Friday 11 November 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ስድስት)

አማኞች፦ ከእኛ ምን ይጠበቃል?
    “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”፤ (ገላ.3፥28) የሚለው ቃል ከክርስቶስ ጋር አንድነት በዘር፣ በማኅበራዊ ኑሮ ደረጃና በጾታ ልዩነት ገደብ የሌለበት መሆኑን በግልጥ ያሳያል፡፡ ክርስቶስ የመሠረታት አዲስ ኪዳናዊት ሕብረት ልዩ የሚያደርጋት ይህ ነው፤ ምንም ምን ልዩነት በሰው ልጆች መካከል ፈጽሞ አያደርግም፡፡ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና”፤ (ሮሜ.10፥12)፥ የሚለው ቃል ደግሞ፥ ጌታን ለማመንና በእርሱ ለመዳን ምንም የዘር ቅድመ ሁኔታ አለመቀመጡን እናያለን፤ (1ቆሮ.12፥13 ፤ ኤፌ.2፥15 ይመልከቱ)፡፡

   በእርግጥም ክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ማኅበረሰብ[ቤተ ክርስቲያን] በአዲስ ሥርዓትና የአኗኗር ዜይቤ መመሥረቱን እናምናለን፡፡ ይኸውም ሁላችንም አንድ እንጂ የተለያዩ ዘሮች አይደለንም፡፡ ሁላችንም በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥረናል፡፡ የትኛውም የሰው ዘር የእግዚአብሔር መልክና አምሳል በእርሱ ላይ አለ፡፡ በእግዚአብሔር መልክ ስለተፈጠረም ሊጠላ (ዘኊል.35፥20)፣ ሊረገም (ያዕ.3፥9)፣ ሊገደል (ዘፍጥ.4፥15 ፤ 9፥6) ፈጽሞ አይገባም፡፡ ይልቅ ሰው ክቡር ፍጥረት ነውና፥ ክብርና አክብሮት ይገባዋል፡፡ አንድ ሰው ሰውን በመግደሉ፣ በመጥላቱና በመርገሙ እግዚአብሔርን ብሎም ባልንጀራውን ፈጽሞ መናቁን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊና እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲህ ካለ ነፍስን ከሚያሳድፍ ነገር ሊርቁ ይገባቸዋል፡፡
    ለዚህም ነው እንግዲህ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደአዲሱ ማኅበረሰብ[ቤተ ክርስቲያን] ስንመጣ ፈጽሞ የለወጣቸውና በእኛ እንዳይኖሩ ከገደላቸው ጠባያት አንዱ ወገንተኝነት ወይም ለአንድ ወገን ማድላትን ነው፡፡ እግዚአብሔር የአይሁድም የአሕዛብም የሁሉ ጌታ ነው፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረውን የልዩነትና የጠብ ግድግዳ ይዋሓዱና አንድ ይሆኑ ዘንድ መድኃኒት ክርስቶስ በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት በደሙ ጉልበት ናደው፤ አፍርሶም ፍጹም ምንም ልዩነቱ ሊታይ እስከማይችል ድረስ አንድ ያደረገን፤ (ኤፌ.2፥14)፡፡
   ከዚህም የተነሣ “በደሙ ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ተዋጅተን” (ራእ.5፥9) ነጻ ሆነናልና፥ በክርስቶስ ለአንዱ ለእግዚአብሔር መንግሥት የተሠራን[የታነጽን] ነን፡፡ ይህን መንገድ በመቃወም የተሻልን እንዲሆን ማሰብ ከጀመርን፥ የተሻለውንና የሚበልጠውን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ፤ አንድ የሆንንበትን የኪዳን ደም እናረክሳለን፤ በመቃወምም በተቃርኖ እንቆማለን፡፡
    መጽሐፍ ቅዱስ፥ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ”፤ (ኤፌ.4፥3) ይላል፡፡ ይህ አንድነት የተገኘው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት ባደረገው ፍጹም እርቅ ነው፡፡ “ሁለቱን ያዋሐደ ... በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው አፍርሶ ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥”(ኤፌ.2፥14-15) እንደተባለ ሁለት ሊቀራረቡ ያልቻሉ [ሊቀራረቡ የማይችሉ የነበሩ አካላት] በክርስቶስ አንድ ከመሆን በላይ ተዋሕደዋል፡፡ ይህን ሕብረት ክርስቲያኖች እንዳይበላሽና እንዳይናድ የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም  የመንፈስ አንድነት ከሰው ለሰው የሆነ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ለሰው የሆነ እንጂ፡፡
    በእርግጥም፥ “እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤”(ኤፌ.4፥1) የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ የፍቅር ልመና፥ አንድነቱ የወንጌልን እውነትን ባመኑና ክርስቶስን በተቀበሉት ዘንድ ቀድሞውኑ የነበረ እንጂ፥ አሁን የሚፈጠር ወይም የምንፈጥረው የመንፈስ አንድነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ አስቀድሞ ላመኑትና በእርሱ ላሉት ፍጹም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ይህን በደሙ መቤዠት ሰጥቷቸዋልና፡፡ የሊቀ ካህንነት ጸሎቱም ይህን እውነት ያስረግጣል፤ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ”፤ (ዮሐ.17፥20,-21)
   በዚህ እውነት ላይ በመቆም ለምድሪቱ መፍትሔ ሆነን የተቀመጥን እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡ ለምድሪቱ ከእግዚአብሔር የሚሆነውን መፍትሔ ባናመጣ ትውልዱ ለዘላለም ከመቅበዝበዙ፤ በኃጢአት ረካሁ ከማለቱ የሚያሳርፈው አንዳች ነገር የለውም፡፡ ለመልካም ነገር ስንጠበቅ፤ ፍሬ ያፈራሉ ስንባል ድንገት ሆምጣጤ ብንሆን፤ ኩርንችት ብናፈራ እግዚአብሔር ሌላ መፍትሔን ለማምጣቱ ሌላ መንገድን መጠቀሙ የሚቀር አይደለም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሐናና ቀያፋ ለቤቱ ክብርና ለቅዱስ ቅንአቱ እንደሚገባ ሆነው ባይገኙ፥ የገሊላዎቹን ዓሣ አጥማጆች ሐዋርያት አድርጐ አስነስቷቸዋል፡፡
   ዛሬም በብዙ ችግር ውስጥ ለሚዳክረው ሕዝባችን እውነተኛና የታመነ መፍትሔ ልናመጣ እንጂ፥ የተጠጋገነ መፍትሔን ልናበጅና ልናመለክት አይገባንም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ነገርን ማንሳት ያስፈልገኛል፤ በአንዳንዶች ዘንድ እንደመፍትሔ ይቆጠራልና፥ ስለሃይማኖት ብሔርተኝነት[1] ጥቂት ማለትን ወደድሁ፡፡ ለሁል ጊዜ እንደመንፈሳውያን ራሳችንን የምንቆጥር ከሆነ ለችግራችን ሁሉ መፍትሔና መላ ማምጣት ካለብን ከቅዱስ ቃሉና ከቅዱስ ቃሉ ብቻ ሊሆን ይገባናል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለሁላችን ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...





   [1] ቃሉን ያገኘሁት በስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ ሲሆን፥ በሃሳቡ ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ጽንአት ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ምሳሌዎችን በማንሳት ያትታል፡፡ በቀጣይ ክፍል ይህን ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ከተላክንለት መንፈሳዊ ተልእኮ አንጻር እንፈትሻለን፡፡ 

No comments:

Post a Comment