Thursday 28 August 2014

የመቶ አለቆቹ (የመጨረሻ ክፍል)





4. የመቶ አለቃው ዩልዮስ (ሐዋ.27፥43)

“የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”
      ቅዱስ ጳውሎስ ለቁጥር በሚታክቱና ምላሳቸው በሳለ ከሳሾች መካከል “እየተብጠለጠለ” ቅንጣት ታህል አለመፍራቱን ሳስብ የጌታ ኢየሱስ “ … አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትዝ ይለኝና ልቤ ይረካል፡፡(ማቴ.10፥19-21) የእስያ አይሁድ፣ የኢየሩሳሌም አይሁድ፣ ጠርጠሉስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ … ስለእርሱ በጎነት የላቸውም፡፡ ፊስጦስም እንደቀደሙት ባዕለ ሥልጣናት ክፉ ልማድ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲዳኝ ይጐተጉተዋል፡፡(ሐዋ.25፥9፤21)
        ቅዱስ ጳውሎስ ነገሩ እንዳላማረ፤ ፊስጦስ ራሱ ወደአይሁድ እንዳደላ ያወቀ ይመስላል፡፡ አሁን በቆመበት የሮማ የፍርድ ችሎት ፊት መዳኘት እንደሚፈልግ በጽናት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቢዳኝ የልባቸውን ክፋት ያውቀዋል፡፡ ይገድሉታልና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለሌለው ሞት ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡(ዮሐ.8፥59) ጳውሎስ “ሰማዕትነት አያምልጠኝ” ብሎ ለስንፍና ሞት ሳይሸነፍ ወደቄሳር ይግባኝ በማለት በሮማዊ ዜግነቱ የተሰጠው መብቱን ተጠቀመበት፡፡(ሐዋ.25፥11)

Monday 25 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል አራት)



የሮማ መቶ አለቆች
3.2. በሰፈሩ ውስጥ(ሐዋ.23፥10)

       ቅዱስ ጳውሎስ ከመገረፍና ጭካኔ ከተመላበት ድብደባ በኢየሱስ መንፈስና ብርታት፤ በየመቶ አለቃውም ቅንነት ተርፏል፡፡ በማግስቱ ሻለቃው አይሁድ እርሱን የከሰሱበትን እርግጡን ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቦ ከፈታው በኋላ፤ ሸንጎውንና የካህናት አለቆችን እንዲሰበስቡ አዞ፤ ጳውሎስን በፊታቸው አቆመው፡፡ የአይሁድ ሸንጎ እንዲሰበሰቡ የተፈለገበት ምክንያት ሻለቃው የጳውሎስን ጥፋት ማወቅ ስለተሳነው የእርሱ ወገኖች እንዲያጣሩ ነበር፡፡ ግን ዳኝነቱ ቀድሞ በአድሎአዊነት አጋድሏል፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ በሸንጎው ፊት በቆመ ጊዜ ሁለት የማይስማሙ ወገኖች ጳውሎስን ለመክሰስ ግን ተስማምተው ቆሙ፡፡ ሁል ጊዜ ይደንቀኛል፡፡ የጌታ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለመግደል፤ ለማሳደድ፤ ለመክሰስ ሁለት ፈጽሞ የማይስማሙ አካላት ይፋቀራሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በሁለት ፍጹም ተቃራኒ የእምነት አካላት የተከሰሱ አማኞችን የአለማዊ ፍርድ ቤት ችሎት እየደነቀው የማየት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አብረው ለመኖር አይስማሙም፣ ይበላላሉ፤ ክርስቶስ ኢየሱስንና እንደጳውሎስ ያሉ አማኞችን ግን ለመክሰስ ከባልና ሚስት ይልቅ ይዋሃዳሉ፡፡

Thursday 21 August 2014

በድንግል ማርያም ላይ የአይሁድ አሽሙር (የመጨረሻ ክፍል)



     አረጋዊው ቅዱስ ስምዖን የናዝሬቱን ህጻን ኢየሱስን ለግዝረት ወደቤተ መቅደስ በእናቱ ክንድ ታቅፎ በወጣ ጊዜ፤  ህጻኑን  ከእናቱ ክንድ ተቀብሎ የደስታና የሚያስጨንቅ ትንቢት ለህጻኑና ለእናቲቱ ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ፦   “እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።”(ሉቃ.2፥35) እመቤታችን ጥልቅ የመከራ ሥቃይ እንደምትቀበል የሚያመለክትና፤ ኢየሱስ ገና በስምንተኛ ቀኑ ሊሞት እንዳለው ለመጀመርያ ጊዜ ተነገረለት፡፡
     በራስ የሚደርስን መከራንና ስቃይን ገና በልጅነት መስማት ከማስደንገጥ አልፎ ያሰቅቃል፡፡ ድንግል ማርያም በነፍሷ ሰይፍ ማለፍ የጀመረው ጌታን መጽነሷ ከታወቀባት ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ከኤልሳቤጥ ዘንድ ወደናዝሬት ከመጣች በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የጌታ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ከድንግል ማርያም መወለድ ሲያስተምር በነበረበት ዘመኑ እንኳ አልተቀበሉትምና፡፡
      ጌታ “አባታችን አብርሃም ነው” ብለው በባዶ ትምክህት የሚመኩትን አይሁድ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር፡፡ … እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ ዲያብሎስ የሚያደደርገውን ነው” (ዮሐ.8፥38፤44) ባላቸው ጊዜ የመለሱት መልስ የአሽሙር ስድብ ነበር፡፡

Monday 18 August 2014

“ … እርሱን ስሙት” (ማቴ.17፥5)



እንኳን ለደብረ ታቦር መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!



    ቃሉን የተናገረው አብ ነው፤ የተነገረለት ደግሞ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ … የሰው ልጅ “ምን እንደሚሰማ እዝነ ልቡናውን አለመጠበቁ” (ማር.4፥24) የህይወት ዘመኑን በጭንቅ እንዲጓዝ፤ ፈቃዱም ከፈጣሪው ይልቅ ወደፍጡር እንዲያዘነብል፤ ሊሰማ የሚገባውን የበላዩን ጌታ ትቶ ከጎን ያለችውን “ወዳጅ ሚስቱን” መስማቱም ማንነቱን ድካም፤ እሾህና አሜኬላ ደግሞ ዙርያውን ለመከበቡ ምክንያት ሆኗል፡፡(ዘፍ.3፥10-21)
     አዳም ሁሉን አዋቂውንና ሰምቶ ከመመለስ ቸል የማይለውን ጌታ አለመስማቱ፥ ለማይሰማውና በጭካኔ ለተሞላው ለሰይጣን አገዛዝ ማንነቱንና ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የእስራኤል ልጆች ወደእግዚአብሔር እረፍት ያልገቡት ጌታ እግዚአብሔር በድምፁና በሙሴ አማካይነት እየተናገራቸው ከመስማት ይልቅ “እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?”(ዘጸ.17፥7)፤ “ … ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው የሚጠጣም ውኃ የለበትም።”(ዘኅ.20፥5-6) ብለው ፍጹም ድምጹን እየሰሙ እግዚአብሔርን በአመጻ ቃል በማስመረራቸውና አልታዘዝ በሚል ልብ በመከራከራቸው ነው፡፡(ዕብ.3፥7)

Saturday 16 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል ሦስት)




3. የሮም መቶ አለቆች
3.1. በማረፊያው ሥፍራ (ሐዋ.22፥24)
     ቅዱስ ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም ጉዞ ከመጀመሩ በፊት የተነገረበት ትንቢት አስጨናቂ ነው፡፡(ሐዋ.21፥10-14) እንደሚገረፍና ለአህዛብ ተላልፎ እንደሚሠጥ ቢያውቅም፤ ጨክኖ ወደኢየሩሳሌም እየወጣ፦ ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን “ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ ጸልዩ።”(ሮሜ.15፥33) በማለት እንዲጸልዩለት ያሳስባል፡፡ ጸሎቱና ጸሎታቸው ተሰምቶ “ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።” ብሎ ጸሐፊው ያስረግጠዋል፡፡(ሐዋ.21፥17)
   ሐዋርያው በኢየሩሳሌም የሚታወቀው “የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና በመዛቱ፤ በቅዱሳንም ላይ ብዙ ክፉ በማድረጉ”ና (ሐዋ.9፥1፤13) ለኦሪት ህግ እጅግ በመቅናቱ ነው፡፡ አሁን ግን ታሪክ ተለውጦ ያሳድድ በነበረው በዚያ ነገር መሰደድ ጀምሯል፡፡ ብዙዎች ወደኢየሩሳሌም እንዳይሄድ አብዝተው የለመኑት ስለዚህ ነገር ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ግን ለእስራት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌምም እንኳ እንዲሞት ልቡን አስጨከነ፡፡ አገልግሎት ሰዎች ባዩልን አልጋ በአልጋ በሚመስለው ይቀናችኋል ቢሉንም ጌታ ባየልን በእሾሁና በጐርባጣው መንገድ በደስታ የሚቀበሉ እጆችን ያሰናዳል፡፡ ምስክርነትና ንስሐ በተካደበትና በተበደለበት መንገድ ሲሆን ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ በግልጥ ያሳደደውን ጌታን ባሳደደባትና ብዙዎችን በበደለባት ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ በዚያች ከተማ ተገኝቶ ታላቅ ምስክርነትን መሰከረ፡፡ በአደባባይ ያሳደደው በአደባባይ ተሰደደ፡፡ ዛሬ ግን በዘፈን፣ በከህደት ትምህታቸው፣ በፖለቲካ … መርዝ ብዙውን ህዝብ በአደባባይ የበደሉ ንስሐቸውን በጓሮ መጨረሳቸውን ከየት እንደተማሩት ግራ ይገባል፡፡ እውነተኛ ንስሐና ምስክርነት በተሠራበት በዚያው መንገድ ቢሆን ብዙ ምህረት ከጌታ በሆነችልን ነበር፡፡

Wednesday 13 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል ሁለት)



ፈጣን ጉዞ ወደ ተራራማው የኤፍሬም አገር
   
    ድንግል ማርያም “እንደቃልህ ይሁንልኝ” ባለች ጊዜ እንደመንፈስ ቅዱስ አሠራር ህጻኑ በማህፀኗ ተፀንሷል፡፡ ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ሳትቆይ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ወደዘካርያስ ቤት ተጓዘች፡፡ ከመልአኩ አንደበት የሠማችው የኤልሳቤጥ መፅነስ ሳያስደምማት አይቀርም፡፡ በእርግጥም ዝጉ ማህፀን ሲከፈት፤ አይቻልም የተባለው ሲቻል፤ አይሆንም ተብሎ የተደመደመው ሆኖ ሲታይ በእርግጥ ያስደምማል፡፡ ደስታ የበዛላቸው በአንድ ተገናኙ፡፡ “አንዱ ለአንዱ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” እያሉ ሊያወሩ፡፡ አዎ! ሠላምታቸው እንኳ ለእግዚአብሔርን ክብርና አምልኮን በመስጠት የደመቀና የሚማርክም ነው፡፡

Friday 8 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል አንድ)




    
እመቤታችን ድንግል ማርያም በጌታ ያመነች ብጽዕት ናት፡፡(ሉቃ.1፥45) ከዳዊት ቤት ወገን የምትሆን ድንግል ብላቴና(ኢሳ.7፥13) ዕድሜዋ ወጣት፣ የገሊላ ናዝሬት ወደምትሆን … “ብዙ ገሊላ አለና ከዚያ ሲለይ እንተ ስማ ናዝሬት፤ ብዙ ደናግል አሉና እንተ ተፍኀረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ፤ ብዙ ዮሴፍ አለና ከዚያ ሲለይ ዘእምቤተ ዳዊት አለ፡፡”(ወንጌል ቅዱስ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው፤1997፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፡፡) ኑሮዋም ባላመኑና በክፉዎች መካከል ቢሆንም(ሉቃ.1፥26) በእግዚአብሔር የምታምን፤ የእስራኤልን አምላክ ብቻ በመፍራት የምታመልክ ነበረች፡፡ ድንግል ማርያም ምንም መልካምነት በሌለባት ናዝሬት(ዮሐ.1፥47) የሚደነቅ መልካም ነገር ተገኝቶባታል፡፡
የመልአኩ ገብርኤል ብሥራት አጭር ቅኝት
    ወደገሊላ ናዝሬት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ሲወርድ፤ የሄደው ወደአንዲት፤ ማርያም ወደምትባል ድንግል ሴት ነው፡፡(ሉቃ.1፥27) ይህ ቃል እግዚአብሔር በየትኛውም ክፉ ዘመንና ሁኔታ ውስጥ የራሱ የሆኑትን ፍጹም ጠብቆ እንደሚያኖር ያሳየናል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰው ህሊናና ማስተዋል በላይ የሚደንቅ ነው፡፡ ቅዱስ ኤልያስ በእርሱ ዘመን ጣዖት ተስፋፍቶ ሰው ሁሉ በዓልን ይከተል ነበር፡፡ ከእርሱ በቀር ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ያለ አልመሰለውም፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ቅዱስ ኤልያስ በማያስተውለውና በማያውቀው መንገድ እንደኤልያስ “ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ።”(1ነገ.19፥9፤18)፤ሮሜ.11፥5) ያለ እግዚአብሔር፤ በናዝሬትም በጸጋው የመረጣትን ቅሬታ፤ ድንግል ማርያምን እናገኛለን፡፡

Saturday 2 August 2014

ብትሮጥም አክሊል የማትደፋው …


Please read in PDF

ፍቅርና ርህራሄ፣ ደስታና ቸርነት፤
የውሃት፣ ቅንነት፣ የበዛ ምህረት፤
ለማድረግ ምክንያቶች የምትደረድረው፤
እኔ በሚል ብቃት ለማድረግ ‘ም‘ጥረው፤
እንዳይመስልህ ፍጹም አንተ የምትችለው፡፡