Thursday 14 July 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
ምን እናድርግ?
1.     በእኒህ ማኅበራዊ የመረጃ መረቦች ላይ የሚጠቅመንንና መንፈሳዊ ነገሮቻችንን ብቻ ልናስተላልፍበት ፤ እንዲሁም የምናየውን ፣ የምናደምጠውን ፣ የምናነበውን ... ከእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ጋር የሚያቃርነን ነገር እንዳይሆን በብርቱ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የተጠራነው በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ነው ፤ እርሱ የጠራን ቅዱስ ነውና(1ጴጥ.1፥14-16)፡፡
    “አባታችን ሆይ”፥ ብለን እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠራን፥ እንደእግዚአብሔር ልጆች ለፈቃዱ ብቻ ልንታዘዝ ይገባል፡፡ እርሱ ፈቃዱ ቅድስና ነው፡፡ ቅድስና ከኃጢአት ከርኩሰት ተለይቶ ፤ ለእግዚአብሔር ብቻ መሆንን የሚፈልግ ዓቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችን በየትኛውም ጉዟችን “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ኢየሱስ ገብተናል፥ ለዚህ ኪዳናችን ታማኞች በመሆን ሁሉን እንደቃሉ ልንመረምር ይገባናል፡፡

2.    “ከዝሙት ሽሹ” (1ቆሮ.6፥18) “ሽሹ” የሚለው ሃሳብ፥ ለአንድ ጊዜ ለቀረበ ድርጊት ሳይሆን ዘወትር የምናደርገው ነገር ነው፡፡ ሁል ጊዜ መሸሽ ፤ በየትኛውም ጊዜ መራቅ ይገባናል፡፡ አንድ ጊዜ ጥሎ መሸሽ ጉብዝና ነው ፤ ቅዱስ ዮሴፍ የተፈተነው ለአንድ ቀን ፤ የሸሸውም ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቃሉ፦ “ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም” (ዘፍ.39፥10) በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ዘወትር የሚፈተነውን ፈተና ዘወትር ይሸሽ ፤ ይርቅም ነበር፡፡
   በየሚድያው የሚቀርቡትን የዝሙት ምስልና ድምጸቶችን አጥብቀን ልንሸሻቸው ፤ ልንርቃቸው ይገባናል፡፡ የሚያዳልጡ ሥፍራዎች ጐበዛዝትን ጭምር ይጥላሉና በራሳችን ከመመካት እጅግ መሸሽ ይገባናል፡፡ ይህን በማድረጋችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ባለማድረግ ለአምላካችን ክብር እንቀናለን፡፡ ቆሞ ከሚጋፈጥ ብርታት ቀሚሱን ጥሎ የሚሸሽ እርሱ መልካምን አድርጓል፡፡
   ቅዱስ ዳዊት ከዝሙት ባለመሸሹ ወይም የዝሙትን ክፉ ምኞት ባለመቃወሙ ምክንያት፥ በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነቱን ሸረሸረበት፡፡ “ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ” (2ሳሙ.11፥4) የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ንባብ ስናነብብ፥ ዳዊት የሥጋው ክፉ ምኞት ለዝሙት ኃጢአት አሳልፎ እንደሰጠው እናስተውላለን፡፡ የዓይኑ ክፉ ምኞትም የነፍሱን ንጽሕና አበላሸበት፡፡ የዓይኑን ክፉ ምኞት ምልከታ መቃወም ሲገባው አልተቃወመምና ፍጹም በልቡ ተሰናከለ፡፡ አደፈም፡፡ ነገር ግን በፍጹም ንስሐ ከኃጢአቱ ታጠበ፡፡ የልብ እድፈት በንስሐ እንጂ በምንም አይጠራምና ተግተን ንሥሐ በመግባት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመታጠብ ፍጹም ልንነጻ ይገባናል፡፡ ደሙ ለዘወትር ያነጻናልና (1ዮሐ.1፥7)፡፡
3.    ከማናውቃቸው ፤ እንዲህ ያለውን የክፋት ሥራ በመሥራት ከተጠመዱት ሰዎች ጋር መጣመድና መወዳጀት አይገባንም፡፡ ምሳሌ ብናነሳ፦ አሸባሪዎች ፣ ግብረ ሰዶማውያን ፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ፣ እንግዳ ትምህርት የሚያስተምሩ የሐሰት መምህራን ... በብዛት አባላትን የሚመለምሉት በእኒህ ማኅበራዊ ድኅረ ገጻት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመኑን እያየን የመዋጀት ሥራ እንድንሠራ፥ “... እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ” (ኤፌ.5፥15-17) ተብለናልና እግዚአብሔርን በመፍራት በትሁት ድፍረት ዘመኑን በሚዋጅና በሚነቅፍ ሕይወት ልንመላለስ ይገባናል፡፡
        ይልቅ ለሕይወቱ ምንም ዕቅድ እንደሌለው እንደሰነፍ ሰው ልንኖር አይገባንም፡፡ ክፉ በሆነው ዓለም ለቅዱስ እግዚአብሔር ልንኖርበት የምንችልበትን አጋጣሚ ሳንጠቀምበት እንዳያመልጠን ድኅረ ገጾችን በእግዚአብሔር ቃል ልንመላቸው ይገባናል፡፡ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናጠና ቅዱሳን ሐዋርያት በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ ወደአህዛብ ከተሞች ሄዶ ማስተማር የቻለው በዚያ ዘመን የነበረው የሮማ መንግሥት በሠራው የከተሞች መንገድ ላይ እጅግ በመፍጠን ፤ በዚያ ዘመን የተገኘውን ዕድል አሟጥጦ በመጠቀም ነው፡፡
     አስተውሉ!  እኒያ ጐዳናዎች ወንጌል ፤ ወንጌል የሸተቱትና እልፍ አእላፍ ሰማዕታት በዚያ ዘመን የተነሡት የጌታ ባርያዎች ሞኝ ሳይሆኑ የተገኘውን ዕድል ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ክብር ስላዋሉት ነው፡፡ እኛም እንዲሁ እግዚአብሔር በዘመናችን ለወንጌሉ እውነት ነፍሱን ፣ ትዳሩን ፣ ኑሮውን ፣ ሥራውን የሰጠ ትውልድ እንዲያስነሣልን ድኅረ ገጻትን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ልንመላቸው ይገባናል፡፡ በዝሙትና እርቃን ምስሎችን በማየት የተጠመዱና ለእኛም የሚልኩ ባልንጀሮች ያሉን ወገኖች ደግሞ አስቀድመን ራርተንላቸው ልንመክራቸው ፤ ልንጸልይላቸው ፤ ልንገስጻቸውም … ካልተመለሱ ደግሞ ልናስመክራቸው ፤ እንቢ ካሉ ግን ለነፍሳችን ወጥመድ እንዳይሆኑብን ልንሸሻቸውና ልንርቃቸው ይገባል፡፡
      ቅዱስ አብ አባት ሆይ! ስረዳኸን አምልኮ ፤ ስግደት  ፤ ውዳሴ ፤ ስባሔ እናቀርብልሐለን፡፡

ተፈጸመ፡፡

1 comment:

  1. and thank you ! facebook ባንጠቀም አይሻልም ?

    ReplyDelete