Sunday, 22 March 2015

ቸር አገልጋይ ማነው?











“በጎ ሥራ እየሠራ ጌታው የሚያገኘው ቸርና የታመነ አገልጋይ ማነው ? ባለው ሁሉ ላይ የሚሾመው ደግሞም  እግዚአብሔር ቸር ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንክ ወደጌታህ ደስታ ግባ የሚለው፡፡
(ቅዱስ ያሬድ)

      የስድስተኛውን የዓቢይ ጾም ስያሜ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ገብር ኄር” ትርጓሜውም “መልካም ባርያ” ሲለው ፤ የዕለቱን የመዝሙር ርዕስ ደግሞ “መኑ ውእቱ ገብር ኄር” ትርጓሜውም “ቸር አገልጋይ ማነው?” ብሎ ሰይሞታል ፤ የሚነበበው የወንጌል ክፍል ደግሞ  ማቴ.25፥14-31 ነው፡፡ በዚህ ዕለት በዋናነት “ስለቅን አገልጋዮችና ስለአገልግሎታቸው ትጋት “ገብር ኄር” እያለ ዋጋን የሚከፍል ፤ ሰነፍና ታካች አገልጋዮችን የሚቀጣም አምላክ እንዳለ በስፋት ይወሳል፡፡”

    በሚነበበው የወንጌል ክፍል ላይ አንድ ሰው ለሦስት ሰዎች እንደአቅማቸው ለአንዱ አምስት ፣ ለአንዱ ሁለት ፣ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት እንደሰጠና በኋላ መጥቶ በተቆጣጠራቸው ጊዜ ሁለቱ በአግባቡ በማትረፋቸው ምክንያት ወደጌታቸው ደስታ እንደገቡና አንዱ ግን የተሰጠውን መክሊት በመቅበሩ ምክንያት ካለማትረፉም በላይ የስንፍናን ቃል በመናገሩ ምክንያት እጅግ እንደተወቀሰና ወደጨለማ ፣ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት እንዲላክ እንደተፈረደበት እናነባለን፡፡
    መክሊት ለእያንዳንዳችን የሚሰጥ ጸጋ ሲሆን መክሊቱን ሰጪ ደግሞ ጸጋ አደላዳይ ወይም የጸጋ ግምጃ ቤት የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ (1ቆሮ.12፥4 ፤ ኤፌ.4፥7) እግዚአብሔር ማንንም ከጸጋ ድኃ አላደረገውም ፤ ለሁሉም ጸጋን የሰጠ አምላክ ነው፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምናያቸውም ሦስቱ ሰዎች ሁሉን ጸጋ ተቀባዮችን የሚወክሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ለአንደኛው አገልጋይ አምስት መክሊትን ነበር የሰጠው ፤ እርሱም ሌላ አምስት መክሊትን አትርፎ “ይኸው አስር መክሊትን አምጥቻለሁ” ብሎ አቅርቧል፡፡ እንዲሁ ሁለት መክሊትም የተሰጠው ሌላ ሁለት አትርፎ አራት መክሊትን አቅርቧል፡፡
   ሁለቱ ባዕለ ጸጎች የተሰጣቸው ጸጋ የሚበላለጥ ቢሆንም ጌታቸውን ያገለገሉት ግን ባለመቀናናት በታማኝነት ነው፡፡ አምላካቸውን በማገልገላቸው ስለሚያገኙት ሰማያዊ ደስታና ስለሚያተርፉት መክሊት እንጂ ለአንድም ጊዜ ወደጎን በማየት ለባልንጀራቸው በተሰጠው የሚበልጥ ጸጋ አላኮረፉም፡፡ እንዲሁም ጸጋን ከሚሰጥ ከእግዚአብሔር አንጻር የተሰጣቸው ጸጋ ትንሽ ቢሆንም የተሰጣቸውን ትንሹን ጸጋ አነሰብንም ብለው አልተሟገቱም፡፡ በእርግጥም ትንሽ የሚባል ጸጋ የለምና በተሰጣቸው እንደሚገባ አገልግለው ተገኝተዋል፡፡ የታማኝነታችን ልኬቱ ያለን የጸጋ ብዛት ሳይሆን በትንሹ ጸጋችን ታማኝ ሆነን በአገልግሎት መገኘታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር  ሙሴን (ዘጸ.3፥1) ፣ ዳዊትን (1ሳሙ.16፥11 ፤ 17፥15) ፣ አሞጽን (አሞ.1፥1) ፤ ኤርምያስንና(ኤር.1፥5) መጥምቁ ዮሐንስን (ሉቃ.1፥14 ፤ 41) ደግሞ ከማህጸን ከእረኝነት የጠራው በትንሹ አገልግሎታቸው ታምነው ስለተገኙ ነው፡፡ የአገልግሎት ትልቁ መለኪያ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያለን ታማኝነት ነው፡፡
   ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ የታመነ አገልጋይ ስለሕዝቡ መዳንና በክርስቶስ ሞት ስለማረፋቸው ፤ እርሱ ከአጋንንት እስራት (ከኃጢአትና ከርኩሰት) ተፈቶ ሕዝቡንም እንዲህ ካለ ነውርና ርኩሰት ስለመፍታት ይጨነቃል ፤ እርሱ ምን “የተደላደለ ቦታ” ቢቀመጥና ቢኖር የሕዝቡ መንፈሳዊ ጉስቁልና ፣ ሥጋዊ ረሃብና ቁስቁልና ፣ ፍትሕ ማጣትና በባዕለ ሥልጣናት መበዝበዝ እጅግ ያንገበግበዋል፡፡ እንዲህ    በታማኝነት ስለሚያገለግለው አገልግሎቱ በሚያገኘው መከራ ፣ ነቀፌታ ፣ ስድብ ፣ ዛቻ ፣ ስም ማጥፋት ፣ የውሸት ክስ … ይታገሳል (ሮሜ.12፥12) እንጂ አያጉረመርምም፡፡     
    ስለታማኝነቱ የሚያገኘው ሽልማት ወይም እግዚአብሔር በነጻ የሚሰጠው ሽልማት “ወደጌታ ደስታ መግባት” ተብሎ ተገልጧል፡፡ እንዴት ያለ ታላቅ ሽልማት ይሆን?! በእውነት እግዚአብሔር በታማኝነት የሚያገለግሉትን አገልጋዮቹን በታላቅ ክብር የሚያከብራቸው ስለቃሉ የታመነ ጌታችን ነው!!!
  ሦስተኛው መክሊት የተሰጠው አገልጋይ የተቀበለው መክሊት አንድ መክሊት ነው፡፡ ለዚህ ሰው የመክሊቱ አነስተኛነት አላሳሰበውም ፤ ያሳሰበው የመክሊቱ ባለቤትነት ጨካኝነትና የነገ ነገር ያስፈራው ነው፡፡ ስለጨካኝነቱ “ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።” ነገር ግን የመክሊቱን ባለቤት ጨካኝነት በሚገባ ቢያስተውል ኖሮ ይበልጡን ተግቶ በመሥራት ያለርኅራሄ ከሚገጥመው መከራ ማምለጥ በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን “ነገ በመጣህ ጊዜ እንዳታጣው ብዬ ቀበርሁት” በማለትም መልሷል፡፡
  ዋጋ ያለውን ገንዘብ መጠቀም (ትርፍ ባይኖረውና ቢያከስር እንኳ) ሲገባ፥ መቅበር በምንም አይነት አመክንዮ አሳማኝ አይሆንም፡፡ ይህ ሰው “በዚህ መክሊት በመነገዴ ወይም በማገልገሌ አንድ ችግር ቢፈጠርስ? አምናለሁ ወይም አሳምናለሁ ብዬ እኔው ራሴ ብክድስ? ደግሞስ አገለግላለሁ ብዬ  ሌላውን ባሰናክልስ? ሳገለግል ክብሬ ቢጎድልስ? ፣ የምወዳቸው ባልንጀሮቼ ቢከዱኝስ? ፣ ሰዎች ቢጠሉኝስ? መንግሥትስ ነገ ቢከሰኝ? ስሜ ቢጠፋስ? … እያለ “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” (ማቴ.10፥32-33) ያለውን ታማኝ ጌታ በመዘንጋት ጊዜያዊውን መከራና ነቀፌታ በመፍራት ከዘላለማዊ ክብር ይጎድላል፡፡
   ቅንና ታማኝ ገበሬ ያማረውንና ደህናውን ዘር ከጎተራው አውጥቶ በባዶ መሬት የሚዘራው ፣ ተኩላና ድብ ባለበት ዱር ውስጥ በጎቹን የሚያሰማራም መልካም እረኛ ከእነርሱ የሚጠበቀውን አድርገው የተቀረውን ደግሞ በአምላካቸው ታምነው ነው፡፡  ገበሬ ድርሻው መሬቱን በሚገባ ማረስና መዝራት ሲሆን ማብቀልና በምርት ማትረፍረፍ ፤ እረኛም በሚገባ ማሰማራትና ጥንቃቄ ማድረግ የእርሱ ድርሻ ሲሆን፥ ከዚህ የከፋ ቢመጣ ጠባቂው እግዚአብሔር እርሱንም በጎቹንም የሚጠብቅ መሆኑን አምነው ነው፡፡ ገበሬ ነገን በመፍራት ከመዝራት እንደማይቆጠብ ፤ እረኛም በጎቹን ተኩላና ድብ በመፍራት ከማሰማራት እንደማይሰንፍ እንዲሁ ታማኝ አገልጋይም ነገ በሚሆነው በመጨነቅ መክሊቱን ከመቅበር “ጎመን በጤና” ብሎ ከመኖር የአገልግሎቱ  (የመክሊቱ) ባለቤት ያው እግዚአብሔር ነውና ተግተን ፤ ከስንፍና በመራቅ ልናገለግል ይገባናል፡፡ የተሰጠን መክሊት ማትረፍ የሚቻለው እንጂ “ባያተርፍስ?” ብለን የምንጨነቅበት አይደለም፡፡
    “ጸጋዬ ትንሽ ናት” ፤ “ነገ እንዲህ ሆናለሁ” ከሚል የስንፍና ቃል ወጥተን መከራም ፥ ጭንቀትም፥  ስደትም ፥ ራብም ፥  ራቁትነትም ፥ ፍርሃትም ፥ ሰይፍም … ሞትም ፥ ውርደትም ፥ ስም ማጥፋትም ፥ በወዳጅ መከዳትም ፥ ማጣትም ፥ ዕለት ዕለት እንደበጎች ብንታረድ እንኳ (ሮሜ.8፥35) ከቶ አገልግሎታችንን አንተውም ብንል እርሱ ጌታችን በሚያስጨንቁን ፊት ሞገስና ግርማን ያለብሰናል፡፡ (ማቴ.10፥19) ችግሩ ከመክሊታችን ሳይሆን ከእኛ አለመሥራት ነውና ተግተን ልናገለግል ይገባናል፡፡ እንኪያስ እንዲህ ያለ ታማኝና ቸር አገልጋይ ማነው?
ጌታ ጸጋና ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡







No comments:

Post a Comment