ከአንድነት ወደመንፈስ አንድነት
እንመለስ!
ቤተ ክርስቲያን የአይሁድና የሳምራውያን፤ የአሕዛብም
ድምር ውጤት ናት፡፡ ይህ ፍጹም የመንፈስ አንድነት የተገኘው እንዲያው ዝም ብሎ ሳይሆን የወልደ አምላክ የክርስቶስ ኢየሱስን ሞትና
የደም ዋጋ የጠየቀ፥ በእርሱም የደም ቤዛነት በተደረገ ዕርቅ የተገኘ ነው፡፡ አንድነቱ ተራ ወጥነት ያለው አንድነት ወይም ተመሳሳይነት
ማለት አይደለም፡፡ አንድ የመሆን አንድነት በራሱ ከውጫዊ ተጽዕኖ የሚመጣ የጫናና የፍጹም ውጥረት ዳርቻ ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ
አንድ ያልሆኑ ልቦች ብዙ ናቸው፡፡
የመንፈስ አንድነት ግን ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነና
ከአንድነት የተለየ መልካም ነገር ነው፡፡ የብዙዎች አንድነት ቅድመ መርኅን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህም አብረው ያሉ፣ የተስማሙ፣
የማይለያዩ፣ የማይከዳዱ፣ የማይነጣጠሉ … ይመስላሉ እንጂ፥ ፈጽመው አንድ አይደሉም፡፡ ትልልቅና የማይፈርሱ የሚመስሉ አንድነቶች
እንዴት እንደፈረሱ እስኪደንቀን ድረስ ፈጽመው ስም አጠራራቸው እስኪጠፋ ፈርሰዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ስለመንፈስ አንድነት አጽንቶ የሚናገረው
ላመኑትና በክርስቶስ የደሙ ቤዛነት ጸንተው ለቆሙት ቅዱሳን አማኞች ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን የመንፈስ አንድነት፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን
ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥
ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፡፡ … ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር
ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት
በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል፤” (ኤፌ.4፥13-16) በማለት፥ ከሕንጻ አመሠራረት ጋር ባለው ግንባታና አሠራር በምሳሌነት ያቀርባል፡፡ ሕንጻ
የሚገነባበት ቁሳቁስ የተለያዩ ቢሆኑም አንዱን ሕንጻ በአንድነት ይሠራሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ ሥፍራ ደግሞ፥ ፍጹም የሆነ የመንፈስ አንድነትን
በአካልና በብልት ሕብረ ምሳሌ አሳምሮ ይገልጠዋል፡፡ “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም
ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤” (1ቆሮ.12፥12)
ምንም እንኳ ቃሉ የሚናገረው ስለመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቢሆንም፥ በውስጡ ደግሞ ክርስቶስ
ራሷ የሆነላትንና እርሷም አካሉ ሆና ፍጹም አንድና አንድ ስለሆነችው፥ ዳሩ የተለያዩ ጸጋዎች ስላሏቸውና ከአንዱ መንፈስ ስለሆኑት
ብልቶች በግልጥ የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ እያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች የተለያዩ ቢሆኑም ዳሩ ግን ለአንድ አካል
ያገለግላሉ፡፡
ይህ የመንፈስ አንድነት ለክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር
አብ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለአማኞች የተሰጠ ነው፡፡ ይህም ከሰው ያልተሰጠ ነውና፥ ክርስቲያኖች በማክበርና በመጠንቀቅ፤
በኃላፊነትም ጭምር ሊጠብቁት እንደሚገባቸው ሐዋርያው ይናገራል፡፡ የመንፈስ አንድነቱ ከሰው የተገኘ አይደለምና፥ ለመጠበቅም መንፈሳዊው
ትጥቅ ምን እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ይዘረዝራል፡፡ “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም
ማሰሪያ …” የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መሠረታውያን ነገሮች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ የምንጠብቅባቸውም መሣርያዎች፦
ትህትና፦ ትህትና ከራስ ይልቅ ባልንጀራ እንዲሻል የሚያስቆጥር ቅን መንፈስ ነው፤ (ፊል.2፥3)፡፡ ትህትና መበለጥና የደካማነት ስሜትን በውስጡ ያዘለ አይደለም፡፡ ከቀደሙት
ቅዱሳን ሙሴ፥ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ፤” (ዘኊ.12፥3)፣ ጌታ ኢየሱስም፥ “ … ከእኔም
ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ …”፤ (ማቴ.11፥29) በማለት ተናገረ፤ እንዲያውም በትሑት መንፈስ፥ “ … የባሪያን
መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ
የታዘዘ ሆነ”(ፊል.2፥6-8)፡፡ ምንም ጌታችን ትሁትና ራሱን ዝቅ ያደረገ ቢሆንም፥ ነፋሳትን ከመገሰጽ እስከ ከቤተ መቅደሱ አመጸኞችን
ገርፎ እስከማባረር የኃይል ሥራን በግልጥ ሠርቷል፡፡
ትዕግስት፦ መከራን ሁሉ የምናልፍበት መንገድ፥ የሚያስጨንቁንና አስቸጋሪ ነገሮችን እንዲያልፉ ከመጠየቅ ይልቅ ነገሮቹን ከነሁኔታቸው
መቀበል እርሱ ትዕግስት ነው፡፡ ትዕግስት ደግሶ የማይመጣውን መከራንም ሆነ፥ ማናቸውንም አስቸጋሪ ነገር አቋርጦ ማለፍን ይጠይቃል፡፡
ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ከሆነች(ኢዮ.7፥1) ያለድል አትጠናቀቅም፤ የድሉ መንገድ አንዳንዴ ከአንበሳ መንጋጋ በጌታ ጉልበት በማምለጥ(ዳን.6፥2)
ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን “እስከ ሞት ድረስ በመደብደብ፤ መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ በመፈተን፤
በድንጋይ ተወግሮ መሞት፥ በመፈተን፥ በመጋዝ በመሰንጠቅ፥ በሰይፍ ተገድሎ በመሞት፥ ሁሉን እያጡ መከራን በመቀበል፥ እየተጨነቁ የበግና
የፍየል ሌጦ ለብሶ በመዞር፤ ዓለም ሳይገባን በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ በመቅበዝበዝ፤” (ዕብ.11፥35-38)
በማለፍ ውስጥ ልንታገስ ያስፈልገናል፡፡
ብዙዎቻችን እጅግ ትልቅ ቦታ መድረስ የሚችል ውብ መንፈሳዊ አንድነቶችን
ያፈረስነውና የናድነው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን፣ ጊዜያዊ ሃሜቶችንና ስም ማጥፋቶችን፣ ጥቂት ማስፈራሪያና ዛቻዎችን በመፍራትና ባለመታገስ
ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ትዕገስት ዕድል መስጠትም ነው፤ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ወንድምና እህቶቻችሁን ስንቶቻችሁ ትታገሳላችሁ?
ታካች ካልሆንን በቀር በሰውነታችን ላይ ያለን ቁስል በአንድ ቀን እንዲድንልን አንሻም፡፡ ምክንያቱም መታገስ ግድ ያስፈልገናል፡፡
ፍቅር፦ የመንፈስ አንድነት ከሚጸናባቸው መንፈሳዊ መሣሪያዎች አንዱ
ፍቅር ነው፡፡ ሁሉን መቀበል የሚችል ፍቅር ከክርስቶስ የተማርነው ነው፡፡ በመንፈስ አንድነት ውስጥ ሁሉን ለመቀበል አቅምና ችሎታችን
ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሌለው እርሱ ምንም የሚታገሰው ነገር የለም፡፡ በሥጋ ወንድማችሁ የሆነውን ሰው የምታፈቅሩትንና የምትታገሱትን
ያህል በክርስቶስ ወንድማችሁ ለሆነው ታደርጉለታላችሁ? በብዙ ጥፋት ውስጥ ብዙ ምሕረትና ይቅርታ የሚሰጥ መንፈሳዊ ጉልበት አላችሁ?
ይህን የማታደርጉ ግን የመንፈስን አንድነትን እየናቃችሁ ነውና ንስሐ ግቡ፤ ምክንያቱም “ፍቅር ይታገሳል፤ ሁሉን ይታገሣል፥” (1ቆሮ.13፥4 ፤ 7)፡፡
ትጋት፦ ምንም እንኳ መዳናችን
በጸጋ መሆኑ የታመነና እውን ቢሆንም፥ ከዳንን በኋላ የተሰጠንን የመንፈስ ቅዱስ ሕብረት በትጋት መያዝና መንከባከብ ደግሞ ያስፈልገናል፡፡
ትጋት የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ የሚደረግ ያላሰለሰ ጥረትን አመልካች ነው፡፡ ትጋት አለማቋረጥን ይጠይቃል፡፡
ሰላም፦ ሰላም የጦርነት ተቃራኒ ገጽታ
ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ መከፋፈልና መለያየት የሚከሰተውና የሚፈጠረው በምን ምክንት እንደሆነ ቅዱስ ያዕቆብ ሲነግረን፥ “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ
ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?”፤ (ያዕ.4፥1) ምቾት ግላዊነትን አመልካች ሃሳብ ነው፡፡ ግላዊነት ወደራስ ብቻ
መመልከት ነው፤ ይህ ደግሞ ሌላውን ላለማየትና ኢሰላማዊ ለመሆን በቂ ምክንያት ነው፡፡ ለጦርነት የሚከፈለውን ትልቁን ዋጋ ያህል
ለሰላም አለመከፈሉ ወይም ለመክፈል አለመተጋቱ ያሳዝናል፡፡
ሰው ወደራሱ ሲመለከት መጀመርያ የሚጣላው ከእግዚአብሔር
ጋር ነው፤ ሰው ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ጠበኛ ከሆነ በምንም መልኩ ከሰው ጋር ስምም መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ከሌላው ጋር ለመስማማትና አንድ ለመሆን
የግድ በሰላም ማሰርያ የመንፈስ አንድነትን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ “በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ
ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ፡፡” እንዲል፤ (ቈላ.3፥15)፡፡
እንግዲህ፥ እንዲህ ባለ መንፈሳዊ ትጥቅ የመንፈስ ቅዱስን
አንድነት እንጠብቅ ዘንድ ክርስቲያኖች ታዘናል፡፡ እንዲያውም ልንጠብቀው የሚገባን ለተጠራንበት ጥሪ የሚገባንንና የሚያስመሰክር ኑሮ
በመኖር፤ እንዲሁም ለሰላሙ ወንጌል ታማኝ በመሆንና የመንፈስ ቅዱስን ምሪት በመከተል ነው፡፡ የመንፈስ አንድነት በሰው ጥረትና ድካም
አልተገኘምና፥ በሰው ብልሃትና በፍጡር ፍልስፍና አንድነታችንን ልንጠብቀው አይገባንም፡፡ ዛሬ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት
እንጂ የመንፈስ አንድነት ያጡት አንድነታቸውን በሰው ብልሃት ለመጠበቅ ስለሚተጉና ለመንፈስ አንድነት ለመትጋት መሻቱ ስለሌላቸው
ነው፡፡ ለዚህም ነው የአደባባይ ነውር ያለባቸውን ሰዎች ጭምር በንስሐ ልብ ሳይሆን በአንድነት በሚመስል ልብ ይዘው “በጌታ ፊት
መቆምን” የሚመርጡት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የመንፈስ አንድነት የጸናና በሁለት እግሩ ቆሞ ቢታይ፥ ዛሬ በአገራችንና በአኅጉራችን የሚታየውን
ነውር ያለንግግር በትክክል መውቀስና ክፉዎችን ዝም ማሰኘት ይቻላት ነበር፡፡
የመንፈስ አንድነትን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን
ዛሬ በከባድ ነቀፋ ውስጥ ናት፡፡ ለክርስቶስ ወንጌል በትክክል አለመኖራችንን ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ የመንፈስ አንድነትን አጥተን፥
ሁላችንም መልካም ወደመሰለን የገዛ መንገዳችን ማዘንበላችን ነው፡፡ ለተከፋፈለውና በዘረኝነት ለተቆራረሰች አገራችንም ሆነ አህጉራችን
መፍትሔና ፈውስ መሆን ያልቻልነው፥ አብያተ ክርስቲያናት ራሳችን የዚህ ክፋት ተጋሪ በመሆናችንና የመንፈስ አንድነትን ፈጽሞ በመጣላችን
ነው፡፡ በተለይም በምዕራቡ ዓለም ያለን “ክርስቲያኖች” ከመንፈስን አንድነት ይልቅ በዘረኝነትና በሰፈር ልጅነትን ያለን አንድነትን
ወደመምረጥ አዘንብለናልና፥ አንድነታችንን በመንፈስ አንድነት ለማደስና ወደመንፈሳዊው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ንስሐን
ቀዳሚ ተግባራችን ልናደርግ ይገባናል፡፡ በአገር ቤትም ያለን አማኞች ራሳችንን ማየትና መመርመር ይገባናል፡፡ የጣልነውን የመንፈስ
አንድነት በማንሳት ወደክርስቶስ ፊታችንን ዘወር እንድናደርግ በክርስቶስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በብርታቱ ይደግፈን፤
አሜን፡፡
Amen!! Wendeme.Yekdusanu Selot Melja Kantega yehun.Zemenke 30,60,100 bemafrat bekrstose bemadege yeleke.Geta abzto yebarke.
ReplyDeleteAmen!! Wendeme.Yekdusanu Selot Melja Kantega yehun.Zemenke 30,60,100 bemafrat bekrstose bemadege yeleke.Geta abzto yebarke.
ReplyDeleteሀሴት በልቤ መሙላት ሌላ ፍለጋ የእድሜ ልክ ፍለጋ ጥልቅ ፍለጋ በልቤ ይጨምርብኛል ሁሉን ትውት እርስት ያስደርገኛል የክርስቶስ እየሱስ ፀጋና ሰላም ይብዛልሕ፡፡
ReplyDelete