Sunday, 24 April 2016

ሆሳዕና - ንጉሥ ያለቀሰላት ከተማ (ሉቃ.19፥41)

Please read in PDF

“... ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ሉቃ.19፥41-44)


    መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል እንደመንፈስ ቅዱስ ተማሪ ቁጭ ብለን ስናጠና፥ ነቢዩ ኤርምያስ አልቃሻው ነቢይ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ኤርምያስን አልቃሻ ያሰኘው፥ የእስራኤልን መጥፋትና መማረክ ፤ የቤተ መቅደሱን መፍረስና የጐበዛዝቱን መውደቅ በተናገረ ጊዜ ሰሚ ማጣቱ ፤ የሕዝቡ አንገተ ደንዳናነት እጅግ ያበሳጨውና ያስለቅሰው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እጅግ ረጅም ጊዜ በማልቀሱ አልቃሻው ነቢይ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ነቢይ ሕዝብን ከእግዚአብሔር በአደራ ተቀብሏልና ሕዝቡ በነፍሱ ሳያርፍ፥ ሲቅበዘበዝ ፣ ሲንከራተት ... ሲያይ አብሮ መባዘኑ መንከራተቱ አይቀርም፡፡ እስኪመለሱም እጅግ በማዘን ይተጋላቸዋል ፤ በተመለሱም ጊዜ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ የነቢይ የዘወትር ደስታው የሕዝቡ በአምላኩ መንገድ መሆን ብቻ ነው፡፡   

     ኤርምያስ ከልጅነቱ ዘመን ጀምሮ የኢየሩሳሌምን መንገድ(ሥራዋን) ያይ ፤ ይመለከትም ነበር፡፡ በእርግጥም ስለኢየሩሳሌም፦ “አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል” (ኤር.4፥19) ፤ “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!” (ኤር.9፥1) “ስለ ነቢያት ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ” (ኤር.23፥9) እስኪል ድረስም ጥልቅ ሃዘን ይሰማው ነበር፡፡ ዘወትርም ከሕዝቡ ጋር ይኖር ነበርና ኤርምያስ የሚያየው ምንም እረፍት ፤ ሰላም አልሰጠውም፡፡ እንደእብድ ቢቆጠርም እርሱ ግን ከልቡ በማዘን ከእግዚአብሔር የመጣለትን የትንቢት ቃል ከመናገር ዝም አላለም፡፡ እስራኤል ግን ልትሰማው ፈጽማ ስላልወደደች ጥፋትና ፍርድን ተቀበለች፡፡
     “እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል” (ሐዋ.7፥37) የተባለለት ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደምድር የመጣበት ዋናው ምክንያቱ፥ “ለድሆች ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ተቀብቷል፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን ይሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ ያወጣ ዘንድ” (ሉቃ.4፥17) ነው፡፡ ብዙ ጊዜም፥ “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዝኖላቸው” (ዘኍ.27፥17 ፤ 1ነገ.22፥17 ፤ ሕዝ.34፥6 ፤ ዘካ.10፥2 ፤ ማቴ.9፥36 ፤ 14፥14 ፤ 15፥32 ፤ ማር.8፥2) ጌታ ኢየሱስ ቃሉን ብቻ የሚያገለግል ፤ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ያለበትን ትክክለኛ ሁኔታ ያሉበት ድረስ ሄዶ በርኅራኄ ያያቸዋል፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ሰማርያን (ዮሐ.4፥4-32) ፣ ጢሮስና ሲዶናን (ማቴ.15፥21) ፣ ኢያሪኮንና (ማር.10፥49) ሎችንም አገራት እያቋረጠ በዚያ ያሉትን ሰዎች በማየት እንኳ ከድሆችና ከችግረኞች ፤ ሊድኑ ከሚገባቸው ጋር ነበር፡፡ እጅግ ስለሚራራላቸውም ለነበሩባቸው ጥያቄዎች ሁሉ የተገለጠ መልስ ነበር፡፡ ሰማያዊ ንጉሥ ቢሆንም ለአባቱ ፈቃድ በመታዘዝ ደግሞም አገልጋይ ነው፡፡
     በምድር ሳለ ሊሞት እንደተቃረበ ባወቀ ጊዜ ወደኢየሩሳሌም ሊወጣ ወደደ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመቅረብ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት በመላክ፥ እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ካለችው መንደር ሄደው የታሰረችን አህያ ውርንጫም  ፈትተው እንዲያመጡለት አዘዘ፡፡ እነርሱም እንደቃሉ ፈትተው አመጡለት፡፡ እርሱም በአህያይቱና በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ከሕዝቡ ፣ ከደቀ መዛሙርቱና ከሕጻናት “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” የሚለውን ንጉሣዊ ምስጋናና አምልኮን ተቀበለ፡፡
     ይህንን ምሥጋና “ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ” ነቅፈውታል፡፡ በየዘመኑ ዳዊትን በማመስገኑ በልቧ እንደነቀፈችው ሴት አስተያየት ሰጪ ሜልኮላውያን መኖራቸው ይገርማል፡፡ ራሳቸው በዋናነት ሊሰጡ የሚገባቸውን ምሥጋና፥ ሌሎች ሲሠጡ ተደምረው በደስታ መስጠት ሲገባቸው መንቀፋቸው ያሳዝናል፡፡ ምናልባት ዛሬ እኛም እንዲህ ሆነን ይሆን? ለጌታ ብዙ ስለተዘመረ የምንከፋ ብዙዎች እኮ ነን! ሰዎች ሁሉ ጌታን በማመስገናቸው ተደምረን ልናመሰግን ሲገባን ዳር ቆመን የምንተቸው ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ ጌታ ልባችንን ያቅናልን፡፡ አሜን፡፡
    ጌታ ኢየሩሳሌምን ባያት ጊዜ፥ አለቀሰላት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በግልጥ ያለቀሰው ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ አልዓዛር በሞተ ጊዜና (ዮሐ.11፥35) ለኢየሩሳሌም ሆሳዕና ተብሎ አምልኮ በቀረበለት እለት፡፡ ንጉሡ ለምን ይሆን ያለቀሰው? ምን ይሆን የጐደለበት? ልቅሶውስ ምን አይነት ልቅሶ ይሆን?
     ጌታ ያለቀሰው እነርሱ ምድራዊ ነጻነትን የሚሰጣቸውን መስፍን እንጂ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደነገራቸውና ተስፋም እንደሰጣቸው መሲሑን ለመቀበል ስላልወደዱና በዚህም ምክንያት የሚያገኛቸውን ከባድ ቅጣትና ፍርድን አይቶ ነው፡፡ ኤርምያስን ዘመኑን ሁሉ የለቅሶ ያደረገው የእስራኤል ወደእግዚአብሔር ለመመለስ አለመውደድና በዚህም ምክንያት የሚደርስባትን መከራና ሰቆቃ በማየቱ ነው፡፡ ጌታም መከራውን ሲያይ እጅግ አለቀሰላት፡፡ የግሪኩ ቃል “አለቀሰ” የሚለውን ሃሳብ እንባ ከማፍሰስ ያለፈና ፍጹም የሆነን የነፍስ ሐዘንና ሰቆቃን ያሳያል፡፡
     አዎን! ኢየሩሳሌም ታስለቅሳለች፡፡ መሲሑን ልትቀበል አልወደደችምና ኢየሩሳሌም እጅግ ታሳዝናለች ፤ ንስሐ ገብታ ከሰላሟ ጋር ዛሬ መስማማትን አልወደደችምና ኢየሩሳሌም ታስለቅሳለች፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ጠፍታ ሳለ፥ መጥፋትዋን አምና ንስሐ ልትገባ አለመውደዷ አስለቅሶታል፡፡  በእርግጥም ንጉሡ ያዘነው መላው የሰው ዘር ንስሐ ባለመግባቱ ሊጠፋ ያለ መሆኑን እየተነገረው መስማት አለመቻሉ አምላክ ነውና ስለሚያውቅ በእውነት ያለቅሳል፡፡
     ትላንት ለኢየሩሳሌም ያለቀሰላት ጌታ ልቅሶውን አይታ ባለመመለሷ ፤ ንስሐም ባለመግባቷ በ70 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ በሮማውያን ወደመች ፤ ያ ትውልድም ሳያልፍ ቅጣቱን ተቀበለ፡፡ እግዚአብሔር ባለመመለሳችን ዛሬም ያዝናል፡፡ ወገኖቼ አሁን ቤተ ክርስቲያናችንና አገራችን በብዙ ለቅሶ ፤ በእልፍ ሐዘን የተከቡበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በብዙ መከፋፈል ውስጥ ናት ፤ አብያተ ክርስቲያናት ለእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ ከመሸነፍ ይልቅ በራሳቸው ሃሳብ የተጠመዱበት ዘመን ላይ ነን ፤ ጌታ ኢየሱስ የሞተለትና መከራ የተቀበለለት የሰው ልጅ መዳንና ከኃጢአት መፈታት ለብዙ አብያተ ክርስቲያናት ሁለተኛ ሥራ ከሆነ ዘመናት አልፈዋል፡፡
     ኢትዮጲያ ልጆቿን መሰብሰብ አቅቷት ስንት ልጆቿን የባሕር ልብና ለሰው የማይራሩት አንገት ቀንጣሽ ሰው በላዎች በሉባት? አገር ቤት ያሉትና በዲያስፖራነት መች ለእርሷ አንድነትና መዋደድ ይሠሩላታል? ዘርና አጥንት ፣ ድንበርና ወንዝ … እየቆጠሩ ይከፋፈላሉ እንጂ፡፡ ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጲያዬ ሆይ! የስንት ትውልድ እንባ ይሆን ያለባችሁ? እግዚአብሔርስ ስንት ዘመን ይሆን ያዘነብሽና እስክትመለሺ ብዙ ዘመናትን የጠበቀሽ? …
     ንጉሡ ዛሬም በሐዘን አለ ፤ ሁሉ ወደመስቀሉ ሥራ ወደሞቱ አልደረሱለትምና ፣ መሲሑን ወደማየት ክብር አልመጡምና ፤ ላለሽበት መከራና ሰቆቃ ሁሉ መፍትሔው አምላካዊ እንደሆነ መሪዎችሽና ልጆችሽ ፍጹም አምነው አልተጠጉትምና ንጉሡ አዝኖብሻል፡፡ የመጐብተኝሽም ወራት እንዳያልፍ ፊትሽን ወደእርሱ ዘወር አድርጊ፡፡ ንጉሡ ከቀረበለት ምስጋና ይልቅ (በባሕርይው ምስጉን ነውና)  ልቡን የነካውና ያስለቀሰው የኢየሩሳሌም ተጠርታ እንዳልተጠራች መሆኗ ነው፡፡ እኛስ የቱን ነን? እንድንድንበት በተሰጠን ልጁ ሞትና ትንሣኤ አምነን በደሙ ልብሳችንን ልናጥብ ዛሬ ወስነናል? ይህ የአፍ ሳይሆን የልብ ውሳኔ ይሻል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትና አገራችን እንድትፈወስ ንጉሡን ካሳዘንበት ሐዘን በንስሐ እንመለስ፡፡ ደግሞ አሁንም አናሳዝነው፡፡ አልያ ግን ከምንሰማው የባሰ (የባሰ የለም እንጂ) መምጣቱ አይቀርም፡፡ “በጥንት ምሳሌ፦ ከኃጢአተኞች ኀጢአት ይወጣል እንደ ተባለ” (1ሳሙ.24፥13) የንጉሡ ቁጣና ክፋታችንም ሳያጠፋን በእጁ እንወድቅ ፤ ንስሐም እንግባ፡፡
      አቤቱ ኢትዮጲያችን ልጆቿን ፤ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ደግሞ አንተን ብቻ በግርማህ እንድናይ አስተዋይ መንፈስን ላክልን፡፡ አሜን፡፡



No comments:

Post a Comment