Saturday 28 September 2013

ከሁሉ በፊት

በአለማችን ላይ እጅግ ታላላቅ ከሆኑ ችግሮች መካከል የመሪ እጦት የቀዳሚነቱን ሥፍራ ከሚይዙት አንዱ ነው፡፡  አለቃነት (አለ-ዕቃ ከመሆን ይሰውራችሁና!) ሁሉም የሚመኘውና አብዛኛው ሆኖ ቢያገኘው የሚደሰትበት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ወደብዙ ቢሮዎች ጎራ ያልን እንደሆነ ቅን ፍትህና መፍትሔ ሳይሆን በቅጥ ያጣ የጉበኝነት አዘቅት ውስጥ የተዋጠን አሰራር አይተን ለመትፋት የሰው ምክር አንሻም፡፡
      መሪነትን በተመለከተ ትልቁ አብነት ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በምሪቱና በመግቦቱ ውስጥ አደላዳይ ሆኖ ለጻድቁና ለኃጥዑ እኩል ፀሐይ ዝናብና ነፋስን … ይሰጣል፡፡እውነተኛ መሪ ነውና ሳያበላልጥ ፍጥረቱን እኩል ይወዳል፡፡ከተፈጥሮ እውቀት እንኳ አንዳች ሳያጓድል ጥበብንና ማስተዋልን አብዝቶ ያጎናጽፈዋል፡፡
      የተረጋጋና ሰላማዊ ሥርወ መንግስትን መመስረት የሚቻለው መሪዎች ለተፈጥሮ ህግና ለህሊናቸው መገዛት እንዲችሉ ሲቀረጹ ነው፡፡የቅን ፈራጅ መንግስት መሰረቱ ቅን መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎች ለጉበኝነትና ለሴሰኝነት ዙፋናቸውን አሳልፈው በሰጡ ቁጥር  አጋንንት የጨበጡትን በትር በመጠቀም ህዝብን ያስጨንቃሉ ድኻ አደጉንም ይበድላሉ፡፡
      መልካምና ቅን መሪዎች ያመኑ ክርስቲያን ባይሆኑ እንኳ ለተፈጥሮ ህግና ለህሊናቸው የታመኑ ከሆኑ በመልካም ስብዕና ታግዘው  ለህዝቡ የሚሆነውን ነገር አሻግረው ቀድመው ያዩለታል፡፡ከሥጋ ድካሙም ያሳርፉታል፡፡ እነማህተመ ጋንዲ ክርስቲያን አልነበሩም ነገር ግን ክርስቲያን ነን ብለው ህዝብና ወገናቸውን በትዕዛዝ ከማረድ እስከማሳረድ ከደረሱ ከሐገራችንና ከአለማችን መሪዎች በተወደደ ስብዕና እጅግ የላቁ ተወዳጆች ነበሩ፡፡

Wednesday 25 September 2013

"አድኃነ ህዝቦ በመስቀሉ" "ህዝቡን በመስቀሉ አዳነ"(ቅዱስ ያሬድ)

ምድራችን ካስተናገደቻቸው አስከፊ ገጽታ ካላቸው ጦርነቶች መካከል አንዱ በተለያዩ ዘመናት "በክርስቲያኖች" የተመራውና ብዙ ሚሊዮኖችን ለህልፈት የዳረገው የመስቀል ጦረኞች ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱን ጳጳሳት በመባረክ፣ካህናት ጸሎት በማድረግ ይራዱ እንደነበርም ተዘግቧል፡፡ሰውን ወዳዱ ጌታ ኢየሱስ የፍጡር ደም መፍሰሱ እንዲያባራ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን በመስቀሉ ደሙን አፍስሶ ሲያድነን አመጸኛ ክርስቲያኖች ግን የሰላም ስሙንና አርማውን አንግበው ምድሪቱን በግፍ ደም አጥለቀለቋት፡፡
       ክርስቶስ ኢየሱስ ፣መድኃኒቱ ጌታ "ስለእኛ የተረገመ ሆኖ ከህግ እርግማን ሊዋጀን" ፤ ከኃጢአታችንም ሁሉ ሊያነጻን ፤የእኛን በኃጢአት መረገም አርቆ የእርሱን ጽድቅና ቅድስና እንዲሁ ያለዋጋ ሊሰጠንና "የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል" እርሱ እንደህጉ የተረገመ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡(ገላ.3÷14) እርሱ የተሰቀለው ህይወት እንዲሆንልንና እንዲበዛልን ፣መዳናችንም እውን ሆኖ ከኃጢአት ባርነት ነጻ እንድንወጣ ነው፡፡
       እኛን ኃጢአተኞችን ከኃጢአት ባርነትና ከህግ መርገም ነጻ ለማውጣትና ለማዳን የተከፈለው ተካካይ የሌለው ዋጋ የመስቀሉ ቃል የተባለ የክርስቶስ ሞትና (ገላ.3÷13) የከበረ ደሙ ነው፡፡(1ጴጥ.1÷19) እርሱ በመስቀል ካልተሰቀለ ደሙንም ለስርየት ካላፈሰሰ በቀር እኛ ወደእርሱ፣ በሰማያት ወዳለአባቱም መቅረብ አይሆንልንም፡፡(ዮሐ.12÷32፤ ኤፌ.2÷13)፡፡
    ከምድር እስከሰማይ የተዘረጋው ያ እውነተኛ የያዕቆብ መሰላል ክርስቶስ(ዮሐ.1÷52) በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ እግዚአብሔርና ሰውን የለየው የዘመናት የጠብ ግድግዳ ፈርሶ ሰውና ሰው፣ ሰውና እግዚአብሔር ፍጹም ታርቀው አንድ ሆነዋል፡፡የነበረብንም የዕዳ ጽህፈትና በደል በተትረፈረፈው በመስቀሉ የደም ዋጋ ተደምስሶልናል፡፡(ቆላ.1÷20፤2÷14፤ራዕ.12÷11)

Saturday 21 September 2013

ያኖራል መዓዛው



የሳሮን አበባ - ፅጌረዳም አይደል
የህብረ ቀለማት - የውበትም ፀዳል
የሚማርክ ነገር - ፍፁም የለበትም
መዓዛው ሌላ ነው - አይደል  የሰሊክም
'ሚሸተው ሌላ ነው - ሮማንም አይመስልም፡፡
ሽቱ አርከፍክፎ
ሱፍ ከረባት ለብሶ
ቁመቱ ቢያማልል
መልኩ ቢያነሆልል
ቃሉ ምን ቢማርክ

Wednesday 18 September 2013

የተሰሎንቄ እብዶች - 2 (ፈጣኖቹ የጠላት እግሮች!!!)


የመንግስቱን ወንጌል ላለመስማት የራስን በር ጠርቅሞ መዝጋት፣የወንጌሉን ዜና የሚናኙትንም እየገፈተሩ ከሐገርና ከከተማ ማሳደድና ማባረር ይቻላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በዘመን ፍጻሜ የተሰጣት ትልቅ ኃላፊነትና አደራ ተኩላዎች በሚበዙባት ምድርና ሐገር ላይ በወንጌሉ ህይወቷን ማነጽና ሳትሰለች ለፍጥረት ሁሉ መናገር ነው፡፡ወንጌሉን ደግሞ አፋችን ተላቆ ገና መናገር ስንጀምረው ተግዳሮቱና ነቀፌታው ሳይውል ሳያድር ያገኘናል፡፡ 
       በተሰሎንቄ ከተማ ያሉ የወንጌል ጠላቶች ወንጌሉንና ወንጌላውያኑን መስማትና ማየት እንኳ ተጠይፈው በጩኸት ድምጽ አሳደዋቸዋል፡፡በጌታ ቃል እንደተነገራቸው ወንጌላውያኑ የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ከከተማይቱ ወጡ፡፡ (ማቴ.10÷14)፡፡ ወንጌል ከእግዚአብሔር ወደእኛ የተዘረጋች የህይወት እጅ ናት፡፡ ለተዘረጋችው እጅ ምላሽ ካልሰጠን እንደጽዋ ለባለተረኛ ትተላለፋለች፡፡ ትላንት እንደዋዛ የሚበዙ እውነተኛ የወንጌል አገልጋዮችን አሳደን ዛሬ ብዙዎቹ አውደምህረትና መድረኮች በፌዘኛና አስቂ ሰባክያን ተይዘዋል፡፡ እውነተኞችን ከመካከላችን ባራቅን ቁጥር ለሐሰተኞችና ለፌዘኞች መገዛታችን ግድ ነው፡፡ ለትልቁ እውነት ካልተገዛን ለትንሹና ለወራዳው ሐሰት መገዛታችን እሙን ነው፡፡ 

Friday 13 September 2013

"ተራ" ምዕመናን አሉን?



        ባለኝ የሥራ ኃላፊነት በአብያተ ክርስቲያናት አለመግባባት መካከል ግጭት ሲፈጠር  አንዳንዴ በአባልነት ፣ሌላ ጊዜ በሽማግሌነት፣አልፎ አልፎ ደግሞ በታዛቢነትና ክስ በማድመጥ የምገኝበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡የሌላውን ልተወውና የእኛን የአንድ ቤተ ክርስቲያን  አማኞች ጎራ ለይተው በ"ለኃይማኖቴ እቀናለሁ" በሚል  ፈሊጥ ሲሰዳደቡ ፣ሲካሰሱ ፣ሲደባደቡ፣ሲነካከሱ፣ዓለማዊ ፍርድ ቤቶች ላይ ሲጨቃጨቁ እንደማየት አስቀያሚና አጸያፊ ነውር የለም፡፡ምንም እንኳ ዛሬ ባይታፈርም፡፡ቤተ ክርስቲያን ጸጋ እግዚአብሔር ሲለያት ጠላት ሳይኖርባት እንደእፉኝት ራሷን በራሷ እየበላች ታልቃለች፡፡
     እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ፍቅር ነው ሲባል በምንም አይነት ተአምር ቅያሜ አያውቅም፣ማፍቀር እንጂ መጥላት አይችልም  ማለት ነው፡፡ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን እንደግብዝ ፈሪሳዊና እንደተፈጥሮ ሰው "የእኛ የሆነውን ብቻ በመውደድ " ሳይሆን ጠላትንም እንድንወድ ጠላት የሆነውን እኛን በወደደ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅርና ርህራሄ ተለምነናል፡፡እኛ ጠላትና ባላጋራ ሳለን ከተወደድን ፍቅሩ አለልክ በዝቶልናል ማለት ነው፡፡ጠላት ሆነን በእንዲሁ ፍቅር ከተወደድን ሌላውን ጠላት ነው ለማለት ሥልጣን ከየት አገኘን? እኛን የያዘ እጅ ሌላውንም የያዘ ነው፡፡የእኛን ጠላትነት በፍቅር የቻለ ልብ የሌላውንም ጠላትነት አብዝቶ የቻለ ነው፡፡አንተ ነውር የተከደነልህ የሌላውን ነውር ታወራና ትከስ ዘንድ ማን ነህ?

Wednesday 11 September 2013

ሺሁ ዕለት አይሞላም!!!



በዕድሜ ስልቻ  በዘመን ቀልቀሎ
ሰው እንዴት ይኖራል ምንም ተሸክሞ?...
ጽድቁ የመርገም ጨርቅ
በጎነቱ ፍትፍትና ምርቅ
መልካምነቱ አሮጌ እራፊ
አሳዳጅና ክፉ ቀሳፊ
ነግሶ ሳለ በዚያ ዘመን
ይገርመኛል ይደንቀኛል እኔን!!!

Saturday 7 September 2013

"በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት"(ሉቃ.13÷8)



          የዘመን መጨመር በራሱ አንድ ሰፊ የንስሐ በር ነው፡፡እግዚአብሔር ብዙ ዘመን በመስጠት ዕድሜ የሚያትረፈርፍልን ኃጢአተኞች መሆናችንን  አውቀን ፈጥነን ወደልባችን በመመለስ ንስሐ እንድንገባ ነው፡፡ዘመን የተጨመረልን ከሞቱት ዘመድና ወገኖቻችን ይልቅ ጻድቃንና የተሻልን መልካሞች ስለሆንን አይደለም፡፡ይልቁን በደሙ ማስተሰርያነት ያላወራረድነው ኃጢአት ስላለብንና በዚያ ኃጢአት እንዳንሞት "ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ እንዲሞት"(ህዝ.3÷18) የማይፈቅድ እግዚአብሔር ዕድል አብዝቶልን ነው፡፡
          ከክፉ ልማዶቻችን መካከል አንዱ በሰው ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ በኃጢአቱና ከእኛ ይልቅ በከፋ ነውሩ እንደደረሰበት አድርገን እናወራለን፡፡እናምናለን፡፡ያ አደጋ እኛን ያላገኘን በተሻለ በጎነታችንም እንደሆነ እናስባለን፡፡በአንድ ወቅት ሰዎች ወደጌታ ዘንድ መጥተው (ሉቃ.13÷1-6) ያሉት ይህንን ነበር፡፡ ጲላጦስ በመሰውያው አጠገብ ያስገደላቸው የገሊላ ሰዎችና በሰሊሆም ግንቡ ተንዶ የሞቱት ሰዎች በህይወት ካሉት ይልቅ ክፉዎች በመሆናቸው ነው ብለው አወሩለት፡፡ 
        አዎ! ብዙ ጊዜ የምሰማው ነገር አለ፡፡ከባህር ማዶ በአውሮፓና በአሜሪካ ከባባድ አውሎ ነፋሶችና የምድር መናወጦች በተከሰቱ ጊዜ ከብዙ ሰው አንደበት "የኃጢአታቸው ዋጋ ነው!!!" እየተባለ ሲወራ

Tuesday 3 September 2013

ልከኛው ጳውሎስ - 2

  Please read in PDF     
    ከአዲስ ኪዳን አገልጋዮች የተደነቀ የንግግር ችሎታ የሌለውና ነገር አቅንቶ መናገር የማይችለው (ከብሉይ ኪዳኑ ጥልቅ አዋቂና ልዩ ተናጋሪው አጵሎስ አንጻር ሲታይ) በጸጋው ያገለገለ ሐዋርያ እንደጳውሎስ ያለ አይመስልም፡፡ ጸጋውን፣ አለዋጋ የተሰጠውን ሐብትና መልካም ስጦታም አስቦ በሥጋ ለመመካት ለአንዲት ሰዐት በመዘናጋት ያዋለ አይደለም፡፡
      የጌታ የትንሣዔውን ኃይል ለእርሱ እንዴት እንደተገለጠ ሲናገር፥ " …  ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም(1ቆሮ.15÷8-11)፡፡