Thursday 3 November 2016

ወዳንተ ቃል ቀዬ


የፍቅር እንጎቻ የእምነት እንጀራ፥
የቸርነት ዳቦ የምሕረት መና፥
ጨለማ ʻማይነካው የዘላለም ጸዳል፤

መፈሪያ ግርማዬ የሞገሴ አክሊል፥
የʻረፍቴ ውኃ ነው ያንተ ታላቁ ቃል፤
የጣቴ ቀለበት ዝናር የወገቤ፥
የእግሬ መጫሚያ የመዳን ራስ ቁሬ፥
የጨበጥኩት ሰይፌ መመከቻ ጋሻ፥
የኃጢአትን ዓፀድ መንቀያ ማፍረሻ፥
የክፋትን ቅጥር ግንቡን መደርመሻ፥
የሰይጣንን ተንኮል ኃይሉንም ድል መንሻ፥
ቃልህ ነው መዝሙሬ የንግግሬ ወዝ፥
ስሄድም ስቀመጥ፥ በመንገዴ ሁሉ፥ የሚለኝ ትዝ ትዝ፡፡
ሁሉ ነገሬ ነው ካባና ላንቃዬ፥
ዋላ ወደውኃ፥ እኔ፥ ወዳንተ ቃል ቀዬ፥
ወደʼርሱ ʻሮጣለሁ  ወደከፍታዬ፥
ወዳʼጽናናኸኝ ቃል ወዳʼንተ ጌታዬ፡፡



1 comment: