Tuesday 16 August 2016

የኢትዮጲያ የ“ማስተዋል” ጸሐይ ምነው አዘቀዘቀ?



Please read in PDF


መንግሥት ሆይ! እባክህ ከማሰር ፤ ከማጐር ይልቅ፥ ራራ! ይቅር በል! ማር!!!
     በምዕራቡ ዓለም በተደላደለ መኖሪያ ቤታቸው ተቀምጠው እንደሰበኩን፥ “ጨካኝ ፣ እብሪተኛ ፣ አምባገነን ፣ አረመኔ ፣ ጉበኛ ፣ ዘረኛ ፣ ሴሰኛ ፣ አድርባይ ፣ አፋኝ …” ያሉት ይህ የአገር ቤቱ መንግሥት ወረደ እንበል፤ ግን እኒህ ዲያስፖራ ፖለቲከኞችና ፈሪሳውያን ሃይማኖተኞች ያልመለሱልን ጥያቄ፥ “ማን እንዲመራን ነው ያቀዱት? ፣ ማንን ይሆን ያዘጋጁልን? እነርሱ ራሳቸው ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሊመጡና ሊመሩን? ፣ ወይስ ከዚሁ አገር ቤት የሚያሰናዱልን ነገር ኖሮ ይሆን?”
     አንድ ሌላ ጥያቄ አለኝ? እኒህ “ዲያስፖራውያን የፖለቲካና የሃይማኖት ዲስኩረኞች” ለመሆኑ ስለአንድነትና ስለመንፈስ አንድነት ለማውራት በእውኑ ሞራሉና ብቃቱ አላቸው? በአንድ ነገር አምናለሁ ፤ የአገር ቤቱ መንግሥት ብዙ ነውር ፣ ዕድፍ ፣ ርኩሰት ፣ ልክፍት ፣ በደል … አለበት ፤ ይህን አምናለሁ፥ አልጠራጠርም፡፡ አንድ ብርቱ መከራከርያ ግን አለኝ፡፡ ከአገር ቤቱ መንግሥት ይልቅ “የአሁኑን የነውጥ እንቅስቃሴ እየመራ ያለው የዲያስፖራው ጐልማሳ” ግን ነውሩና ርኩሰቱ ከአገር ቤት መንግሥት ይበልጣል ባይ ነኝ፡፡

     እውነት እንናገር ከተባለ፥ በአሜሪካና በአውሮፓ ፣ በካናዳ የሚገኙ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፣ የፕሮቴስታንትና የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢትዮጲያውያን ዘንድ ሌላው ይቅር እንዴት የምትሰባሰቡት? በእውኑ በአብያተ እምነቶቻችሁ የምትሰባሰቡት የአማራ ፣ የኦሮሞ ፣ የትግሬ ፣ የከንባታ ፣ የሃዲያ ፣ የወላይታ ፣ የሙርሲ … እየተባባላችሁ አይደለምን? ከዚህ ሲከፋም በአማራ ሳታቆሙ ጎንደሬ ፣ ጐጃሜ ፣ ወሎዬ ተባብላችሁ አትዘነጣጠሉምን? በኦሮሞነትስ ሳታቆሙ ወለጋ ፣ አርሲ ፣ ሐረርጌ ፣ ሸዋ ፣ ሰላሌ ፣ ባሌ ፣ ቦረና … ተባብላችሁ አትቆራረሱምን? በትግሬስ ሳታቆሙ ሽሬ ፣ አድዋ ፣ መቕለ ፣ አዲግራት … ተባብላችሁ የምትከፋፈሉ ከእናንተ የባሰ አስነዋሪና አጸያፊ አለን? ያውም በ“ቤተ እግዚአብሔር”ና በእምነት ሽፋን? እና፥ እናንተ ናችሁ ስለአገር አንድነትና ስለእምነት አንድነት የመናገር ብቃትና ሞራል ያላችሁ?
    በእናንተ ዘንድ አንድ ሰው፥ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት ስለሆነ ብቻ ዘር ማንዘርን ማዕከል ሳያደርግ ወደቤተ እምነቱ መሄድ ይችላል? ቢመጣስ እጃችሁን ዘርግታችሁ የምትቀበሉ ስንቶች ናችሁ? የእኛን ጉድፍ ልታጠሩ ስትመጡ ምነው የእናንተ ምሰሶ በአይናችሁ ተጋድሞ ማየት ተሳናችሁ? በትምህርት ቤት የተማራችሁትን ግርድፉን እውቀት እንደወረደ ማዝነብና ነባራዊውን የሕዝባችንን እውነታ በማስተዋል መናገር ፣ ማስረዳት ምዕራብ ከምሥራቅ የሚርቀውን ያህል ይርቃል፡፡ ይህን ማድረግም አዋቂነት ወይም ሊቅነት አይደለም፡፡
       ኸረ ለመሆኑ ስለእናንተ መልካምነት ይህን ያህል ከተናገራችሁ፥ እስኪ “እኛን” (ይህን እንደአንድ የመንግሥት ፓርቲ ደጋፊም ተቃዋሚም አልልም) የምትቃወሙትንና የማትቃወሙትን ለይታችሁ ንገሩን? ለመሆኑ ከእኛ መካከል ምን የሚመቻችሁ ነገር አለ? አዎን! ከከብቶቹ ጋር በአንድ ጉረኖ የሚኖረውን ፣ ተረከዘ ስንጥቁን ፣ ልብሰ አዳፋውን ፣ “ባልተመቻቸ የኑሮ ዘይቤ” የሚኖረውን ድሃውን ወገናችንን የምትጠየፉ ብቻ አይደላችሁም ፤ ሃሳባችሁን የምንሞግተውን እኛንም ጭምር እንጂ፡፡ (ይህን የምለው እዚያው ሆነው በብዙ የሚታገሉና ተቃውሟቸውን የሚገልጡ፤  በአግባቡ የሚሞግቱ ጥቂት ወገኖቼን መርሳትና መተው አልሻም)
     ይህ የዘረኛነት ሐረግ በረጅሙ ተመዝዞ ዛሬ እርስ በእርስ ደም ለመፋሰሳችን ሥረ ምክንያት ሆኖናል፡፡ ደግሞ መርዘ ልውስ ሃሳባችሁን ከሥልጣኔና ከዕውቀት ለማዳቀል መሮጣችሁ እንዴት ያጠይፋል፡፡ ይህ የተጣባ ክፋታችሁን አዳም ረታ በሰላ ብዕሩ እንዲህ ብሎታል፥
 “ …. ልወደድ ባይነትን ፣ በትምህርት ቤት የሰበሰቡትን መረጃን እንዳለ መድፋትን ፣  ከፖለቲከኞች ጋር ተደጋግፎ ሆይ ሆይ ማለትን፣ ከባዴ መታከክን፣ ብልጣ ብልጥነትን፣ የማወናበድና የመዋሸት ተውህቦን ከምሁርነት ያምታቱታል፡፡” አዳም ምንም ሳይፈራና ሳይተባ እኛንም ይሸነቁጠናል፥ “ … ለመሆኑ እግዚአብሔር ተፈጥሮንና ሰውን እንዴት ፈጠረው? በቃሉ ትዕዛዝ ነው፡፡ ሰው ሁን አለ፡፡ ሰውም ሆነ፡፡ ዛፍ ሁን አለ፡፡ ዛፍም ሆነ፣ ወዘተ …. ባዕዳን ተጣሉ ሲሉን መጣላት፡፡ ሩጡ ሲሉን መሮጥ ፡፡ ራቁታችሁን ሁኑ ሲሉን መሆን፡፡ ሁሉ ነገራችን ከዚያም ዝቅ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም (በተለይ በፖለቲካ ሳይንሱ) ተንትኖ የሚከላከለን የሚበጀንን የሚያሳየን የልሂቅ ሰልፈኛ ስለሌለን ነው፡፡” [1]
    ከዚህ “ገልቱ ሃሳባችሁ” የዘለለ እውነት አላችሁ ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ከ“ጐበዝ አለቃ” ሩጫችሁ የሚቀድመውና አምነን እንድንቀበላችሁ ከፈለጋችሁ መጀመርያ “ከዘረኛነትና ብሔርተኛነት አባዜ ተላቀቁ” ብለን ልንመክራችሁ እንወዳለን፡፡
    ይበልጥ ልብ የሚያደማው አገር ቤት ያለው ኢትዮጲያዊ ሊደማመጥ አለመቻሉ ፤ ሊቀባበል አለመፍቀዱ ነው፡፡ ለመግደል ፣ ለመሳደብ ፣ ለጥላቻ ፣ የልማት ተቋማትን ለማፍረስና ለማቃጠል ተስማምተን እንዴት ባልንጀራን ለመቀበል መስማማት ያቅተናል? እንዴት ለእውነት መሸነፍ ይሳነናል? የሩቁ “ወገን ነኝ ባዩ” ቁስላችንን እያከከ እንዳይድን የሚያስይዠውን አምነንና ሰምተን፥ እንዴት ነው የቅርቡ ወገናችን ቁስላችንን ሊያክም ሲደክም “ፈጽሞ አንሻህም!!!” አልነው? በምዕራቡ ዓለም የተቀማጠለ ኑሮ እየኖሩ ባማሩ ሶፋዎቻቸው ላይ ተቀምጠው የቴሌቪዥን መስኮት እየቀያየሩ ደማችን ሲፈስ ፣ ንብረታችን ሲወድም ፣ ፈተናችንን ሲያሰርቁ … በደስታ የሚያዩትን የጐበዝ አለቆችን የሚሰሙ፥ ሰምተውም አገር የሚንጡ ፣ የጐበዙ አለቆቹን ቃል እንደፈጣሪ ቃል ተቀብለው በሥራ የሚተረጉሙትን ማስተዋላችሁን ምን ወሰደባችሁ? ልል እወዳለሁ፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው “ጠላት ያሉትን “መንግሥት” ሲጠሉ እውነተኞችንም አብረው በአንድነት መማገዳቸው ነው፡፡ ሰይጣን ካልሆነ በቀር እንዴት አንድ ነገር መቶ በመቶ ክፉና ጥፉ ይሆናል?
     እንዴት ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ አብሮ ይወቀጣል? ሰዶምና ገሞራ ሙሉ ለሙሉ በክፉ ኃጢአት ቢዋጡም ጌታ ግን ጥቂቶቹን ታማኞች ሊያድን መላእክቱን ላከ፥ “ … ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው ፤ እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል” (ዘፍ.19፥12-13) እንዳለው፡፡ እየሆነና እየተባለ ያለው ግን ከኢትዮጲያ ውጪ እንጂ ኢትዮጲያ ውስጥ ምንም መልካም የለም ነው፡፡ ይህ የእናንተ ሃሳብ እንዴት ሙሉ ለሙሉ እውነትና ትክክል ሊሆን ይችላል? እኛስ ይህን ማስተዋል እንዴት ይሳነናል? ከኢትዮጲያ ውጪ ያለው የእነርሱ መልካምነት ምንድር ነው ብሎ መጠየቅ እንዴት ይሳነናል?
    “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ?” (ያዕ.4፥1) እንደተባለ ይህ ሁሉ ነገር ከወዴት አገኘን? ይቅር መባባልና መቀባበል ስለምን ተሳነን? እንዴት ሰው የሚያህል ክቡር ፍጡር ላይ ስለት ይሳላል ፤ ባሩድ ይጤሳል ፤ እሳት ይነዳል ፤ ጥይት በሰውነቱ ይታመሳል ፤ እንዴት እኛው ለእኛው ሞት ደግሰን ፤ ሞት እንመግባለን፡፡ እውነት ተናግረን የማንችል መሆናችን ዓለም በሞላው ይወቀው ማለታችን ነው? ኸረ ወንድማማች ሆይ እንደማመጥ? ነፍጡን አቆይተን በሃሳብ እስኪ መሟገትና የተሻለውን በመውሰድ የተሻለ ትውልድ “እንፍጠር”፡፡ ለዚህ ደግሞ፥
-       መንግሥት ለተፈጠረውና እየተፈጠረ ላለው ነገር ሁሉ ግልጥ ይቅርታ መጠየቅና ላሰራቸውና በየማረሚያና እስር ቤት ላሉ ወገኖች ይቅርታ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይቅርታ ሁሉን ኃጢአት የማስተሥረይ ብቃት አለው፡፡ መንግሥት ይህን አምኖበት ሊያደርገው ይገባዋል፡፡
-       የአንዲት ኢትዮጲያ ክፋይ አካላት ፤ የሰው ልጆች መሆናችንን አንካካድ፤ በዲያስፖራነት አንድ አህጉር ላይ ሆነው እዚህ የሚንጡንን፥ ስሜታችን የማይሰማቸውን፣ ሃሳባችንን የማይረዱትን፣ ያለንበትን ነባራዊ እውነት የማያውቁትን የጐበዝ አለቆችን በማስተዋል መንፈስ ልንቀርባቸውም ልንርቃቸውም ይገባናል፡፡
-       ወጣቱ ትውልድ ደግሞ “ሚድያ አጠቃቀማችን ጤናማ ነውን?” ብለን ብንመዝነው መልካም ነው፡፡ ኸረ ለመሆኑ ሚድያውን ለማጋጨት ፣ ለማፋጀት ፣ የተጠቀምነውን ያህል ለመፍትሔ ተጠቅመነዋል? ዘረኝነትን እንደእኛ ከዘር ፣ ከነገድ ፣ ከቋንቋ ... በታች አውርዶ በክፍለ ከተማና ቀበሌ ፤ እስከመንደር የወረደ ዘረኛነትን ያንጸባረቀ ከእኛ በቀር ማን አለ? እኛ አይደለን ወይ የእገሌ ክፍለ ከተማ ልጅ ነኝ ባዮቹና አመጽ ቀስቃሾቹ? ታዲያ አጠቃቀማችንን መመዘኑ አይበጀንም?
-       ሁላችንም ላልታዘዝንበት ዓመጻችን ንስሐ እንግባ ፤ ወደብሔራዊ እርቅ እንምጣ ፤ምድሪቱን የደም ምድር ከምናደርጋት፣ እጃችንን በደም ከምናጨቀይ ንስሐ እንግባ፡፡ ከጭፍን ጥላቻም ወደመንፈስ አንድነት ልንመጣ ያስፈልገናል፡፡ ያዘቀዘቀውን የማስተዋል ጸሐያችንን ሳይጠልቅ እንቅደመው፡፡
   አቤቱ አባታችን አብ ሆይ! ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡


    [1] አዳም ረታ ፤ የስንብት ቀለማት ፤ 2008 ዓ.ም ፤ አሳታሚ ርኆቦት አሳታሚ፡፡ ገጽ.24

2 comments:

  1. አዎ እውነት ነው ሁሉም ጋር ተከፋፍለዋል። ግን በካሊፎርኒያ ግዛት በሳን ሆዜ ከተማ ያለችው የኢትዮጵያ ክርሲያኖች ሕብረት ቤ/ክ የምትባለው የፕሮቴስታንት ቤ/ክ ሁሉን ዘር ኤርትራውያንም ጭምር በእኩልነት አቅፋ የያዘች ናት። ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታትዮች እንኳን ርዳታ ያደረገች (ሕንጻ በሚገዙበት ወቅት) እንደሆነች ሰምቻለሁ። ወንድሜ ያልከው ሁሉ እውነት ቢሆንም እግዚአብሔር ግን አሁንም በእውነት የሚያመኩት ቅሬታዎች አሉት። እግዚአብሔር አምላካችን አገራችንን ይጠብቅልን፣ ሕዝባችንንም ይማርልን! አሜን።

    ReplyDelete
  2. ልክ ብለሀል። በእውነት ተባረክ። እንዳንተ የሚያስብ ልባም ሰው ነው ያጣነው

    ReplyDelete