በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት፥ ቅዱስ ያሬድ እንደሰየመው አሰያየም ፥ያለንበት
ሳምንት “ኒቆዲሞስ” ይባላል፤ ቅዱስ ያሬድ፥ ጌታ ኢየሱስ ነገረ ጥምቀትን ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረው በማውሳት “ሆረ ኃቤሁ ዘስሙ
ኒቆዲሞስ” ማለትም “ኒቆዲሞስ የሚባለውም ወደእርሱ ሄደ” ብሎ ርዕስ ሰይሞ ዘምሮታልና ፤ ቤተ ክርስቲያንም ይህን በማሰብ የጌታን
ፆም አንዱን ሳምንት ሰይማ ፥ ጌታዋን ታመልክበታለች፡፡
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊና በትምህርቱ ፤ በሥልጣኑና በሐብቱ በአይሁድ ላይ ከተሾሙት
የአይሁድ አለቆች አንዱ የነበረ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው በሌሊቱ ክፍል ወደጌታ ዘንድ በመምጣት ተግቶ ዘወትር የሚማር ነው ፤ በሌሊቱ
ክፍል ላይ የሚመጣበት ምክንያት ሁለት ሊሆን ይችላል፦
1. አይሁድ ከኢየሱስ ጋር የሚተባበረውን ማንኛውንም ሰው
ከምኵራባቸው ያገሉ ፤ ያባርሩም ነበርና ፥ ይህን ከመፍራቱ የተነሳ ፤(ዮሐ.9፥2 ፤ 22 ፤35)
2. ሕዝብ በተሰበሰበበት የግል ውይይት ስለማይመችና በግሉ
እንደሚገባ በጸጥታ ለመማር ከመፈለግ የተነሳ ይሆናል፡፡
ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ እንደመሆኑ መጠን ከእርሱ ጋር አብረውት የሚሠሩትን
ሰዎች ማንነትና ጠባይ የተመለከትን እንደሆን ብርታቱን ማየት እንችላለን፡፡ የአይሁድ አለቆች የተባሉት አንዳንዶቹ እውነተኛና ቅን
የሆኑ ፣ የሃይማኖት ቅንአት ያላቸው ቢሆኑም ፣ ከጌታ ጋር ሲከራከሩ
ከነበሩት ብዙዎቹ ግን ግብዞች ፣ ምቀኞች ፣ ግትሮችና ወግ አጥባቂዎች የነበሩ ፤ በምኵራብ አስተማሪዎች ፣ በሕዝቡም ዘንድ የእምነት
ምሳሌዎች ተደርገው የሚቈጠሩና ሕጉን ለማስከበርና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ራሳቸውን የሾሙ ናቸው፡፡
እኒህ የፈሪሳውያን አለቆች ከአባቶቻቸው በዘልማድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን
ወግና ሥርዓት ፣ እንደቅዱሳት መጻህፍት ሥልጣን ያለው አድርገው ይቊጥሩ ነበር፡፡ ጌታችን “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ
ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ።” (ማር.7፥8) እንዳላቸው
ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለሰው ሥርዓት የሚታዘዙና የሚቀኑ ፤ የሚቆጡም ነበር፡፡
ስለዚህም ጌታ ኢየሱስን “ያሳድዱት ፤ ሊገድሉትም አብዝተው ይፈልጉት ነበር።”
(ዮሐ.5፥16 ፤ 18) ሰላዮችንም ቀጥረው(ልከው) አብዝተው ይከታተሉት ነበር፡፡ (ማር.2፥6) እኒህ ፈሪሳውያን ፣ ሕዝቡና ሎሌዎቹ
ስለጌታ ኢየሱስ ምን አይነት አተያየት እንዳላቸው በአንድ ምዕራፍ ላይ ያንጸባረቁትን አስተያየት ማየቱ በቂያችን ነው፡፡
- “በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ
ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ
ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር።” (ዮሐ.7፥12-13)
- “አይሁድም፦ ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን
እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር።” (ዮሐ.7፥14)
- “ሕዝቡ መለሱና፦ ጋኔን አለብህ፤
ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት።” (ዮሐ.7፥20)
- “ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል
ሲሰሙ፦ ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤
” (ዮሐ.7፥40)
- “ሌሎች፦ ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤
ሌሎች ግን ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ፣ ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ
አላለምን? አሉ።” (ዮሐ.7፥41-42)
- “ሎሌዎቹ፦ እንደዚህ ሰው ማንም
እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።” (ዮሐ.7፥46)
- “ፈሪሳውያን፦ እናንተ ደግሞ ሳታችሁን?” (ዮሐ.7፥47)
- “ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ
ያመነ አለን?” (ዮሐ.7፥48)
እንግዲህ ኒቆዲሞስ ከእነዚህ መካከል የተገኘ የታመነ ቅን አገልጋይ ነው፡፡
ኒቆዲሞስ በዚሁ ምዕራፍ ላይ እርሱ አባል የሆነበትና በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአይሁድ ሸንጐ ኢየሱስን ሊከሱትና ሊፈርዱበት ሎሌዎችን
ልከው ፣ ሎሌዎቹ ጌታ ኢየሱስን ይዘውት ሳያመጡ በቀሩ ጊዜ ፤ ሸንጐው ሁሉ በታላቅ ቁጣ በሎሌዎቹ ላይ በተነሳ ጊዜ ኒቆዲሞስ ግን
“ሕጋችን አስቀድሞ
ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።” (ዮሐ.7፥51)
በዚህ በኒቆዲሞስ ጥያቄያዊ መልስ ሁለት የሚያስገርሙ ነገሮችን እናስተውላለን፦
1. ፈሪሳውያን ከአይሁድ ባዕለ ሥልጣናት መካከል በእርሱ
ያመነ ማንም እንደሌለ አስረግጠው ሲናገሩ ፤ ኒቆዲሞስ በእርሱ እንዳመነ አላስተዋሉም፡፡ በእርሱ እንዳመነ ብቻ ሳይሆን ስለእርሱም
ሲመሰክር እናየዋለን፡፡
2. በሌላው መልኩ ፈሪሳውያን ሕዝቡን “ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም
ነው” (ዮሐ.7፥49) ይበሉ እንጂ ኒቆዲሞስ እንደተናገረው እነርሱ ከሕዝቡ በባሰ ክፋት ከሕጉ በተቃራኒው ባለመጠበቅ መንገድ ሲሄዱ
እናያለን፡፡
ኒቆዲሞስ
ባለበት የሥልጣን ዙፋኑ ላይ ለጌታ የታመነ አገልጋይ ነው፡፡ በጠማሞች መካከል የበቀለ መልካም ዛፍ ነው፡፡ በጠማማ ትውልድ መካከል
ኖሮ ራሱን ከጠማማ ትውልድ ያዳነም ነው፡፡ (ሐዋ.2፥40) ባለንበት በየትኛውም የሥልጣን ፣ የፍርድ ፣ የትምህርት ፣ የንግድ ፣
የምርምርና ጥናት መስክ የተሰማራን ለክርስቶስ መታመናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እውነት ሁኑታዊ ወይም አንጻራዊ አይደለችም ፥
በመልካሞችም በጠማሞችም መካከል እውነት ያው እውነት ናት! ክርስቶስም ያው ክርስቶስ ነው፡፡ እንደኒቆዲሞስ እንዲህ ልንታመን ተጠርተናል!!!
ፈሪሳውያን ሕጉን የመጠበቅና የማስጠበቅ ሙሉ ኃይል በእጃቸው ጨብጠው ፣
ነገር ግን ካለመጠበቃቸውም አልፈው ሕዝቡ ባሰቡት ጥመት መንገድ ባለመሄዱ እጅግ ተናደዋል፡፡ መሪዎች ሕግ የማይጠብቅና ድንበር የለሽ
የልባቸውን ሙሰኝነት ፣ ፍረደ ገምድልነት ፣ ሴሰኝነት ፣ አግበስባሽነት ፣ ሰብዓዊ ጥሰትን … ሳያስተውሉ ሌላውን ሲቀጡ ፣ ሲዘልፉ ፣ ሲኮንኑ መዋላቸው እንዴት ያሳዝናል?!
እኛስ ባማሩ ቃላት እየሰበክን ፣ እየዘመርን ፣ እየጻፍን ፣ እያገለገልን ነገር ግን የውስጣችንን አመጽና ለእግዚአብሔር አለመታዘዝን
ሸሽገን የምንኖር አይደለንምን? ሳንጠብቅ ጠብቁ የምንል ግብዞች ፣ ሳንሰበር ባልተሰበሩት ያውም በእኛው የክፋት ስብከት የምንበሳጭ
… አይደለንንምን? መንታ ምሰሶ በአይናችን እያለ ሌላውን ስለምን ትንሽ ጉድፍህን አታጠራም ለማለት እንደፍራለን? ፊሪሳዊው ኒቆዲሞስ
ላልታዘዙትና ሕግ ተላልፈው ያዘዙትን ፈሪሳውያንን፥ በነቀፈበት ነቀፌታ ያልተያዝን ስንቶች እንሆን?
ጌታ በሚያበራ ብርሃኑ ልባችንን ያብራ፡፡ አሜን፡፡
ዋወ- ድንቅ ነው
ReplyDelete