Sunday 12 June 2022

መንፈስ ቅዱስና አማኙ

 Please read in PDF

  ከግሪኩ “ፓራክሊቶስ” ወይም ከዕብራይስጡ “ፕራቅሊጥ” ከሚለው ግስ የተገኘው፣ “ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ትርጉሙ፦ “አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ካፉ ማር ጠብ የሚል።…፤ ናዛዚ፣ መጽንዒ፣ መስተፈስሒ፤ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተርጉመውታል።[1]

   ጌታችን ወደ ሰማያት ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ “ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል … ” (ዮሐ. 14፥16) በማለት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን አጽናኝነት በመግለጥ ለደቀ መዛሙርቱ፥ ልክ እንደ እርሱ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን እንደሚያደርግላቸው የተስፋ ቃልን ሰጥቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን ደግሞ፣ ጰ[ፐ]ራቅሊጦስ የሚለውን ቃል በቀጥታ ፍቺው “ፓራ” ማለት “አጠገብ” ማለት ሲኾን፤ “ካሌው” ማለት ደግሞ “መጥራት” ብለው በመተርጎም፣ ሲተነትኑት “ሊራዳ፤ ከአማኝ ጐን የሚቆም” በማለት ተርጉመውታል። ይህም ሊያጽናና፣ ሊያበረታታ፣ ሊያረጋጋ፣ ሊራዳ፣ ሊያማክር፣ ሊሟገት፣ ወገንና ወዳጅ ሆኖ ሊቀራረብ ከአማኝ ጐን ይቆማል የሚል ሃሳብን በውስጡ ይይዛል ብለዋል።

ከዚህም የተነሣ፣ ከሦስት አካላት አንዱ መንፈስ ቅዱስ፣ በዓለም እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ጭምር ተግቶ የሚሠራ ነው፤ (1ቆሮ. 12፥1-13)። መንፈስ ቅዱስን ለማወቅም ከመንፈስ ቅዱስ በቀር ሌላ ብርሃን የለም፤ “ወልድንም[ኢየሱስን] ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም” (ሉቃ. 10፥22) እንዲል።መንፈስ ቅዱስ ራሱ ወዶ ካልገለጠልን በቀር፣ መንፈስ ቅዱስን እናውቀው ዘንድ አንችልም።

መንፈስ ቅዱስንም ኾነ ክርስቶስን በትክክል ለማወቅ ደግሞ፣ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ግድ ያስፈልገናል። ይህም ማለት፣ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ መጠመቅ ይገባናል” (ሮሜ 6፥3) ማለት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ደግሞ፣ ክርስቶስን በማመናችን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን ብልቶች እንኾን ዘንድ ከክርስቶስ አካል ጋር እኛን ሕያዋን የሚያደርግበት እጅግ አስደናቂ እውነት ነው። በዚህ መንገድ ከእርሱ ካልተወለድን በቀር፣ እርሱ ሊራዳን፣ ሊያጽናናን፣ ሊሟገትልን፣ መካር ሊኾነን፣ ሊያበረታታን ከእኛ ጐን የሚቆም አይደለም።

እውነተኛን የእግዚአብሔር ልጅነት በማግኘት፣ እግዚአብሔር ራሱን ማስደሰት የምንችለው በራሱ በእግዚአብሔር መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። ወደ መንፈስ ቅዱስ ታላቅ እውነት ለመምጣት ደግሞ በኢየሱስ ማመን እጅግ አስፈላጊና ተቀዳሚ ነገር ነው። መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ የሚሠራው ትልቁ ሥራም፣ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐ. 14፥26) በማለት መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ትልቁ ሥራ ኢየሱስን ማስተማርና ስለ ኢየሱሰም ማሳሰብ እንደ ኾነ፣ ሌላኛው አጽናኝ የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ተናግሮአል።

እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አዳኝ እንደ ኾነ የምናምን፣ በማመናችንም የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት በመጠመቅ ልጆች የኾንን ኹላችን፣ ሁልጊዜ ከሥጋና ከደም ጋር ያይደለ (ኤፌ. 6፥12) ከመንፈሳዊያን የክፋት ሠራዊት ጋር፣ ከኃጢአትና ከክፉው ዓለም ጋር ከፍ ያለ ውጊያ እንዳለብን ልንዘነጋ አይገባም፤ ውጊያው ደግሞ ለሥጋ ጠባይ እጅግ ደስ የሚያሰኝ አይደለምና ብርቱ ክርክር፣ ፍትጊያ፣ ስቅየት(ስቃይ)፣ መከራና ትግል አለበት፤ ይህን ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቆ ልጅ የኾነ ብቻ እንጂ ማንም በሥጋው ይቋቋመው ዘንድ አይችልም። የምንዋጋቸውን በሥጋ አቅም ልንዋጋ የማንሞክራቸው ከኾነ፣ የውጊያው ስልቱና መሣሪያውም መንፈሳዊ ከኾነ፣ እስከ መጨረሻ በውጊያው ለመጽናትና ድል ለመንሣት ብርቱ አጽናኝ፤ አጠገባችን ቆሞ የሚያበረታታ፣ “አይዞህ ካንተ ጋር ነኝ” ባይ ብርቱ ወዳጅ ያሻናል።

ቅዱስ ጳውሎስን፣ “በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ” (ሐ.ሥ. 23፥11) ብሎ ያበረታው ያ ብርቱ መንፈስ፣ ያ አጽናኝ መንፈስ፣ ያ የሚያበረታታ መንፈስ … ዛሬም ለኹላችን ያስፈልገናል። እርሱ ስለ ኢየሱስ እንድንመሰክር በብርቱ ይሻል፤ ይወዳልም፤ ይናፍቃልም፤ በውስጣችንም ስለ ክርስቶስ ባለመመስከር ስንዝል፣ስንደክም ይቃትታል፤ እንነቃም ዘንድ ይተጋል፤ አሜን እንዲህ ይብዛልን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

 

 



[1] [1]ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ።(1948 .) አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። ገጽ 907)

No comments:

Post a Comment