳዝነው መንፈሳዊ ካባ ለብሰው ፤ ምርቅነታቸውን በመንፈሳዊ ቃላት ለመግለጥ የሚሞክሩ ሃይማኖት
ለበስ ሰዎችን በየአደባባዩ ሲበዙ ስናይ ነው፡፡
አዲስ ታሪክን በመፍጠር የመጀመርያው ስም አጥፊ ዲያብሎስ ነው፡፡ ለሔዋን
ስለእግዚአብሔር እንዲህ አላት፦ “እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም
መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍጥ.3፥4-5) እግዚአብሔር ከፈጠራቸው መልካም ፍጡራን
መካከል አንዱ በሆነው በእባብ ራሱን ሰውሮ የቀረበው ታላቁ አታላይና ዋሾ ባልታዘዙ ጊዜ ጌታ እግዚአብሔር ትሞታላችሁ ያላቸውን እውነተኛ
ቃል (ዘፍጥ.2፥17) ሐሰተኛ በማስመሰል (እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ በማሰብ) አትሞቱም አለ፡፡ እንደገናም እግዚአብሔር ለሕዝቡ
ያለው ልብ ወይም ፈቃድና ሃሳብ በጐ እንዳልሆነ አድርጐ በማቅረብ ሰይጣን እግዚአብሔርን በስድብ ቃል ይከሳል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ
ኢዮብ ጻድቁን ሰው ሲከሰው እናያለን (ኢዮ.1፥9-11 ፤ 2፥4-5)፡፡
በየድኅረ ገጹ ከሚለቀቁት ጽሁፎች ትልቁን የአስተያየት መስጫ ሳጥን(comment)
በጽሁፍና በተለያየ የምስል ማሳያዎች የሚመሉት የሚሰለቹ ፤ አስነዋሪ ስድቦች ናቸው፡፡ “በዓለማውያን” መካከል ቢኖር ምንም ላያስደንቅ
ይችላል፡፡ ነገር ግን ከመንፈሳውያን ጽሁፎች ግርጌም ይህ ነገር በዝቶ መታየቱም “የት ነው ያለነው? ምን እየሆንን ነው? ይህ ትምህርት
በእውኑ ከእግዚአብሔር አለመሆኑ ጠፍቶን ወይስ አውቆ የተኛን እንደሚባለው ሆኖብን ይሆን?” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በደንብ ያጭራል፡፡
እውነት ግን በሙያ ቃል ግን መነጋገር አይቻልም? ስድብ ሙያ ከሚሆነን ምነው መልካሙን ቃል መምረጥ ተሳነን? ከሰይጣን ጋር ፍጹም
በሚያመሳስለን ጉዳይ አንድ መሆናችን እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡
በማኅበራዊ ድኅረ ገጾች የሚተላለፉትን ነገሮችን ስንከታተል የሚገጥሙን
ችግሮች እኒህ ብቻ አይደሉም፡፡ በተለይም ከእግዚአብሔር ቃልና ፈቃድ አንጻር ካየነው ኃጢአት ምን ያህል የአደባባይ ተከታዮችን እያፈራ
እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ እንግዲህ እኛም ሳይታወቀንም ሆነ አውቀን ከእግዚአብሔር ጋር ስንጣላ እንዳንገኝ ማድረግ ያለብንን እንደቅዱስ
ቃሉ አሁን መወሰን አለብን፡፡
4. የመናፍቃን ሴራ
መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ ፣ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የሚንቁ ፣ የተቀደስንበትን
የኪዳኑን ደም ከፍጡር ሥራ ጋር የሚያስተካክሉ ፣ የጸጋውን መንፈስ የሚያክፋፉ ፣ የትንሣኤ ሙታንንና ዳግመኛ መምጣቱን እንደተረት
የሚቆጥሩ ፣ ትምህርተ ሥላሴን የሚሳደቡ … ከፊት ይልቅ በዝተው በየማህበራዊ የመረጃ መረቡ መረባቸውን ጥለው “ያለድካም” ሲያጠምዱ
እናያለን፡፡ ትላንት ስለክርስትና በቅንአትና በመቃጠል የሚያወሩ ሰዎች ዛሬ ዘወር ብለው ሲሳደቡና ሲንቁ ስታዩ ምን ያህል ልባችሁ
እንደሚሰበር ይሆን?
መልካም ሥፍራ እንደሚደርሱ የተመኛችሁላቸው ሰዎች ድንገት በተቀበሉት እንግዳ
ትምህርት ምክንያት ራሳቸውን አጥፍተው ፣ ጠጪ ፣ አመንዝራ ፣ ከግብረ ገብ በታች ወርደው በባሰ ክፋት ስታዩዋቸው የመናፍቃን ትምህርት
ምን ያህል ሥር ሰደደና አደገኛ እንደሆነ ማስተዋል አያዳግትም፡፡ መናፍቃን ዋና ኢላማቸው አይቻልም እንጂ ቢቻላቸው፥ ክርስቶስ በሞቱና
በትንሣኤው የገደለውን የሰውን ትምህርትና ሥርዓት ፤ የኃጢአትንም መውጊያ ሕያው ማድረግና ከሙታን መካከል ጌታ ኢየሱስን ዳግመኛ
መቅበር ነበር፡፡ ይህን ከአሰቃቂ አላውያን ነገሥታት የበለጠ መናፍቃን ቢሞክሩትም አልተሳካላቸውም፡፡
እውነት ለመናገር ይህን እኩይ ተግባራቸውን በቅዱስ ቃሉ ዓይኖች አይተን
ለትውልዱ የራራን ስንቶች እንሆን? መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምኅሮዎችን ለመከላከልና በሐሰተኛ ወንድሞች እንዳይበረዝ በመንፈስ ቅዱስ
ጉልበት የምንጠብቅ ስንቶች ነን? ስንቶች እንሆን ከእነማን ጋር ምን ማውራት እንዳለብንና እንደሌለብን የምንጠነቀቅ? ለስንቶቻችን
ይሆን ከባልንጀራ ፍቅር ይልቅ የጌታ ፍቅር እንደሚበልጥብን የምናስተውል? ቃሉ ስለቀደሙት መናፍቃን [ግኖስቲካውያን] በግልጥ፦
“ … በክርስቶስም
ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት
ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።” የሚለውን ቃል አስተውለን ይሆንን?
አቤቱ ጌታችን
ሆይ! ማስተዋልን እንድታበዛልን እንማልድሃለን!!! አሜን፡፡
ይቀጥላል …
እነዚህን የስድብ ጸሐፊዎች አጠገባችን ያሉትን መክረናል ? አንተም ግዴታህን ተወጣ ። የክርስትና መንገድ ይህ አይደለምና ። እግዚአብሔር ሁላችንንም ያውቀናል ።
ReplyDelete