Saturday 27 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሦስት)

በእኛ መካከልስ ምን ይመስል ነበር?
   ዘረኛነትን በተመለከተ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብንነሳ፥ ኢትዮጲያ ከሰማንያ አራት በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባትና በተለያየ ብዙ ቋንቋዎችም የሚነጋገሩ ሕዝቦች ያሉባት አገር ናት፡፡ አንዱ አንዱን ለመብለጥ ምክንያት የሚመስሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሰዎች ከአንድነት ይልቅ በየራሳቸው ነገር ላይ ትኩረት ሲያድርጉ ሳያውቁት ሌላውን በመጻረር የሚቆሙበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ ሰዎችን ወደሌላ የክህደት መንገድ ለመምራት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ በዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ሆነው የቀሩ ሰዎች ያሉትን ያህል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠግተው ለራሳቸው ምስክርነት እየፈለጉ በዘረኛነት ክፉ ኃጢአት የተያዙ ብዙ ናቸው፡፡
    መጽሐፍ ቅዱስን ተገን ተደርጐ የሚሠራ ኃጢአት እጅግ አስከፊ ኃጢአት ነው፤ በእኛ መካከል ያለው የዘረኛነት መንፈስ እንዲህ ያለ ነው ብንል ማጋነን አለበት አያስብልም፡፡ አንድ ሃይማኖት የተወሰኑ ወይም የአንድ ብሔር እስኪመስል ወይም እስኪባል ድረስ በመካከላችን የሚታየው ነገር አስነዋሪ ነው፡፡ ይህንን በአንድ ጽሑፍ፦
“ … አሁን አሁን ነገራችን እንደዖዝያን ለምጽ ሊሸፈንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ራሱ ችግሩም “አለሁ፣ አለሁ” ብሏል፡፡  የለህም ብንለውም ራሱን በራሱ ያስመሰክራል፡፡ ሙስናው ፣ የዘመድ አሠራሩ …ወዘተ አግጥተው ወጥተዋል፡፡” [1]

    አንድ ነገር እስከአሠራር መሆን የሚደርሰው በልማድ በሚገባ ሲዳብር ነው፡፡ ልማድ ሲደጋጋም ትምህርት ይቀረጽለታልና፡፡ በቀደሙት ረዥም ዘመናት አንዱን ብሔር በመጥላትና አንዱን የበላይና አለቃ አድርገው ይሾሙት የነበሩት ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክህነት ጸሐፊዎች ጭምር ናቸው፡፡ መልአከ ብርሐን ብርሃኑ አሥራት የአሜሪካው የዘረኝነት ጦስ ፍጻሜው ወዴት እናዳመራና ምን እንዳስከተለ ሲነግሩን፦
“ብዙዎች ጥቁሮች ነጮች ይፈጽሙት በነበረው የዘረኝነት አስከፊ አድራጎት የተነሳ በፕሮቴስታንት ክርስትና እምነት ላይ ጥላቻ ስላደረባቸው ወደእስልምና ተቀይረዋል፤ ግማሾቹም “ራስን ማወቅ” በሚል ዓላማ ተነሳስተው የዘር ሃረጋቸውን ሥር እስከመፈለግ ደርሰዋል፡፡ የአፍሪካ አህጉራችንና የአፍሪካ ባህልችንን እንመሥርት፣ ወደኢትዮጲያ አገራችንን እንመለስ የሚል ሕልም እንዲያልሙ አድርጓቸዋል፡፡ … ይህ ትግል “ዘ ኔሽን ኦፍ እስላም እና ራስ ተፈሪያን” ተብለው የሚጠሩ አዲስ የእምነት ዘርፎች እንዲመሠረቱ መንገድ ከፍቷል፡፡” [2]
ብለው ቢገልጡም፥ በእኛ መካከል የነበረውንም በሚገባ ላጠናው ብዙዎች ለመጎዳታቸውና ከእምነታቸው ፈቀቅ ለማለታቸው አሌ የማይባሉ ሐቆች መኖራቸውን ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡
       ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት አንዱና ትልቁ የነበረበት ነቀፌታው፥ “ራሱን እንደቅዱስ ትውልድና ነገድ ቆጥሮ” ሌላውን ብሔርና ነገድ እንደሁለተኛና ከእነርሱ እንዳልተካከለ አድርገው መቁጠራቸው ነበር፡፡ ሌላውን ዘር እንደታናሽ መቁጠራቸው እንደድርጊት ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን በጽሑፎቻቸው ጭምር ማስቀመጣቸውን ፦
   “... ባላገሩን እንደእንጨት ጠርበው፣ እንደጭቃ አድቦልቡለው የሠሩት ያስመስሉት ነበር እንጂ እንደእነርሱ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ አይመስላቸውም ነበር፡፡” [3]
ተብሎ ተነግሯል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በአገራችን ላሉ ለአንዳንድ ብሔረሰቦች የተሰጡ አጸያፊ ስያሜዎችም ነበሩ፡፡ ያላባራው የዘረኝነት ጉዳችን “ጥቃቅኑን” ግን የተከበረ ሥራ ይሠሩ ለነበሩትም አፈር ገፊ ፣ መጫኛ ነካሽ ፣ ፋቂ … የሚሉ ጸያፍ ስድቦችም ይሰይም ነበር፡፡
አሁንስ በእኛ መካከል ምን ይመስላል?
     የሚያሳዝነው የዚያ አጸያፊ ትውልድ ቅሪቶች ዛሬም በመካከላችን አሉ፡፡ [4]ዘራቸውን የሚያሽሞነምኑ፣ የሚያንቆለጳጵሱ፣ የሚያመሰጋግኑ … የሌላውን ዘርና ነገድ ለመናቅና ዝቅ ለማድረግ የሚጀምሩ እጅግ ብዙ አሉ፡፡ በተለይም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ተሰግስገው፤ በአብዛኛዎቹ የግል ባንኮችና ሆስፒታሎች ውስጥ ተደራጅተው፤ ጥቂት በማይባሉ የእግር ኳስ መድረኮችና የኮሌጅና የዩንቨርሲቲ እንዲሁም በልዩ ልዩ የትምህርት ተቋማት፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ገደቡን አልፎ ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡
     ዘረኛነት ድንበር የለሽ ኃጢአት እንደመሆኑ መጠን በየትኛውም ብሔርና ነገድ፤ የመንግሥታት ሥርወ መንግሥት ውስጥ ሲንጸባረቅ ኖሯል፤ አሁንም አለ፡፡ የሰለጠነውን አለም እንኳ በጥቁርና በነጭ ዛሬም ድረስ የከፋፈለው ክፉ መርገም ቢኖር ዘረኛነት ነው፡፡ ጥቂት ያይደሉ ጳጳሳት፣ ዲያቆናትንና ቀሳውስትን፣ ቆሞሳትንም ጭምር በአገር ተወላጅነት ደብራቱንና አድባራቱን ሲያጥለቀልቁት እናያለን፤ ባለሥልጣናቱም በተመሳሳይ መልኩ ሲሾሙና ሲሸለሙ ምክትላቸውንና ዋና ዋና ቦታቸውን የሚያሲዙት “የገዛ ወገናቸውን” ነው፡፡ ይህ ቤተ ክህነቱም፤ ቤተ መንግሥቱም ያመሳሰላቸውና የተያዙበት፤ የተጠመዱበትም ክፉና አስነዋሪ ነውር ነው! 
   አገራችንን ጭምር በአህጉረ አፍሪካ ትልቁን የታሪክ ሽፋን የሚይዘው ጦርነት ሲሆን፥ የጦርነቱ ዋና መንስኤ ሆኖ ሰፊውን ምክንያተ ቦታ የሚይዘው ደግሞ ዘረኛነት ነው፡፡ በእኛም መካከል ትልልቅ የጥላቻና የልዩነት ሃሳቦች ማጠንጠኛቸው ዘረኛነት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ከተዘፈቅንበት የድህነት አረንቋ ያለመውጣታችን ትልቁ መነሾ ምክንያት የዘረኛነትን መንፈስ ከመካከላችን አስወግደን ለመቀባበልና ለመከባበር፤ ለመተናነጽና ለመመካከር አለመፍቀዳችን ብንል ምንም ግነት የለበትም፡፡ አለ የሚል ካለ ሙግቱን መስማት እወዳለሁ፡፡
     የቱ ብሔር ነው የቱን የሚያከብር? የትኛውስ ነው ለማንኛው ብሔር በእሽታ መንፈስ በፍቅር የሚታዘዘው?! በእውነት እድልና ቀን ቢገጣጠምልን ሥልጣንና በትር ብናገኝ ከማረድ፤ ከማጋዝና ከማፈን የማንመለስ ስንቶች እንሆን?! በእርግጥም ዛሬ የሚታየው ባሕርያችን ይኸንኑ ይመሰክርብናል፡፡ ለዚህ ነው ብሔራዊ ንስሐ ያሻናል፤ ሁላችንም በድለናልና [ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም] ወደፈጠረንና ወደበደልነው አምላክ ፊታችንን ዘወር እናድርግ የምንለው፡፡
    ጌታ አባታችን አብ ሆይ! ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...







    [1] ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን) ፤ ስማችሁ የለምና ሌሎችም ፤ 2006 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚ አግዮስ ኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላ.የተ. የግል ማኅበር፡፡ ገጽ.15
  [2] መልአከ ብርሃን ብርሃኑ ብሥራት ፤ ኑሮና ክርስትና በአሜሪካ ፤ 2001 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ኤች ዋይ የኅትመት ሥራ ድርጅት ኃላ.የተወ. የግል ማኅበር፡፡ ገጽ.17
   [3] አፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስ ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጲያ ፤ 1901 ዓ.ም ፤ ሮም፡፡ ገጽ.4
   [4] በዚህ ረገድ አንድ ሰው ማንሳት እወዳለሁ፥ ተስፋዬ ገብረ አብን፥ በአጻጻፍ ችሎታው የሚደነቅ ሰው ቢሆንም የዘረኛነትን ልቦለድና እውነታን አደባልቆ በማቅረብ ተወዳዳሪ ያለው አይመስልም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ በአንድ ጽሁፉ “አምኖ የጻፈበትን ነገር” በሌላ ጽሁፉ በተቃርኖ ሲቆም “ምነው አያስተውልምን?፣ የሚሮጠው የቀደመውን እየጣለ ወደፊት ብቻ ነውን?” ያስብላል፡፡ ምሳሌ፦ በየደራሲው ማስታወሻ መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፥ “ … እኛ የአፍሪቃ ቀንድ ዜጎች የምንመኘው ዘመን ባለቤት እንሆን ዘንድ መሥራቴ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ አንድ ነገር ከማድረግ ባሻገር ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ እንደስነጽሁፍ ሰው ደግሞ ፋና ወጊ የመሆን ግዴታ አለብኝ፡፡” …  “አንድ ሰው እና አንድ ጠመንጃ በፍጹም አይናቁም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡   … ስለዚህ አንድ ችግር መፍጠር የማይችል ሕዝብም ሆነ ግለሰብ የለም፡፡ እኔ በግሌ ግለሰብ ነኝ፡፡ በአንድ ወቅት ወያኔዎች፣ “ምን ያመጣል?” ብለው ተመጻድቀው ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ያቺን ቃል አይደግሟትም፡፡ በተመሳሳይ በርካታ የተናቁ ሆኖም አንድ ነገር ማድረግ የሚችሉ ግለሰቦች በእንያንዳንዱ ግዙፍ ቡድን ጉያ ውስጥ ምን ጊዜም አሉ፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው … ” (ተስፋዬ ገብረ አብ፤ የደራሲው ማስታወሻ ፤ 2002 ዓ.ም ፤ ዋሽንግተን ዲሲ ፤ ነጻነት አሳታሚ፡፡ ገጽ.14 እና345-346) እንዲህ ብሎ የተናገረው ተስፋዬ ገብረ አብ ሳያፍር ደግሞ፥ “በኦሮሞ አጀንዳ ላይ የማነሳቸው ጉዳዮች የስጋት ምንጭ ሊሆኑ የሚገባ አይመስለኝም፡፡ አንድ ተራ ደራሲ ሰፊ ቁጥር ያለውን የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የማጋጨትም ሆነ የማፋቀር አቅምና ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡” (ተስፋዬ ገብረ አብ ፤ የጀሚላ እናት ፤ 2014 ዓ.ም ፤ ምጽዋ - አሥመራ ፤ አሳታሚው ያልተጠቀሰ ፤ ገጽ.2)
     የራሱን የበላይነትና ወያኔ በሚላቸው “ጠላቶቹ” ላይ ያለውን ጡንቻውንና “ሁሉን ቻይነቱን” ለመግለጥ ሲፈልግ “አንድ ሆኖ ብቻውን ብዙ ነው”፡፡ በራሱ ቋንቋ ስጠቀም ብቻውን ሆኖ “የሚረጨው የዘረኛነት መርዝ” ብዙዎችን ሲነድፍና ሌሎችን ሲጐዳ ግን አንድ ሰው ብቻውን “እርባና ቢስ” ነው፡፡ ለጸሐፊ፥ ብዕርና ምላሱ ሁለት ከሆነ አደገኛና መርዛማነቱ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ተስፋዬና መሰሎቹ በዚህ ነገር የተካኑ ናቸው፡፡ አንድ ሰው በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ የጋሽ ገብረ አብ ልጅ ባይለውም እውነታነቱ አያጠያይቅም፤ የዘሩት የዘረኛነት ዘር አፍርቶ ሲጐመራና ምሬቱን ሲያዩት ግን “አንድ ሰው ተራ ነው” ማለት በትውልድ ሕሊና እንደመቀለድ ነው፡፡ ተስፋዬ እንደመራው መሄዱ እንጂ የጻፈውን ቢያስተውል፥ ደራሲ በዓሉ ግርማ የጻፈው ምርጥ ግጥም እርሱንም እንደሚመለከት ባስተዋለ (ከእብድ ገላጋይ አንዱ እርሱ ራሱ ተስፋዬም ነውና)፥
“የአንድ እናት ልጆች፥
በአስተሳሰብ ተጣልተው፥
በአመለካከት ተለያይተው፥
የእብድ ገላጋይ በዝቶ፡፡”
     የዘረኝነትን በተሐ ጠጅ እያጠጡ፥ በዘረኝነት ሰክሮ ጨርቁን የማይጥል ትውልድ አይመጣም ብሎ ማሰብ እነተስፋዬ ገብረ አብ ያላስተዋሉት ገሃድ ሐቅ ነው፡፡ እውነታው ይኸው ነው፤ “ለአንድ ወገን መጨቆንና መጠቃት” ሚዛናዊ በሆነ ቋንቋና አስተሳሰብ ከእውነተኛ ማስረጃ አንጻር መናገርና መጻፍ ካልቻልን፥ ከእኛ ግራ መጋባት ባሻገር ትውልድን ግራ ማጋባታችንና ማፋጀታችን ፤ ቂምና ቁርሾን ማክረማችን የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment