ሃይማኖታዊ “ብሔርተኝነት” ምንድር ነው?
“
... የሃይማኖት ብሔርተኝነት መነሻው አገራችን በሰማይ፤ ኑሮዐችን በዓለመ ነፍስ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት
ሲባልም ሃይማኖትን በሃይማኖት እናት፣ አባትና ብሔር አድርጐ መውሰድ ወይም በአጭሩ የሃይማኖት ወገንተኛ ማለት ነው፡፡ ከዚህም
የተነሣ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ወንዝ- ጐጥና ዘውግ ዘለል መሆኑን ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በቤተ ክርስቲያናችን
የነበረና የቆየ ማእከለ አንድነት እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ [1]
... የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እያጸጸ መምጣቱንና ውስጡ ጥቅመኝነት ሆኖ ሽፋኑ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ የሆነ
ብሔርተኝነት መሠረት እየያዘ መሆኑን ነው፡፡ እናም መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለና በጐ ከማድረግ አኳያ የጊዜውን አበው፣
ሊቃውንትና ምእመን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ዋጅቶ ከወንዛዊ- ጐጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት ደዌ መፈወስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ
ነው፡፡
... ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ከባድ ግን ልትወጣው የምትችለው ፈተና አለባት፡፡ በቃላት የሚፈታና የሚነገር ሳይሆን
በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚፈተነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣዩ ጉዞ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እጅ ለእጅ መያያዝንና ጠንካራ አንድነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለምን አልተጣሉም? ለምን አልተከፋፈሉም?
የሚሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አርፈው የሚቀመጡበትም ሁኔታ እንደሌለ መገንዝብ ይቻላል፡፡ ... ብፁዓን አበውም፣ ሊቃውንተ ቤተ
ክርስቲያንም ምእመናንም ይህን አውቀው በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ጠንክሮ መጓዝ ይጠበቅባቸዋለን እንላለን፡፡” [2]
|
ይህ አጭር
ግን ውስብስብ ትርጉም፥ በውስጡ ብዙ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን ይዟል፡፡ ሃሳቦቹን በጥያቄ እያወዛን ብናነሳ፥ ለመሆኑ ሃይማኖታዊ ወገንተኝነት
ከቤተ ክርስቲያን ቅድስናና ኩላዊነት አንጻር እንዴት ሊታይ ይችላል? ደግሞስ ሃይማኖታዊ “ብሔርተኝነት” እንዴት ሆኖ ነው፥ የቤተ
ክርስቲያን ማዕከለ አንድነት ሊሆን የሚችለው? በእውኑ ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው ከፈጠረው የሚበልጥ አንድነትን ማስገኘት የሚቻለው
ነውን? ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ውጪ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትን የሚያመጣ ሌላ አቅምና ብቃት አለ ማለትስ፥ በክርስቶስ ሞትና
ትንሣኤ ላይ መዘበት አይሆንምን? እውንስ ቤተ ክርስቲያን የተሻለና በጐ ለማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ በሃይማኖት ብሔራዊነት
መዋጀት ነውን? እንዲህ ባለ ነገር እጅ ለእጅ መያያዝ ያስፈልጋልን? የክርስቶስ ውጅትና በደሙ የመሠረተው ሕብረትና የመንፈስ አንድነት
ከዚህ ጋር ይዛመዳልን? ቤተ ክርስቲያን የዓለሙ ሁሉ የሆነች አንዲት
ሕብረት ናት የሚለውስ ከዚህ ጋር የሚዛመድ ነውን?
እንግዲህ እኒህን ጥያቄዎች ለመመለስ በዋናነት “ብሔር” የሚለውን ቃል
ፍቺና “ብሔርተኝነት” በክርስትናው ዓውድ ውስት ሊጠቀስ ይገባዋል ወይስ አይገባውም የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንፈትሻለን፡፡
ብሔር ምንድር ነው?
·
“ብሔር፦ ቦታ፥ ሰፈር፤ ስፍራ፤ በሀገር ውስጥ ያለ ታናናሽ ክፍል፡፡
... (ኢሳ.፵፱፥፳፡፡ ኢዮ.፳፰፥፩ ፤ ፲፪፡፡ ማቴ.፲፬፥፲፭ ፡፡ ፳፯፥፴፫፡፡ ሉቃ.፬፥፴፫፡፡
·
ምድር፤ ሀገር፤ ከተማ፤ ገጠር፤ አውራጃ፤ ግዛት፤ ታላላቅ ክፍል በስምና
በሹም በወሰን በድንበር የተለየ፡፡ መላይቱ ምድር የብስ ዓለመ ሰብእ፡፡
·
ሰው ወገን ነገድ፤ ሕዝብ አሕዛብ በቋንቋ በመንግሥት በሕግ በሥርዓት
የተለየ፡፡
|
የማርክሲስት ሌኒሲስት መዝገበ ቃላትም፦
“ብሔር (Nation)፦ በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ማኅበረሰብ ነው፡፡ አንድ ብሔር በመጀመርያ ደረጃ የሚለየው
ባሉት የወል ቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎች ነው፡፡ በአንድ መልክአ ምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር፥ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፥ በአንድ ቋንቋ መጠቀም፥
በጋራ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የወል ሥነ ልቦናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካከቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች ናቸው፡፡ ... ” [4]
|
በማለት ይፈታዋል፡፡
በዚህ ትርጉም “ብሔር” የሚለው ቃል ቦታንና ሥፍራን እንጂ ወገንን ወይም
አንድን ሕብረት ወይም ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞ ሊወክል አይችልም፡፡ ይህን የእውነታ ስህተት በግልጥ ቃል ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ከትክክለኛው
ትርጓሜ ጋር በመስማማት ቃል እንዲህ ብለውታል፡፡
“የኢትዮጲያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አራማጆች “ብሔር” የሚለውን ቃል አላግባብ ተጠቅመውበታል፡፡
ኋላቀርነትን ያንጸባርቃል በሚል ከጐሳ ጋር አምታትተውታል፡፡ ስህተት ነበር፡፡ ብሔር ጐሳን አይተካም፡፡ ቦታን ነው የሚያመለክተው፡፡
ብዙውን ጊዜ ትልቅ ወይም ትንሽ አከባቢን ይጠቁማል፡፡ ለምሳሌ፦ ቡልጋ፣ ሸንኮራ፣ ... የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡” በመቀጠልም
ስለብሔረሰቦች የሩሲያው ጆሴፍ ስታሊንን ፍቺ፥ “ ... አንድ ጂኦግራፊያዊ አከባቢ እና አንድ ዓይነት ባህል ያላቸው ሕዝቦች”
[5]
|
በማለት ያስቀምጠዋል፡፡
ብሔርተኝነትስ(Nationalism) ምንድር ነው?
“ሕዝቦችን በብሔር የሚከፋፍል የአንዱ ብሔር ሕዝብ የሌሎች ብሔሮችን ሕዝቦች በጥላቻ፥ በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲመለከት
የሚገፋፋ የቡርዧው ርዕዮተዓለም አድኃሪ አዝማሚያ ነው፡፡ ብሔርተኝነት ከካፒታሊዝም የሚመነጭና በብሔሮች መካከል ያለውን የተዛባ
ግንኙነት የሚያንጸባርቅ ሲሆን በሁለት መሠረታዊ መልኮች ይከሰታል፡፡ የመጀመርያው በአንድ ወቅት በፖለቲካና በኢኮኖሚ የበላይነትን
የያዘው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ገዥ መደብ በሚያሳየው ትምክህተኝነት ሲያንጸባርቅ፥ ሁለተኛው ደግሞ ከዚሁ በመነጨ ሁኔታ በጭቁን
ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች በዝባዥ መደቦች አከባቢ በሚታይ የጠባብ ብሔርተኝነት አዝማሚያ ይገለጻል፡፡ ... ” [6]
|
በዚሁ ጽሁፍ ስለብሔርተኝነት፥ “ብሔርተኝነት
ለብሔር የሚኖረን አመለካከት ወደሌላ ጽንፋዊ ጫፍ ረገጥ አመለካከት ሲያድግ፥ ብሔርተኝነት (tribalism) እንደሚባል ብዙዎች
ሲያነሱ፥ “ሕዝቦችን በብሔር የሚከፋፍል፣ የአንዱ ብሔር ሕዝብ የሌሎች ብሔሮችን ሕዝቦች በጥላቻ፣ በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲመለከት
የሚገፋፋ” መሆኑንና፥ ይህንኑ ሃሳብ “ሕዝቦችን በብሔር (ወይም በነገድ፣ በጐሣ፣ በወገን) በመከፋፈል የአንዱ ብሔር ሕዝብ ከሁሉ
በላይ እንደሆነ በመቍጠር ሌሎችን ለመግዛት መብት አለው የሚል ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በአጭሩ “የእኔ ብሔር ከአንተ ብሔር ይሻላል”[7]
የሚል ጽንፋዊነትን በውስጡ የያዘ ሃሳብ ነው፡፡
ብሔርተኝነት በራሱ የመደብ አድልዎና የራስን ማኅበረሰብ ማዕከል ማድረግ
አለብን የሚል መንፈስ በውስጡ የያዘ ነው፡፡ የሚከፋው ነገር ደግሞ ከክርስትና ፈጽሞ ያልተቀዳ መሆኑ ነው፤ ክርስቶስ ስለሁላችን
አንድ መሆን ራሱን አሳልፎ የሰጠ ነውና፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለሁላችን
ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...
[1]
ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት
አንጻር ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት መነሻውም መድረሻውም ዋና መሠረት ክርስቶስና ቅዱስ ቃሉ ብቻ ነው፡፡ ቤተ
ክርስቲያን በምድር ላ የተተከለችበት የራሷ ፍጹምና ቅዱስ ዓላማ አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ስለሆነች፣ ራሱም በወርቀ ደሙ
ስለዋጃት(ሐዋ.20፥28)፣ በትንሣኤው ኃይል ስለመሠረታት (ኤፌ.1፥19-20) “ቤተ ክርስቲያኔ” (ማቴ.16፥18) ብሎ ጠርቷታል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትም ዓለት ራሷ ክርስቶስ እንጂ ሌላ ምንም የለም፤ (1ጴጥ.2፥4-8)፡፡ ስለዚህም ሕልውናዋና ተግባርዋ፣
ዘላለማዊው ፍጹም አንድነቷ ጸንቶ የቆመው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ብቻ መሆኑ ከማናቸውም ሕብረቶች ልዩና ወደር የለሽ ያደርጋታል፡፡
በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ፍጹም ልደቷን
ያከበረችው በበዓለ ሃምሳ ፍጹም ልደቷን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ በማጽናት ነው፡፡ ብሔርተኝነት በከፊል ጎራ ለዪነትን የሚያንጸባርቅ
እንጂ ክርስቶስ በመስቀል የሞተለትን የመንፈስ አንድነትን በውስጡ በፍጹም የያዘ አይደለም፡፡ ስለዚህም በምንም አይነት መንገድ ለቤተ
ክርስቲያን የመንፈስ አንድነት ለመጠበቅ፥ ክርስቲያናዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር
ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ የፈለገ”(ኤፌ.5፥27) ራሱ ክርስቶስ ነው ካልን፥ ለቤተ ክርስቲያን
መውደቅ መንገድ አመልካችና ትመላለስበትም ዘንድ የተሰጣት ተመርቆ የተከፈላት አዲስና ሕያው መንገድ (ዕብ.10፥19) እርሱ ራሱ
ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከክርስቶስ ቃልና ከደሙ ቤዛነት በታች የሆኑትን ነገሮችን[መፍትሔዎችን] መፍትሔ ብሎ ማቅረብ በራሱ፥ ከባድና
አደገኛ አለማዊነትን[ምድራዊ መፍትሔን] ወደቤተ ክርስቲያን ለማስገባት መሞከር ነው፡፡ ቃሉ ደግሞ በግልጥ፥ “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር
ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” በማለት ይናገራል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ኢየሱስ ገንዘብና ንብረት ናት ካልን፥ ከክርስቶሰ ቃልና ምክር ውጪ ምንም ሊያስፈልጋት አይገባም፡፡
ተባረክ ወንድሜ
ReplyDelete