1.
ሌላውን የሚንቁ
ዘረኛነት ባህርይው
ራሱ “የእኔ ነገር ትልቅ ነው” የሚል ነገር በውስጡ አለበት፡፡ ንቀት ”እኔ ከሌላው እሻለለሁ ወይም እበልጣለሁ” የሚል ክፉ ሃሳብን
ያዘለ ነው፡፡ ጀርመናውያን በይሁዲዎች ላይ ከመነሳታቸው በፊት ሲመለከቷቸው የነበረው በንቀት ነበር፡፡ በአገራችንም ያለውን እውነት
ብናይ አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር ሲንቅ ያየንበት፤ የምናይበትም ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ለሥራ ጉዳይ
ወደአንድ ክልል ሄዶ ነበር፤ በዚያም መኪናችን ቆሽሻ ነበርና ልናሳጥብ ወደአንድ መኪና ማሳጠቢያ ገባን፤ የመኪናችንን ታርጋ ብቻ
አይተው በሚጠየፍ ማንነት ነበር አጣቢዎቹ የተመለከቱን፤ ሊያጥቡልንም ፈቃደኞች ስላልነበሩ ትተን ሄድን፡፡ በጥቆማ ግን ወደሌላ ሥፍራ
ሄደን አሳጥበናል፡፡ ያጠበልን ልጅም ግን “የታርጋው አከባቢ ነዋሪ” እንደነበር በኋላ ላይ ሰማን፡፡
“ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር” (ምሳ.18፥3)
እንዲል ንቀት ሰዎችን በሰውነታቸው ብቻ ካለመመልከት የሚመጣ ነው፤ ማንም የተወለደበትን ዘር መርጦ አልተወለደበትም፤ “የሚጠላ፣
የሚናቀው” የምንለውንም ዘር ያ ወገናችን በምርጫው አልተወለደበትም፡፡ ዘረኛነትን የሚሰብኩና መርዙን የሚረጩት አካላት ግን ሌላውን
ሲንቁ፥ ያሉበትን ዘር እግዚአብሔር መርጦ የሰጣቸው ይመስላል፤ ነገር ግን ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ሰውን የሚንቅ እርሱ ራሱ የተናቀ
ነው፡፡
የራስ ዘር እስካልሆነ ድረስ ተቸግሮ እንኳ እስካለመርዳት የሚያደርስ ክፉ መንፈስ
በዘረኝነት የሚመጣ የንቀት መንፈስ ነው፡፡
2.
ልዩነትን (መለያየትን)
ይፈጥራሉ ፤
ንቀት ሲያድግ
ራስን ከሌላው መለየት ይመጣል፡፡ ታላቁ መጽሐፍም “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል” (ምሳ.18፥1) ይላልና፡፡ ዘረኛነት መጽሐፍ
ቅዱሳዊውን “የእርስ በእርስ” ግንኙነት በመለያየት የቅዱስ መንፈስ ሕብረት ይንዳል፡፡ ክርስቲያን “… ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል
ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” (ሮሜ.12፥18) ተብሏልና፥ ከሌሎች ጋር ስንኖር ልዩነትን ገንዘብ በማድረግ ሊሆን አይገባንም፡፡
መለያየት የሥጋ
ፍሬ ነው (ገላ.5፥20)፡፡ ዘረኛነት የእግዚአብሔር ትምህርት አይደለም፤ ይህን ትምህርት የሚያስተምሩ ደግሞ እግዚአብሔር የማይደግፈውን
ትምህርት ያስተምራሉና ከእግዚአብሔር አይደሉም፡፡
3.
ትኩረታቸው ሁሉ
የገዛ ነገራቸው ላይ ብቻ ላይ ያደርጋሉ፤
የራስን ዘር፣
የራስን ወገን፣ የራስን መልክ፣ የራስን ነገድ … ብቻ ማፍቀር አገባብ አይደለም፡፡ ለገዛ ወገን በልክ ማሰብ አገባብ ነው፤ የራስን
ብቻ እያዩ ግን ሌላውን መርሳት፣ መክዳት፤ ብሎም መቃወም እጅግ ነውር ነው፡፡ ዘረኛ ሰዎች ከራሳቸው ውጪ ላለው ወገንና ሕዝብ ምንም ስሜት አይሰጣቸውም፤ መለያየትን ብቻ
ሳይሆን የሚዘሩት ከእነርሱም ሌላ፥ ሌላ ነገር ትኩረታቸውን አይስብም፡፡
እንዲያውም ለእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች አለማሰብ እጅጉን የከፋ መሆኑን፥ “…
ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” (1ጢሞ.5፥8)
በማለት ቃሉ እጅግ ያስጠነቅቃል፡፡ ትኩረታችንም በክርስቶስ ኢየሱስ ከተሰበሰበው አንድነት ይልቅ ወደራሳችን በማድረግ፤ ቅዱሱን ቤተ
ሰብ ችላ ብንል ቅጣታችን እጅግ የከፋ መሆኑን ማስተዋል አይከብድም፡፡
4.
ሌላውን በጠላትነት
እስከመፈረጅ ይደርሳሉ፤
የዘረኛነት አንዱና እጅግ አስቀያሚ ገጽታ የአንዱን የአዳም ዘር ከሁለት መክፈሉ
ብቻ ሳይሆን የጠላነውን ወገን እስከጠላትነት ደረጃ በመፈረጅ ይጠመዳሉ፤ በሌላ ትርጉም ወንድማማችነት፤ እህትማማችነትን ፈጽሞ ያካክዳል፡፡
እኛ አገር ይህንን ማየት እጅግ ቀላል ነው፤ ለዘመናት የተጠመድንበት ነውራችን ነው፡፡
የራስን ዘር እንጂ የሌላውን ብሔር ለጋብቻ አለማጨት ወይም ለማግባት አለመፈለግ
አንዱ መገለጫው ሌላውን ዘር በጠላት እስከመፈረጅ ያለው ብሔርተኝነት አመለካከታችን ነው፡፡ ዘረኞች ሌላውን በጠላትነት የሚፈርጁት
እነርሱ እንጂ ሌላው እንደእነርሱ ምርጥና ንጹህ እንዳልሆነ እርግጠኞች ስለሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እርግጠኝነት፥ በእርግጥም መወገድ
ያለበት ነው፡፡
5.
ሌላውን ዝቅ አድርጎ
ማየት፣ ከሥራ ማፈናቀልና መግደልን እንደተፈቀደ ይቆጥራሉ፤
ብዙዎች ለከፋ ጥላቻ ተጋልጠው ውቡን የሥላሴ እጅ ሥራና እንደእነርሱ ሰው የሆነውን
ሰው ከመጥላት የሚደርሱት ይህ መርገም ነው፡፡ ምናልባት በዚህ መንፈስ የተጠመዱ ሰዎች ቆሞ የሚሄደውን ውድ ሰው ለምን ትጠላላችሁ?
ዝቅስ አድርጋችሁ ለምን ታያላችሁ? ከገዛ እንጀራቸውስ ለምን ታፈናቅላላችሁ? ለምንስ ትገድላላችሁ? ቢባሉ ምክንያቶቻቸው ከዓመታት
በፊት የተፈጸመውን ድርጊት እያሰላለሰሉ ለምን ሆነብን? ያኛውስ ወገን ለምን አደረገው? … የሚል የቂመኝነትና የበቀል ሃሳብን ነው
የሚያነሱት፡፡ ግና ለምንድነው ሌሎችን የሚጠሉትና የማይወዱት? መግደሉስ ለም አስፈለገ? በዚህች ምድር ብቻችንን ለመኖር ስለምንፈልግ
ነውን? መልሱ በሁላችን ሕሊና አለ፡፡፡
እኒህ ሰዎች ከዓመታት በፊት ልክ እንደተፈጸመው ግድያና ዕልቂት አሁንም ዕድሉን
ቢያገኙ አደረሱብን በሚሉት ዘርና ብሔር ላይ ተመሳሳይ ድርጊትን መፈጸም ይዳዳቸዋል፡፡ ምናልባትም ይህን ሲያደርጉ በታላቅ ድፍረት
ለሃሳባቸው ማስደገፊያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ከመጥቀስ የማይመለሱም ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም አንድ መንጋ፤
አንድ ቤተሰብ አድርጎናል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ጽድቅ የሆነውን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ እንዳናክፋፋ እንዲህ ካለ ኃጢአትና
ነውር በመራቅ ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡
ጌታ አባታችን አብ ሆይ! ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...
No comments:
Post a Comment