ሰውን በማረድ ፣ በማዋረድ ፣ በመስደብ ፣ በማንጓጠጥ ፣ በማሰቃየት
፣ በማረድ … የሚረኩና የሚደሰቱ ከሥነ ምግባር የወረዱ “ሃይማኖት ለበስ” የሰይጣን ደቀ መዛሙርት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን
በግ ሳለች በተኩላ መካከል የተላከች ታማኝ መልእክተኛ ናትና እኒህን ልትታገሳቸው ፤ ወንጌልን ተግታ ልትመሰክርላቸው ይገባታል፡፡
አሠማሪው ጌታ በክፋትና በነውር በሚጨክነው ተኩላና የተኩላ ዓለም ላይ ቤተ ክርስቲያን ለእውነትና ለዘለዓለም ሕይወት እንድትጨክን
የኃይልን መንፈስ ሰጥቷታል (ኢሳ.11፥3)
“እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ
እንዲደረግ እናውቃለን” እንደሚለው፥ እግዚአብሔር የታመኑና የጽድቅ ምስከር የሆኑ ልጆቹን ከሞት በማዳን ፤ ከአንበሳ መንጋጋ በማላቀቅ
፤ ከሰይፍ ስለት በማስመለጥ ፤ በወኅኒ ከመጋዝ በመታደግ … ብቻ አይከብርም፡፡ እንዲሞቱ ፣ በአንበሳ እንዲበሉ ፣ በሰይፍ ስለት
እንዲቀሉ ፣ በወኅኒ እንዲጋዙም በመፍቀድና በመውደድ ክብሩን ይገልጣል፡፡ ክርስትና መስቀል የመሸከም መንገድ እንደመሆኑ መጠን ለእውነተኛው
የጌታ ወንጌል ፈጽሞ እንድንጨክን ተጠርተናል፡፡
እግዚአብሔር ይህ እንዲሆን የፈቀደው የመንገዱን ሕማም ሳያውቀው ወይም
የማያውቀው ሆኖ አይደለም፡፡ እርሱ የሕማም ሰው ነውና (ኢሳ.53፥3) ፣ በሥጋና በደም ተካፍሏልና (ዕብ.2፥14-15) ፣ ከኃጢአት
በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነውና (ዕብ.4፥15) የመከራ ሕማምን ስሜት በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ዳሩ ከተሰቀለው ሙሽራ
ጋር ሙሽሪት መከራውንና ሕማሙንም ልትካፈል ይገባታልና አማኞች የክርስቶስን መከራ ወይም በስሙ የሚመጣውን መከራ በደስታና በሳቅ
ሊቀበሉት ይገባቸዋል፡፡ “ … ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ … ” “
… ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ” (ሐዋ.5፥41
፤ 1ጴጥ.4፥12-13) እንዲል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ለኃጢአትና ለዚህ አለም ምኞት ሙትና የተሰቀለች ብትሆንም፥
ለኢየሱስ መንፈስ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ግን ሕያው ናትና እጅግ ብዙ ጠላቶች አላት፡፡ በእርግጥ የውስጥ ጠላቶቿ የሚጐዷትንና የጐዷትን
፤ በመናጠቅና በጭካኔ ልጆቿን የሚገድሉባትንና የሚሰብሩባትን ያህል የውጪ ጠላቶቿ ብርቱና ክንደ ሃያል አይደሉም፡፡ ይህ ማለት ግን
ምንም ጉዳት አላደረሱም ወይም አያደርሱም ማለት አይደለም፡፡
ከሰሞኑ ከወደጅማ የሰማነው ድርጊት ይህን ሃሳባችንን ይበልጥ ያጎላዋል፡፡
በጅማ ሃገረ ስብከት በየም ወረዳ በቁንቢ ቀበሌ የሆነው ክስተት “ተራ” ግድያና ድንገት ያልተከሰተ መሆኑን፥ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ
አካላት [በአክራሪ ሙስሊሞች] ያስተናገደ መሆኑ ፣ ክርስቲያን የተባሉ ወገኖች ኢላማ መሆናቸውና የእነርሱም ወገን ሆነው ሃሳባቸውን
ያልደገፉት በአንድነት መግደላቸው ጥቂት የማሳያ ምስክሮች ናቸው፡፡
ስለአክራሪ ሃይማኖተኞች ሳስብ የሐሰት ትምህርት ምን ያህል አደገኛና ከመርዝ
ይልቅ አጥፊ እንደሆነ አስተውላለሁ ፤ የሃይማኖት አክራሪዎች ደቀ
መዛሙርቶቻቸውን እስከሞት ድረስ እንዲታመኑ አድርገው የሚያሰለጥኑት በትምህርትና በትምህርት ነው፡፡ ትምህርት አንድን ማኅበረሰብ
ለመንቀልም ሆነ ለመትከል ዋና መሠረት ነው፡፡ በዛሬ ዘመን መናፍቃን ለሐሰት ትምህርታቸው የሚተጉትንና የሃይማኖት አክራሪዎች ሰውን
ለማጥፋትና ለመደምሰስ የሚዋደቁትን ያህል ቤተ ክርስቲያን ገና ምንም እንዳልሠራች ለመናገር ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ እኛ እንዲያውም
“ትልቁን አቅማችንን” የተጠቀምነው ለመለያየት ፣ ለመወጋገዝ ፣ በጥላቻ ለመተቻቸት … [በሥነ ምግባርና በውበት በመፍትሔ አበጅ
ሒስ መወያየት ፤ መነጋገር ስንችል] ነው ማለት ያስደፍራል፡፡
ግና ጠላት ተባብሮ ቤታችንን ካጠቃና ቅጥራችንን ደጋግሞ በክፋትና በደም
ማፍሰስ ከረገጠው፥ እኛ ምላሻችንን በሚራራ ልብ በሕብረትና በመንፈስ አንድነት ቆመን የእግዚአብሔር መንግሥት ሠራተኞች መሆናችንን
ማሳየት ነበረብን፡፡ እንዲያውም እጅግ መጠንቀቅ ያለብን ነገር የሚመጣው መከራ፥ “በገዛ ሥጋችን የዘራነው ከሥጋችንም መበስበስን
ያጨድንበትና” (ገላ.6፥8) የገዛ ኃጢአታችን ፍሬ እንዳይሆነን መጠንቀቅ ይገባናል ወይም ምናልባት ቃሉን ብቻ በመስማት ዳሩ ግን
ካልኖርንበት ግብዝ ክርስትናችን (ማቴ.13፥21) መጥቶብንም ከሆነ ራሳችንን ማየቱ ይገባናል፡፡ ወገኖቼ በተለይ በዚህ ዙርያ ራሳችንን
በንስሐ መመልከቱ አይገባም ትላላችሁ?
እግዚአብሔርን ብቻ ስለማምለካችን መከራ እንደሚመጣብንም ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር
ባለመታዘዛችንም ጭምር መከራ እንደሚያገኘን ቅዱስ ቃሉን ስናጠና የምናስተውለው እውነት ነው (ኢያ.7፥1-9 ፤ መሣ.2፥15 ፤
6፥1)፡፡ በአንድ ጐኔ ቤተ ክርስቲያንን “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያጽናናሽ” ማለትን ብወድም፥ ሌላና ከባድ ሕመም ደግሞ በምድራችን
ላይ አሁንም አለ፡፡
ኢትዮጲያና ኤርትራ [መለያየት የማንችላቸው ወንድማማቾችና እህትማማቾች]
ከሰሞኑ ጦር ተማዘዋል፡፡ ወንድም ወንድሙን አድብቶ ሳይሆን በአደባባይ ገግሎ “ሊሸልልና ሊፎክር” አንዳቸው በሌላው ላይ ዘምተዋል፡፡
ዕውቀት ፣ ጥበብ ፣ ሥልጣኔ … መጥቆበታል በተባለው በዚህ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን፥ እኛ ግን ገና ከወንድማችን ጋር ላለመስማማት
ቆርጠን በድንቁርና አለም ውስጥ ነን፡፡ ትላንት ያደረግናቸውና እልፍ አእላፍ ወገኖቻችንን ያረገፍንበት ጦርነት ምንም ሳይመስለን
ዛሬም ምድሪቱን አኬልዳማ ለማድረግ ጨክነናል፡፡
ረሃብ የሚቆላውን ወገን ማሰብ ተስኖን ጥይትና መግደያ ብረትን በውድ
ዋጋ እንገበያያለን ፤ ደዌ ያደቀቀውን ወገን ዘንግተን እጅና እግርን ቆርጠን እልፍ ድውያንን ልናመርት እንዝታለን ፤ በደም ጭቃ
መጨማለቅ አሁንም ገና አልበቃንም ፤ በገዛ ሰይፋችን የገዛ ወገናችንን
ብልት መቁረጥን አሁንም ለእኛ ከሥልጣኔያችን አንዱ መሆኑን ለአለም ሁሉ ልናሳይ ፊት አውራሪ ሆነናል ፤ “ተዉ” የሚለንን ላንሰማ
ራሳችንን በጦር ማዋቀርና ማደራጀት ሥራ ተጠምደናል ፤ የድኅነትና የችጋር ማሳያ ምሳሌዎች መሆናችንን ለመፋቅ ዛሬም እንኳ አልጨከንንም፡፡
ኸረ እኛን ምን ይሆን የሚበጀን? ለትውልድ መቃብር የምንቆፍር ፣ ለኋለኛው
ሊመጣ ላለው ጨቅላ ትውልድ ቂምና ቁርሾ አዳቅለን ፤ አዋልደን ፤ አሳድገን የምናዋርስ ቁልቁል አደግ ፣ ጦም ለሚያድረው መሬት ፣
የእርሻ ኁዳድና ሆድ መላ ከማፈላለግ ስለግድያና ደም ማፍሰስ የምንጨነቅ ታካች፥ ከእኛ በላይ እብሪተኛና ግብዝ ማን አለ? ምነው
ሶርያ ፣ አፍጋኒስታን ፣ ሶማሊያ ፣ ኢራቅ … አልታይ አሉን? እስኪ እነርሱ በጦር የከሰሩትን አይተን መማር ይሳነንን? የተሰደዱትን
ወገኖቻችንን ምነው ማሰብና ማስታወስ አቃተን? እውን እጃችንን በአይናችን ላይ ማንሳት ከማን ተማርን? ምነው እኒህ ሁለት ጥቁር
አፈሮች መተቃቀፋቸውን ማን ነጠቀው? “ኢትዮጲያዬና ኤርትራዬ ሆይ!” ኸረ እግዚአብሔር ምህረቱን ይላክላችሁ ፤ ይማራችሁ፡፡ አሜን፡፡
መች ይሆን ከቂም ፣ ከበቀል ፣ ከቁጣ ፣ ከጠብ … ነጽተን ለእግዚአብሔር
ተዋርደን ለወገናችን የደስታ ጮራ የምናፈነጥቀው? እውን እንዲህ እየሆንን ከመከራ የምንድን ነንን? ደም እያፈሰስን ከመኖርና ደማችንም
እየፈሰሰ ከመኖር ማረፊያ ቀናችንመች ይሆን?
ቤተ ክርስቲያን ሆይ፦
ü ስለሞቱት ልጆችሽ
እግዚአብሔር ያጽናናሽ ፤
ü ልጆችሽም ግን
ይኸው ደም በማፍሰስ ተጠምደዋልና፥ “ምነው ተዉ ለማለት አንደበትሽ ታሰረ? ሁለቱን ወንድማማች ምነው ብትሸነግያቸውና ብታስታርቂያቸው?”
፤ ፍርሃቴ ደግሞ ልጆችሽ በሲኖዶሱ ውስጥ መስማማት አቅቷቸው ፖለቲከኛው መሪ ሊያስታርቃቸው ሲገባ አይቼ፥ ‘ሳይታረቁ ማስታረቅ የለም’
ብዬ ባንቺ በማፈር አዘንኩ ፤ እባክሽን ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የተውሽውንና የጣልሽውን የጽድቅ መታጠቂያሽን አንሺው!!!
ü ደግሞም፥ ኢትዮጲያንና
ኤርትራን ደምን ከማፍሰስ ተቆጥበው ደሙን ያፈሰሰላቸውን ቅዱስ ኢየሱስን ማየት እንዲችሉ ወንጌልን ስበኪላቸው፡፡ [ዳሩ አንቺ ግን
ወዴት ነሽ?] አዎ! ወንጌሉን ንቀዋልና ፤ የራሳቸውንም ወንጌል ደርሰውና አምነው ጦር በማወጅ ተጠምደዋልና የጽድቁ ወንጌል ለሁላችን
ለመንፈሳውያንና ለምድሪቱ ባለ ሥልጣናት መስበክ ፣ ማወጅ ፣ መመስከር ያስፈልግሻል፡፡ “አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም
ነበር ፤” (1ቆሮ.2፥8) እንደተባለ፥ የክብሩን ወንጌል ሃይማኖተኛ ሙስሊም አክራሪዎቹም ፤ ኢትዮጲያና ኤርትራም ቢያውቁት ኖሮ
ሰላማዊው መንገዱ መወያትና ፤ መሸመጋገል እያለ የገዛ ክቡር ወገናቸውን በቦንብ ጢስና በስለት ሕይወቱን ሊቀጥፉት ባልቸኮሉ ነበር!!!
ጌታ ኢየሱስ
ሆይ እባክህን ለሕዝብህ የእጅህን ችንካር እንዲያዩ ማስተዋልህን አብዛላቸው! አሜን፡፡
Bebzu Tebarek Wendeme!! Zemenh Bebetu Yelemlm.
ReplyDeleteGod Bless You!
ReplyDelete