Thursday, 2 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (ክፍል አንድ)


Please read in PDF
   የፍጥረትን አፈጣጠር የሚነግረን ቅዱስ ሙሴ የኦሪቱን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፍ ሲጀምር፥ “…ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ …” (ዘፍ.1፥2) ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን እስኪል ድረስ፥ ጨለማው በምድር ሁሉ ላይ ሰልጥኗል ፤ ማለትም፥ ምድር ለሥራ የማትመችና የማትታይ ፣ ቅርጽ አልባና ባዶ ፣ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ የተወረሰች ነበረ ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ ግን፥ ለሥራ የማትመቸዋ ምድር ታየች ፣ ተገለጠች ፣ ሕልውናዋ ታወቀ ፤ ቅርጽ አልባና ባዶ የነበረችው አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ልታበቅል ዝግጁ ሆነች ፤ አስደሳችና ውብ ውበትን ለበሰች ማለት ነው፡፡ ጨለማዋን የእግዚአብሔር ብርሃን ገልጦላታልና፡፡
    ለተፈጠረችው ምድር ጨለማ ቀድሞ ሰልጥኖባት እንደነበረው እንዲሁ፥ ዋናው ብርሃን ዘእምብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሊሰለጥንና በሕይወታችን ብርሃንን ከማብራቱ በፊት የኃጢአት ጨለማ በልባችን ለዘመናት ሰልጥኖ ነበር፡፡ ምድር ስትፈጠር ብርሃን ይሁን ያለው እግዚአብሔር ወልድ፥ አሁንም በአዲስ ኪዳን ልደት፥ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” (2ቆሮ.4፥6) በማለት፥ በዚህ ቃል ቀድሞ ምድር ሕልውናዋ እንደተገለጠ፥ አሁንም ለእኛ በጽድቅ መኖርና መገለጥ ክርስቶስ መሠረትና ዋናችን ሆኖልናል፡፡ እርሱ በደሙ ቤዛነት ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን አውጥቶናልና፡፡

    በአገራችን “ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” የሚል የቆየ ብሒል አለ ፤ በእርግጥም ከምድር መዋብ በፊት ጨለማ ሰልጥኖባት ነበር፡፡ ጥልቅ ጨለማ ከብርሃን በፊት ነበርና፥ ከጥልቁ ጨለማ በኋላ ውብ የእግዚአብሔር ብርሃን መጥቷል፡፡ ዛሬ ላይ በኢትዮጲያዬ ጨለማው ለምን ከበደ? ምነው ጨለማችን መልኩን እንዲህ አወዛብን? ሰቆቃችን ምነው ሕጻን ፣ ወጣት ፣ ጐልማሳ ፣ ሽማግሌ አልመርጥ አለ? የኢትዮጲያ ጨለማ ከስንት ዓመት በኋላ ይለቅ ይሆን? ይህን ጨለማ ገፋፊስ ማን ነው? (ሕሊናዊ ሙግት) በእርግጥ እንዲህ “የጨለመብን” ሊነጋልን ይሆን? … (እግዚአብሔር አዋቂ ነው!)
   የኢትዮጲያ ቤተ መንግሥት “ሠራተኞች” የሚበዛ ነገራቸው አልጣፍጥ እያለንም እንኳ፥ ለዓይኖቻችን አሁንም የማያልቅ ጉድ ያሳዩናል፡፡ የአገር ዓቀፍ ፈተናን መስረቅ በትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ ከመቀለድ የበለጠ ነውና፥ ከዚህ የሚበልጥ አስቀያሚ ነገር ምን አለ? ፈተና የሚሰርቅም ፤ የተሰረቀውን የሚያሰራጭም ለእኔ ምንም ልዩነት የላቸውም ፤ ሁለቱም፥ እንኳን የሰማይን፥ የምድራዊውን የሞራል ሕግ የማያውቁና ሕሊና ቢስ ትውልድ ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በተደላደለው ቅንጡ ምድራዊ ዓለም ላይ በዲያስፖራነት ኑሯቸውን በውጪው ዓለም መሥርተው እየመሩ፥ እዚህ ባለው “ድኃው” ዜጋ (ከእነርሱ አፈ ስልነት እንጂ ከንቱ ሕሊናነት የእኛ ድኅነት ከመልካም ሕሊና ጋር እጅግ የተሻለ ቢሆንም) የሚያላግጡ “ታጋይ ነን ባዮች አጋጋዮችን” የልጅ ሥራቸውን “ተዉ” ባዩ መጥፋቱ፥ የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ከፍካት ወደመደብዘዝ ይወስደዋል፡፡
    ብዙ ስለተባለው የአሥራ ሁለተኛ ክፍል አገር ዓቀፍ ፈተና መሰረቅ እግረ መንገዴን ካነሳሁ፥ ወደዋናው ሃሳቤ ልሂድ እስኪ፡፡ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” ይባልም የለ? ከሰሞኑ ሌላም የሚብስ ነገር ገጥሞንም አይደል? ሲኖዶሳችን አንድ ጉዳይን መቋጨትና መፍታት ተስኖት እርዳታ ከቤተ መንግሥት ሲጠይቅ አይተንም አይደል? ይህ ጉዳይ ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሣ ይጋብዘናል፡፡ … የመንግሥት አካል ግን በሲኖዶሱ መካከል እንዲገኝ ያስፈለገው ለምን ነበር? የአባቶች አለቃ ለሆነው ፓትርያርኩ እንደራሴ በመሾምና ባለመሾም ለተነሣው አለመግባባት ብቻ ነውን ወይስ የአንዳንድ ጳጳሳት ባሕርይ “መላ ቅዱሱን አጥቶ” ይሆን? ኤጲስ ቆጶሳት ይህን ያህል እንዳያግባባ ያደረጋቸው ምን ነገር አለ? እውነት ይህን “የሲኖዶስ አለመረጋጋትን” የሚፈጥሩ ኤጲስ ቆጶሳት፥ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ.28፥19-20) የሚለው ታላቁ ተልእኮን ከግብ ለማድረስ በብዙ ተጨንቀው ነውን? የማያግባባ ነገር ቢፈጠር እንኳ፥ ከመጨቃጨቅና አለመግባባት ውስጥ ከመግባት ይልቅ በትሁት ልብና ንግግር በመወያየት እጅግ የሚሻለውን መንገድ መምረጡ አይሻልም ነበር ወይ?
      ለኤጲስ ቆጶሳት ከቀረቡት መመዘኛዎች አብዛኛው ይህንን የሚያመለክት ነው፡፡
     “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር ፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል (1ጢሞ.3፥1-7)


    “… ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ ፤ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው። ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን ፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና” (ቲቶ.1፥5-9) (የተሰመረባቸው አንዳንድ ቃላት በጸሐፊው የገቡ ናቸው)
   በመጽሐፍ ቅዱስ ኤጲስ ቆጶስነት ወይም ሽማግሌ የሚለው ቃል በተለዋዋጭነት የሚያገለግል ቃል ነው፡፡ ሽማግሌ የሚለው ቃል ብቃትን ፣ ብስለትንና በልምድ የካበተን ችሎታን ሲያመለክት፥ ኤጲስ ቆጶስ የሚለው ደግሞ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የመምራት ኃላፊነትን የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥም፥ የኤጲስ ቆጶስነትን ሥራ የሚፈልግ፥ ይህን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ይዟልና (የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለዚህ ኃላፊነት የበቃ ሆኖ ተገኝቷልና እንዲሉ) መልካም ሥራን ተመኝቷል፡፡ ኤጲስ ቆጶስነት ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን በታማኝነት እንድንሠራው የተሰጠን ሰማያዊ አደራ ነው ፤ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ.20፥28) የሚለው ቃል፥ የታመነና የጠባቂነት አደራው ሰማያዊ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
    ስለነቢዩ ቅዱስ ሙሴ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፥ “ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጕልበቱም አልደነገዘም” (ዘዳግ.34፥7)፡፡ ይህ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው፥ የእግዚአብሔር ሞገስ ከብቦታልና እድሜው እንኳ “ጃጅቶ” ሁለንተናው ብርቱ ነው፡፡ በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል በብርታት ቆሞ ሲያገለግል ነበር፡፡ ለምን? ብለን ብንጠይቅ አንድ ብርቱ ምስጢር በሙሴ ሕይወት እናገኛለን፡፡ ይኸውም፦ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ” (ዘኊ.12፥3) ይለናል ፤ ጌታ ኢየሱስ እጅግ የተወደደበት ዋናው ነገሩ አለልክ ዝቅ ዝቅ ማለቱ ወይም ፍጹም ትህትናው አይደለምን? ሙሴም በዚህ ዕድሜው እንኳ ተተኪውን ኢያሱን በማዘጋጀት ተጋ እንጂ፥ እንደራሴ ሹሙልኝ ወይም እስራኤልም ካልሾምንልህ ብለው አልተገዳደሩትም፡፡ አንድ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖም እንኳ እግዚአብሔር ሞገስን ይሰጣል፡፡ ሌሎችንም አገልጋዮችን እንዲህ ማንሳት እንችላለን፡፡
    ከላይ ያየነው የኤጲስ ቆጶሳት መመዘኛም ይህን እውነት ያጐላዋል፡፡ ኤጲስ ቆጶስነት ሹመት አይደለም ፤ በአጋንንት ፊትና በምድራውያን ተገዳዳሪዎቹ ፊት በመንቀጥቀጥ የሚፈራውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ይመራልና ብርቱ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ነው፥ እግዚአብሔር ለታማኝ አገልጋዮቹ  የበዛ ሞገስና ግርማን የሰጠው፡፡ ይህን የእግዚአብሔርን ቃል ሚዛንነት ጠብቀን የዛሬዎቹን አንዳንድ ኤጲስ ቆጶሳትን ነባራዊ ሁኔታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ዳኝነት በቀጣይ ክፍል እናያለን፡፡
     አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ለምድራችን ልቦናን ስጥ ፤ አብዛም፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል …



1 comment:

  1. ካንተ ድርጊት የበለጠ የሚያሳፍር ነገር አለ እንዴ? ወሬኛ ነገር። ማፈሪያ። ደሞ ካንተ ብሶ የአንተን የስህተት አዝመራን ሲያርሙ ስለሚውሉ ልትሰድባቸው ትሞክራለሀ እንዴ? አሳፋሪ።

    ReplyDelete