Sunday 25 December 2016

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ“አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አንድ)

   Please read in PDF
     የዚህ ጽሁፍ ዋና ጭብጥ፥
1.      ዋናችን ጌታ ኢየሱስን በክርስትና ሕይወታችን ሁሉ ትኩር ብለን እንድንመለከት፤
2.     ዋናችን የሆነውን ጌታ ኢየሱስን ትተን በእርሱ “ሎሌዎች” ላይ ዓይናችንን የተከልን፥ በንስሐ እይታችንን እንድናጠራ፥ ከሰባኪ አድናቂነትና ተከታይነት ወደጸጋ አደላዳዩና ሠጪው ጌታ እንድናተኩር፤
3.     አገልጋዮች የሆንንም፥ “የሚከተሉንን” ምዕመናንና ምዕመናት የተሰጠንን “ስጦታ” ሳይሆን፥ ሰጪውንና ሁሉን አድራጊውን እንዲመለከቱ፥ በሁላችንም ላይ የሚፈርደውንና የሁላችንን ሥራ ለሚያየው ጌታ ሕይወታቸውንና መንገዳቸውን አሳልፈው በማስጨከን እንዲሰጡ በማሰብ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምልከታ ነው፡፡
መንደርደርያ
    ለብዙ ዘመናት ሰይጣን ሰዎች ዋናውን ጌታ እንዳይመለከቱና “ሥጦታውን መመልከት ሠጪውን የመመልከት ያህል ነው” ወደሚል ከንቱ ማታለል ብዙዎችን ሲመራ አይተናል፡፡ በተለይም በዘመናችን ይህ እውነታ ጎልቶና ደምቆ በመካከላችን በሚገባ ይስተዋላል፡፡ ሰዎች ሰባኪ[ሎሌውን] ብቻ መስማትን ልክ እግዚአብሔርን እንደመስማት ሲቆጥሩት፥ ቅዱሱን ወንጌል ከመመርመርና ጌታ ኢየሱስን በትክክል በመመልከት የክርስትና ሕይወት ሩጫቸውን ከመሮጥ ተዘናግተዋል፤ [ይህ በወንጌሉ ፍጹም እውነትነት ላይ የቆሙትንና ለቃሉ ፍጹም በመታመን በማገልገል ያሉትን የጌታ ታማኝና እውነተኛ አገልጋዮችን አይመለከትም]፡፡

    አዎን! በነገር ሁሉ የምንሮጥለት አንድ ጌታ አለን፤ የክርስትና ሕይወት ሩጫችንም ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የታወቀና መንገዱ ተመርቆ በመድኃኒታችን ክርስቶስ ኢየሱስ የተከፈተ ነው፤ (ዕብ.10፥19-20)፡፡ በዘመናት ግን ሰይጣን እውነተኛውን የክርስትና ሕይወት ሩጫ እንዳንሮጥ በብዙ ነገር ያዘናጋናል፡፡ ሰይጣን እጅግ በጣም ተንኮለኛ ነው፤ በ“መልካም ነገር” ውስጥ እንኳ፥ የእንክርዳድን መዝገብ ሊያኖር ይወዳል፡፡ ይህንን በማድረግ በዚህ ዘመን፥ እጅግ በጣም የተሳካለት ይመስላል፡፡ በተለይም ከሠጪው ይልቅ ሥጦታውን በማስበለጥ፡፡
    ጠላት ዲያብሎስ ወደሠጪው[ዋናው] እንዳንሮጥ በሠጪው ሥጦታ ላይ ብቻ ዘመናችንን እንድናባክን ያደርገናል፡፡ ስጦታው በራሱ ክፉ አይደለም፤ እዚያው ሥጦታው ላይ ከቀረን ግን እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ነው፥ የክርስትናችንን የሕይወት ጉዞ እንዴት ባለ መልኩ ማድረግ እንደሚገባን በአጽንዖት ደጋግሞ የሚናገረን፡፡



የማያቋርጥ የዘወትር የሕይወት ጉዟችን
    እግዚአብሔር ከእርሱና ከቃሉ ባልመነጨ ነገር ፈጽሞ፤ ከቶውንም አይከብርም፡፡ ክርስትናም ዋና ትኩረቱ እግረ ልቡናዎች ሁሉ ወደክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያመሩ ማድረግና ለእርሱም ክብርን እንዲሰጡ[እንዲያመጡ] ማድረግ ነው፡፡ ለዘወትር ወደክርስቶስ የማይገሰግሱ እግሮች የሚያዳልጡና የሚጥሉ አደገኛ ኃጢአተኞች፤ አንቀው የሚይዙ ከባድ የነውር ወጥመዶች ሳያገኟቸው አይቀርም፡፡
  የክርስትና ጉዞ በዋናነት በሩጫ፣ በወታደርና በአገልጋይ(ባርያ) ተመስሏል፡፡
    ፦  ቃሉ፥ “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ፡፡ ሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን፡፡ ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤” (1ቆሮ.9፥24-26) ይላል፡፡
     ቅዱስ ጳውሎስ ሞትንም፥ ስደትንም፥ መከራንም፥  ጭንቀትንም፥ ስደትንም፥ ራብንም፥ ራቁትነትንም፥ ፍርሃትንም፥ ሰይፍንም …(ሮሜ.8፥35) እንዳይፈራ ያደረገው፣ ለክርስቶስ ወንጌል ሕይወቱንም እንኳ ሳይሰስት እንዲሰጥ ፈቃደኛ ያደረገው ነገር ቢኖር፥ በሕይወቱ የነበረውና ዘወትር ችላ የማይለው[ሊለው የማይፈቅደው] አንድ ነገር ብቻ ስለነበረው ነው፡፡ እርሱም፥ “ለሞትም ሆነ ለሕይወት ምንም እንዳይጓጓና ደንታ እንዳይኖረው ያደረገው ዋና ዓላማው፥ “ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር”(ሐዋ.20፥24) እና “በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ እንዲከብር፤” (ፊልጵ.1፥20) በማለት ተናግሯል፡፡
     የዕብራውያን ጸሐፊም ይህን የቅዱስ ጳውሎስን ሃሳብ በማጽናት፥“ … እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና፤” (ዕብ.12፥1-2) ቅዱስ ጳውሎስም ሆነ የዕብራውያን ጸሐፊ፥ እኒህን ብርቱ ንግግሮች የተናገሩት፥ በብሉይ ኪዳን በመከራና በብዙ ተቃውሞ ያለፉትን በእምነታቸው ድል የነሱትን ቅዱሳንን በማንሳት፥ እኛም የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን በማየት እንደእነርሱ በእምነትና በታማኝነት መሮጥ እንደሚገባን ለማሳሰብ ነው፡፡
ሩጫና የክርስትና ሕይወት ጉዞ የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለ፤ ይኸውም፥
1.      ሩጫው ተካፋዮች ነን፦ በሩጫ ብዙ ተሳታፊ እንዳለ እንዲሁ፥ በክርስትና ሕይወትም ሁሉም ክርስቲያን አማኝ ተካፋይ ነው፤ የሩጫውም ሜዳ ሕይወት ነው፡፡ የሩጫውም ፍጻሜ በሥጋ ሞት የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ነገር ግን እስከሞት [እስከመጨረሻው ድረስ] በእሽቅድምድሙ ሥፍራ በታማኝነትና በእምነት ጽናት መሮጥ ይገባል፡፡
    በክርስቶስ ኢየሱስ ካመንበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ መም(የሩጫ መስመር) ገብተናል፤ የእርሱ መሆናችንና እርሱን ለመከተላችን ማረጋገጫው የክርስቶስ ሩጫ በመሮጥ ተካፋይነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ “ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር ለመተባበር ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር መተባበርና”(ሮሜ.6፥5) የሕይወትን ሩጫ ከእርሱ ጋር መሮጥ ግዴታችን ነው፡፡ ጀምረን ከተካፋይነት ራሳችንን ብናገልል የሚጠብቀን እጅግ አስከፊ ነገር ነው፤ ሰይጣንን ከሸኘን በኋላና ክርስቶስን ከተቀበልን ሩጫችንን ከክርስቶስ ጋር ባንሮጥና ፈቅደን በመመለስ ዳግም አሳቹን ለመቀበል ብናስብ፥ በግልጥ ቃል መጽሐፉ እንዲህ ተብሏል፤  “ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል” (ማቴ.12፥45)፤ “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል፡፡ አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና፤” (2ጴጥ.2፥20-21)፡፡
    እንኪያስ ታድያ፥ ከክርስቶስ ጋር ጨክነን በጽናትና በታማኝነት ልንሮጥ ይገባናል እንጂ ወደኋላ ማለጽ ፈጽሞ አይገባንም፡፡ በክርስቶስና በጸጋው ወንጌል ማመናችን መንገዱንና ሩጫውን የማወቅ ኃላፊትንም ጭኖብናል፤ ስለዚህ አላወቅሁም ማለት አይቻለንም፤ ከመሮጥና በመንገዱ ከመመላለስም ወደኋላ በመዞር በኃጢአት ብንጠላለፍ የኋለኛው ሕይወታችን እጅግ የከፋ ነው፡፡ ካመንን ያመንነውን በማወቅ ተግተን ልንጓዝበት ይገባናል፡፡ ብዙዎቻችን ክርስቲያን የሚለው ስሙን እንጂ፥ ክርስትና የሚፈልገውን የተመሠከረለት ወይም ክርስቶስን የሚመሰክር ሕይወት የለንም፡፡ ያመንን ሁሉ ግን የሩጫው ተካፋይ መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! የክርስትና ሕይወት ሩጫችንን ከክርስቶስ ጋር እንድንሮጥ እርዳን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል… 

1 comment: