ጌታ ኢየሱስ ከጾመም በኋላ እንደሰውነቱ
ተርቧል፡፡ “አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ” (ሉቃ.4፥2) እንዲል፡፡
ጾም የዝግጅት ጊዜ ነው ፤ የዝግጅት ጊዜም ስለሆነ ጌታ ወደአደባባይ አገልግሎት ከመውጣቱ በፊት
ጾምን ጾመ፡፡ ከጾመ በኋላ ደግሞ መራቡን እናስተውላለን፡፡ በዓውዱ ያስተዋልን እንደሆን የተራበው መብልን ይመስላል፡፡ ዋናውና ትልቁ
የጌታችን ረሃብና ጥም ምግብና መጠጥ እንዳልሆነ ግን ቅዱስ ወንጌልን
ስናጠና እናስተውላለን፡፡
በአንድ ወቅት በሰማርያ፥ ደቀ መዛሙርቱ ምሳን ሊገዙ ወደከተማ ሄደው ቆይተው፥
ምሳን ገዝተው ሲመለሱ ጌታ ኢየሱስ ከአንዲት ውኃ ልትቀዳ ከመጣች ሴት ጋር ሲያወራ አገኙት፡፡ በአይሁድ ልማድ አንድ ረቢ (ወንድም
ቢሆን) ከሴት ጋር (ሚስቱንም ቢሆን) በመንገድ ላይ አያናግርምና እርሷን ያውም ሳምራዊትን ሴት በማናገሩ ደቀ መዛሙርቱ ተደነቁ፡፡
ምሳ እንዲበላ በለመኑት ጊዜ “እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው” (ዮሐ.4፥32)፡፡ እነርሱ
ከመምጣታቸው በፊት ከሴቲቱ ጋር የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መሠረታዊ ትምህርትን ሲያስተምራትና መሲሕነቱን እየነገራት ነበር፡፡ ከደቀ
መዛሙርቱ አንዳቸውም ስለምን ከሴቲቱ ጋር እንደሚያወሩ ጌታንም ሆነ ሳምራዊቷን ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም፡፡
ጌታችን ቅድሚያ
መሰጠት ስላለበት ነገር ቅድሚያ ከመስጠት ወደኋላ ፈጽሞ ፈቀቅ አይልም፡፡ ወንጌላዊው ደቀ መዛሙርቱ ሲመጡ ጌታችን ከሴቲቱ ጋር ያደርግ
የነበረውን ንግግር አቋርጦ መንፈስ ቅዱስ እንደነዳው በጌታና በደቀ መዛሙርቱ መካከል የተደረገውን ውይይት ይዘግብልናል፡፡ እነርሱ
ቅድሚያ የሰጡት ለቁሳዊ መብልና መጠጥ ሲሆን እርሱ ግን እናንተ “ለጊዜው” የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው፡፡ በመንፈሳዊው
ዓለም ቅድሚያ ባለመስጠታችን የከሰርናቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለሥጋ ተግባር ብቻ ትኩረት ሰጥተን በኖርንባቸው ዘመናት በነፍስ ምን
ያህል እንደተራቆትን እንደኖርን አስተውለን ይሆን?
ደቀ መዛሙርቱ አሁንም በሃሳባቸው፦ “የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት
ይሆንን? ይባባሉ” ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ሴቲቱም ስለምን ዓይነት ምግብ እንደሚያወራ ያስተዋለች አይመስልም፡፡ በሥጋና በደም አዕምሮ
ሰማያዊውንና የከበረውን ሃሳብ መረዳትና ማስተዋል እንደማይቻል (ማቴ.16፥17) እንዲሁ ደቀ መዛሙርቱ ቅድሚያ የሰጡት ሥጋዊውን
መብል ነበርና መፍትሔ ብለው የሚያስቡት በዚሁ መንፈስ ሆነው ነው፡፡ ቅድሚያ መስጠት ለሚገባን ቅድሚያ መስጠት ካልቻልን ኋለኛውን
እንጂ ፊተኛውንና የላቀውን ማሰብ አይቻለንም፡፡
በሃብት መታለል (ማቴ.13፥22) ፣ ሌላውን ነገር በመመኘት (ማር.4፥19)
፣ ምድራዊ ብልጥግናንና ደስታን እስከመታነቅ ድረስ አብዝቶ መፈለግ (ሉቃ.8፥14) ፣ ሥልጣን ፣ ዝና ፣ ምድራዊ ክብር ፣ መብልና መጠጥ እንዲሁም ሌሎችም አማኞች ሊጠነቀቁባቸው በእነዚህ ነገሮችም
ከመጠመድ ሊጠበቁ ይገባቸዋል፡፡ ቀዳሚውና ዋናው ነገር እንድንኖርለት የታዘዝነውን የክርስቶስን ፈቃድ መፈጸምና ለዚያም መኖር ነው፡፡
ለጌታ ኢየሱስ ትልቁ መብልና መጠጥ ፤ በመራብም ውስጥም ሆኖ እንኳ የሚታወሰውና የሚያስቀድመው፦ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ
አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” የሚለው ነው፡፡ በእርግጥም ለእኛም የተባለልን፥ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን
መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ.6፥33) የሚለው ንጉሣዊ ወርቃማ ቃል ነው፡፡
አስተውሉ! የተራበ ሰው ሊበላና ሊጠጣ እጅግ ይጓጓል ፤ እጅግም ይመኛል፡፡
እውነተኛ መንፈሳውያንና “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ” (ገላ.5፥24) የሚለውን ሕያውና
እውነተኛ ቃል ከልብ በማስተዋልና በማሰላሰል ምኞታችንና መሻታችን ፤ መራብና መጠማታችን የምንፈጽመው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሊሆን
ይገባል፡፡ በሕይወታችን ከብሮ ሊፈጸም የሚገባው የምንኖርለት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ለኢየሱስ ዘወትር ረሃብና ጥሙ ለአባቱ
መታዘዝና የእርሱን ሥራም ከምንም አስቀድሞ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ የሕይወት ምስክርነት ነው፡፡ እኛንም እንዲህ አድርጉ
ሊለን ውብ የሆነውን የጽድቅ ሕይወትን ኖሮ አሳየን፡፡
በእውነትም፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም
የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና” (ሮሜ.14፥17) መብልና መጠጥ ወይም ምድራዊ ደስታና ተድላ ለአማኝ ቀዳሚ
ትኩረትን የሚሻ አይደለም፡፡ ደስታ ከክርሰቶስ ሕይወት የሚበቅል የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንጂ የግል ጥረትና የመብልና መጠጥ ውጤት
አይደለም (ገላ.5፥22)፡፡ ለዋናው ነገር ትኩረት አለመስጠት የክርስትናን ኑሮ ዋና መሠረት መተውና ፍጹም መዘንጋት ነው፡፡ ይህ
ደግሞ፥ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና … ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና” (ሮሜ.8፥6-7) ለሚለው ጽኑ ወቀሳ ራስን
አሳልፎ መስጠት ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመ በኋላ የተራበው ተራውን ቁሳዊ ምግብ ብቻ
አይደለም፡፡ የተራበውና የተጠማው፥ “የላከውን ፈቃድ ያደርግ ዘንድ ሥራውንም ይፈጽም ዘንድ ነው”፡፡ አባቱን በመታዘዝ አባቱን ደስ
ማሰኘት ክርስቶስ ከተራበ በኋላ የተጠማው ጥማቱ ፤ የተራበው ረሃቡ ነው፡፡ እኛ ከጾማችን በኋላ ምንድር ነው የተራብነው? እውነት
ጽድቁን ተርበን ይሆን? ወንጌል ላልደረሰላቸው ወገኖች መድረስን ተርበን ተጠምተን ይሆን? የጌታ ሥራን ለመሥራት ጨክነን ተነስተን
ይሆን? ለመሆኑ ጾም መንፈሳዊ ነገርን ለመሥራት ቀዳሚ ዝግጅት እንደሆነ ገብቶናል? ከገባንና ከጾምነው ይህን ያህል ጊዜ ምን ለመሥራት
ጾምን?
ቅዱሱ ወንጌል “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና”
(ማቴ.5፥6) ይለናል፡፡ ይህ መራብና መጠማት ቅዱሳን ሁሉ እጅግ ተርበውታል ፤ ተጠምተውታልም፡፡ ቅዱስ ነቢይ ዳዊት፦ “ዋላ ወደ
ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ
ፊት መቼ አያለሁ?” (መዝ.42፥2) ሲል፥ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥
ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።” በማለት ፍጹም የሆነ መራብና መጠማታቸውን ይነግሩናል (ፊልጵ.3፥10)፡፡
ከጾምን በኋላ የእኛ መሻትና ምኞት ፤ ናፍቆትና መጐምጀት ምን ይሆን?
ከጾም በኋላ ምን እየሠራችሁ ነው? ብዙዎቻችን “ብዙ በመጾምና በመጸለይ ስለደከምን” መንፈሳዊ ሕብረትን በዚህ ዘንግተናል ፤ አንዳንዶቻችን
ተግተን ወንጌል የምንመሰክርባቸውን ዓውደ ምሕረቶች ዘግተን “ተሰውረናል” ፣ አንዳንዶቻችን “ዕረፍት ነው” ብለን አውጀን ጉባኤያትን
ሁሉ አጥፈናል ፣ መብልና መጠጥ ፤ ሥጋዊ ዕረፍትና ቅጥ ያጣው ምቾትን ፍለጋ ጸሎትን ተግቶ ቃሉን ማንበብ ትተነዋል ፣ ጌታ ከሙታን
የተነሣው እኛን ለሕይወት አቁሞ ለኃጢአት እንድንሞት ነበር ፤ እኛ ግን በሥራ ዘመን በቅምጥልነት ተዘልለናል፡፡
በእውኑ ግን
ከጾምን በኋላ ምን መንፈሳዊ ጥማትና ረሃብ ተከሰተልን? ተገለጠልን? ከጾምን በኋላ የእግዚአብሔር ፈቃዱን መፈጸም ምግብና መጠጥ
ካልሆነን ለጾምነው ጾም ራሱ ንስሐ እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እናንተ የጾማችሁ ምን እየሠራችሁ ነው? ጾማችሁን
ጨርሳችሁ ወደቁሳዊ ምግብ ነው የተሰማራችሁት ወይስ ለአባታችሁ ሥራ ከፊት ይልቅ ተግታችሁ ልትሠሩ አስባችኋል? እንግዲህ አስተውሉ!!!
ጌታ ኢየሱስ ሆይ ለልባችን ማስተዋልን
አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
Thanks God bless you
ReplyDelete