Saturday, 8 October 2016

ኢትዮጲያ ሆይ! ላሁኑ ብቻ ያይደለ፥ ላለፈውም ጥፋትሽ ማቅ ለብሰሽ ንስሐ ግቢ!!!


   Please read in PDF

  አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው።” (ነህ.1፥5-11)


      ልብ የሚሰብር ጸሎት የጸለየው የእግዚአብሔር ሰው ቅዱስ ነህምያ ነው፡፡ ነህምያ የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ያጽናናል” ማለት ነው፡፡ በእውነትም ሕይወቱና ንግግሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሊያጽናናበት የተጠቀመበት ምርጥ ሰው ነው፤ ነህምያ፡፡  ይህ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እጅግ የተወደደ፥ ለእኛም ብዙ ምሳሌና ልንማርበት የሚያስችል የቅድስና ሕይወት የነበረው ነው፡፡

1.     ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ለሚሠራው ሥራ እቅድና እንዴት መሥራት እንዳለበት የሚያውቅ የሕዝቡ መሪ ነበር፡፡ ንጉሡ ዘንድና በእግዚአብሔር ፊት በቀረበ ጊዜ ምን እንደሚናገር በትክክል የሚያውቅ ነው፡፡ ችሎታውንም በመናገር የማያባክንና የማይመካም ሰው ነበር፤ (2፥12)፡፡ በዝምታው ውስጥ የእግዚአብሔርን ንግግር የሚሰማና ለሕዝቡ ያለውንም ቅዱስ ምሪት የሚጠይቅና የሚያውቅ ነው፤ ነህምያ፡፡

2.    ደፋር ነበር፤ በሕዝቡና በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር በጠላቶቹ መካከል በመመላለስ በትክክል ተመልክቷል፡፡ “በኢየሩሳሌም ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ ውስጥ መሆናቸው፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር መፍረሱና፥ በሮችዋም በእሳት መቃጠላቸው”፤ የጠላቶቻቸው ከፍ ያለው ጽኑዕ ተቃውሞና ማስፈራራት ምንም ሳይመስለው ሥራውን መሥራት የጀመረና መንፈሳዊ ድፍረት የነበረ ሰው፤ ነህምያ፡፡

   የጠላቶቻቸው ባሕርይ “በንቀት የሚሳለቁ፥ ቀላል አድርገውም የሚያንቋንሽሹ”(2፥19)፤ “አላጋጮች”(4፥1)፤ “የምድሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ የሚያደክሙ፥ እንዳይሠሩም የሚያስፋራሩ ነበሩ፥”(ዕዝ.4፥4)፡፡ ነገር ግን ነህምያ የበረታ የጠላት ተቃውሞና ማስፈራራት ቢኖርም ከእግዚአብሔር ሥራ ከቶ ችላ ማለትን አልወደደም፡፡ የእግዚአብሔርን ረዳትነትና አከናዋኝነት በማመን የጠላቶቹን ንቀትና ማንቋሸሽ ከምንም አልቆጠረውም፡፡ ተገዳዳሪ እያለ ሥራ ለመሥራት መነሣት ታላቂቱ የእግዚአብሔር ክንድ ካላበረታችን በቀር አይቻለንም፡፡

   ይህም ብቻ ሳይሆን ለንጹሐንና ለችግረኞች ሥቃይ ቸል ሳይል በተገለጠ ክፋት ላይ የሚቆጣና ኢፍትሐዊነትን የሚቃወም ደፋር ነበር፤ (5፥6)፡፡ ዛሬ በአገራችንም አንዱና መሠረታዊው ነገር፥ ለሆነውና እየሆነ ላለው ግፍ በተግሳጽና በእግዚአብሔራዊ ቁጣ የሚቈጣ ሽማግሌና አዋቂ መታጣቱ ነው፡፡ ሁሉም ከፍርሃቱ የተነሳ እንደጌዴዎን በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴን በመውቃት የተጠመደ ይመስላል፡፡

3.    እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈራም ነው፡፡ ድፍረት እግዚአብሔርን ከመፍራት ካልተባበረ አመጽና ትዕቢት ብቻ ሆኖ ምድሪቱን ሊያስጨንቃት ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ስለነበር ሥልጣኑን በመጠቀም የራሱን መብት በማስከበርና ጥቅም በመሰብሰብ አልተጠመደም፡፡ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተጠቀምን በእግዚአብሔር መጠየቅና መወቀስ እንዳለ መርሳት የለብንም፡፡ የእኛ መሪዎች ይህን እውነት ምን ያህል አስተውለን ይሆን እየሠራን ያለነው? እግዚአብሔርን ትፈሩ፥ ሰውን ታከብሩ ዘንድ የሚገባችሁ አይመስላችሁምን?  

4.    ጽኑና የጸሎት ሰው ነበር፤ ጸሎት የእውነተኛ አማኝ ዋና መገለጫ ነው፡፡ የችግሮቻችን መፍትሔ ሁሉ ያሉት በንጹህ ልብ በምንወደው አምላካችን ፊት በቅንነት ከመጸለይና ካለመጸለይ ብቻ የሚያያዝ ነው፡፡ እውነተኛ የንስሐ ጸሎት ጌታን ከዙፋኑ ያስነሳዋል፤ እንዲወርድ ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔር ከወረደ ደግሞ ሥራ ሳይሠራ ፈጽሞ አይመለስም፡፡ አስተውሉ! በሰናዖር ወረደ፥ (ዘፍ.11፥5) የክፋቲቱን ከተማ ሰዎች ቋንቋቸውን በዚያ ደባለቀው፤ በግብጽ የወረደውን ጌታ ተመልከቱ፥ (ዘጸ.3፥8) “ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር … አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ፡፡” ብሎ በቃሉ ተናገረ፡፡ አዎ! በእውነተኛ የንስሐ ጸሎት ጌታን ከጠራነው፥ ጌታ ወርዶ ታላቅ ሥራን ይሠራል፡፡

    ነህምያ የችግሮቹ ሁሉ ቁልፎች መክፈቻ በጸሎት ውስጥ የተሸሸጉ መሆናቸውን ስላመነ ወደአምላኩ ፊት በመቅረብ በብርቱ ጸሎት ቆመ፡፡ ነህምያ፦

3.1. በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ የደረሰውን ውርደትና ንቀት አይቶ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው፤ ምሪትም እንዲሰጣቸው፤ በሕዝቡ ላይ የደረሰው ጒስቁልናና ሰቆቃ እንዲያበቃ ለአራት ወራት ያህል ከእንባ ጋር ይጾምና ይጸልይ ነበር፡፡ በአጭር ጸሎቱ ወዲያው የተሰማውና ሕዝቡ እሺ በእጄ ብሎ የታዘዘለት በእግዚአብሔር ፊት ደጋግሞ ስሙን በመጥራቱ፥ የታሸና የላመ መንፈሳዊ ሕይወቱን ቀድሞ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ነው፡፡ 

3.2.         በጸሎቱም ከላይ እንዳነበብነው ኃጢአትን በመናዘዝ የተመላ ነው፡፡ እርሱም የአባቱም ቤት የሠሩትን ኃጢአት በግልጥ ይናዘዛል፡፡ ለእስራኤል ሁሉ የበረታ ምልጃን ያቀርባል፡፡ ለመሪዎቻችሁና ለሕዝባችሁ የምልጃ ጸሎትን የምታቀርቡ አማኞች ስንቶች ናችሁ? ለመሪዬ መበላሸትና መርከስ የእኔም እጅ፤ ኃጢአት አለበት የምትሉ አገልጋዮችና አማኞች ስንቶች ናችሁ?

3.3.         ለእግዚአብሔር ደግሞ የተናገረውን ቃል፥ “ … ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ።” በማለት ለራሱ ለእግዚአብሔር ያሳስባል፡፡ መሐሪው እንዲምር በገባው በራሱ ኪዳን መለማመን እንዴት ያለትልቅ ማስተዋል ነው!!!

3.4.        ደግሞ እግዚአብሔር በሕዝቡና በምድሪቱ ላይ ያለውን ውድና ቅዱስ ዓላማ በመቆርቆር ያነሳል፡፡ ሕዝቡ ትልቅና ለእርሱ የተለየ መሆን ቢገባውም አሁን ያለበትን ውድቀትና ማደፍ ሳያይ በመማርና ይቅር በማለት ወደቅዱስ ርስቱ ማስገባቱን እንዳይዘነጋ አጽንቶ ይናገራል፡፡ ዛሬ እንዲህ ያሉ መምህራን ኖረውን ይሆን? ፊት ሳያደሉ ለእግዚአብሔር ዓላማና ሃሳብ ብቻ ጸንተው የቆሙና የሚቆረቆሩ?

5.    ለሕዝቡ መንፈሳዊ ተሃድሶ እጅግ ተግቶ ከዕዝራና ባልንጀሮቹ ጋር ይሠራ የነበረ ሰው ነበር፡፡ “ካህኑም ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን በማኅበሩ በወንዶችና በሴቶች አስተውለውም በሚሰሙት ሁሉ ፊት አመጣው።”(8፥2) የሚለው ቃል፥ ነህምያ ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር የእግዚአብሔርን ሥራ የሚሠራ ሠራተኛ እንደነበር እናስተውላለን፡፡

   ቅዱስ ነህምያ ያገኘን ሁሉ ያገኘን “እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም” በማለት ምንጩ ኃጢአት እንደሆነ በጽኑ እምነት ያምናል፡፡ በደለኛ መሆናችንን ካላመንን የሰው እንጂ የራሳችን ነውርና እድፈት አይታየንም፡፡ ከአገር ልማትና ከኢኮኖሚ ግንባታ በፊት በፊት የሰው ሕይወት ልማትና የመንፈስ ግንባታ ያለቅድመ ሁኔታ መከናወን አለበት፡፡ ይህ ሊሆን የሚቻለው ደግሞ በንስሐና በታደሰ መንፈሳዊ ሕይወት በጌታ ፊት መቅረብ ሲቻለን ነው፡፡  

    አገሬ ኢትዮጲያ እግዚአብሔርን ዘወር ብላ ልታየው ይገባታል፡፡ እሾህን በእሾህ፤ ደምን በደም ለማጥራት እየሄድንበት ያለው መንገድ የመመለሻና የመፈወሻ ቀናችንን እጅግ ያረዝመዋል፡፡

   የቤተ ክህነቱና የቤተ መንግሥቱ መሪዎች እስኪ አስተውሉ! የሚጮኸውን ሕዝብ በትክክል ለማድመጥ ልባችሁንና ጆሯችሁን ክፈቱ፡፡ እንደነህምያ በሕዝቡ ላይ የሆነውን ነገር በትክክል ውረዱና ተመልከቱ፡፡ የተናቀውን ሕዝብ፣ የአንድነት ቅጥሩ በዘረኝነት መፍረሱን፣ ፍትህ በማጣት የተቃጠለ መንፈሱን፣ መልካም አስተዳደር አጥቶ መባዘኑን፣ በጉቦና በመማለጃ መሳቀዩን፣ የግፍ ደም አዙሪት ያሰከረውን ሕዝባችሁን ወርዳችሁ እስኪ አስተውሉት!!! እውነት “ከዚህ በላይ ቢቆጣ የሚገባው” አይደለምን? የእናንተ ምላሽስ ይህ ነውን? ዳቦ ለለመነ ድንጋይ፣ አሳ ለለመነ ዘንዶ፣ ምህረት ለለመነ ጥይትና መራዥ ጭስ እንደበረከት መሸለም?

   ምድሪቱ ደምን ጠግባለች፤ እስኪ አስተውሉ! በአንድ መቶ ዓመት ዕድሜ እንኳ፥ በራስ ተፈሪና በንጉሥ ሚካኤል መካከል(1909 ዓ.ም)፣ በራስ ተፈሪና በራስ ጉግሳ መካከል(1922 ዓ.ም)፣ በኢትዮጲያና በኢጣሊያ መካከል ከ1928ዓ.ም ጀምሮ ከአምስት ዓመታት በላይ፣ በኢትዮጲያና በሶማሊያ መካከል (1969 ዓ.ም)፣ በደርግና በኢህአዴግ መካከል ከ15 ዓመታት በላይ፣ በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል የተደረገውን አሰቃቂ ጦርነቶችን ተደርገዋል፡፡

     የእነዚህ ትውልዶች ሁሉ ደምና ግፍ ዛሬም በእጃችን ነው፡፡ ስለነዚህ ስላፈሰስናቸው ደም ልባችን ደነደነ እንጂ ንስሐ ለመግባት ዛሬ እንኳ አልወደድንም፡፡ ብዙ በንስሐ ያልተዘጉ የደምና የግፍ ታሪክ የበዛብን ነን፡፡ ኢትዮጲያ የብዙ ቅዱሳንና ንጹሐን ደም የሚጮኽባት ምድር ናት፡፡ እኒህ ሁሉ ጦርነቶች በንስሐ የተደመደሙና የተዘጉ አይደሉም፡፡ አባቶቻችን ቂምን፣ ጥላቻን፣ መናናቅን፣ አለመቀባበልን፣ ዘረኝነትን፣ ጦርነትን፣ ደምን … እንጂ ይቅርታና ምሕረትን፣ እሺ በእጄ መባባልን አላወረሱንም፡፡

  ኢትዮጲያ ሆይ! ላሁኑ ብቻ ያይደለ፥ ላለፈውም ጥፋትሽ ማቅ ለብሰሽ ንስሐ ግቢ!!! ዛሬ እየሆነ ላለው ሁሉ ጌታ ምህረትና ይቅርታን እንዲያወርድና እንዲታረቅሽ የቀደመውንና የአሁኑን በደልሽን በንስሐ እንባ እጠቢው፡፡ አባቶችሽም ልጆችሽም በአመጻ መንገድ እንጂ በእውነትና በፍቅር መንገድ ላይ አልቆሙም፤ ከዓመታት በፊት ደምን ያፈሱ እንደነበሩ እንዲሁ፥ ዛሬም ዛሬም ደምን ከማፍሰሱ አልተከለከሉም፡፡ የሞተላቸውን ክርስቶስን ገፍተውና ንቀው የገዛ ወንድማቸውን በመግደል ተጠምደዋል፡፡

     ለኢትዮጲያ አንድና ግልጽ መፍትሔዋ በእጅዋ ነው ያለው፤ እርሱም የሞተላትንና በደሙም ሊቀድሳት እጁን የዘረጋላትን የአብ አንድያ ልጅ ክርስቶስን መቀበልና ፊቷን ወደእርሱ መመለስ ብቻ ነው፡፡ ይህን መናቅም መቀበልም፤ መተውም መውደድም ምርጫዋ ነው፡፡ ምክንያቱም በእርሱ የሆነ የንስሐ ልብ ከሌለን አንቀባበልም፤ ምልስ ልብ ከሌለን አንዳችን ለሌላችን አንራራም፡፡ አቤቱ በብርቱ ጩኸት ወዳንተ እንጮኻለንና በበዛ ምህረትህ ተመልከተን፡፡ ለገዛ ምኞታችንም አሳልፈህ አትስጠን፡፡ ማስተዋልህንም አብዛልን፡፡ አሜን፡፡

 

3 comments:

  1. Amen!!
    geta hoy ante mdretwan kaltebek Tebaki bekentu yedekmal

    ReplyDelete
  2. "ለኢትዮጲያ አንድና ግልጽ መፍትሔዋ በእጅዋ ነው ያለው፤ እርሱም የሞተላትንና በደሙም ሊቀድሳት እጁን የዘረጋላትን የአብ አንድያ ልጅ ክርስቶስን መቀበልና ፊቷን ወደእርሱ መመለስ ብቻ ነው፡፡" እዉነት ነዉ!!!

    ReplyDelete
  3. Very good article.Pleas God Help the Ethiopians

    ReplyDelete