Monday, 23 May 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (ክፍል አንድ)

please read in PDF

    

 ማኅበራዊ ድኅረ ገጾች ለብዙ ዓመታት የተለያዩትን ቤተሰቦች ፣ ዘመዶች ፣ ወገኖች የመገናኘት ምክንያት ሆነው፤ ለንግዱ ማኅበረሰብ ሥራዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያስተዋውቁና እንዲያሻሽጡ ፤ ለተጠቃሚውም ዝቅተኛ የገበያ ዋጋ ፣ በጥራትና በዋጋ የተሻለውን ለመምረጥ ፤ በማኅበረሰቡና በአገራት መካከል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ፤ የአንዱን ማኅበረሰብ መልካም እሴት ለሌላው ለማስተላለፍ ፣ ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ፣ ስለተለያዩ ነገሮች የተለጠፉ “አስፈላጊ” የሆኑ መረጃዎችን “ለመጠቀም” ፤  “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥” (ማቴ.24፥14) ተብሎ እንደተነገረ፥ ወንጌልን “ለዓለሙ ሁሉ” ለማሰራጨትና ለሌሎችንም ፋይዳዎች ያስገኙትን ያህል የዚያኑ ያህል (ምናልባትም በሚበልጥና በከፋ ሁኔታ) አሉታዊ ጎናቸውም እጅግ ሰፊና አሳሳቢ ነው፡፡

   የብዙዎችን አገራትና ባህሎቻቸው ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወረራን ከማስከተሉም ባሻገር ማንነትን እስከማስለቀቅ ወይም እስከማደብዘዝ ደርሷል፡፡ “ዓለም አንድ መንደር ሆናለች” በሚባለው በሉላዊነት ዓለም፥ አንዱና አስከፊው ነገር የኃጢአትና የዓለማዊነት ፈጣን ስርጭትና በአንድ ሥፍራ የተለመደንና የተሠራን ነውርና ኃጢአት ሽርፍራፊ በሆኑ ደቂቃዎች ፍጥነት በአንድ ጊዜ በእኒህ ማኅበራዊ ድህረ ገጾች “በሁሉ ዘንድ” መድረሱ ነው፡፡ በዚህም አንድን ኃጢአት “እንደኖህ ዘመን” በዓለሙ ሁሉ እንዲሠራ ማድረጉ ነገሩን ይበልጥ ያከፋዋል፡፡ አስተውሉ! የኖህ ዘመን ሰዎች ሙሉ ኃይላቸውን በተመሳሳይነት ለኃጢአት አውለውታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ፥ “በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ” (ሉቃ.17፥26-27) ብሎ የተናገረውን ትምህርታዊ ትንቢት ሳስብ በእኛ ዘመን መፈጸሙን የሚያሳይ ብዙ ነገር አለ፡፡ በኃጢአት አንድ እንደመሆንና እንደመስማማት እጅግ መራራ ነገር ይኖር ይሆንን?
      የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን፥ በምርኰ ወደባቢሎን በወረዱ ጊዜ ከአምልኮ ፍጹም ተቆራርጠው ነበር፡፡ ምክንያቱም የአምልኮ መፈጸሚያ ንዋያቱ ተማርከው ወደናቡከደነጾር ግምጃ ቤት ሲገቡ፥ የአምልኮ መፈጸሚያ መቅደሱ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ነበርና፡፡ በባቢሎን ምድር ከእግዚአብሔርና ከሃሳቡ ላለመራቅ አስበው በዘዚያ ምርኮ ምድር ምኵራብን ሠሩ፡፡ በምኵራቡም ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነቡ ፣ ይተረጉሙ ፣ ጸሎትንም ያደርጉ ነበር፡፡ ብዙ ቅሪቶች ለእግዚአብሔር የተረፉበት አንዱ መንገድ ይህ ነበር፡፡
      እንዲሁ በየዘመናቱ የሰዎችን ሃሳብ የሚገዙና የሚማርኩ ፤ የሚፈታተኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ከታሪክ አስተውለናል፡፡ ምርኮ ባህል ይደባልቃል ፤ የራስን እሴት ያስጠፋል ፤ ሃይማኖትን ይበርዛል ፤ የእስራኤል ልጆች በዚህ ላይፈተኑ ምኩራብን ሠሩ፡፡ ዛሬም እንዲህ ያስፈልገናል ፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ያለው ትውልድ እግዚአብሔርን በመከተል የሚያርፍ ሳይሆን እያዘነ ያለ ትውልድ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በሌላ ታሪክ፥ አዝኖ እግዚአብሔርን መከተል በአንድ ወቅት በእስራኤል ልጆች የሆነ ነው፡፡ “የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ” (1ሳሙ.7፥2)
    ከእግዚአብሔር ጋር አብረው ሆነው ግን አላረፉም ፤ አብሯቸው እንዳለ ይሰማቸዋል፥ ግን ሕልውናውን አይረዱም ፤ በአንዱ ልባቸው በኃጢአት ተጨማልቀው በባዕድ አምልኮ ተጠምደው ፤ እግዚአብሔርን በደባልነት ያመልኩ ነበርና፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ልከኛው ሳሙኤል ልባቸውንና ነፍሳቸውን በፊቱ እንደውኃ በማፍሰስ እንዲመለሱ በብርቱ ተግሳጽ ተናገራቸው፡፡ እስራኤልም ተመለሱ፡፡ ከንስሐ በፊት እየተከተሉት ቢያዝኑም፥ ከንስሐ በኋላ ግን ጠላቶቻቸውን ተዋግቶ ድልን አልብሶ አሳርፏቸዋል፡፡
    እግዚአብሔርን እየተከተልን እንድናዝን ካደረጉን ማራኪዎች አንዱ በማኅበራዊ ድኅረ ገጻት የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ናቸው፡፡ በማኅበራዊ መገናኛ መረብ በተለይም በዋናነት በፌስቡክ በአብዛኛው የሚተላለፉትና የሚሰራጩት ነገሮች ትውልዳችንን ከማበላሸት አልፎ መርዞታል ማለት ያስችለናል፡፡ ምሳሌ ብናነሳ፦
1.    የቅርባችንን እየሸሸን የሩቁን ፍለጋ ፤
    ለአብዛኛዎቻችን የማናውቃቸው ሰዎች የፊት ገጽ (facebook) “ባልንጀሮቻችን” ናቸው፡፡ አንዳንዶች በቤተሰብ መካከል ፣ ከወዳጅ ጋር ተቀምጠን ፣ ከባልና ከሚስት ጋር ሆነን ፣ ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ሆነን … ከፊታችን ያለውን ሰው ትኩረት ነስተን በፊት ገጻችን ላይ ካሉትና ከማናውቃቸው “ወዳጆች” ጋር ስንታገል እንውላለን፡፡ የሚያሳዝነው ብዙዎቻችን እንዲህ የምንሆነው ለአጭር ጊዜ ሲሆን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ባልንጀራ ፍለጋ ስንከራተት እንታያለን፡፡
    የምናውቀውንና ከጎናችን ያለውን ወዳጅ እየገፋን የማናውቀውንና ያላየነውን ወዳጅ መናፈቅ እንዴት ልብ የሚነካ ፤ የሚያሳዝን ተግባር ነው፡፡ ምናልባት ወዳጅነት ረክሶብን ፤ በግብዝነት ተጠምደን ፤ ሁሉ ነገራችን የለብ ለብ ሆኖብን ይሆን? ብዙ ሰዓታችንንስ እያባከነ ፤ መንፈሳዊ ሕይወታችንንም አቀጭጮብን ይሆን? ደግሞስ ላገኘናቸው ወዳጆቻችን የሚያንጽና የሚያስተምር ነገር እናስተላልፍበት ይሆን? እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ድርጊት አልተጠመድን ይሆን?
2.   የዝሙት ምስሎችና ቪዲዮዎችን ማየትና መልቀቅ
    በድኅረ ዘመናዊው ዓለም ዝሙት ኃጢአት እንዳልሆነ የሚሰብኩ ሰዎች አሉ ፤ ዕርቃን ምስሎችንም ጭምር፡፡ ለዚህም ነው እኒህ አካላት በአንድ ተደራጅተው ዓለምን በርኩሰታቸው ለመበከል ቀን ከሌሊት ሲተጉ የምናየው፡፡ እኒህ አካላት በዋናነት ራሳቸውን የሚገልጡበት መድረክ እኒህ ማኅበራዊ የመረጃ መረቦችን ነው፡፡ በእኒህ መረቦች ሰፊውን ሽፋን የያዙትም እነርሱ ናቸው፡፡
    በእኒህ ማኅበራዊ ድኅረ ገጻት ከሚለቀቁት ምስለ ድምጽና የዝሙት ስዕላት በማየትም ሆነ ለሌሎች በማስተላለፍ ምድርን በርኩሰት ከሚመሉት መካከል እኛ አለንበት ወይስ የለንበትም? በዚህ ነገር ምን ያህልስ ጥንቁቅ ነን? ቆመን የምናሰላስልስ አንኖር ይሆን? በምንወደው ወዳጃችን ሲላክልንስ ለመቃወም ምን ያህን ዝግጁ ነን?
   አስተውሉ! ዝሙትን በትግል አናሸንፈውም ፤ በመሸሽና ከአከባቢው ፍጹም በመራቅ እንጂ (1ቆሮ.6፥18)፡፡ ያንን የእግዚአብሔር ሰው ዮሴፍን አያችሁት? ቀሚሱን ጥሎ ከአከባቢው ሸሸ እንጂ ቆሞ አልታገለም፡፡ በዝሙት ዓለም ቆሞ መታገል ፤ አይቶ መፋለም ጀግንነት አይደለም ፤ ሸሽቶ መራቅ ግን አስተዋይነት ነው፡፡ ወደራሳችን ስንመለስ፥ በዚህ ጉዳይ የማንጠብቃቸው ሰዎች ጭምር ተመርዘው ልናገኛቸው እንችላለን፡፡ በሞባይላቸው ሸሽገው ፣ በላፕቶፕና በኮንፒውተሮቻቸው ቀብረው ፣ በፍሌሻቸው ሰውረው … ከሰው ተደብቀው ዕርቃን ምስልና የዝሙት ፊልሞችን የሚያዩ … የአደባባይ ጨዋ የእልፍኝ ዓለም አቀፍ “ዱርዬዎችን” ቤት ይቁጠራቸው፡፡
   አዎን! እጅግ ብዙዎች ለዚህ ነገር ባርያዎችና ሱሰኞች ናቸው፡፡ ቃሉም፦ “ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባርያ ነውና” (2ጴጥ.2፥19) ይላልና፡፡ ካላዩ የሚበሳጩ ፣ የሚናደዱ ፣ የሚደበቱ ፣ የሚፈዙ … ሲያዩ ደግሞ የሚነቃቁ ፣ የሚበረታቱ … የሚመስላቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ አዎ! ትውልዳችንን የመረዘው ነገር ብዙ ነው!!! ሰንቶች ነን በጌታ ፊት ሕሊናችንን ንጹህ ለማድረግ ስለአምልኮአችን የምንጠነቀቅ?
ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል…
 

3 comments:

  1. አንተ ሰው ጌታ በእውነት ይባርክህ

    ReplyDelete
  2. ጥሩ እይታ ነው እ/ር ይበልጥ ማስተዋልን ያድልህ

    ReplyDelete
  3. በትክክል የቀረበ እውነተኛ ፅሁፍ

    ReplyDelete