Wednesday, 28 September 2016

የጳጳሱና የሰባክያኑ ቤተ ክርስቲያንን “መለካዊ” የማድረግ ሃሳባቸው እስከምን ድረስ ነው?!

Please read in PDF      

          ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ “አልቃሻው ነቢይ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ዋናው ምክንያት፥ ሕዝቡ በኃጢአትና በነውር ምድሪቱን እጅግ በማርከሳቸውና ፊታቸውን ወደንስሐ ዘወር እንዲያደርጉ፥ ከእነርሱ ጋር እየተራበና እየተጠማ በመካከላቸው ሆኖ አዘውትሮ ቢናገራቸውም፥ እስራኤል ሊሰሙት ካለመውደዳቸው ባሻገር አጥብቀው ስለተቃወሙትና ሊቀበሉት ፈጽመው ስላልወደዱት ነው፡፡
    በዚህም ምክንያት በጥልቅ ሐዘን መዋጡን፥
    “አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም፡፡ … ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም፡፡”፤ (ኤር.4፥19-22)፤ “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ፡፡ ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ፡፡”(9፥1-5)፤ “እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል፡፡”(10፥21)፤ “ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ፡፡ ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ ማሰማርያ ደርቆአል፤ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም፡፡ ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (23፥9-11)
የሚለው የነቢዩ ንግግር የሚያየው የእስራኤል ክፋት ምን ያህል እንዳቆሰለውና እንዳሳዘነው በትክክል ይገልጠዋል፡፡

    እስኪ ነቢዩ ከገለጣቸው ኃጢአቶች በእኛ መካከል የሌሉት የትኞቹ ናቸው? እኛ ለክፋት ብልሃተኛ አይደለንምን? በጐ ነገር ከማድረግ እጅግ ዘገምተኞች አይደለንምን? አመንዝሮችና አታላዮች በመካከላችን የሉምን? የሐሰት ምላስ በእኛ መካከል አልነገሠምን? በሐሰት ላይ የበረታን ለእውነት ግን ልምሾዎች አይደለንምን? ከባልንጀራችን ጋር የምንነጋገረው እውነትን ብቻ ነውን? አንወሻሽም? ባልንጀራችንን አናታልልም? ሕዝቡን የሚመሩት ነቢያትና መምሕራንስ በጐቹን እንደሚገባቸው የሚያሰማሩ ናቸው? በስንፍና የተያዙ አይደሉምን? ሊጠብቋቸው የሚገባቸው በጐች የተበተኑና የተቅበዘበዙ አይደሉምን? በእግዚአብሔር ቤት ውስጥስ የእነርሱ ክፋት በእግዚአብሔር ፊት የወጣች አይደለችምን?
    እስኪ እውነት እንናገር፥ እኛ ነን የክፋት ብልሃተኞች ያልሆንን? የመንግሥት ባለሥልጣኑ መማለጃና ጉቦ የሚቀበለው እንዴት ነው? ጉቦን የሚሰጠው ሰውስ በብልሃት አይደለምን? ነጋዴው ሙዝን ከቅቤ፣ አሸዋን ከስኳር … ቀላቅሎ ሲሸጥ ሰው ሁሉ እያየው ነው ወይስ በብልሃት? … ኢትዮጲያ በዓለም ካሉት “የዝሙት ቱሪስት አቅራቢ” አገራት መካከል አንዷ ወደመሆን መድረሷን ስንቶቻችን እናውቃለን? የንስሐ ልጁን ከሚያማግጥ ካህን ጀምሮ በቁመቱ ልክ በዝሙት የወደቀ ትውልድ በእኛ መካከል የሌለ ነውን? ኢትዮጲያ  አታላይ ደላሎች ብቻ ሳይሆኑ አታላይ ሪፖርት አቅራቢ ሠራተኞች ያላት አገር አይደለችም? ራሱ መንግሥት እንኳ ሕዝብን የሚዋሽበት ጊዜ የለም?
    እስኪ ከእኛ መካከል ያላተለለ ማን ነው? ወላጁን፣ ዘመዱን፣ ገዢውን፣ ሠራተኛውን፣ ልጁን፣ ሚስቱን፣ ባሏን፣ ፍቅረኛውን፣ ውድ ጓደኛውን፣ ሕዝብን፣ መንግሥትን … በሐሰት ቃል ያላተለለ ማን አለ? ስንት ዘመን ይሆን[አሁንም ጭምር እንኳ] ከሚስታችንና ከባላችን፣ ከቤተሰባችና ከጓደኛችን ጋር በሽንገላና በውሸት ቃል ስንነጋገር የኖርነው? ዛሬም በዋሸነው ውሸት ንስሐ ከመግባት ይልቅ ራሳችንን በጸጸት ጅራፍ የምንገርፍ ስንቶች እንሆን? በወንድማማች መካከል አጸያፊ ውሸትን በመዋሸት እጅግ የሚዋደዱ ሰዎችን የለያየን የለንም? እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ነገሮች ዋነኛው፥ “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ”(ምሳ.6፥19) መሆኑን እያወቅን ከመሥራት ያልታቀብን ጥቂት አይደለንም፡፡
    ሕዝቡን የሚመሩ ጳጳሳት፣ ሰባክያን፣ መምህራን … ምን ያህል ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት የተሻሉ ናቸው? በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የእነርሱ ክፋት ያልወጣ ነውን? ሙስናቸውና እጅ መንሻቸው እስከምን ድረስ ነው? ያለዘመድና አድልዎ ሹመት ሽልማት የሚሰጡ ናቸው? የዝሙት ረመጥ አልገረፋቸውም? በጐችን በመጠበቅ ታማኝ ናቸው? ከሕንጻ ግንባታ ይልቅ የሰው መንፈሳዊና “ሥጋዊ” ሕይወት መታነጽ ግድ የሚላቸው ናቸው?
    እንግዲህ አልቃሻው ነቢይ በብዙ ያነባ፣ ሕይወቱንም በሐዘን እንዲከበብ ያደረገው ይህ ሁሉ እየታየው ነበር፡፡ በአገር ላይ ለሚፈስሰው ደም፣ በየሐገሩ ተሰድዶ ለሚኖረው ሕዝብ፣ ለፍትሕ ማጣቱ፣ ለድሆች መጨቆን፣ ለሠራተኞች ደመወዛቸው መነጠቅ … ዋናው ምክንያቱ እኛና እኛ ብቻ ነን!!! በኤርምያስ ዘመን የነበረው ኃጢአት ዛሬም በዘመናችን እንዲሁ አለ፤ በዚያን ዘመን ይህን ኃጢአት ተመልክቶ ሕዝቡን የቀጣው እግዚአብሔር ዛሬም አልተለወጠም፡፡ የተለየው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታላቅ ምህረትን ማብዛቱ ብቻ ነው፡፡
    ምሕረት ማብዛቱም ኃጢአትን እንድንሠራ፤ በበደል እንድንጸና አይደለም፡፡ “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?”(ሮሜ.3፥4)፤እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም፤” (ሮሜ.6፥1) እንደተባለ የእግዚአብሔር ምሕረት ለንስሐና ለመመለስ እንጂ ለሌላ ለምንም  ነገር አይደለም፡፡ ንስሐ መግባት ያለባቸው ደግሞ ቤተ ክህነትም፤ ቤተ መንግሥትም ሁሉም ናቸው፡፡ አሁን እየሆነ ላለው ነገር ሁሉ ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም ተጠያቂዎች እንጂ አንዱ ባንዱ ላይ ማላከክ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ከመጀመርያው መገሰጽና መምከር የነበረባት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የሕዝብ ቁጣ ሲገነፍል ደርሳ ብትቆጣ፥ “በጐችን የሚከተሉ እረኞች” ማፍራቷን እንጂ ሌላ ምንም ልንል አንችልም፡፡ በሌላ ቋንቋ መንግሥትም እኛም ንስሐ መግባት አለብን እያልን ነው፡፡  ነገር ግን ጳጳሱና ሰባክያኑ ከዚህ መንገድ በጣም ርቀው መመልከቴ እጅግ አሳዝኖኛል፡፡
    “በሕዝብህ አለቃ ላይ በክፉ አትናገር” የሚለውን አምላካዊ ቃል ሳልዘነጋ፥ ለአቡነ አብርሃም ጥያቄ አለኝ፤ በባህር ዳሩ “የደመራ አውደ ምሕረት” ላይ ተገኝተው የተናገሩትን ካደመጥሁ በኋላ፥ ብዙ ጥያቄዎች ወደውስጤ ጎረፉ፤ “ለጳጳሱ እንደፖለቲካ አለመናገር አንድ ነገር ቢሆንም፥ እንደሃይማኖት አባት መናገር እንዲህ ነው ወይ? በድፍረት መናገር ማለት ነውርን ሁሉ “መንግሥት” ላይ መደፍደፍ ነው ወይ? እውነት ቤተ ክርስቲያን ምንም ያልበደለች፤ እኛስ ምንም ያላጠፋን ንጹሐን ነንን? [ዛሬም ደግሜ እላለሁ፥ መንግሥት ትልቅ ጥፋት ስለማጥፋቱ ምንም ጥርጥር የለኝም፤ ያጠፋውም ጥፋት ደረጃ የሚወጣለት አይደለም፡፡] መቼም፥ “የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡”(መሳ.6፥1) የሚለውን ቃል ሲያነቡ ኃጢአት ለምን አሳልፎ እንደሚሰጥ ያስተውላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ያውም እኛ ደግሞ ነውርን ያደረግነው በገዛ ወገናችንና በራሳችን ላይ መሆኑን ካልዘነጋን፥ ለሚብስ መከራና ሰቆቃ ያልተዳረግነው ምሕረቱ ጋርዶን ነው፡፡ ግና ንስሐ ለመግባትና በደላችንን ከማመን ከዘገየን “የፈራነው ከባድ መከራ” እንደማይቀርልን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
    ሌላው፥ ለመሆኑ ሐዋርያት ደፍረው ተናገሩ የተባለው ምንን ነበር? የመዳኑንና የጸጋውን ቅዱስ ወንጌል አይደለምን? እርሱም በክርስቶስ ኢየሱስ ካልሆንን ወይም በሞቱና በትንሣኤው ካላመንንና በደሙ ካልነጻን ሁላችን ኃጢአተኞች መሆናችንን የሚያመለክተውን አልነበረምን? እውነት ደፍረው መናገር ቢኖርብዎት ቤተ ክርስቲያን ራሷ ንስሐ እንድትገባ አልነበረምን? እርስዎ ከሚመሩት ጀምሮ እስከታች ያለው ቤተ ክህነት በምን አይነት አስከፊ ዘረኝነትና ጉበኝነት እንደተዋጠ አላዩትምን? ተሰብሮ የሚሰረቀው የድኃው አስራት በኩራት አልታየዎትም? የሚመሩት መንጋ በዝሙትና በርኩሰት ተውጦ ዕረፍት አጥቶ ሲቀበዘበዝ አላስተዋሉትምን? ለመሆኑ ለዚህ ሕዝብ ምን ነበር የእርስዎ ምላሽ? ጉድፍ ከማጥራት ምሰሶ ማውጣት አይቀልም ወይ? ከመንግሥት ይልቅ የእርስዎ ኃላፊነት እንደሚከብድ አስተውለውታል?! ለወታደር ከመናገርስ የሚመሩትን ሕዝብ ንስሐ እንዲገባ መናገር አይቀልም ነበር ወይ? እርስዎ በንስሐ በአምላክዎ ፊት ቢወድቁ፣ ሕዝቡም እርሶን አይቶ ንስሐ ቢገባና ቢመለስ፥ እግዚአብሔር ቅንና ታማኝ መሪ ለአገራችን እንደሚሰጣት አያምኑምን? ነው ወይስ የሕዝብ ብሶት እየቀሰቀሱ “እንደካድሬ ባማረ ቋንቋ” ተናግሮ ማስጨብጨብ መፍትሔ ይመስልዎታል? እውን ንስሐ ቢያውጁና ሕዝቡን ወደአምላኩ ቢመልሱት ለሕዝቡ እግዚአብሔር የዕረፍት ጸሐይ ያወጣለት ነበር፡፡
     ግና እርሶም እግዚአብሔራዊ መፍትሔን ተው፤ ታዲያ የዚህች ቤተ ክርስቲያንና አገር ተስፋዋ ንግግርና ጦር ብቻ ሊሆን ነውን? ኸረ ለመሆኑ “አባታችን” ከዓመት በፊት የዲያስፖራው ዓለም በኢትዮጲያ የግብረ ሰዶም ሕግ ይጽደቅ ብሎ አለም አቀፍ የግብረ ሰዶማውያንን ስብሰባ ጠርቶ፥ “በኢትዮጲያዊነታችን እንኮራለን፤ በኢትዮጲያዊነታችን አናፍርም፤ ፍቅር ያሸንፋል” የሚል መፈክር ይዞ ሲጮህ ሲደነፋ ለምን ነበር ዝም ያሉት? እውነት የሕዝብ ነገር ከገደዶት ይህ ለእርስዎ ምንም ትርጉም የለውም? … ዛሬም ከውጭ ሆኖ ባጋደለ ሚዛኑ ባልዋለበት ኩበት ልልቀም የሚለውን ይኸንኑ ዲያስፖራ ምን አሉት ይሆን?[ለአገራቸው በቅንነት የሚተጉና ወገናቸውን አብዝተው የሚወዱትንና ለሠላሟ የሚተጉትን በአክብሮት ሳላስብ ግን አላልፍም]

     ሌላው ደግሞ የ“ሰባክያኑ” ኤፍሬም እሸቴና የዘመድኩን በቀለን ጽሁፎች አይቼ፥ “እውን ምንድር ነው የሚያገለግሉት?” እንድል አድርጐኛል፡፡ ኤፍሬም “ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ለውጥ እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ጽሑፉ ላይ፥ የሕዝቡ እምቢተኝነት መንግሥትን እስከማውረድ መፋፋም እንዳለበትና በዚህም ውስጥ ቤተ ክርስቲያን “በመሳተፍ ለታሪካዊው ጥሪ ምላሽ” እንድትሰጥ በምጥ ቃል ይጣራል፡፡ በጽሁፉ “ሰባኪው” የቤተ መንግሥቱንም የቤተ ክህነቱንም እጣ ፈንታ ትልማዊ በሆነ መንገድ ወስኖ አስቀምጧል፡፡ ኤፍሬም “ከእምነት የሚያፈገፍጉ ሰዎች የመጨመሩ አንዱ ምክንያትና የማያስደንቀውም” ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለው መንግሥት ጋር መሻረኳ ነው በማለት ከማስተዋል ይፎርሻል፡፡ አስተውሉ! “ሰባኪው” ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ወይም በድላችኋልና ንስሐ ግቡ’ ከሚለው አዋጃዊ ቃል ምዕራብ ከምሥራቅ የሚርቀውን ያህል ምን ያህል እንደራቀ?

   ኤፍሬም በአንድ ጐኑ፥ የአሁኗ ቤተ ክርስቲያን አሁን ካለው መንግሥት ጋር መሻረኳ አግባብ አይደለም እያለ፥ በሌላ እይታው ግን ይህንን መንግሥት ለመጣል ከሚታገሉት አካላት ጋር መታገል አለባት ይላል፡፡ ከሳቱ አይቀር እንግዲህ፥ እንዲህ እስከመጨረሻው መሳት ይሏል ይኼ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህች ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለውን መንግሥት ለመጣል ትታገል እንበል፥ ከዚያ በኋላ ከመጪው መንግሥት ጋር ትሻረካለች ወይስ ምንድር ነው ዕጣዋ?

    ኤፍሬም ሆይ! እሰብከዋለሁ የምትለው ወንጌል እንዲህ ይላልን? እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ለመሆኑ ከየትኛው መሪ ጋር ነበር ተስማምታ ጦር ያዘመተችውና ከዓለማውያን መሪዎች ጋር ግንባር ገጥማ ደም በማፍሰሰው የተጠመደችው? እንዲህ ያለውን ነውር የሠራችው የካቶሊክ  ቤተ ክርስቲያን የአለምን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቋን ዘነጋኸውን? በምን ስሌት ነው ቤተ ክርስቲያን አለማዊ መንግሥት ለመጣል ከታጋዮች ጋር የምታብረው? ምነው ጐበዝ መሬት፤ መሬት መሽተትህ? እውነት እኛ ፊታችንን ወደጌታ ብንመልስ እርሱ ወደእኛ የሚመለስ አይደለምን? “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል፤” (ሆሴ.6፥1) ብትል ምን ነበረበት? ለመሆኑ አንተው የተጠቀምክበት “መለካዊነት” ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ስለመጋባት እንደሚያዛምድ ምነው ጠፋህ? ቤተ ክርስቲያን የማታድፈውና ለዘለዓለም ከፊት መጨማደድና ከርኩሰቷ ነጽታ ልትኖር የምትችለው ከሙሽራዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ብቻ ጸንታ የቆመች እንደሆን ብቻ ነው፡፡

    ለምን እንደሆን ባላውቅም ወደዲያስፖራው ዓለም ብዙዎች ሲቀላቀሉ እንግዳ ካባ መልበስን ይወዳሉ፡፡ ዘመድኩን በቀለ በዲያስፖራነት ሲደላደል “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” በማለት ከመንፈሳዊነት ፎረሸ፡፡ መቼም ከይሁዳም፣ ከእስራኤልም ከአሕዛብም የተነሱ ነቢያት አመጽንና ጦርነትን መሠረት አድርገው ተነስተው ይሆን? ቅዱሳን ሐዋርያትስ ለብዙ አብያተ ክርስቲያናትን መልዕክትን ሲጽፉ ምንን ይሆን መሠረት አድርገው የጻፉት? ከንስሐና ከበደላችሁ ተመለሱ ከሚል መልዕክት ውጪ ምን ቃል ነበራቸው? እኒህ ነቢያትና ወንጌላውያን ትንቢቱና መልዕክቱ ከጌታ ስለመጣላቸው ሲናገሩ አልዋሹም፡፡ ሕዝቡም በአመጻ ካልጸና በቀር አልሰማችሁም አላላቸውም፡፡ “ሰባክያኑ” ሆይ! ይህንን ለመሆኑ አስተውላችኋልን?

    ጌታ ግን አሁንም በዙፋኑ አለ፡፡ ሕዝብ ለንስሐ ዘግይቶ ለዓመጻ ቢበረታም፣ አገልጋዮች ሕዝቡን ወደእረኛው ባይመልሱትና አብረው ስለማመጽና ስለመጥፋት ቢመክሩም ጌታ ግን አሁንም አለ፡፡ ዛሬም ለንስሐ፣ ለምሕረት ይጠብቀናል፡፡ የሚጠቅመን በፊታችን መልካም መስሎ የታየንን ማድረግ አይደለም፤ የእግዚአብሔር ሃሳብ በአገራችን ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ንስሐ እንግባ፣ በልጁም የተደረገልንን ሕያው ጽድቅ ለመቀበል የልባችንን እጅ እንዘርጋ፡፡   

    እግዚአብሔር ሆይ ሕዝብህን አስብ፤ የንስሐ ልብም ስጠን፡፡ አሜን፡፡ሐወዋረርየያተት ሐወረሐሐኸሐሐሐሐሀሀሀሀሀገገገገገረገግግገበሰስስገግሀሄተትጀከኩኩ6ከኮወውው በበበበበተረ5ረሩሩረ57ደ5ደ44

4 comments:

  1. እጅግ መልካም እይታ!

    ReplyDelete
  2. ተባረክ፡፡ ጌታ ለሁላችንም ማስተዋልን ይስጠን፡፡ጠፍተናል

    ReplyDelete
  3. ዋዉ!!!! ብሩህ እይታ!

    ReplyDelete