Sunday, 4 September 2016

የኢትዮጲያ “መካከለኞች” ወዴት ናቸው?

Please read in PDF     

       ቺቸሮ “አለመግባባት መፍትሄ የሚያገኘው በሁለት መንገዶች በውይይት ወይም በኃይል ነው፡፡ የመጀመርያው የሰው ባሕርይ ሲሆን ሁለተኛው የአራዊት ነው” ይላል፡፡ ባለመታደል ሁላችንም ሁለተኛውን መረጥን፡፡ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍን ያለመቀበል እንደባህል አድርገን በመያዛችንና በሃገሪቱ የፖለቲካ ልምድ ካለመኖር ጋር ተዳምሮ የኢትዮጲያ ተራማጆች ኃይልን መርጠው በመንቀሳቀሳቸው የደም መፋሰሱንና የጥፋቱን መጠን በማባባስ ለሃገር ግንባታ ይውል የነበረ ወጣት ለቅስፈት ተዳርጓል፡፡ (ሌ/ኰሎኔል ፍሥሐ ደስታ፤ አብዮቱና ትዝታዬ ፤ 2008 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት)

       ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም “እርምጃ እንዲወሰድ ከማዘዛቸው” በፊትም ሆነ በኋላ፥ የሕዝብ ኩርፊያ አሁንም ጋብ ያለ አይመስልም፡፡ ሕዝብ እንደሚናጠቅ የአንበሳ ደቦል “በገዛ ወገኑ” [እርስ በራሱ] ላይ ያደባ ይመስላል፤ “መንግሥት ሆይ!  ችግር አለብህ፤ ተስተካከል” ለማለት እየሄደበት ያለው አቅጣጫና አንዳንዶች እንደሚሉት ሕዝቡን የሚመራው “ሦስተኛው አካል” ዓላማና ግቡ ምንም እንደሆነ በትክክል አለመታወቁ ነገሮች የበለጠ እንዲወሳሰቡ ያደረገ ይመስላል፡፡
     እርግጥ ነው፥ የአብዛኛው ሰው ስሜት ሲደመጥ፥ “ይኼ መንግሥት በቃው፤ ይውረድ” ይመስላል፡፡  ይህ አካሄዱ ግን ፍጹም ኢ መንፈሳዊነት ብቻ ሳይሆን ኢ ሰብዓዊነት፣ ኢ ሥነ ምግባራዊነትና ኢ ሞራዊነት የሰፈነበት መሆኑ ነገሩን አስጨናቂና እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ምንድር ነው አስጨናቂና አሳሳቢ የሚያደርገው? ብንል፦
1.     ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ምን ሆነው? በማን ላይ ነው እርምጃ እንዲወሰድ አዝዣለሁ ያሉት? ከእርምጃው በፊት ማወያየትና ማነጋገር አይቀድምም ወይ? ምክር አይፈለግም ወይ? እርምጃ የመጀመርያ ደረጃ መቀራረቢያና መግባቢያ መንገድ ነው ወይ? ሕዝብን ማድመጥና ፍላጐቱን መጠየቅ አይገባም ወይ? በደፈናው ከመፈረጅ ጥንተ ምክንያቱን ማጥናት፤ መረዳት አይገባም ወይ? ወይም ለምንድነዉ መንግስት በፖለቲካ አቅጠጫ ማሸነፍ የተሳነው? የሚሉና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን መምዘዝ ይቻላል፡፡

    ሌላው፥ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ትዕዛዝ በራስ ሕዝብ ላይ የወጣ እና የሚፈጥረውስ ችግር በትክክል ታውቋል ወይ? መቼም፥ መባል ስላለበትና ውጤትን አስቦ ማለት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ክቡር ሚኒስቴር ግን ይህን በሚገባ አጢነውታል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ የቀደሙት የደርግ ባለሥልጣናት ከተናገሩት የዘመን ስህተት ሚኒስትሩ ምነው ምንም ሳይማሩ ቀሩ?
2.    አብያተ እምነቶቻቸውንና አማኞቻቸውን የወከሉት አባቶችስ ስለተባለው መንግሥታዊ እርምጃ ምነው ወደሚኒስትሩ ገብተው አልጠየቁ? ምን የሚሉት እርምጃ ነው? እርምጃ እንዲወሰደበት “የታወጀበት” አካል የእነርሱ እረኝነት የማያስፈልገው ነውን? ባያሰፈልገውስ የሰው ሞት ሊገዳቸው አይገባምን? በእውኑ የሟቹን ሞት መሞት አብረው የሚተባበሩ እነርሱ ኃላፊነቱን ከተቀበሉት አምላካቸው ዘንድ የማይጠየቁ ናቸውን?
   በአጭር ቃል የአገር ቤት ጳጳሳትና ሲኖዶሱ ዝምታን የመረጠበት ምክንያቱ፥ አንድም ፍርሃት ወይም ለሚሆነው ሁሉ ድጋፍን በመስጠት የተባበረ ይመስላል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እውነቱን እውነት ስህተቱን ስህተት ማለት በተገባ ነበርና፡፡
3.    በውጪ አገር የሚኖረዉ የአገር ልጅ የያዘዉ የአሳብ ጠርዝ ይበልጥ ነገሮችን የሚያወሳስብ መሆኑ፤ በተለይም በመምራት ላይ ካለው መንግሥት ጋር ሙሉ ለሙሉ በጠላትነት ጐራ ራሱን ማሰለፉና በጥላቻ ላይ መቆሙ ነገሮች ወደመፍትሔ እንዳይቸኩሉ አድርጓቸዋል፡፡ የውጭው ሲኖዶስና አብዛኛዎቹ ጳጳሳትም ደግሞ የውጪውን ዲያስፖራ የጥላቻ ሃሳብና የአገር ቤቱን መንግሥት ተቃዋሚዎች ሙሉ ለሙሉ በመደገፍ የቆመ ስለሆነ ለእርቀ ሰላም ብቁዓን ናቸው ማለት አያስደፍርም፡፡
    ይህ እጅግ በጣም አስጨናቂ ነው፤ ቤተ ክህነቱ ባሩድ ባሩድ ሸትቷልና፡፡ የውጪው ዲያስፖራ የገመደው ገመድ፤ የሸረበው ሴራ ተቻችሎ የኖረውን ሕዝብ አቃቅሯል፡፡ አንዱ ብሔር ሌላውን ዓይንህን ላፈር ያለው የውጪው ዲያስፖራ የቀመረው የመርገም ቀመር ለማሳየት፥ የቅርቡን የመተማውን ድርጊት ማንሳቱ ብቻ  ይበቃል፡፡
4.    ሕዝብስ ከ20 ዓመታት በላይ የመራውን መሪና ፓርቲ ምነው መግባባት ተስኖት ድንገት ጀንበሩን አዘቅዝቆ ለጐበዝ አለቆች ራሱን አሳልፎ ሰጠ? ግልጥ ጥያቄውን የልማት ተቋማትን በማፍረስና በማቃጠል፣ አንቡላስን፣ የፍርድ ቤት መዝገብ ቤትንና ፖሊስ መምሪያዎችን በማውደምና ሰውን በመግደልና በማቁሰል የሚመጣ ምን ጤናማ መግባባትና መስማማት ሊመጣ? ወደብጥብጥና ወዳለመስማማት ከመሄድ ጥያቄን ማቅረቢያ እልፍ አዕላፍ መንገዶች አልነበሩም ወይ?
5.    ኸረ ለመሆኑ ኢትዮጲያ የምትባል አገር የአገር ሽማግሌ፥ በመንግሥትና በሕዝብ ዘንድ የታፈሩና የተፈሩ፣ በሥነ ምግባራቸውና በታማኝነታቸው፣ በአገር ወዳድነታቸውና ለወገን ባላቸው ተቆርቋሪነታቸው የተመሰከረላቸው ሽማግሌና ወጣቶች የላትም ወይ? በሕዝብና በመንግሥት መካከል ገብተው “ቆይ እስኪ ተረጋጉ፤ ተደማመጡ፤ ተቀባበሉ፤ ጠባችሁን አቆዩና ለሰላም ቅድሚያ ስጡ” የሚል አንድ ጨካኝ ሰው እንዴት ታጣለች? እንዴት የሚገደው ሰው ማፍራት ተሳናት? ይህን ድልድይ ሠሪ ልጆችን ኸረ እንዴት አጣች?
    አንድ ነገር አምናለሁ፤ በሕዝባችን ዘንድ መካከለኞች ፈጽሞ እውቅና እንደተነፈጋቸው፣ ሥፍራ ሊሰጣቸው እንዳልተቻለ አያለሁ፡፡ ወደተከሳሽ ወይም ወደከሳሽ፣ ወደገፊ አልያ ወደተገፊ፣ ከገዳይና ተገዳይ አንዱን መርጠን ጐራችንን በግልጥ ራሳችንን ካላሳወቅን ከሕዝባችንና ከመንግሥታችን የሚሰጠን ምላሽ የባሰ እንደሆነ እያስተዋልን ነው፡፡
   አዎን! መካከለኛነት ያማል፤ ሕመሙም ጽኑ ሕመም ነው፡፡ አዎን! እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ካህን መሆን፥ ነፍስን ከገለባ በሚያቀል ማንነት ውስጥ እንደድናልፍ ያደርጋል፡፡ አንድ ካህን ለክፉም ለደጉም፣ ለኃጢአተኛውም ለቅዱሱም፣ ለሟቹም ለገዳዩም ... አባት ነው፡፡ አንዱን አቅርቦ ሌላውን ወደገሃነም ወይም ወደሰይጣን መንጋ ማሳደድ አይቻለውም፡፡ ይህን ካደረገ የተሰጠውን አደራ ሸቃቅጦበታልና ከቅጣት ፈጽሞ አያመልጥም፡፡ “ ... የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ ... እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ ... እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ ” (ሕዝ.34፥16 ፤ 20-21) የሚለው ቃል አንድ ካህን(እረኛ) ለበጐች አድሎዓዊ ልዩነት ማድረግ እንደሌለበት ሰባራውንም ደህናውንም እኩል መጠበቅ እንዳለበት በግልጥ የሚያሳይ ነው፡፡
   እስኪ፥ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ ሲሆን ምን እንደተባለ አስተውሉ! “የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም” (ኢሳ.53፥3) ጌታ ኢየሱስ ለምን በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላና የተናቀ ሆነ? ለምን የሕማም ሰው ሆነ? ሰው እርሱንስ ማየት እስኪጠየፍ ድረስ ለምን ይሆን ሰውን ፊቱን የመለሰበት? አዎን መካከለኛነት ጠባዩ እንዲህ ነው፡፡ ሰውን ለማዳን ሲል፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ለማስታረቅ መካከለኛ የሆነው ውዱ ጌታ በሰው ሁሉ ፊት የተናቀና የተዋረደ ሆነ፡፡
      አስተውሉ! መካለኛነት የሁለት ወገንን ሕመም መታመም ነው፡፡ የተበዳይንም የበዳይንም ሕመም፣ የአንሺውንም የተጣለውንም ጣዕር፣ የቅዱሱንም የርኩሱንም ደዌ፣ የቆመውንም በቁመቱ ልክ የወደቀውንም ቁስል መሸከምና ማስታመም ይፈልጋል፤ መካከለኛነት ይህን ያህል ትልቅ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን የመካከለኝነት ሕይወት ሳስብ ሁለት ነገር ያስጨንቀኛል፤
1.     እንዲህ ያሉ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ቆመው የሚሸመግሉ ወገኖችን ማግኘት አለመቻላችን ምን ያህል ከመልካም ሥነ ምግባር የራቀ ማኅበረሰብን ማፍራታችንን የሚያሳይ ሲሆን፤
2.    በዚህም ምክንያት አንድን ነገር የምንለካበት ልኬት ወይም የምንመዝንበት ሚዛን አጥተን፥ በፊታችን መልካም መስሎ ለታየን ነገር መገዛታችንን ክፋታችንንና ድፍረታችንን ከእግዚአብሔር ቃል ለማስታረቅ መሞከራችን ከሁለት ዓለም የተሰደድን መሆናችን ልብን የሚያስጨንቅ ነገር አለው፡፡
    አዎን! ኃላፊነት የሚሰማችሁ መካከለኞች ወዴት ናችሁ? በዚህ ዙርያ ማን ሊሆን እንደሚችል ሳስብ ነፍሴ በጣም ትጨነቃለች፡፡ ሸምጋይ ያስፈልገናል፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል እውነትን በመናገርና በእውነት በመፍረድ የሚያስተራርቁ፣ የሚያቀራርቡ፣ የሚያደላድሉ ... የታመኑ ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶች፣ ሰባክያን፣ ዘማርያን፣ ጳጳሳት፣ ፕሮፌሰሮች[ምሁራን]፣ ተማሪዎች ... ያስፈልጉናል፡፡ 
   አውቃለሁ መንገዱ ከባድ የሕማም መንገድ ነው፤ አለመደገፍ ወይም መደገፍ ለሁለቱም ወገን ጠላት ሊያስመስል ይችላል፤ እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ የተገኘውን ኑግ ሁሉ ወደሰሊጥነት የመቀየር ወቀጣ፣ ፈጽሞ የማጥፋት ሥራ ከመሆኑም ባሻገር ይኸው ደም ከማፍሰስና ነፍስ ከማጥፋት ሊታደገን፤ በገዛ ወገናችንም ላይ ጥይትን ከማዝነብ፣ ከጥላቻና ከንቀት ፈጽሞ ሊያድነን አልቻለም፡፡
     እውነት እንናገር ከተባለ አስታራቂ ሀሳብ የሚያነሳ፤ ከየትኛውም ወገን የሚደረግ ጥላቻ፣ ነቀፋና ግድያ እንዲቆም የሚታገል፤ ሁሉንም ወገን ወደ እርቅና ሰላም የሚገፋ መካከለኛ ሰው መጥፋቱ ለሀገሪቱ ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ተሸንፋለች፤ ዘረኛነታችን ጫፍ ላይ ደርሷልና፡፡ ጥላቻ በእልልታ ዜማ እየተሰበከ ነውና፡፡ ግደለው፣ እረደው፣ አባረው ቋሚ መፈክራችን ሆኗልና፡፡ ለዚህም ከዚህ የሚታገዳት መካከለኛ ሰው አገራችን የግድ ያስፈልጋታል፡፡
     እንደ እነ አባ መላኩ ታከለ፣ እንደ እነ አባ ገዳ አጋ ጠንጠኖ(ክቡር ዶ/ር)፣ እንደ እነ አባ ገዳ ጎርጎር ቡሌ(ክቡር ዶ/ር)፣ እንደ እነካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፣ እንደ እነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ፣ እንደ እነ  ጄኔራል ጃካማ ኬሎ፣ እንደ እነ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣  ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ፣ እንደ እነፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ እንደ እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ(አትሌት)፣ እንደ እነ መአዛ ብሩ፣ እንደ እነ ዶክተር ቶሎሳ ጉዲና፣ እንደ እነ ዶክተር መለሰ ወጉ፣ እንደ እነ ጌታቸው በለጠ (የደራስያን ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበሩት)፣ እንደ የሕግ ባለሙያው አብዱ  አይነቱ ሆደ ሰፊ እጅግ ያስፈልጉናል፡፡
     አዎን! በኢትዮጲያ ቁስል ላይ እንጨት የሚሰድና ቀንበር የሚያጸና ብዙ አለን፡፡ ይህ ቸግሮንም አያውቅ፥ ነገር ግን ... የኢትዮጵያን ችግር የሚሸከም ያስፈልገናል፡፡ ደግሞ ለችግሯ የሚቆረቆር፣ ለመድማቷ የሚያነባ፣ ለውድቀቷ የሚቆጭ መካከለኛ ሰው ምነው ጠፋ? የሚል ትልቅ አገራዊ ጥያቄ ማንሳት ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ በሌላ መልኩ አሁን በተፈጠረው ችግር የእነዚህ ሰዎች ድምጽ ምነው ጠፋ ወይም ታፈነ? ለምን ዝምታን መረጡም የሚለው የዘወትር ጥያቄዬ ነው፡፡ ለአንድ ሰው መሞት የሚደረገውን ከፍ ያለ አባ ገዳዊና አገር በቀል የካሳና የእርቅ መንገድ ማስፈኛ በበዛባት አገር፥ ይህ ሁሉ ሰው ሞቶ፤ ይህ ሁሉ ንብረት ወድሞ ዝም ማለት በታሪክ ፊት ከመወቀስ፤ በእግዚአብሔር ፊትም ከመጠየቅ አያድንም፡፡ አዎ! እሳት በተለኮሰበት ማፋፋም ተገቢ አይደለም፤ ይልቅ መካከለኝነት እጅግ እጅግ ያስፈልገናል፡፡ ኸረ የኢትዮጲያ “መካከለኞች” ሆይ! ወዴት ናችሁ?
      ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በክርስቶስ ኢየሱስ በቤዛነቱ ጉልበት አስተዋይ መካከለኞችን አስነሳልን፡፡ አሜን፡፡


2 comments:

  1. አዎ! እሳት በተለኮሰበት ማፋፋምም ማጋጋምም ተገቢ አይደለም።
    በኅብረ ቀለም ጽሁፍ የሰጠህቸው አስተያየቶችሀና አስተማሪነታቸው በተገቢው ወቅት በትክክል ተስተጋብተው እያለ እከሌዎችና እነእከሌዎችም ሳይኖሩበት መልዕክትህ - መልካም ፤ ይበል ፤ይበል የብዙዎቻችን ነው እላለሁ። ግና፡ ግ ን ፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ተዕዛዝ ሰጥቻልሁ ባልካት ሀረግ አልተግባብተንም ባይ ነኝና ምናአልባት በመሠረታዊ አባባላቸው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ህጋዊ ሥረዓት ሲፋለስ የተመደብኩበትን ሥራ መሥራት አለብኝ በሚል የተናገሩት እንጂ ከዚህ በፊት በምናውቀው የገዢዎች የፍለጠው ቁረጠው አካሄድ አልተናገሩም ባይ ስሆን በመግቢያዬ ዐረፍተ ነገር በአንተ ቃል ላይ የራሴን የጨመርኩት በትህትና ይገልጽልኛል ብዬ አምናለሁ። ለማንኛውም ለሀገራችን ማለትም ለራሳችን በቆምንበት ነገር ሁሉ የቀና ልቦናን ይስጠን። አሜን !!!

    ReplyDelete
  2. Very good article.Pleas God Help the Ethiopians

    ReplyDelete