ንጉሥ ዳዊት የገዛ ቤተሰቡ
ማለትም አቤሴሎም ልጁ ሳይቀር፣ ከሥልጣን ሊያወርዱት በክፋት አሲረውበታል፤ ፍጹም ካሴሩበት ሰዎች እግዚአብሔር እንዴት ባለ
ታላቅ ትድግና እንደሚያድነው በመተማመን ያቀረበው የጸሎት ክፍል ነው። ጸሎቱ የኪዳኑን አምላክ በማሰብና በመታመን (2ሳሙ. 7)
የቀረበ ሲኾን፣ በጌታ ላይ ያለውን ጽኑ እምነትም በይፋ የሚመሰክርና የሚያውጅ ጸሎት ነው። ጠላቶቹ የቱንም ያህል ጠንካራና
ብርቱዎች ቢኾኑም፣ ለመዝሙረኛው ግን እግዚአብሔር ብርሃንና የኹሉ ነገር ምንጭ፤ ሰላምና መታመኛው ነው።
መዝሙረኛው የጌታን መቅደስ
ወይም ቅዱሱን ማደሪያ የሚመለከተው እንደ ምሽግ ነው፤ ይህም ማለት ጌታ ራሱ የመዝሙረኛው ምሽግ ነው። በዚያ መኖርን ይሻል፤
ይህም በጎነቱንና ፍቅሩን የሚያመለክት ነው። ከጠላቶቹ የስም ማጥፋትና ስድብ ለመዳን፣ ማምለጫው በዚህ ስፍራ መሸሸግና ከኹሉ
ነገር ማምለጥ ነው።
እግዚአብሔር አምላክን
ዘወትር በመቅደሱ ኖሮ ማገልገል መታደልም፤ ብጽዕናም ነው፤ እግዚአብሔርን ስናገለግል ደግሞ ትኵረታችንን ኹሉ በመስጠት ሊኾን
ይገባል። ይህም በሕይወት ዘመን ኹሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ መኖርን የሚያመለክት ነው። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር
ቤት ውስጥ መኖር ይህን ኹሉ ይጨምራል፤
·
በጸሎትና በቃለ እግዚአብሔር ንባብና ጥናት፣ በጾምና በምህላ፣ በስብከትም፣
በዝማሬ፣ ሕጻናትንና ወጣቶችን፣ መላውን ቤተ ክርስቲያን በማገልገል በኅብረት ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኾን።
·
መንፈሳዊ ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ አይደለም፤ በተለይም በበጐ
ምግባራት፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ፣ እንዲኹም በጨዋታና በጉዞ ኹሉና በሌሎችም ስፍራዎች በጌታ መግቦታዊ ጥበቃ ውስጥ መኾን።
·
ከዚህ ባሻገር ከኀጢአተኝነትና ከኀጢአት ጋር በመጋደል፣ ለሴተኛ
አዳሪዎችና ለኀጢአተኞች በምናደርገው ቸርነትና ርኅራኄ በጌታ ጥላ ወይም ማደሪያ ስር መኾን ይገባል።
የጌታ ድንኳን መሸሸጊያ
ነው፤ ከመከራም ኹሉ መሰወሪ ነው፤ በእግዚአብሔር ቤት፤ በድንኳኑ መኖር እጅግ መታደል ነው፤ ድንኳኑ ዕረፍትና መጽናናት፤
ደስታና እልልታ የበዛበት ነው፤ በቤቱ በመኖር ለሥራው ስንተጋ መንፈስ ቅዱስ፣ በጠላቶቻችን ራስ ላይ ከፍ ከፍ ያደርገናል፤
መዝሙረኛው በፍጻሜ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፣
“አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥”። እግዚአብሔርን
የሚያውቁና ፈቃዱን የሚፈጽሙ ብቻ ለጸሎታችው በጎ ምላሽ አላቸው። እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ እጅግ የላቀ ነው፤
በቤቱ የሚኖሩና ዘወትር ከእርሱ ጋር ኅብረት የሚያደርጉ ብቻ እግዚአብሔርን በትክክል ያውቁታል።
እንዲህ ያለ ሰው እንዲህ ሊባል
ይገባዋል፤ “እግዚአብሔርን ተስፋ
አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።” እናም ቃሉ በትክክል በሕይወታችን
እንዲፈጸም፣ እምነታችንን ከሚያበላሽ ማናቸውም ነገር ኹሉ መራቅ ይገባናል፤ ጌታ እንዲረዳንም ፈጽሞ ልንታመንበት ይገባናል!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ
ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
God bless you God bless you
ReplyDeleteTebarek tsega yibzalih
ReplyDelete