Monday 12 December 2016

ጸሎትና ጾም ለኢትዮጲያ(የመጨረሻ ክፍል)


2.     “እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ መቅበዝበዝን ወድደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፥ በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፡፡ እግዚአብሔርም፦ ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው፡፡ በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ፤” (ኤር.14፥10-12)
     በኤርምያስ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች ወደእግዚአብሔር በፍጹም ንስሐ ከመመለስ ይልቅ በክፋታቸው በመጨከናቸው ምክንት ሊመጣ ያለውን ቅጣት ነቢዩ ይናገራል፡፡ በልባቸው ወደጣዖት አምልኮ አዘንብለውና በእግራቸው ወደዚ እየቸኮሉ ነገር ግን ጾምን ቢጾሙ፣ መሥዋዕትን ቢያቀርቡ እግዚአብሔር በዚህ ፈጽሞ አይረካም፡፡ ኤርምያስ እንዲህ ላለ ሕዝብ ፈጽሞ እንዳይማልድ በተደጋጋሚ ተክልክሏል፤ በክፋቱ የጸና ሕዝብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይተዋል እንጂ ምንም አይነት እርዳታ አይደረግለትም፡፡

     በተመሳሳይ መልኩ፥ በሆሴዕ ዘመን የነበረው ሕዝብም በተመሳሳይ በደል ውስጥ ነበር፤ “መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፤ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤” (ሆሴ.8፥13)
   ንስሐ፣ ጾምና ጸሎት በሚመለስና ከልብ በሆነ ማንነት እንጂ፥ በግብዝነት ባሕርይ ከክፋት ሳይላቀቁ ለታይታ የሚደረግ ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከልብና ከእውነት ያልሆነ ነገር ፈጽሞ አይማርከውም፤ ሜዳዊና ውጫዊ ንስሐ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርጉትን ሕዝቦች ቅዱስ ቃሉ፥ “በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን አድራጊዎች” በማለት ይወቅሳቸዋል፤ (ኢሳ.58፥3)፡፡ በእርግጥም ንስሐ ሳይገቡና የበደሉትን በይቅርታ ሳይምሩ(ማቴ.5፥23-24) መሥዋዕትን[ስብከትን፣ ቃሉን መስማትን፣ ዝማሬን፣ ምጽዋትን፣ እልልታን፣ ሽብሸባን፣ መጸለይ፣ መቀደስና ማስቀደስ … ] በራስ እጅ የዘጉትን በር እንደማንኳኳት ከንቱ ድካም ነው፡፡
   እስኪ ወደአገራችን እውነታ እንመለስ፥ በዓለም ላይ እንደኛ አገር “ክርስቲያን” ብዙ ቀናትን “የሚጾም” ያለ አይመስለኝም፤ ይህን ሁሉ ስናደርግ ግን ራብና ቸነፈሩ ዛሬም ከምድሪቱ አላባራም! ለምን? በእውኑ የትላንቱ እግዚአብሔር ያው አይደለምን? ጆሮን የፈጠረ አይሰማምን? ዓይንን የሠራስ አያይምን? እርሱ መለወጥ የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ነው፤  ይሰማል፤ ያያልም፡፡ እኛስ ግን እንደፈቃዱ የምንጾም ነንን? ከእህል እንጂ ከኃጢአት እንቆጠባለን? ከዘረኛነት ጽዱ ነን? ሁሉ በክርስቶስ ለእኛ እኩልና አንድ ነውን?
    ኪዳኑን የሚሽሩ ሁሉ ቀድሞ በሕጉ እንደተነገረው(ዘሌ.26፥25) ከእርግማኑ ከቶውንም አያመልጡም፤ ዛሬም በኃጢአታችን ብንጸና ዘላለማዊው ቅጣት ብቻ ያይደለ ምድራዊው ቅጣትም አይቀርልንም፡፡ ታድያ እጃችንን ስለምሕረቱ መዘርጋት አይገባንምን?
3.  “በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥራት፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፥ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ፡፡ የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ወኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፤ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በልቶአል፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ … በግብጽ እንደ ነበረው ቸነፈርን ሰደድሁባችሁ፤ … ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ፥ እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ፤” (አሞ.4፥8-12)፡፡
     እስራኤል ዝናብን በመከልከል፣ ጥማትን በመስደድ፣ በዋግና በአረማሞ በመምታት፣ አትክልቶቻቸውን ሁሉ ተምች እንዲበላው በማድረግ፣ ቸነፈርን በመስደድ፣ “ጥርስን ማጥራት” እንዲል የሚላስ የሚቀመስን በመከልከል … እንዲመለሱ ቢያደርግም እነርሱ ግን ሊመለሱ አልወደዱም፡፡ እግዚአብሔር ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ መቅሰፍትና ቸነፈር ይጠቀማል፤ (ኢዮ.33፥19 ፤ ምሳ.3፥11)፡፡ እስራኤል ግን እጅግ ከሚያስከፋው የኃጢአት ሕይወታቸውን ወጥተው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን አልወደዱም፡፡ በዚህ ሁሉ መቅሰፍትና ቁጣ ሊመለሱ ስላልወደዱ የተቆረጠው ፍርድ እንደማይቀር ነቢዩ፥ “እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤” (ቁ.12) ብሎ እግዚአብሔር የተናገረውን ተናገራቸው፡፡
    ሊመጣ ያለው ፍርድ በአሦራውያን እጅ መውደቅ ነው፤ አሦራውያን ደግሞ እስራኤልን ባድማ ያደርጓታል፤ ይህ ደግሞ እጅግ ሊሸከሙት የማይቻላቸው አስፈሪ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ውድቀት የዳረጋቸውን ኃጢአቶች ነቢዩ አሞጽ ይዘረዝራቸዋል፤
1.      በቅይጥ አምልኮ መያዝ፦ ነቢዩ በግልጥ፥ “የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ”(4፥4) በቤቴል የነበረው ቅይጥ አምልኮ ለእግዚአብሔር ይቀርብ የነበረውን ቅዱስ አምልኮ በመበረዝ ከነዓናውያን ለጣዖቶቻቸው ከሚያቀርቡት ጋር ተቀይጦ ነበር፤ ከዚህም የተነሳ የኪዳኑን ቃላት ተዘንግተዋል፤ በኪዳኑ ሕግ ውስጥ እንዲደርጉት የታዘዙትን ባለማድረግ ተጠምደው ነበር፡፡
    ጣዖት አምልኮ ከእግዚአብሔር ፍጹም ይለያል፤ የኪዳኑንም ሕጎች ይበርዛል፤ አዳዲስ ከንቱ አምልኮዎችንና አስተሳሰቦችን እንድንለማመድ ያደርጋል፤ በእስራኤልም የሆነው እንዲህ ነው፤ ጣዖት በማምለካቸው ምክንያት፥
1.1.    ፍርድን ወደ እሬት ለወጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ ጣሉ፥(5፥7)
1.2.  ድሀውንም ደበደቡ፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወሰዱ፣ ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ለራሳቸው ሠሩ፥ ስለዚህም እንዲህ ተባሉ፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም።(5፥11)
1.3.  ጉቦንም ተቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ አጣመሙ፥ በደላቸውም እጅግ በዛ፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ጸና፤ (5፥12)
    ያላቸውና የሌላቸው ሰዎች በሚኖሩባት በዚህች ምድር፥ ብዙውን ጊዜ ምድራዊ ሃብትን የሚያከማቹ ሰዎች ከድሆች በመበዝበዝ ለራሳቸውን ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ (ኢሳ.3፥14 ፤ ኤር.2፥34 ፤ ያዕ.2፥6)፡፡ በእውኑ በአገራችንስ ከዚህ የተሻለ ምን ነገር አለ? ነጋዴዎቹ ሚዛን አይሰልቡም? ከንጹሑ ነገር ጋር ባእድን ነገር ቀላለቅለው ለሽያጭ አያቀርቡም? ጉበኝነትና ሙስና በቤተ ክህነትና በመንግሥት ቤት ምን ይመስላል? ድኃው ያለጉቦ ምን የሚከናወንለት ነገር አለ? የችጋረኛው ፍርድ አይጣመምም? ንጹሑ አይበደልም? …
    እግዚአብሔር ግን የድኻውና የችግረኛው ጠበቃ ነው፤ መጠጊያ ረዳታቸው፤ ታዳጊ መጋቢያቸውም ነው፤ (1ሳሙ.2፥8 ፤ መዝ.14፥6 ፤ 40፥17 ፤ 68፥10 ፤ 132፥15)፡፡ እውነተኛ አማኝ ሁል ጊዜ ከተጠቃው ማኅበረሰብና ወገን ጐን መቆም ይገባዋል፡፡ በማናቸውም ሰዓት ድኾችን ሊረዱና መጠቃታቸውን ሊያውቁላቸው ይገባቸዋል፤ እግዚአብሔርም ድኾች በመካከላቸው እንዳይኖሩ ለኪዳኑ ልጆች አስጠንቅቆም ነበር፤ (ዘጸ.22፥25 ፤ ዘዳግ.15፥7 ፤ ዘሌ.25፥35)፡፡ ጌታ ኢየሱስም ስለተጠቁትና ድኾች መላኩን ተናገረ፤ የተጨቆኑትንና የተጠቁትንም ሳምራውያንን፣ ለምጻሞችን፣ መበለቶችን አዳነ፣ ረዳም፤ (ማቴ.8፥2 ፤ ሉቃ.4፥17 ፤ 7፥11 ፤ 20፥45)፡፡ ደቀ መዛሙርትም ድኾችን በመርዳት የታወቁ ነበሩ፤ (ሐዋ.11፥28 ፤ ሮሜ.15፥26 ፤ 2ቆሮ.8፥1-2)፡፡
     ዛሬ ግን፥ ይህ የደመቀው የመጽሐፉ እውነት ፍጹም ተገፍቷል፤ አብያተ ክርስቲያናት የደለበና የካበተ የባንክ ሂሳብን አስቀምጠው በደጆቻቸውና በበሮቻቸው ግን እልፍ ድኾች የሚላስና የሚቀመስ ነገርን አጥተው ተቀምጠዋል፤ በእውኑ ስለእነዚህ ድኾች እኛ አይገደንምን? አብያተ ክርስቲያናትስ ድግ አይላቸውምን? ምድሪቱ ብዙ ጊዜ በራብና በቸነፈር የመመታቷ ምክንያት ይህ ሆኖ ቢሆንስ ከትውልዱ ማን ነው ያስተዋለ? የፍትሕ አካላት ስለሚቀበሉት ጉቦና ስለሚያጣምሙት ፍርድ ማን ይሆን ተቆርቋሪው? እኛስ ጎቦን በመስጠት ከማሳት እጃችን መች ይሆን የሚሰበሰበው? …
     አዎን እየደጋገመ የሚያጠለሸንና የሚያጎብጠን ራብና ቸነፈር ምክንያቱ የተቀረጸው “የልማት ፖሊሲ” መሬት ስላልደረሰ፣ ገዢው መንግሥት በአግባቡ ስላልሠራ፣  … ብቻ አይደለም፤ በነውራችንና ንስሐ ባልገባንበት ኃጢአታችን መሆኑን በማመን ንስሐ ልንገባና እርቅ ልንመሠርት፤ ምሕረትን ልንለማመን ይገባናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምንም የተትረፈረፈ ምርት ቢበዛ፣ የተቀማጠለ ነገር ቢኖረን … “የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ፤” (መዝ.106፥15) እንደተባለ ምድራዊው ነገር “ተሟልቶ” በነፍሳችን ክሳቱን እንዳናገኘው፤ ለምድራዊውም ለሰማያዊውም መንገዳችን ፈውስ ንስሐ እንግባ፤ እንመለስም፤ ስለልጁና ስለስሙ ብሎ እንዲታደገንም በልቅሶና በዋይታ እንመለስ፡፡
ኢትዮጲያ ሆይ! እጆችሽን ወደአምላክሽ ዘርጊ፤ በስሙም ይቅር እንዲልሽ ስሙን ጥሪ!
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡


1 comment:

  1. Meskrem K Dallas Tx14 December 2016 at 03:27

    Amen!! Wendme Geta Leberket Yadergeh Dengel tetebkhe 30,60,100 yemtafera hune. Geta wde Ewent yemelsen.

    ReplyDelete