Monday, 8 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሁለት)

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
    Please read in PDF

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
     ይህ አለም አቀፍ አዋጅ በዘረኛ ጠባይና ድርጊት በሚከተሉ ሰዎች በግልጽ ከመሻሩና ከመጣሱም በላይ፥ በአለም ላይ ዘረኛነት በግልጥ የታየበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በሥልጣኔ ከመጠቁት እስከ በሥልጣኔ ወደኋላ በቀሩት ሕዝቦች መካከል ከሚታይ ጥላቻ እስከትውልድ መደምሰስ የሚያደርስ የዘረኝነት ተክል በአለም ሁሉ ፊት  በቅሏል ፤ አብቧል ፤ ፍሬውም ሆምጣጤ ሆኖ በክፉ ምሳሌነቱ ታይቷል ፤ አሁንም ድረስ እየታየ ነው፡፡ ዘረኛነት ድንበር ሳይከለክለው በጸሐፍት፣ በባዕለ ሥልጣናት፣ በምሁራን [1] ፣ በጳጳሳት ፣ “ለምድር የከበዱ በሚባሉ ብዙ ሕዝቦች” ዘንድ ተገልጧል፡፡
       ሄሮዶተስ (Herodotus) [2] በሊብያ በረሃ ደቡብ ምዕራብ ጠረፍ ስለሚኖሩ ሕዝቦች ማንነት ሲናገር፥ “… ከአደገኛ አውሬዎችና ልዩና አስገራሚ ፍጥረታት ጋር የሚኖሩ ፣ ጭንቅላት የሌላቸው ፣ ዓይናቸው በደረታቸው ላይ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ናቸው” [3] በማለት ለአፍሪካና አፍሪካዊ ማንነት የሰጠው ተፈጥሮን ተቃራኒ ንግር ነበር፡፡ [4] ጥቁር በመሆን ብቻ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ፥ ሌሎች የእስያና የሌሎችም አህጉራት ሕዝቦች እጅግ ከባድ ውርደትና አጸያፊ ጥላቻን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ምናልባት ይህ እጅግ በራቀው ክፍለ ዘመን ፤ ሥልጣኔና አመለካከት ባልዳበረበት ዘመን ነው ብለን ብንሞግት እንኳ፥ አሻራው ሳይደበዝዝ በዚህ በዛሬው ጊዜ ፍንትው ብሎ ፤ በመካከላችንም ጭምር እናስተውለዋለን፡፡

    በተለይም ለዚህ እማኝ የሚሆነንን የቅርቡን ትዝታና የዘረኝነት ትንኰሳ በምሳሌነት ብናነሳ፥ ሁለቱ በዓለም ላይ የተከሰቱትን አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽሞ መዘንጋት አይቻለንም፡፡ ጀርመናውያን “ደማችን ንጹሕ መሆን አለበት ፤ በጀርመኖች ደም ሥር ውስጥ መመላለስ ያለበት የጀርመኖች ደም ብቻ ነው ፤ በመሆኑም ደማችን ከቆሸሸበት ነገር ሁሉ መጽዳት አለበት” [5] በማለት ፤ ቆሻሾች ወይም ንጹሐን አይደሉም ያሏቸውን ይሁዲዎች ሁሉ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ተነሳስተው ከስድስት ሚሊየን በላይ አይሁዶችን ገድለዋል፡፡ ይህ የዘረኛነት መንፈስ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ንጹህ፥ እንደተጻራሪ የሚያዩዋቸውን ደግሞ እንደፍጹም አስቀያሚ የሚያዩበት ዋናው ምክንያት ምንድር ነው? ብንል ከዘረኛነት መንፈስ ውጪ ምንም ልንል አንደፍርም፡፡
    ከዚሁ ጋር የምናነሳው ጥቁር በመሆኑ ብቻ በአሜሪካ ምድር ብዙ መከራና እንግልት የደረሰበት “ I have a dream …” በሚል “ንግግሩ” የሚታወቀው ታላቁ የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ፥ [6] አሜሪካ “ጥቁርና ነጭ እኩል ነው” የሚለውን ሕገ መንግሥቷን እንኳ ማክበር እንዳልቻለች በመውቀስ፥ በዋሽንግተን ዲሲ ከፕሬዘዳንት አብርሃም ሊንከን የመታሰቢያ ሃውልት ፊት ለፊት ባለው የንግግር ሥፍራ ላይ በመቆም በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጡ ሕዝቦች ፦
“ … የሕዝባችን መሪዎች ቀያሾቹ የነበሩት በሚደነቅ ቃላት የነጻነት አዋጁን እና ሕገ መንግስታችንን በተግባር ለመግለጥ የፈረሙት ፊርማ እያንዳንዱን አሜሪካዊን የአገሪቷ ወራሽ የሚያደርግ መስሎን ነበር፡፡
ይህ የቃል ኪዳን ስምምነት ማስታወሻ ኹሉም የአዳም ዘር አዎ! ጥቁሮችንም እንደነጮች የሚመለከት የማይገፈፍ ከአምላክ የተሰጠ የመኖር መብታችን ሕይወት ፣ ነጻነትንና ደስታን የሚደነግግ ተስፋን ሰጪ ስምምነት ሆኖ ሳለ ፤ ዛሬ ግን በአሜሪካ ግልጽኾኖ የሚታይና በተለይም ዜጎቿ ጥቁሮችን በተመለከተ ይህን የተላለፈልንን የተቀደሰ ዓላማ ግብ ከማድረስ ይልቅ አሜሪካ ለጥቁር ልጆች የሰጠችው “ምላሽ” መጥፎና የተበላሸ ስም (ኔግሮ) ነው፡፡ … የተስፋውን ቃል አልጠበቀችም …
… በኹሉም ግዛት እና ከተማ ይህ የነጻነት ደወል ይደወል፡፡ ይህም በሚኾንበት ጊዜ ኹላችንም የእግዚአብሔር ልጆች መኾን እንችላለን፡፡ …”
የሚል ልብን የሚነካ ንግግርን ተናገረ፡፡ ይህም የእርሱ ጠንካራ ንግግር ምዕራቡ አለም ጥለ ዘረኛ እንዲሆን ጽኑ መሠረት መጣሉን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
    በተመሳሳይ መልኩ በሩዋንዳ የአገር ተወላጅ በሆኑ በሁለቱ ጐሳዎች[7] መካከል የተፈጸመው ከባድ እልቂት መነሻው የዚሁ የዘረኛነት መንፈስ የመጨረሻ ውጤት ነው፡፡ እንደሰርብያና ሌሎችየተለያዩ አገራት መካከል ዘረኛነትን በተመለከተ ይንጸባረቁ የነበሩት አመለካከቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መጥተው ዛሬ የአለማችን አንዱና አሳሳቢ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ዘረኝነት ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡
    ይህንን በዓለም ላይ ያለውን ገጽታ በተመለከተ ፥ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ሲገልጠው፦
“ … ፈረንሳይና እንግዚዝ በአፍሪካ ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ የፈጸሙትን ፣ በኋላም አሜሪካን እናቀናለን በሚል ሰበብ የሀገሪቱን ቀይ ሕንዶችየጨፈጨፉበትን ፣ ከአፍሪካ ጥቁሮችን በማጋዝ ለባርነት የዳረጉበትን የዩናይትድ ስቴትስ ነጮችንና ፣ ጀርመኖች አይሁድን የጨፈጨፉበትን የናዚ የዘረኝነት ታሪክ ማውሳቱ ይበቃል፡፡
     በአሁኑ ጊዜም የዚሁ የዘረኝነት ጠንቅ በተለይ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ይፋ ይሁንታ አጊኝቶ በመቀጠል ላይ ሲሆን …
በማለት በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡ ምድራችን ለሰማያዊው እውነት ልቧን ከፍታ ልትቀበል ባልወደደች መጠን የገዛ ልጆቿን የሚበሉ ሰው በላ “የሰው አውሬዎችን” ማስተናገዷ ግድ ይሆንባታል፡፡ ዘረኝነት ሰው ሰውን የሚበላበትና ሰው መሆኑን የማይቀበልበት የአውሬነት መንገድ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ክርስቶስ ግን በደሙ ዋጅቶናልና በዚህ ነገር ዳርቻችን ፤ መልሳችንም ነው፡፡ ጌታ ሆይ ለሕዝብህ ማስተዋልን አብዛ፡፡ አሜን፡፡


   [1] በአገራችን ባሉ በፕሮፌሰርነትና በታሪክ ጸሐፍት መካከል ዛሬም ያለው ስውርና ግልጥ የሆነው የዘረኝነት መንፈስ ከመልካምነት ምሳሌው ይልቅ ክፉ ምሳሌነቱ የጐላ ነው፡፡ የአንዳንዶች የሃሳብ ፍትጊያ የጥንቱን የዘረኛነት መንፈስ አሁንም “ማስቀጠል” የሚፈልጉ ሲሆኑ ፤ ሌሎቹ ደግሞ የትላንቱን መንፈስ የተዋጉ እየመሰላቸው “ሳያውቁት” አሁንም “በቀልን በበቀል ብድራት” ለመመለስ የተሰናዱ ወይም እየተሰናዱ ያሉ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ፦ ታቦር ዋሚ ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች ፤ 2006 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ.8 ፤መስፍን ወልደ ማርያም(ፕሮ.) ፤ መክሸፍ እንደኢትዮጲያ ታሪክ ፤ 2005 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ ፤ ገጽ.79)
      ወደአገር ቤት ነባራዊ እውነታ ስንመጣ አንዳንዶች “ኢትዮጲያዊነትን በኦርቶዶክስ ክርስቲያንና በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪነት ብቻ መወሰናቸው” ለዛሬው ትውልድ ምን መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ሲታሰብ መልሱ ግራ ነው፡፡ (ዶር. አለሜ፤ “Whose History is Ethiopian History?”, 1975 ዓ.ም ፤ ያልታተመ፡፡) ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱን ምሁራን አተያያቸውን ላስተዋለ አንድ ቁም ነገር ከመጨበጣችንም ባሻገር “ምሁራኖቻችን” ወዴት እያመሩ ስለመሆኑ ጥቂት ማመላከቻ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ግን ታሪክን ተወቃቅሶ ፤ በሙያ ቋንቋ ተተቻችቶ ፤ ተገሳስጾ ፤ ተናንጾ ፤ በይቅርታ ምዕራፉን መዝጋት ፤ አዲስ የአብሮነትና የቅዱስ ጉርብትና ወዳድ ትውልድ መፍጠር ከእኛ የሚጠበቅ ትልቅ መንፈሳዊና ሰብዐዊ የቤት ሥራ ነው፡፡ አልያ ከጥንቱ ያንን የታሪክ ጸሐፊና ያንን ጨቋኝ ብሔርና ወገን እየረገሙ ወይም እየደገፉ መጻፍ የሚረባው አንዳች ፋይዳ የለም፡፡
     በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፥ “ … ልቡና ካልገዙ ሁለቱን ሕዝቦች ላላስፈላጊ ብጥብጥ እና ደም መፋሰስ መዳረጋቸው አይቀርም፡፡ … ስለዚህ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ መፍትሔው በነዚህ በሁለቱ ተጻራሪ ሃይሎችና አመለካከቶች መካከል አማካይ መንገድ መሻት ነው፡፡ … ባጠቃላይም በኢትዮጲያ ሕዝቦች መካከል ስምምነት ፣ መግባባት ፣ ፍቅር እኩልነት ፣ የርስበርስ መከባበር ፣ መቻቻል ፣ እና በሰላም አብሮ የመኖር ባሕል ያመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” የሚለውን “ቅንነት የበዛበትን ሃሳብ” ማንሳቱ ትልቅ ማስተዋል ይመስለናል፡፡ (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ፤ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ሐረግ ምንጭ ፤ ሐምሌ 2008 ፤ ቫሌሆ ፣ ካሊፎርኒያ ፤ አሳታሚ ኔባዳን ኃላ. የተ. የግል ማኅበር፡፡ ገጽ.13-14)
   [2] ከ480-425 ዓ.ዓ የኖረ
    [3] Rawlinson;s , Ancient Monarchies, vol 1
    [4] አቡነ ጐርጐርዮስ “የኢትዮጲያ ሕዝብ በጉልበት ኃያላን ፥ በውበት የተደነቁና በጠባይ ጭምቶች ፥ ትሕትናን የተመሉ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከግሪክ ፲፪ አማልክት አንዱ የመጀመርያውና ትልቁ እንደአባት የሚቆጠረው ዜውስ ኃያላኑን ኢትዮጲያውያኑን ለማየት ከእነርሱ ጋር ለመብላት ወደውቅያኖስ አከባቢ ወረደ“ ካሉትና ፤ ሔሮዶቶስ፥ ኢትዮጲያንና ኢትዮጲያውያንን ባነሳበት መጽሐፍ ኢትዮጲያን ፤ በውበት ፤ በቁመናና በኃይል ከሰዎች ሁሉ የሚበልጡ ናቸው፡፡ ብሏል” ከሚለው ሃሳብ ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው፡፡  (አባ(ጳጳስ) ጐርጐርዮስየኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ(ሁለተኛ እትም) ፤ 1986 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡) እኒህ የታሪክ ጸሐፍትና ፈላስፎች በቅርብ ዘመናት መካከል ሆነው እንዲህ ያለ ተቃራኒ ነገሮችን የጻፉበት ምክንያት እንዲህ ብሎ ማስቀመጥ ቢከብድም፥ ለአፍሪካዊ ማንነት የሰጡት አንዱ ጥላቻ ነው ብሎ መገመት ግን የሚያስችግር አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በአመክንዮ የሚያምን አንድ ፈላስፋ አይደለም አንድ ተራ ግለሰብ አንድን ነገር ያለማስረጃ ማቅረብ አይቻላቸውምና፡፡ እንዲያውም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፥ “በስትሮንግ የተዘጋጀውን የግሪክን መዝገበ ቃላት እንመልከት “ኢትዮጲያ” የግሪክ ቃል ከሆነ በተነገረን መሰረት “ፊቱ በጸሐይ የተቃጠለ” ከሚለው ፍቺው ጋር በግክ መዝገበ ቃላት ውስጥ መገኘት አለበት፡፡ በግሪክ በጸሐይ የተቃጠለ ማለት “ካውማትዲዞ” (kawmatdozo) ነው፡፡ ፊት ማለት ደግሞ “ፔሪካሉፕቶ” ነው፡፡ ስለዚህ በግሪክ “ፊቱ የተቃጠለ” ማለት “ካውማትዲዞ-ፔሪካሉፕቶ” (penikalupto) ነው፡፡ (strong’s Greek Lexiconp.239 and p.4020)በዚህ ሁኔታ “ኢትዮጲያ”የሚለው ቃል “ካውማትዲዞ-ፔሪካሉፕቶ” መሆን ነበረበት፡፡ … ግሪክ “ኢትዮጲያ” ብላ ሰየመችን ብሎ ማሰብ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ እዩ! ፍጹም ሐሰት ነው፡፡” (ገጽ.53-54) በግልጥ ድፍረት ይናገራሉ፡፡
     ምናልባት እነዱሩሲላ ዲንጅ ሒውስተን ያሉት ጸሐፍት ኩሻውያንን፦ “እናንተ የተናቃችሁና የተንቋሸሻችሁ ኩሽ ኢትዮጲያውያን! አባቶቻችሁ ጽፈው ያኖሩላችሁን መልእክት ራሳችሁን ቀና አድርጋችሁ አድምጡ፡፡ … ጥንታውያኑ ኩሻውያን የመጀመርያዎቹ አስደናቂና ሥልጡን የሰው ዘሮች ፣ ነገር ግን አሳዛኝ የታሪክ ቅሚያና በደል የተፈጸመባቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ እንደዛሬው ዘረኝነት ሥር ከመስደዱ በፊት ፣ ጥንታውያን ተጓዦችና ሊቃውንት ፣ የመጀመርያዎቹ የሥልጣኔና የከተሞች መሥራች መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ የዛሬዎቹ ዘር ማንዘሮቻቸው ኢምንት ሥፍራ የተሰጣቸው እነዚያ ጥንታዊ አስደናቂዎቹ ኩሽ አውሮፓን ትላልቅ ሥፍራ የሰጡዋቸውን የሕንድ አስደናቂ ጥበቦች ፣ የባቢሎንን ከተማና ብርቅዬ የንግድ ምርቶች እንዲሁም ፣ የትንሹ እስያን የቅድመ ታሪክ ሥልጣኔ የመሠረቱ ሥልጣኔ ፏፏቴ ናቸው፡፡ የአስደናቂው ኩሽ ዘር ተቋማት ፣ ሕጐቻቸው ፣ ባሕሎቻቸው እና ጽንሰ ሐሳቦቻቸው የዛሬዎቹ ባሕሎቻችን የቆሙባቸው መሠረቶች ናቸው፡፡ በጥንታዊቷ ግሪክና ሮም ይመለኩ የነበሩት ሳተርን ፣ ዳዩንሱስ ፣ ኦሲሪስ ፣ አፖሎ ፣ ዜዩስ እና ሄራክለስ የተሰኙት አማልክት ከጥንታዊ ኩሽ ሰማዕታት መሪዎች ስም ፣ ክብርና ዝና የተወሰዱ ናቸው፡፡” በማለት ለመምከር ያነሳሳቸው ይኸው ምክንያት ይሆን!?
    አንዳንዶች ግሪካውያን በመጀመርያ እኛን ለመጀመርያ ጊዜ የጠሩበት “ኢትዮጲስ” የሚለው ስም ትርጉሙ፥ “የተቃጠለ ወይም የጠቆረ ፊት” እንዲሁም በደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላትም ላይ “ኢትዮጲያ ማለት የመልክና  የሕብር ስም፡፡ ጥቍር ፣ ጠቋራ ፣ ከሰልማ ፣ ማለት ነው፡፡” የሚለውን ስያሜ ሊሰጡ የቻሉበትን ምክንያት፥ አንዳንዶች የዘረኛነት ሃሳብ እንዳለበት የሚያስረዱም የታሪክ ምሁራን አሉ፡፡ (ደስታ ተክለ ወልድ ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ 1962 ዓ.ም ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ገጽ.147-148)
    [5] ምኒልክ አስፋው፤ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ርእሰ ጉዳዮችና ተግዳሮቶች ፤ 1999 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ራእይ አሳታሚ፡፡
    [6] ማርቲን ሉተር ኪንግ እጅግ ተወዳጅ የጥቁሮች የነጻነት ታጋይና መሪ የነበረ ነው፡፡ በእርሱ ዘመን ጥቁሮች ከነጮች ጋር እኩል እንዲታዩ በተከታታይ በበርሚንግሃምና አላባማ ጐዳናዎች ላይ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች በአደገኛ የፖሊስ ውሾች ተነክሰዋል ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ በዱላ ተደብድበዋል ፤ ብዙዎችንም ንጽዕናው በጎደለ እስር ቤቶች እንዲታሰሩ አድርገዋል፡፡
    [7] እኒህ ጐሳዎች የሁቱና የቱትሲ ጐሳዎች ሲሆኑ፥ በተነሳው የዘረኛነት ግጭት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች የዕልቂቱ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡

2 comments: