Tuesday 18 July 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አራት)

                                                                                   Please read in PDF
2. ዋጉ፦ በክርስቶስ ኢየሱስ ካመንንበት ቀን ጀምሮ ከክፋት ሁሉ አሠራርና ከዲያብሎስ ጋር ውጊያ ለመግጠም ፊት ለፊት ተፋጥጠናል፡፡ ደጋግመን እንዳነሣነው ውጊያችንም ከሥጋ ለባሽ ፍጡር ጋር ሳይሆን፣ ከጀርባው ለራሱ ክብርና አምልኮን ለመቀበል ከሚሠራው[ወንጌል የጨበጡ አገልጋዮችንም ጭምር በመጠቀም] ከክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት አለቃ ከሆነው ከዲያብሎስ ጋር ነው፤ (ኤፌ.6፥12)፡፡ ውጊያውን በተመሳሳይ መንገድ በመቆም እንጂ በግል ማንነታችን ብቻ ማሸነፍ እንደማንችል መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡
     “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን፤ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፤” (2ቆሮ.10፥3-5) እንዲል፣ ሰይጣን የሚሰወርበትንና የሚሰውርበትን የክፋትን ምሽግ፣ የስህተትን ትምህርት፣ ርኩሰትና ኃጢአትን ሁሉ ለማፍረስና ለመደምሰስ ፍጹም የሆነ ብቃት ያለውና ጠንካራው መሣርያ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ጦር ዕቃ ብቻ ነው፡፡

Friday 14 July 2017

ላ'ንተ ብቻ

የበገናው የመሰንቆው ኅብረ ዜማ
የዋሽንቱም የክራሩም የከበሮው ጥዑም ቃና
የግዕዛን ፉጨት የሕያዋን ቅኝት
የአምልኮ እልልታ የእንሰሳት የአራዊት
ላንተ ብቻ ይሁን ለክብር መንግሥትህ
ክብር ተጠቅልሎ አንተን ብቻ ያክብርህ!!!

Monday 10 July 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ሦስት)

Please read in PDf
3.    ይጣን፦ ብዙ ስሞች ያሉት ያሉት ሲሆን፣ ሰይጣን በዕብራይስጡ አሰናካይ፣ ስም አጥፊ፤ (ኢዮ.1፥6 ፤ ዘካ.3፥1 ፤ ማቴ.4፥10 ፤ ራእ.12፥9)፤ ዲያብሎስ ደግሞ ስም አጥፊ፣ ከሳሽ፤ ቤልሆር ማለት ደግሞ የማይረባ ከንቱ (2ቆሮ.6፥15)፤ አብዶንና አጶልዮንም አጥፊ (ራእ.9፥11) ተብሏል፤ በሌላ ሥፍራ ደግሞ የዚህ ዓለም ገዥ(ዮሐ.12፥311)፣ ወይም የዚህ ዓለም አምላክ (2ቆሮ.4፥11) ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በተለይም ደግሞ ስለተንኮለኛነቱና አታላይነቱ የቀደመው እባብ ወይም ታላቁ ዘንዶ(ራእ.12፥9)፣ ዛቻ ወዳጅና የሚያስፈራራ ስለመሆኑ ደግሞ “የሚያገሳ አንበሳ” ተብሏል፤ (1ጴጥ.5፥8)፡፡
     ሰይጣን ዋና ዓላማው ሰዎች ለጌታችን ኢየሱስ ያላቸውን ትኩረት ማስነፈግ ነው፡፡ ትኩረታቸውንና ፊታቸውን ከኢየሱስ ዘወር ባደረጉ ጊዜ ለማን እንደሚያደሉና ወደማን እንደሚያቀኑ በትክክል ያውቀዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ስውር መረቡን ይዘረጋል፡፡ የክፋት መረቡንም ለመዘርጋት የሚራዱ ብዙ ኃይላትና ሠራዊት፣ ተባባሪዎችም አሉት፤ (ኤፌ.6፥10)፡፡ ከዚህም ባሻገር ልናጣጥልና ልንንቀው የማንችለው የክፋት ጥበብንም የተመላ ነው፡፡

Friday 7 July 2017

ዘፈን - የወደቀው መልአክ እንጉርጉሮ (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
እግዚአብሔር ዘፈንን አይባርክም!

    ከዘፋኞች በተደጋጋሚ የምናደምጠው፣ “እግዚአብሔር ዘፈናቸውን እንደሚባርክ፣ ለዘፈን የሚኾን ድምጽ እንደሰጣቸው፣ በመዝፈናቸው እግዚአብሔርም ጭምር ሊደሰት እንደሚችል፣ እንዲያውም ለመዝፈናቸውና ካሴት ለማሳተማቸው ጭምር እግዚአብሔር እንደረዳቸውና እንደባረከላቸው” ሳያፍሩ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እኔን ብዙ ጊዜ እንደገባኝ ግን፣ “እግዚአብሔር” ሲሉ፣ ቅዱሱንና ለኃጢአት ልጁን አሳልፎ የሰጠውን እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔር ብለው እንደማይጠሩ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ዘመን ቅዱሱ እግዚአብሔር ከኃጢአት ጋር የተደራረደረበትና “ኃጢአትን የባረከበትን ሂደት” ሰምተንም፤ አይተንም አናውቅምና፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዲህ ያለውን ምስክርነት ፈጽመው አላስቀመጡልንም፡፡
     እግዚአብሔር ዘፈንን የሚባርክ ከሆነ፣ ከዘፈን ጋር የተጠቀሱትንም የሥጋ ፍሬዎች “ዝሙትን፥ ርኵሰትን፥ መዳራትን፥ ጣዖትን ማምለክን፥ ምዋርትን፥ ጥልን፥ ክርክርን፥ ቅንዓትን፥ ቁጣን፥ አድመኛነትን፥ መለያየትን፥ መናፍቅነትን፥ ምቀኝነትን፥ መግደልን፥ ስካርን፥ … ይህንም የሚመስለውን ሁሉ” መባረክ አለበት እያልን ነው፡፡ ሌላውን ሁሉ ጥሎ፣ ነጥሎ ዘፈንን ይባርካል ማለት፣ እግዚአብሔርን የስንፍና ሃሳባቸው ደጋፊ ለማድረግ ከማሰብ የመነጨ ተላላነት ነው፡፡ እንጂማ ዘፈን ከምንና ከማን ጋር እንደተጠቀሰ በትክክል ቢያነቡት፣ “እግዚአብሔር ዘፈንንም ይባርካል” በማለት እግዚአብሔር ላይ ለመሳለቅ ባልደፈሩ ነበር፡፡