Tuesday 5 July 2016

“VOA”ና ባልንጀሮቹ ከኃጢአት በቀር “ሥርየት”ን መች ይሆን የሚዘግቡት?

   በኃጢአት ውድቀታችን የሰይጣን ልጆች ስንሆን፥ በትንሣኤ ልቡና በምናደርገው የንስሐ መመለስ ደግሞ ከክርስቶስ ሞትና ከትንሣኤው ኃይል የተነሣ የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን፡፡ ማደፍ ፣ መርከስ ፣ መውደቅ የሥጋ ባሕርይ ነውና ሁላችን በዚህ በኩል፥ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ... አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ ...” (ሮሜ.3፥11-14) የሚለው ፍርድ የአዳምን ልጆች ሁሉ አጊኝቷቸዋል፡፡
    እናምናለን፤ ሁላችንም ያለክርስቶስ የሚታይ ምንም መልካምነት የሌለን ከንቱዎች ፤ የእግዚአብሔር ክብር የጐደለን እርባና ቢስ ነን፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ ከነበርንበት ጨለማነት ፣ ጠላትነት ፣ የቁጣና ያለመታዘዝ ልጅነት ፣ የኃጢአት ባርያ (ሮሜ.6፥20) የኃጢአተኝነት ሕይወት ፍጹም በማውጣት ወደሚደነቅ ብርሃን ፣ ወዳጅነት ፣ የመታዘዝና የእግዚአብሔር ልጅ ወደመሆን በደሙ አጽድቆ ፣ ቀድሶ ያፈለሰንና ወደአባቱም ንጹሐንና ነውር የሌለባቸው አድርጐ ያቀረበን፡፡

     ስለዚህም ምንም ያለነቀፋ የመኖር አቅም በራሳችን ባይኖረንም ከክርስቶስ የተነሣ ግን ንጹሐን ሆነን ያለነቀፋ መኖር ተብሎልናል፡፡ ይህ ማለት ግን አንወድቅም ፣ አንሰናከልም ፣ ፍጹም ፍጹማን ነን ማለት አይደለም፡፡ ከፈራሹ አካላዊ ማንነት ገና ያልተላቀቅንና ያልወጣን ነንና ልንወድቅ ፣ ልንሰናከል ፣ ተጠላልፈን ልንወድቅ እንችላለን፡፡ በዚህም ጊዜ ቢሆን እንኳ፥ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” (1ዮሐ.2፥1-2) የሚል ትልቅ የዋስትና ሰነድ አለንና እጅግ ተስፋ እንደሌለውና እንደማያምን በከንቱ ራሳችንን አንቧጭርም፡፡
   “እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። ... ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤” (ሮሜ.6፥1 ፤ 6-8) ጸጋ ስለበዛልን በኃጢአት አንጸናም፡፡ ኃጢአትንም ለመሥራት መብት የለንም ፤ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት ለዚህ አለም ኃጢአት ሞተናልና፡፡ ነገር ግን ይህ እውነት፥ “ከእግዚአብሔር ለተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ ለተወለዱ” (ዮሐ.1፥13) ፈጽሞ የሚገባቸው አይደለም፡፡
    ሌላም ተያያዥ እውነት እናንሳ፦ “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥” (ኤፌ.5፥11) የሚለውን ቃል ስናነሣ ኃጢአትን ለመቃወምና ለመግለጥም በዚያው ልክ የሚጨክንና የማናፍርበት ማንነት አለን፡፡ ምክንያቱም ከጨለማ ከወጣንና የሚደነቀውን ብርሃን ለብሰናልና፡፡ ብርሃን በባሕርይው ደግሞ በጨለማ ውስጥ ያለውን ማናቸውንም ነገር ይገልጣል፡፡ በተለይም ደግሞ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በሕይወታቸው አምነው የተቀበሉና በሕይወታቸውም ላይ የሾሙ ልጆቹ ሁሉ ከጨለማ ሥራ ጋር የሚተባበሩ ግድ የለሽና ምንም የማይሰማቸው ተላላዎች አይደሉም፡፡  በብዙ መንገድ ሊገለጥ የሚችለውና ነውርና ኃጢአት መምከር ፣ መገሰጽ ፣ ማጋለጥ ፣ መኰነን የሚችሉና ለማድረግም ዝግጁዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም፥ “ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል” (ዮሐ.7፥7) ፤ “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” (15፥19)  እንደሚለው ለክርስቶስ ታማኝ ሆነን ለዓለሙ ጠላት መሆናችንን የምናስመሰክርበት ነው፡፡
    ከዚህ በተቃራኒ ግን በኃጢአት የወደቀን ሰው ማንነት እንደትልቅ የዜና አጀንዳ መዘገብ የዚህ ዓለም ልጆች ዋና ሥራቸው[እንጀራቸው] ነው ማለት እንችላለን፡፡ ይህን አባባል የሚያጐላው ቪኦኤ በአማርኛ መርሐ ግብሩ አንድ ዘገባ ከወራት በፊት ሠርቶ ነበር፡፡ ምናልባት ይህን ዘገባ በዋናነት በምሳሌነት የምናነሳው ስለሁለት ነገር ነው፦
1.     ለአንድ ኦርቶክሳዊ አማኝና አገልጋይ ስለሌላ ቤተ እምነት አገልጋይ መናገርና መንገድ ማመላከት በእኛ አገር ትውፊት እንደሚያስወግዝ አውቃለሁ፡፡  ግና “መጽሐፍ ቅዱስን ጨብጠው በሃሳብ ያልተስማሙት” ኦርቶዶክስም ፣ ካቶሊክም ፣ ፕሮቴስታንትም የጋራ በሆነው ነገራቸው ላይ መስማማት እንዳለባቸው አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ክርስቶስን ገለል አድርጐ በ“እንስማማ” መርሕ ኃጢአትን ማሸነፍም ሆነ ማንጻት አይቻልም፡፡ ያስማማን ክርስቶስ ከሆነ የምንለያይበትም ዋና ነገራቸችን እርሱና ትምህርቱ ብቻ ነው፡፡
    ስለዚህም በክርስትና አገልጋዮች ላይ የሚቃጣውን ማናቸውንም ኢ - ሥነ ምግባራዊ ድርጊቶችን አግባብነት በጐደለው መንገድ ፤ ኢ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መልኩ የሚነቅፉትንና ክርስትናን ለማዋረድ የሚሠሩትን ለመቃወምና ከሠሙም ለመምከር ነው፡፡ መሪዎችን ዒላማ አድርጎ የሚሠራ ዘገባ ብዙ ጊዜ ከማዋረድና ማኅበሩን ዝቅ ከማድረግ አንጻር እንጂ ንስሐን ከማሰብ አንጻር አይደለም፡፡
      በእርግጥ ቤተ ክርስቲያንና መሪዎቿ በአለማውያን ፊት የሚዋረዱትና ነውራቸው የአደባባይ የሚሆነው ንስሐን ችላ ሲሉና የጌታን ምሕረት ሲገፉ ነው፡፡
2.    ውድቀቱን ከዘገቡ ትንሣኤውንምና ንስሐውንም ሳያፍሩበት መናገር ይበልጥ ሚዛናዊነትን ያሳይ ነበር፡፡ አልያ ግን ግልጥ ጎራቸውን መለየት አያዳግተንም፡፡ ምክንያቱም በሁሉም ቤተ እምነት ውስጥ ከግብረ ሰዶማዊነት እስከአጸያፊ ውስልትና ፤ ሥር የሰደደ ስርቆትና ሙስና ሰፍኖ እያዩ ዝም ማለት አድሎአዊነት ካልሆነ በምንም ሚዛን እኩልነት ነው ማለት አያስደፍርም፡፡ እውነት ላይ ቆመን ዘገባ የምናቀርብ ከሆንን፥ የሰውን ውድቀት እውነት ነው ብለን “የፕሮግራማችን ማጣፈጫ አድርገን” ከዘገብን ንስሐ ገብቶ መመለሱንም ለመዘገብ ሊመረን ወይም ሊጐመዝዘን አይገባንም፡፡
     ለእኔ ከ“ዘማሪው” ውድቀት ይልቅ፥ እርሱን ከነውድቀቱ ተቀብላ ትዳርዋን በይቅርታ “የፈወሰችው” ሚስት እጅግ ታላቅነት ይታየኛል፡፡ የባልየው ውድቀት ትልቅ የወሬ ርዕስ ከሆነ፥ ምነው የሚስትየው ባልዋን ማንሣትና እጅዋን ዘርግታ ተቀብላ ለብዙ ባለትዳር ሴቶች ምሳሌ የሚሆነው መልካም ምግባሯ የዜና ዋና ርዕስ አልሆን አለላችሁ? አያችሁ! እንደእናንተ ቢሆን ባልየው ለዘለአለም ከነእፍረቱ ይኖር ነበር ፤ ጠንካራዋ ሚስት ግን እፍረቱን ሳታፍርበት ይቅርታ አብዝታለት ታደገችው!!!
  በእርግጥ፥ ከኩርንችት በለስ አይለቀምም ፤ የጥላቻ ፖለቲካንና የአንድ ወገንን ስሜት አክርሮ ከሚያቀርብ የዜና ምንጭ [ቪኦኤና ባልንጀሮቹ] እንዲህ ያለውን ጠንካራ የይቅርታ መንፈስ፥ ርዕሰ ዜና አድርገው ያቀርባሉ ብሎ መጠበቅ በራሱ ከየዋህነት ያለፈ ጅልነት ይመስለኛል፡፡
    ይህች ክብርት ሴትና ባልየው ትልቅ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በተለይም ዛሬ አገልጋይ ሆነው በነውር ተተብትበው የሌሎች መጠቀሚያና የሰነፎች መጫወቻ የሆኑት፥ ነውራቸውን ለጌታ ተናዝዘው በደሙ መታጠብና መንጻት እየቻሉ በአደባባይ ይቅርታ ላለመጠየቅና ንስሐ ላለመግባት ታስረው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእኛ መካካል እንኳ፥ ለቁጥር የሚታክቱ ቀሳውስትና መነኮሳት ፤ ዘማርያንና ሰባክያን [የተወሰኑ ጳጳሳትንም ይጨምራል] ንስሐ ገብተው ፤ በደሙ ታጥበው ያለነውርና እድፈት መቆምና ማገልገል ሲገባቸው በቀደመ ነውራቸው ምክንያት ተሸማቀው የማይገባቸውንና ከእነርሱ የማይጠበቅ ሥራን ሲሠሩ እያየን ነው፡፡
    በአደባባይ የሚገልጠው ፈራጁ ጌታ ሳይመጣ፥ እኛ ዛሬ ገልጠን ብንናገረውና የበደልናቸውን ይቅርታ ለምነናቸው መዳናችንን ብናቀርበው እጅግ መልካም ነው፡፡ ስንሠራው ካላፈርን አሁን ልንናዘዘውና በደሙ ልንታጠበው ስለምን እናፍራለን? እኔን ጨምሮ ብዙ አገልጋዮች እንዲህ በሚያሳፍር ብዙ ነውር ውስጥ ያለፍንና የረከስን ነበርን ፤ “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል” (1ቆሮ.6፥11) እንደተባለ፥ “በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶናልና” (ሮሜ.8፥2) ማንም [እንኳን ሰው ሰይጣንም ቢሆን እንኳ!] በቀደመው ኃጢአት ሊከስሰን አይችልም፡፡ ንጉሡ ኢየሱስ በደሙ አንድ ጊዜ ደምስሶታልና ፤ እኛም ይህን እናምናለን፡፡
    እንኪያስ! በትላንት ማንነታችሁ የታሰራችሁና ለሌሎች ባሮች የሆናችሁ ሁሉ፥ በይቅር ባዩ ጌታ ስም እመኑና  ዛሬ ንስሐ ግቡ ፤ በደሙም ታጠቡና ነጽታችሁ ነጻ ውጡ፡፡ ቪኦኤና ባልንጀሮቹም ነውርን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባችን የተቸገረበትንና ቢያደርገው ሽንፈት የሚመስለውን ይቅርታንም መዘገብ፥ መሸነፍ ወይም አላዋቂነት አይደለምና ለዚህም አንደበታችሁ እንዲከፈት እንማልድላችኋለን፡፡ 

   አቤቱ አብ ቅዱስ አባት ሆይ! ለሕዝብህና ለአገልጋዮችህ ማስተዋልን አብዛ፡፡ አሜን፡፡

1 comment: