Monday, 22 August 2016

በአዲስ አበባ፥ ምነው በሰበበ “ሰላማዊ ሰልፍ” ሁከት አልተቀሰቀሰም?!

Please read in Pdf 
የኢዮአታምን ምክር የማይሰማ ሕዝብና መሪ መጨረሻው ጥፋት ነው!!!
     ትላንት ማምሻውን ስልኬ ከወደብዙ ቦታ በተደረገላት ጥሪዎች ስትንጫረር ነበር፡፡ ከ“ክፍለ አገር” እና ከውጪው ዓለም፡፡ “አዲስ አበባ ሰላም ዋለችን? ከመገናኛ ብዙኃን ምንም መረጃ አጣን? ምንም ሁከት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ አልነበረም? ... ምንም ምን አልነበረም? ... ” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ወንድሞችና እህቶች፡፡
     ከዚህ የጥያቄ ግርፍ በኋላ ለረጅም ሰዓት ቆም ብዬ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ሰው ከሰላም ይልቅ “ሰላማዊ ሰልፍ” ለምን ተጠማ? ከጸጥታ ይልቅ ግርግርና ሁከት ለምን መረጠ? የማያስማማ፣ የማያነጋግር፣ የማያወያይ፣ ጅምር ላይ ሆነን ፍጻሜ መተለም የማያስችል ክፉ መንፈስ ከወዴት ይሆን የተጣባን? የቀደመው ዘመን ታሪክ ስለምን መማርያ አልሆነንም? ከዚህ ቀደም የ“ንጉሠ ነገሥቱን” ሥርዓት ሰለቸን ብለን፥ ከአርባ ዓመት በላይ “የመራንን” ንጉሥ አዋርደን፣ ከሰውነት ተራ አውጥተን፣ “ለባዕድ” የማይነፈገውን የቀብር ቦታ እንኳ ለ“ንጉሠ ነገሥቱ” ነስተን፣ ስም አጠራሩን አጥፍተን ... ወታደራዊውን መንግሥት “በእልልታ በሆታ” በራሳችን ላይ ሾምን፡፡
እርሱም የዘራነውን አሳጨደን፡፡

    የእስራኤል ልጆች ወደተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ምክንያት ለሚያስጨንቋቸው አህዛብ ተላልፈው መሰጠታቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (መሳ.2፥1-3)፡፡ በዚህ ወቅት አልቅሰው በፊቱ ንስሐ በገቡና መሠዊያቸውን ባደሱበት ጊዜ እግዚአብሔር “የሚታደጋቸውን” መስፍን ያስነሳላቸው ነበር፡፡ ጌዴዎን በመስፍንነት ከተነሳላቸው በኋላ መጽሐፍ፥ የጌዴዎንን አገልግሎት፥ “ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች።” (መሳ.8፥28) በማለት ይገልጠዋል፡፡
   ጌዴዎን ካረፈ በኋላ ልጁ አቤሜሌክ በበኣል ረዳትነት ራሱን የከነዓናውያን ከተሞች ንጉሥ ሊያደርግ ሞከረ፡፡ በዚህም በእግዚአብሔር ላይ የጸና እምነት ከነበረው ከአባቱ በተቃራኒ መንገድ ቆመ፡፡ከነዓናዊነት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል እንዲያቆጠቁጥ አቤሜሌክ ምክንያት ሆነ፥ ይህን እንዳያደርጉ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቃል ኪዳን ባስገባበት ሥፍራ በዚያ ሊያደርግ እጅጉን ደፈረ (ኢያ.24፥14)፡፡
    ስለዚህም ወደሴኬማውያን በላከው መልዕክት ከሰባው የጌዴዎን ልጆች ይልቅ እርሱ አንድ ብቻውን በእነርሱና በእስራኤል ላይ ሊነግሥ እንደወደደ፤ እንዲመርጡትም ነገራቸው፡፡ የሴኬም ሰዎችም ወደእርሱ አዘነበሉ ፤ ለመስማማታቸውም ሰባ ሰቅል ናስን ሰጡት፡፡ በተሰጠውም ዋጋ፥ “አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት”፡፡
    አቤሜሌክ ሥፍራውን እንደያዘ ያደረገው ነገር ቢኖር፥ ከኢዮአታም በቀር ሰባውን የጌዴዎንን ልጆች [የገዛ ወንድሞቹን]ሁሉ በአንድ ድንጋይ ላይ ልክ ለመሥዋዕት እንደሚቀርብ እንሰሳ፥ በአንድነት አረዳቸው፡፡ ወንድሞቹንም አርዶ የንግሥና በኣሉን አከበረ፤ (9፥6-7)፡፡ አስተውሉ! የገዛ ወንድሞቹን አርዶ በእነርሱ ላይ ሲነግሥ እሺ በእጄ ብለው ተቀበሉት፡፡ ለገዛ ወንድሞቹ ያልሆነ እኛን በፍቅር ይገዛናል ብለው ማሰባቸው፥ ለእግዚእሔር ሕዝብ እንዴት ያለ መታለል ነበር?! በቀደመው ዘመን በእኛም መካከል የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ ስድሳውን የአገሪቱን ሚኒስቴር መሪዎች በአንድ ምሽት ታርደው በአንድ ጉድጓድ ሲጣሉ፥ ይህን ያደረገው አካል እኛን ይመራናል ብለን በደስታ ተቀበልን ፤ ጅማሬውን እንዳየን ፍጻሜውን ደማችንንና እሬሳችንን በየሜዳው አየን፡፡ ልጆቻችንና ዘመዶቻችን የተገደሉበትንም ጥይት ጭምር እንደዋጋ ከፈልን፡፡ ከዚህ ታሪካችን እንኳ ዛሬም አልተማርንም፡፡
    አንድ ነፍሱን በሽሽት ያስመለጠው ኢዮአታም የወንድሞቹ በዘግናኝ ሁኔታ በወንድሙ መታረድን ሰማ፡፡ ወደገሪዛን ተራራም ጫፍ ወጥቶ ለሴኬማውያን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፡፡ ዛፎች በአንድ ወቅት ንጉሥን በላያቸው ሊሾሙ ወድደው፥ “ወይራውንም፦ በእኛ ላይ ንገሥ አሉት፡፡ ወይራው ግን፦ እግዚአብሔርና ሰዎች በእኔ የሚከበሩበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው፡፡ ዛፎችም በለሱን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት፡፡ በለሱ ግን፦ ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው፡፡ ዛፎችም ወይኑን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት፡፡ ወይኑም፦ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው፡፡ ዛፎችም ሁሉ እሾህን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት፡፡ እሾሁም ዛፎችን፦ በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ፡፡ እንዲሁም ባይሆን እሳት ከእሾህ ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል አላቸው፤ (መሳ.9፥8-15)”
  በዚህ ምሳሌ ኢዮአታም እጅግ የሚያስደንቅ መልዕክትን ነው ያስተላለፈው፥ ወይራ፣ በለስና ወይን መልካምነታቸውንና የዘወትር ሥራቸውን ትተው መሄድ እንደማይፈልጉ ሲናገሩ፥ እሾህ ግን “በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ” በማለት ተናገረ፡፡ አስተውሉ! የእሾኽ ቁጥቋጦ ለዛፍ ጥላ ሆነ ማለት፥ ነገሥታት ለሕዝባቸው ከለላ ሆነው የሚጫወቱት ሚና አርኪ እንዳልነበረ የሚገልጥ ምጸታዊ አነጋገር ነው፤ ይህንን አይነትአገላለጥ ነቢዩ ኢሳይያስ “ከአፌም ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ይጸኑ ዘንድ በግብጽም ጥላ ይታመኑ ዘንድ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ ይሄዳሉ፤ 30፥2፤ ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው!፤(31፥1)ሲናገር፥ ኤርምያስም በሰቆቃው፥ “ስለ እርሱ፦ በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ፤(4፥20)በማለት የማያምኑ አህዛብን ለረዳትነት የመረጡበትን መንገዳቸውንና ውድቀታቸውንም ተናገሩ፡፡
    የእሾኽ ጥላ፤ ጥላ መሆን አይችልም ፤ ቢጠጉት ቅጠል ብቻ የሌለው አይደለም፤ ወግቶ የሚያደማም ነው እንጂ፡፡ ሴኬማውያንና አቤሜሌክ ለእስራኤል እንዲህ ነበሩ፡፡ የሚጠቅማቸውንና መልካም የሚያደርግላቸውን ትተው ደማቸውን የሚያፈስሰውንና የማያስጠልላቸውን መረጡ፡፡ እኛስ ዛሬ ምን እያደረግን ነው፤ ከመንግሥታችን ጋር በወቀሳና በፍቅር ከመነጋገር ወዴት ፤ ወዴት እያመራን ነው?
   በዚህ ክፍል የወቅቱን ጊዜ ብንቃኝበት፥ መንግሥትንም የሚመለከተው ብርቱ ነገር አለ፤ መንግሥትን ለሕዝቡ ጥላ ወይም ከለላ ያልሆነባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ሕዝብ ቅሬታ እያቀረበ ነው፥ ይህንን ቅሬታ እያቀረበ ካለው ሰላማዊና አገር ወዳድ ሕዝብ ዝግ በማለት በትህትና ዝቅ ብሎ ሊሰማ ይገባዋል፡፡ ሕዝቡ ያገኘው መንገደኛና የጐበዝ አለቃ ሁሉ እየመራ ያለው መንግሥት መስማትን ሊሰማ ስላልወደደ ይመስላል፡፡ ሕዝቡ በድንግዝግዝና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከሚያርደው ጋር ተወዳጅቶ ሳይጨርስ መንግሥት ሊያደምጠው ቢችል መልካም ነው፡፡
    እናውቃለን፥ አገር ውስጥ ሁከት ሲያስቀሰቅሱ በጀት የሚበጀትላቸው፣ በሰው ሠላም ማጣት ረብጣ ብር የሚታደላቸው፣ በሰው ሞትና ደም እንጀራቸውንና ድርጅታቸውን የሚያሰፉ፣ የእሾኽ ጥላቸውን እንደዋርካ ያሰፉና ያንዠረገጉ ከመንግሥት ጉያ ሥር ጭምር እንዳሉ እናውቃለን፡፡ መንግሥት ይህንን በማስተዋል ሊነቅሰው ፤ ሊያስተካክለው ይገባዋል፡፡ አልያ ሊመጣ ያለው አጸያፊና ጆሮ ጭው ሊያደርግ  የሚችል ነገር ይሆናል፡፡
    ኢዮአታም ያለው ይኸንኑ ነው፡፡ “እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ፤ ቁ.20” ኢዮአታም የሴኬም ሰዎች እርስ በርሳቸው በጥፋት እንደሚተላለቁ የተናገረው አስፈሪና ከባድ ትንቢት ነው፡፡ ምናልባት እሳቱ ያገኘውን ሁሉ እንደሚበላ ሰደድ እሳት ሊመስል ይችላል፤ የማይደርስ የመሰላቸውና አንድ እንደሆኑ ያስቡ የነበሩት ሴኬማውያንና አቤሜሌክ “እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ፤ ቁ23”እንዲል የመከዳዳት፣ ያለመተማመንና የጥላቻ ክፉ መንፈስ አገኛቸው፡፡ መንግሥቱን ያጸናውና ያቆመው በተንኰልና በግፍ ነበርና እርሱንም ተንኰል ጠልፎ ጣለው፡፡ የሐሰት መሐላና ኪዳን በፍጻሜው ይፈታል፤ የተንኰልም መንገድ በመጨረሻ ዕርቃኑን ይገለጣል፡፡
    ኢዮአታም ቀድሞ ሁሉን ነገር ተናግሮታል፥ የአቤሜሌክን መንገድ የተከተሉ ሁሉ ጥፋታቸው የከፋ ሆኗል፡፡ ቀድመው የአቤሜሌክን የግፍና የአመጻ መንገድ ሳይቃወሙ፥ ከአመጹ ጋር ተባብረው በፍጻሜ ሰላም ታገኘናለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው፥ ከኋላ ሊመጣ ያለውን “ዳፋና ገዳፋ” ሳናስተውል፥ እያደረግን ያለው ነገር ፍጻሜው ወደማንመለስበት እንዳያደርሰን ቆም ብሎ ደጋግሞ ማሰላሰሉ መልካም ነው፡፡
  ዛሬም ደግመን መጠየቅ ያለብን እውነት አለ፤ ከማን ጋር ነው የቆምነው? መንግሥትን እኛ ራሳችን ነን እንዲለወጥልን አግባብ ባለው መንገድ እየጠየቅን ያለነው ወይስ ዓላማቸውንና ግባቸውን፤ ፍጻሜያቸውንም ከማናውቃቸው አካላት ጋር ነው በደመ ነፍስ የምንፋንነው? ይኼ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚለው ጉዞ የት ድረስ ነው የሚወስደን? ኢዮአታሞች መች ይሆን የሚሰሙት ወይም መሰማት የሚጀምሩት? ቆመን ልንሰማ ባልወደድን መጠን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለገዛ ሕሊና መተውም አለና ወደልባችንን መመለስ፤ የቅንነትን መንገድ መፈለጉ ይበጀናል፡፡ 
    ፍጻሜውን ስለማያውቁ ነው ብዙዎች የአዲስ አበባን ደኅንነት በፍርሃት የጠየቁት? የክፉዎች ክፋትና ጥፋት እንዳያገኘን ቆመን ማሰብ ብንጀምር፣ የሚፈሰው የወገን ደምና የሚጠፋው ሕይወት ቢያሳስበን መልካም ነው፡፡ አልያ ግን በምዕራቡ ዓለም ቁጭ ብለው ከዘረኝነት ባልጸዳ ሕሊናቸው የሚደግሱልን “የሞት መንገድ” ፍጻሜያችንን ከእባብ ወደዘንዶ እንዳያደርገው ያሰጋል፡፡ስለአንድነት የሚያወራና የሚተጋ መሪ ለማግኘት እኛ አንድ መሆን እንደሚያስፈልገን ቀድሞ ማወቅ የሚገባን ይመስለኛል ፤ ስለአገር አንድነት ልማትና ብልጥግና ለማውራት ስለጎረቤታችን ልማትና ዕድገት መጨነቅን መዘንጋት የለብንም፡፡
    ከምንም በላይ ክርስትናችን የሚለውን ቅዱስ መርሕ መርሳት የለብንም፡፡ እውን በአዲስ አበባ ሰልፍ አለመሆኑ ነው ወይስ መሆኑ ነበር የሚያስጨንቀው? ግራና ቀኙን ባልለየ ትውልድና ሕዝብ ፤ ማንን እንደሚደግፍና ምንን እንደሚቃወም በማያውቅ ሰልፍ መሳተፍም ፤ በአከባቢውም መገኘት ውጤቱ መራራና ጎምዛዛ ነው፡፡ ሞት ለማበራየት ለምን ሁከት አልተነሳም ብሎ ወሬ ማራገብ ያለንበትን መንፈሳዊ ዝቅጠት ፍንትው አድርጐ ያሳያል፡፡ “አዲስ ሲጠብቁን ሪዮ በቆረጣ ተገኘን” የሚል የስንፍና ንግግርም አይረባንም፡፡ ከፍጻሜው ይልቅ ወደፍጻሜው የተኬደበት መንገድ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ እየሆነ ባለው ነገር እልህ መጋባትና ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ የሚለው አካሄድ መፍትሔ አይሆነንም፡፡ እንደማመጥ፤ መንግሥትም እንደጎበዝ አለቃ አይቸኩል፤ ወደመልካም ነገር ለመምጣት እንተያይ፡፡ መንገዱ ጥፉ ሆኖ ከሚመጣ ችኩል አቤሜሊካዊ ሰላም፥ መንገዱ መልካም ሆኖ ዘግይቶ የሚመጣ ጥቂት ሰላም እጅግ መልካም ነው፡፡

ጌታ አብ አባታችን ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

3 comments:

  1. Enter your comment...are bekihi polotikawan la polotikagnochu tewaw wengel wengel sheteta indezi aynet kadiree atemeselegnem neber

    ReplyDelete
  2. አዕይንተ እግዚአብሄር ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ነዑዳን አባቶች እባካችሁ ታሪክን ብቻ ከመስበክ የወቅታዊ ሁኔታን፤ እንደማር በሚጥመው የዚህን ጽሑፍ ትምህርታዊ ጥቅስ በየዓውደ ምህረቱ ስንሰበሰብ ብዕምነታችን አስተምህሮ ብቃት መንጋዎቻችሁን በትጋት አስተምራችሁ አሳውቃችሁ በእውነተኛው መንገድ ምሩን። ካለበለዚያ ሁኔታዎችን ሽፍንፍን እራሳችሁንም ሽፍንፍን አድርጋችሁ ብትቀመጡ የጊዜ አምላክ ጠብቆ ሁላችንንም የሚያስቀምበት ስፍራው
    ዝግጁ እንደሆነ ሁላችንም እናውቀዋልንና አሁንም ጊዜው አይረፍድም ያላችሁን እይታና ዕውቀት በአንድነት መክራችሁ ዘክራችሁ አትጉን። በተረፈ በየወቅቱ የመንፈሳዊ ዕርጋታ በተሞላበት የምታስተምሩን ብርሃኖቻችን መምህራንን ቃለህይወት ያሰማልን። አሜን !!!

    ReplyDelete
  3. የሆዳም ዲስኩር።

    ReplyDelete