Wednesday 30 December 2020

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፫)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

·        ኀጢአት

በመጽሐፍ ቅዱስ ኀጢአት ወይም ኀጢአትን ማድረግ አንድና ወጥ ትርጉም ያለው ብቻ አይደለም፤ በተለይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአምስት በተለያዩ መንገዶች ተገልጦ እንመለከተዋለን፤

1.   ሃማርቲያ[ሺያ]፦ (ዒላማን መሳት)፦ ይህ ቃል በአዲስ ቃል ውስጥ ኀጢአት ወይም ኀጢአተኛ ተብሎ ከ250 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል፤ ትርጕሙም እግዚአብሔር ወዳቀደላቸው ዓላማና ግብ ኀጢአትን በማድረግ፣ በገዛ ፈቃዳቸው ወይም ምርጫቸው ባለመድረሳቸው አዳምና ሔዋን[የሰው ልጆች] ዒላማ መሳታቸውን የሚያመለክት ነው፤ እግዚአብሔር ወዳሰበላቸውና ወዳቀደላቸው ዐሳብና ክብር አልደረሱምና ከእግዚአብሔር ክብር ጎደሉ (ማቴ. 9፥2፤ ዮሐ. 1፥29፤ ሮሜ 3፥23)።

Saturday 26 December 2020

ውርርዱ በገብርኤል አልነበረም!

 Please read in PDF

መግቢያ

በመጽሐፎቻቸው ምዕራፍ ብዛት ዓበይት ነቢያት ተብለው ከሚጠሩት አንዱ፣ የነቢየ እግዚአብሔር የዳንኤል ትንቢት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ጸሐፊ ራሱ ለመኾኑ በራሱ በትንቢት መጽሐፉ ውስጥና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት አለ (9፥2፤ 10፥2፤ ማቴ. 24፥15ን ከዳን. 9፥27 እና 11፥31 ጋር ያስተያዩ)። የዳንኤል መጽሐፍ ዋና ሃሳብ ወይም ሊነግረን የወደደው እግዚአብሔራዊ መልእክት፣ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ጌትነትና ድል ነሺነቱን ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ጌታ ስለ ኾነ፣ “ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ የወደደውን ያሰለጥናል” (5፥21)።

Wednesday 23 December 2020

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፪)

 Please read in PDF

መግቢያ ፪

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ሰጊጎት የሠራባቸው ቃላት

ካለፈው የቀጠለ …

ቀጥታ ወደ መጽሐፉ ምዘና ከመሄዳችን በፊት፣ በመጽሐፉ ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከአማናዊት ኦርቶዶክሳዊት[1] እምነት ወይም እይታ ውጪ፣ ትርጉም ስለ ተሰጣቸው ቃላት መመልከቱ እጅግ ጠቃሚ መስሎ ታይቶናል። በተለይም በመግቢያ ላይ ካለው፣ ከመዳን ትምህርት ጋር ተያይዘው የተነገሩትን ቃላት መመልከት፣ ብዙ ሳንደክም የ“መድሎተ ጽድቅን”፣ መድሎተ ስሑትነት በሚገባ እንድናስተውል ይረዳናል። ጸሐፊው ቃላትን በማጣመም ለራሱ ትምህርት ተጠቅሞባቸዋል። እንዲያውም በአንዳንድ የነገረ መለኮት ቃላት ላይ አንዳች ግንዛቤ የለውም ወይም ኾን ብሎ ያምታታል።

Monday 21 December 2020

“ዲያቆን” ሄኖክ ሃይሌና አዲሱ ኑፋቄው!

 Please read in PDF

“እመቤታችን ማማለድ አይደለም አፍርሳን መሥራት ትችላለች” [እውነት?!]

“ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” (1ቆሮ. 3፥17)

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ቅዱስ ቃሉ የሚናገረውን ብቻ መናገር ኑፋቄነት፣ ቅዱስ ቃሉ የማይለውን መናገር ደግሞ አማኝነት ወይም “የቤት ልጅ” የሚያስብለው ተግባር ከኖረ ሰነባበተ። ለቅዱሳን መላእክትም ኾኑ ሰዎች፣ “ቃሉ ከተናገረው በላይ መናገር ትክክል አይደለም፣ የተነገረው ብቻ ሊነገርላቸው ይገባል” ስንል፣ “ጸረ ቅዱሳን፣ ጸረ ማርያም፣ ጸረ መላእክት …” የሚል ስድብ ያስቀጥላል። ነገር ግን ለቅዱሳን፣ ቅዱስ ቃሉ የሚናገረውን ብቻ አለመናገር የቅዱሳኑ ጠላቶች መኾናቸውን በቅዱስ ቃሉ ላይ ጨምረው ተናጋሪዎቹ ያስተዋሉ አይመስሉም።

Wednesday 16 December 2020

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፩)

 Please read in PDF

መግቢያ

እውነተኛ መድሎተ ጽድቅ ወይም የእውነት ሚዛን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። “መሠረቱ የጌታችንና እርሱ አድሮባቸው ቀድመው ትንቢት የተናገሩ የነቢያት በኋላም ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የተረጐሙና ያስተማሩ የሐዋርያት ትምህርት ነው። ከዚህ ውጭ አልተንቀሳቀሱም።”[1] ራሱ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ምንም ሊነጻጸርና ሊወዳደር በማይችል መልኩ አክብራና አልቃ የምታምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው” በማለት ቢመሰክርም፣ ለዚህ ታላቅ እውነት ግን ጸሐፊውም ኾነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተግባራዊ ምላሽ ሲሰጡ አይስተዋልም።[2]

Monday 14 December 2020

“ዘማሪት” ትርሃስና “ወደ ኋላ አልልም ከእንግዲህ” የሚለው መዝሙሯ!

 Please read in PDF

“አልወጣሁም እያልሽኝ ነው፤ … እያልሽ ያለው ነገር ግን እየተዋጠልኝ አይደለም፤ እየተቀበልኹትም አይደለም … ” ይህን የተናገረው ቃለ መጠይቅ ያደረገላት ልጅ ነው፤ ጌታ ኢየሱስን የሚያፍሩበት ኹሉ እንዲህ ሊዋረዱና ሊያፍሩ ይገባቸዋል! በልጁ የሚያፍር፣ በምድር ማንም ባያምነውና “ንግግርህ አይዋጥልኝም” ቢለው ትክክል ነው፤ ትርሃስ እንዲህ ስትባይ ምን ተሰምቶሽ ይኾን? በኢየሱስ አፍረሽ ማን እንዲመሰክርልሽ ወደሽ ነበር?!

Wednesday 9 December 2020

ላ’ንዱ የ’ኔ ቢጤ

Please read in PDF

   ጥንት  እንደ ሰማነው በቃየል እጀታ

   በኋላኛው ዘመን በኢየሱስ ጌታ

Monday 30 November 2020

ጽዮን፣ ታቦትን አይወክልም!

 Please read in PDF

መግቢያ

በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አሳታሚነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕሥራ ምዕት(አዲሱ ሚሊኒየም) ላይ “የራስዋን” አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ አሳትማለች። መጽሐፉ በተለምዶ “ሰማንያ አሐዱ” ተብሎ የሚጠራ ቢኾንም፣ ነገር ግን አያሌ ግልጽ ስህተቶችን በውስጡ እንደ ያዘ ወይም እንዲይዝ ታስቦበት የታተመ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በተለይም በግልጽ የተቀመጡና የታወቁ ሐረጋትን በመቀየር ድፍረት ያለበትን ስህተት ሠርቶአል። ከሠራቸው ስህተቶች አንዱም የእግዚአብሔርን ታቦት ለግል ዓላማቸው ከእግዚአብሔር ይልቅ ለማርያም[ለታቦተ ጽዮን] ለመስጠት በሚመች መንገድ ወደ ሴት ጾታ መለወጣቸው ነው።


Wednesday 25 November 2020

በኢየሱስ የሚያፍሩ የማርያም ባርያዎች!

 Please read in PDF

መግቢያ

ተአምረ ማርያምን የስህተት መጽሐፍ ከሚያሰኘው እልፍ ነገሮች አንዱ፣ “ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ፣ የእመቤታችን ክብሯ ምስጋናዋ ሁሉ ተጽፎ ቢኾን ምን ብራና በቻለው ነበር፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እርስዋን አክብሯት ለእናንተ ለኀጥአን መድኀኒታችሁ ናትና …” የሚሉ ሐረጋትን በመጠቀም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናውቃት ከኢየሱስ እናት ማርያም በተቃራኒ፣ እንግዳና ልዩ የኾነችውን፣ አምልኮ ወዳድዋን ማርያምን ለመሳል በብርቱ በመጣሩ ነው። ይህ ላይደንቅ ይችላል፤ ነገር ግን ወንጌል ተረዳን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አነበብን፣ እንዘምራለን፣ እንሰብካለን፣ ዐሰረ ክህነት አለን … የሚሉቱ ከተአምረ ማርያም ያነሰ እውቀት መያዛቸው፣ ጌታችን ኢየሱስ በናዝሬት ሰዎች የተደነቀውን ያህል እኛም እጅግ እንደነቅባቸዋለን። አለማመናቸው በእውነት ያስደንቃል!

Tuesday 24 November 2020

Monday 16 November 2020

“ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃ. 13፥5)

 Please read in PDF

  ሉቃስ ወንጌላዊው በቅዱስ ወንጌሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለመላለሙ የመጣ መድኀኒት” እንደ ኾነ በስፋት ይጽፍልናል (2፥14፤ 3፥3፤ 9፥52፤ 10፥33)። “ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያይ” ዘንድ ሰው ኹሉ ንስሐ ይገባ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ በየመንደርና ከተሞች እየተዘዋወረ ማስተማሩን ደጋግሞ ይነግረናል። “መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥” እንዲል፤ (ሐዋ. 10፥38)።

ሉቃስ በወንጌሉ ትኵረት ከሰጣቸው ትምህርቶች አንዱ ደግሞ ንስሐና የክርስቶስን ፍጹም ርኅራኄ ነው፤ በተለይም ደግሞ ማኅበረ ሰቡ ፍጹም ስላገለላቸው ኀጢአተኞች፣ ቀራጮች፣ ሳምራውያን (7፥36፤ 9፥52፤ 10፥33፤ 15፥1፤ 19፥5)፣ ከራሱ ጋር ለተሰቀለው ወንበዴ (23፥39) ክርስቶስ ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ እንዳሳየ ሉቃስ አምልቶ ይነግረናል። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ለኀጢአተኞች ያሳየውን ርኅራኄ በሚያስደንቅ ዕይታ፣ አንጀት ስፍስፍ በሚያደርግ መልኩ ገልጦልናል። ዛሬም ድረስ ይህ እውነት ፈክቶና ደምቆ መታየቱ እንዴት ይደንቃል!?

Friday 6 November 2020

ሰዱቃዊ ጠባይ ከመያዝ ተጠበቁ!

 Please read in PDF

የሰዱቃውያንን ጠባይ ያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፦

1-   የመሲሑ ክርስቶስን መምጣት የማይቀበሉና የማያምኑ፣

2-   የሙሴን ሕግ ብቻ እንጂ የመዝሙራትንና የትንቢትን መጻሕፍት የማይቀበሉ፣

3-   ትንሣኤ ሙታንን፣ መላእክትንና መንፈስ ቅዱስን የማይቀበሉና መኖሩንም የማያምኑ(ማቴ. 22÷23-33)፣

4-   ባለጠጐችና በጊዜው በጣም የተሻለውን ቅንጡ ኑሮ የሚኖሩ፣ የካህናት ቡድን የኾኑ፣

Tuesday 3 November 2020

Saturday 24 October 2020

ከፖፑ ባሻገር፣ የእኛስ ነገር?

 Please read in PDF

ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ ስላለበት ኹኔታ ፍርሃት አለኝ!

ከጥቂት ዓመታት በፊት በእጅ ስልኬ ላይ አንዲት እህት ደወለች፤ አነሳሁት። ሰቅጣጭ ልቅሶና መራራርነት ከድምጿ ይነበባል። እናም ሕይወቷን መጥላቷን፣ ራሷንም ልታጠፋ መዘጋጀቷንና የመጨረሻ የመፍትሔ ዕድሏን ለመሞከር መደወሏን ነገረችኝ። ከብዙ ተማህጽኖና ምክር በኋላ ላገኛት ወስኜ አገኘኋት። ሳገኛት መርዝና ገመድ አዘጋጅታ ራስዋን ለማጥፋት ወስና የተዘጋጀች መኾኑን አስተዋልኩ። በጌታ ብርታት ክፉ ተግባርዋን እንድትተው ካደረግሁ በኋላ ታሪኳን መስማት ጀመርኩ።

Thursday 22 October 2020

ፖፑን ምን ነካቸው?

 Please read in PDF

መግቢያ

የሮሙ ፖፕ ፍራንሲስ ያለፈው ማክሰኞ ግብረ ሰዶማውያን በአንድነት እንዲኖሩ መፍቀዳቸውን፣ ይህም የእግዚአብሔር ፈቃድ መኾኑንና እኛም ዕውቅና ልንሰጣቸው እንደሚገባቸው መናገራቸውን እየሰቀጠጠኝ ተመልክቻለሁ። ምክንያታቸውንም ሲያቀርቡ፣ “እነሱ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ግብረ ሰዶማውን የቤተሰቡ አባል የመኾን መብት አላቸው። … እኛ መፍጠር ለብን የሲቪል ማኅበራት ሕግ ነው። በዚያ መንገድ በሕጋዊነት ተሸፍነዋል። ለዚህም ቆሜአለሁ።”  በማለት ተናግረዋል።[1]

Tuesday 20 October 2020

ስላንተ ልጣላት

Please read in PDF

አልወድህም አንተን አልወድህም የምር
ከአንደበት አያልፍም ላንተ ያለኝ ፍቅር

Monday 12 October 2020

የልጁን መልክ መምሰል (ክፍል ፬ና መጨረሻ)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ…

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

እግዚአብሔር ሃይማኖታዊ ዝንባሌና መልኩ ብቻ እንዲኖረን አይወድም። “ሙሉ ሰው ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ” ለማደግ፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት መምጣት (ኤፌ. 4፥13)፤ ስለ እውነት ስለ እግዚአብሔር ልጅ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል።

Wednesday 7 October 2020

የልጁን መልክ መምሰል (ክፍል ፫)

Please read in PDF

እንዲህ ነበርን!

ካለፈው የቀጠለ...

5. በአሳባችን ጠላቶች ነበርን፦ ኹላችን በእግዚአብሔር ፊት፣ “… ክፉ ሥራንም በማድረግ በአሳባችን ጠላቶች ነበርን” (ቈላ.1፥21-22)፡፡ እጅግ ክፉዎች ከመኾናችን የተነሣ በእእምሮአችንና በልባችን ለራሳችን የምናዳላ ራስ ወዳዶች ነበርን፡፡ በምድር ላይ አንድም መልካም ሰው መገኘት እስከማይችል ድረስ ኹላችንም ለእግዚአብሔር ጠላቶች ነበርን፡፡

Wednesday 30 September 2020

እሬቻ አምልኮ አይደለምን?!

 please read in PDF

መግቢያ

   ስለ እሬቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምንሰማቸው ልዝብ አሳቦች አንዱ፣ “የኦሮሞ ባህልን የምናንጸባርቀበት ብቻ እንጂ አንዳችም አምልኮአዊ መልክ የለውም” የሚለው ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። ይህን ለማለት ያስደፈረው እውነታ ደግሞ በክርስትና ጥላ የተጠለሉ አያሌ ኦርቶዶክሳውያንና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት “አማኞች” እና ስለ እሬቻ ዘብ የቆሙ ሰዎች የሚያቀርቡት የተለሳለሰ ዐሳብ ነው። እሬቻን የሚያከብሩት ኦርቶዶክሳውያንና የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናት አማኞች፣ አምልኮአዊ መልክ እንዳለው ስለ ገባቸው ወይም ስለ ተጠራጠሩ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ “ባህላችንን እንወዳለን” የሚል አባባይ ምክንያት በመጥቀስ ለማስረዳት ሲንገታገቱ አስተውያለሁ።



Saturday 26 September 2020

መስቀሉን የማያውቅ መስቀል

 Please read in PDF

መግቢያ

  በአገራችን በኢትዮጲያ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ከደመራ ጋር ተያይዞ የሚከበረው በዓል  ነው፤ በዓሉ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እንጨቱ መስቀል፣ ለዓመታት ከተቀበረበት ቦታ መውጣቱን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው። በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን፣ ይህ የመስቀል በዓል በአያሌ የአገራችን ሕዝብ ባህሎች ውስጥ የተለያየ መልክና ቅርጽ ይዞ ሲከበር እንመለከታለን። ሃይማኖታዊው ትውፊት መስቀሉ ከተቀበረበት መውጣቱን በማሰብ ሲያከብር፣ አያሌ ባህሎች ደግሞ ከዘመን መለወጫ ጋር በማያያዝ በዓሉን ያከብሩታል።

Wednesday 23 September 2020

የአሸናፊ ገብረ ማርያም(ቀሲስ) “ጐስአ ልብየ ቃለ ሰናየ” ማርያም ናትን?

 Please read in PDF

መግቢያ

  አሸናፊ ገብረ ማርያም(ቀሲስ) ጥቂት የማይባሉ መዝሙሮችን “ሠርቶ”፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ጀምሮ ተጠቅመንባቸዋል፤ ታንጸንባቸዋል፤ አምልከንባቸዋል። ለጌታ የሚሠራቸው መዝሙሮች እጅግ መሳጭና ትኵረትን ቀንብበው የሚይዙና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው ናቸው። በዚህ ረገድ ከማከብራቸውና ከምወዳቸው ዘማሪዎች መካከል አንዱ ነው።

Saturday 19 September 2020

የልጁን መልክ መምሰል (ክፍል ፪)

Please read in PDF

እንዲህ ነበርን!

    አዳም “የመታዘዝን ፍሬ” ባለመብላት እንዲታዘዝ ቢነገረውም፣ እርሱ ግን የሰይጣንን ድምጽ ተከትሎ በመሄድና የተከለከለውን ወስዶ ከበላበት ቀን ጀምሮ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እርሱና ልጆቹ ሁሉ፣ እግዚአብሔር የተወን እየመሰለን አብዝተን ኃጢአትን ሠራን፤ ጨመርንም። ከዚህም የተነሣ፦

Thursday 10 September 2020

Tuesday 8 September 2020

ያለ ኢየሱስ ስርየት የለም!

 Please read in PDF

  ጳጉሜ 3 ብዙዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚላተሙበትን ድርጊት የሚፈጽሙበት ቀን ነው፤ በሌላ ቋንቋ፣ “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?” (ዕብ. 10፥29) የሚለውን ቃል በግልጥ የሚቃወሙበት ቀን ነው፤ “በመልአኩ ሩፋኤል” ስም መጠበል ወይም መጠመቅ ከኀጢአት ያነጻል የሚል ከንቱ ልፍለፋ።

Thursday 3 September 2020

Sunday 30 August 2020

የልጁን መልክ መምሰል (ክፍል ፩)

Please read in PDF

    “ሁላችን በሃይማኖትና የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ፍጻሜ ልክ የአካል መጠን እንዲደርስ ፍጹም ሰው እንሁን” (ኤፌ.4፥13)

መግቢያ

    በዘመናችን ሰዎች ክርስቶስን በትክክል መኾን እንደሚቻላቸው አያሌ የስህተት ትምህርቶችን መስማት ከጀመርን ሰነባብተናል። አንዳንዴ ክርስቶስን የፍጥረቱ አካል በማድረግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እኛ ራሱ ክርስቶስን ልንኾን እንደምንችል በአደባባይ ታውጆአል፤ በተለያየ መንገድ ይህን ትምህርት ፊት ለፊት በመቃወም፣ የትምህርቱን ስሑትነትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተቀዳ መኾኑን ተናግረናል፤ አስተምረናል። ዛሬም ክርስቶስ የፍጥረት አካል እንዳይደለ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩንን፣ ፍጹም አምላክነቱና ፍጹም ሰውነቱን  ደፍረን እንናገራለን።

Tuesday 18 August 2020

የመጽሐፍ ቅዱሱ ክርስቶስ - ክብሩና ሞቱ (ሉቃ. 9፥28-36)

  Please read in PDF

  በግርማ መለኮት የተፈራውና ማንም ሊቀርበው የማይችለው ጌታ፣ በክበበ ትስብእት በናዝሬት ከምትኖር ከአንዲት ድኻ ሴት ከማርያም ተወልዶ፣ በተዋረደው ዓለም በውርደት ተመላለሰ። ከመሰቀሉ በፊት ሰውን ሥጋ በመልበሱ ብቻ ተዋረደ። በበረት ከመወለዱ በፊት፣ በናዝሬት መንደር ከአንዲት ሴት ማኅፀን በማደሩ እጅግ፤ እጅግ ዝቅ አለ። ከኀጢአተኞች ጋር በመቈጠሩና ከእነርሱም ጋር በመዋሉ ደግሞ ኢየሱስ፣ ስድባችንን ኹሉ በመሸከም መስቀሉን በመላ ዘመኑ ታገሠ።

Saturday 15 August 2020

ስለ ማርያም “ከሚሸቅጡ” ተጠበቁ!

Please read in PDF

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ብቻ መናገር አስተዋይነት፤ ያልተናገረውን ደግሞ አለመጨመር ፍጹም ታማኝነት ነው። እኛ ሰውን ደስ ለማሰኘት የተናገርነው “እውነት”፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ያልተናገረው ሐሰት ሊኾን የሚችልበት አንዳች ሚዛን የለም፤ የእውነት እውነተኛው ሚዛን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ከኾነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተናገረውና ያላለው ኹሉ ሐሰት፣ እርሱ የተናገረውና በእርሱ ያለው ብቻ እውነት ነው። ሚዛንን ስቶ ሚዛናዊ መኾን ፈጽሞ አይቻልምና።

Thursday 13 August 2020

የመጽሐፍ ቅዱሱ - ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው መሲሕ (ሉቃ. 19፥41-44)

Please read in PDF

   ጌታችን ኢየሱስ ስለ ማልቀሱ የተነገረው እጅግ በጣም ውሱን ቦታ ብቻ ነው፤ ካለቀሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ያለቀሰው ልቅሶ ነበር። ያለቀሰው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ፣ ከተማይቱን ፊት ለፊት በመመልከት ነበር። ሚስቱን አብዝቶ የሚወድድ ጐልማሳ፣ ሚስቱ በተወችው ጊዜ በስብራት እንደሚያለቅስ እንዲሁ፣ ኢየሱስም የከተማዋ ኹለንተና ከሚታይበት ከደብረ ዘይት ተራራ ፊት ለፊት ተቀምጦ ለኢየሩሳሌም አለቀሰላት።

Tuesday 4 August 2020

ክርስቲያኖች ወደ ቄሳር ሲጠጉ እፈራለሁ!

  ለምንኖረው ሕይወትና ለማናቸውም የክርስትናችን የኑሮ ዘይቤ፣ ማዕከሉ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ያልተኖረ የሕይወት አብነት የለንም፤ የተኖረና በድል የተጠናቀቀ የሕይወት አብነት ግን አለን፤ እርሱም የክርስቶስ። ክርስቶስ ያልኖረውን ሕይወት ኑሩ አላለንም፤ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤” (ማቴ. 11፥28) ያለን ጌታ፣ “ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልናል” (1ጴጥ. 2፥21) ስለዚህ የማይጨበጥ፣ በንግግር ብቻ የሚተረክ፣ በተመስጦአዊ ስብከቶች የሚሰበክ ብቻ ያይደለ፤ የሚኖር፣ የሚሻተት፣ የሚቀመስ፣ የሚጣጣም ቅዱስ ሕይወትን ሰጥቶናል።

Saturday 1 August 2020

የአፍላህን ጊዜ

Please read in PDF

ወዲያ ገረገራ፣ ጥግ ላይ ያለኸው
ያለህ  የምትመስል፣  ሻግተህ  ያረጀኸው

Sunday 26 July 2020

የልቤ ሙሾ! (ስለ ወገኖቼ፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ክፋት ማገንገን)

Please read in PDF
 
   በባሌ አጋርፋ(አምቤንቱ)፣ በሻሸመኔ፣ እንዲሁም “በትውልድ መንደሬ” በአርሲ ነጌሌ የተፈጸመውን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ዘግናኝ ተግባር ሰምቼ፣ አይቼ በሰውነቴ ተሸማቅቄአለሁ፤ ለረጅም ሰዓት አልቅሼአለሁ፤ በባሌ አጋርፋ(አምቤንቱ) በአካል ተገኝቼ የኾነውን ኹሉ አይቻለሁ፤ አቤቱ! ይህን ለምን አሳየኸኝ? የአዛውንቶችን ሰቆቃ ለምን አመለከትኸኝ? የማልችለውን ለምን አሸከምከኝ? ሆደ ባሻውን ለምን ድንጋጤንና ፍርሃትን የሚያጭር ነገር እጎበኘው ዘንድ ወደድክ? አንተ ለደካሞች አልተከላከልክላቸውም፤ እኔ ምን እንዳደርግ አመለከትኸኝ ይኾን?

Saturday 25 July 2020

ቀናነት እንዳንተው!

Please read in PDF


ደም እንዳሰከረን ደም እንደ ተጣባን
እንደ ንዳድ ወርሶ ቂም እንዳጐበጠን

Sunday 28 June 2020

የእምነት እንቅስቃሴ አገልጋዮች የክርስቶስን ዘላለማዊ ልጅነት አያምኑም!


(“የእምነት እንቅስቃሴ - የዛሬቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና”፣ ከሚለው መጽሐፍ ገጽ 61-63 የተወሰደ)
3.1.   ከአምላክነቱ ያልተነጠለ ልጅነቱን መካድ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ የተናገረውንና የተነገረለትን ልክ ለመለኮቱ እንደ ተነገረ ተቈጥሮ ሲካድ እንመለከታለን። ለዚህም እንደ ዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት፣ “የክርስቶስን ከዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ አለመኾኑን” ኹለት ሃሳቦችን በአንድነት በመስፋት ነው። እንዲህ በማለት፦

Thursday 25 June 2020

የእምነት እንቅስቃሴ አገልጋዮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን አይቀበሉም!


በቃለ አዋዲ የዘመኑ መልክ ላይ የእምነት እንቅስቃሴ አማኝና አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የማይቀበሉ መኾናቸውን እንዲህ አውግተን ነበር! ተከታተሉት!

Wednesday 24 June 2020

ድንገት እንዳይደፋን!

Please read in PDF

ትንሺቱ አዚም እጀ ሰብዕ ጥንቆላ
እንዴት ቀዬአችንን፤ እርሻችንን ትብላ?

Saturday 20 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፰ - የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
8.   ምስክርነት፦ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ምስክርነት ከድፍረት ጋር በቀጥታ ተጠቅሶ እንመለከተዋለን፤ ሐዋርያት ሲጸልዩ እንዲህ ብለው ጸለዩ፣ “… ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው” በማለት፣ “ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።” (ሐዋ. 4፥29፡ 31)፤ አስቀድሞም ወንጌልን ይመሰክሩ የነበሩት በድፍረት፤ ያለ አንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ ነበር፤ (2፥29፤ 4፥13)።

Wednesday 17 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፯)

Please read in PDF
  6.      እግዚአብሔርን መምሰል፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፣ የእነርሱ መልክ ከበግ ጋር የተቀራረበ የተኩላ መልክ ነው፤ በበጎች መካከል ኾነው ይጸልያሉ፤ ይማራሉ፤ ያስተምራሉ፤ የበግ ጠባይ የያዙ መስለው ይመላለሳሉ። ዓላማቸው በጉን ለራሳቸው መንጠቅና በእረኛው እንዳያርፍ ማባዘንና ማቅበዝበዝ ነው።

Saturday 13 June 2020

ባላንጣዎቹ ደቀ መዛሙርት

Please read in PDF

ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የጠራቸው እጅግ ከተለያየ ቦታና ከተለያየ የሥራ ገበታቸው ነው። የአንዳንዶቹ ተግባራት ፈጽሞ የሚያቀራርባቸው ብቻ ያይደለ ደም የሚያቃባቸውም ጭምር እንደ ነበር ታሪካዊ ዳራዎችን ስናጠና ማስተዋል እንችላለን። ለዚህም በምሳሌነት ከአሥራ ኹለቱ መካከል ኹለቱን ደቀ መዛሙርት በማንሳት እንችላለን።

ከኢየሱስ ጥሪ በፊት

  ቅዱስ ማቴዎስና ቀናተኛው ስምኦን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠራቸው ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት መካከል ናቸው፤ ማቴዎስ የተጠራው ከቀራጭነት ቦታ ሲኾን (ማቴ. 9፥9)፣ ቀናተኛው ስምዖን ደግሞ በቅጽል ስሙ እንደ ተጠራው ቀናተኞች ከኾኑት አይሁድ መካከል ነው። ማቴዎስ አይሁዳዊ ቢኾንም ለሮማውያን ተቀጣሪ በመኾኑና ግብርን ከአይሁድ ተቀብሎ ለሮማውያም በመሰብሰቡ በአይሁድ ዘንድ ፈጽሞ የተጠላ ነው። የትኞቹም አይሁድ ለሮማውያን የሚሠሩ አይሁድን የሚመለከቱት እንደ ከዳተኛና ከአሕዛብ ጋር እንደሚተባበሩ ነው።

Friday 12 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፮)

Please read in PDf

5.      ስቀሉን፦ ኀጢአተኛና የወደውን ዓለም ባለመናቅ፣ ኀጢአትን ፍጹም በመጥላትና በመጠየፍ፣ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን አንድያ ልጁን በመስቀል አሳልፎ ሰጠ። በአዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ የመስቀልን ትርጉሞችን ያስቀምጥልናል፤ በሌላ ንግግር የኀጢአት መገኘት፣ ፍርድና የኀጢአት ኃይል በተጠቀሰበት የአዲስ ኪዳናት ምንባባት ውስጥ ኹሉ፣ ነገረ መስቀሉ በአብዛኛው ተያይዞ እንደ ተጠቀሰ እናስተውላለን።

Sunday 7 June 2020

ጰራቅሊጦስ

Please read in PDF
በምድር ዳርቻ ፍጹም ምድረ በዳ
ደግሞ በእልፍኜ በውስጤ ውስጥ ጓዲያ
በመከራ ሰዓት በመከሩ ደስታ

Friday 5 June 2020

ድኃ አገልጋዮችና “ሃብታም” አገልጋዮች


  ልከኛ አገልጋይ፣ በሰማይና በምድር ሥልጣን የተሰጠው የጌታ ኢየሱስ ኹነኛ መልእክተኛ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱን የላከው የሰማይ አምባሳደር አድርጎ በመሾም ነው፤ (2ቆሮ. 5፥20)። ሰፊው መከር፣ ወንጌል በመስማት የሚድኑ አማንያን እንደ ኾኑ እንዲኹ፣ መከሩን ለማገልገል የሚያስፈልገው በረከትና አቅም ደግሞ እዚያው በረከት ውስጥ ያለ መኾኑን እናስተውላለን። ጌታ ኢየሱስ፦ “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ (ማቴ. 9፥፥38)።

Wednesday 3 June 2020

ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ፣ ከኮሮና በፊት አልነበረምን?

Please read in PDF
    የትኛውንም የሕፃናት ሰቆቃ መስማት ያማል፤ ያስደንግጣል፤ ልብ ይሰብራል። በተለይም የቀኖቹ ክፋትና ዓመጽ፣ የምድሪቱን እርጅናና መወየብ አጉልቶ ከማሳየቱ ባሻገር፣ ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጭካኔና መራርነት እጅጉን አስፈሪ ኾኖአል። ግን እንዴት ችለን ይኾን የወለድናቸውን ሕፃናት፣ ቅርጥፍ አድርገን ስንበላ የጣፈጠን? እንዴት ቻለ አንጀታችን? የሰቈቃውን ስቃይ እየሰማን እንዴት አስቻለን? አውሬʼኮ የገዛ አውሬውን ስቃይ ይሰማል፤ ይራራልም፤ እንዴት እንዲህ ደበስን?!

Friday 29 May 2020

ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን “መከፋፈል” ጊዜው ነውን?

Please read in PDF

  ከወደ ጐጃም የተሰማው ዜና መልካም አይመስልም፤ ቅብዐቶች ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አንድነት በመለየት የራሳቸውን አገረ ስብከት በመመስረት፣ ጳጳሳት መሾማቸው እየተሰማ ነው። ነገር ግን ይህ ምሳሌነቱ መልካም አይመስልም። በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ፕሮቴስታትንት ወይም ሐድሶአውያን ተብለው የማይወገዙ፣ ቢያንስ አራት ትምህርቶች አሉ፤ ቅብዐት፣ ጸጋ፣ ዘጠኝ መለኮትና ካራ፤ እኒህ ኹለቱ የትምህርት ይትበሃሎች ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ [ከተወሰኑ ግጭቶች በቀር] በአብሮነት አሉ።

Wednesday 27 May 2020

ዕርገቱ - የቤዝወታችን ፍጻሜና ተስፋችን!

Please read in PDF
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ማረጉ ባለፈው ሳምንት በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ይታሰባል፤ ዕርገቱን አንዱ ወንጌላዊ፣ በመንፈስ ቅዱስ መነዳት ኹለት ጊዜ ዘግቦልናል፤ ሉቃስ ወንጌላዊው፤ (ሉቃ. 2450-52 ሐዋ. 16: 11) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱም ስለ ዕርገቱ አስቀድሞ ተናግሮአል፤ (ዮሐ. 142: 13 2017) ነቢያትም ትንቢት ተናግረውለታል፤ (ዳን. 79-13)

Sunday 24 May 2020

“እመቤቴ ቤዛ ብትኾን ምንድር ነው?” (የማያልቀው የዶ/ር ዘበነ ለማ ተረት)

Please read in PDF

   ዶ/ር ዘበነ ለማ፣ በአገረ አሜሪካ የሬዲዮ ፕሮግራም አለው፤ ከጠያቂዎች ለሚመጣለት ጥያቄ ኹሉ መልስ የሚመልስበት። ትኩረቴን ከሳበውና ለዛሬ እንዳካፍላችሁ የፈለግኹት፣ በአንዲት እህት አማካይነት፣ በቤዛነት ዙሪያ የተጠየቀውንና የመለሰውን መልስ በማንሣት ይኾናል፤ የተዘጋጀው “የመናፍቃን ምላሽና የዶ/ር ቀሲስ መምህር ዘበነ ለማ መልስ ክፍል 6” በሚል ርእስ ነው። ለቀረበለት ጥያቄ ዘበነ የመለሰው፣ ጭምቀ ዐሳብ በአጭሩ እንዲህ የሚል ነው፦



Friday 22 May 2020

ከ"ምኞት" ወይም ከ"ጉምዠታ" ወንጌል ተጠንቀቁ!


የብልጽግና ወንጌል መምህራን ብዙዎችን ካታለሉበት መንገድ አንዱ፣ ሥጋዊ አምሮትንና መሻትን ባልሞተው አዳም ውስጥ በማስገባት እና በመቀርቀር ነው። ይህ መንገድ ደግሞ ከዚህ ቀደም ሰይጣን ራሱ ያደረገውና ብክለትን ወደ ሰው ያስገባበት ጥበቡ ነው። በኢየሱስ ላይ ዓይኖቹ ትክ ያላሉ ኹሉ፣ በዚህ ጥበብ መታለሉ አይቀርም።