Thursday 28 July 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል አንድ)

Please read in PDF
ያለነው እንደሸማኔ መወርወርያ በሚፈጥነውና በሚቸኩለው ዘመን ፤ ኃጢአትም ከተመሸገበትና ካደባበት ሥፍራው ላይ መገለጥና “እነሆ አለሁ” በሚለው አካላዊ ማንነቱን ማሳያ ዘመን ላይ ነን፡፡ ከቀደመው ዘመን ይልቅ የኃጢአት ጽዋ በዓለም መካከል ብቻ ሳይሆን “የእግዚአብሔር ነን” በሚሉትም መካከል እየሞላና እየፈሰሰ መሆኑን እያስተዋልን ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ፦ “ … ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” (2ጴጥ.3፥9) እንዲል እየሆነ ያለው እግዚአብሔር ስለሌለ አይደለም፡፡

       በዚህ አጭር ጽሁፍ ትርጉም ፣ በአለም ላይ የነበረውን እሳቤና ያስከተለውን አሉዊ ፣ ኢ ሥነ ምግባራዊና ኢ ሞራላዊ ፤ እንዲሁም ኢ ሰብዓዊ ተጽዕኖዎችን እናይበታለን፡፡ በተለይም “በሰዎች ልብ ሥፍራ ባላቸው ጸሐፍትና መሪዎች” ዘንድ ምን አይነት እይታ እንዳለው በጥቂቱ ለማሳያ በሚሆንና ትኩረታችንን ማስፋት እንድንጀምር በሚያስችል መልኩ በጥቂቱ ዳስሰናል፡፡
      በተለይም እኛ አማኞች ዘረኝነትንና ብሔርተኝነትን በተመለከተ ሊኖረን ስለሚገባን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ ሊሆኑ የሚገባቸውን ቁም ነገሮች በሚገባ አስቀምጠናል፡፡ ይህን በማንበብም መልካም የሆኑ ነገሮችን እንደምታገኙበት አምናለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ትርጉም
      “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሣ ራስን የተሻለ አድርጐ በመገመት ሌላውን መናቅ ፣ መጨቆን ፣ የበታች አድርጐ ማየትና ሲቻልም ማስገበር ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የዘረኝነት ተግባርም በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ ጐሳዎች ፣ ነገዶች ወይም ዝርያዎች ወይም ደግሞ በዘር ፣ በቀለም ፣ በመሳሰሉትና በተለያዩ ምክንያቶች ላይ ተመርኩዞ ልዩነቶችን በመፍጠር የአንድ አገር ሕዝብ በሌላው አገር ሕዝብ ላይ ሊፈጽመው የሚችል ነው፡፡ … በቋንቋና በባህል ልዩነት ምክንያትም የዘረኝነት ድርጊት የሚፈጸምባቸው ሁኔታዎች ብዙ ናቸው፡፡” (ማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ፤ 1978 ፤ አዲስ አበባ ፤ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ፤ ገጽ.413-414)
   በሌላ ዕይታ ዘረኛነትን፦  “የዘር ልዩነት ፤ በዘር መድልዎ [1] ላይ የሚፈጸም የተመሠረተ አስተምህሮ ፥ ፖሊሲ አመለካከት፡፡” በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ [2] በዚህ የአተረጓጐም ዘይቤ ዘረኛነት ድርጊቱ ራሱ ትምህርት የተበጀለት ፤ “ፖሊሲ የተቀረጸለት” መሆኑን እስናስተውላለን፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች ይህን በመንተራስ “ዘረኝነት አንድ የኅብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ በዘር ካገኘው ውርስ የተነሣ የሚፈጸም የተደራጀና የተቀናበረ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ” እንደሆነ በስፋት ሲተነትኑት የሚስተዋሉት፡፡ በእርግጥም ዘረኝነት ቀለል ተደርጐ ልማድና ድርጊት ደረጃ ላይ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል ፤ ትምህርት ተበጅቶለት በሁሉ ዘንድ ያለ መሆኑን እያየን ነውና፡፡
      ይኸንኑ አመለካከት በሌላ እይታ፥ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “መንደርተኛነት” በማለት ይገልጡታል ፤ ሲያብራሩትም “ … መንደርተኛነት ምንድር ነው? ዘር ነው ፤ ቋንቋ ነው ፤ ሃይማኖት ነው ፤ ባህል ነው ፤ መንደርተኛነት ባህል ምንድን ነው? ብሎ አይጠይቅም ፤ መነሻውም መድረሻውም የመንደሩ ቋንቋ ፣ የመንደሩ ሃይማኖት ፣ የመንደሩ ባህል ከሌላው ሁሉ የተሻለና የበለጠ ነው የሚል ጠባብ አስተያየት ነው ፤ መነሻውም ሆነ መድረሻው ልዩነትን ማጉላት ነው፡፡ … ” በማለት ያስቀምጡታል፡፡ [3]
     ብሔርተኝነት ለብሔር የሚኖረን አመለካከት ወደሌላ ጽንፋዊ ጫፍ ረገጥ አመለካከት ሲያድግ ብሔርተኝነት (tribalism) እንደሚባል ብዙዎች ሲያነሱ “ሕዝቦችን በብሔር የሚከፋፍል ፣ የአንዱ ብሔር ሕዝብ የሌሎች ብሔሮችን ሕዝቦች በጥላቻ ፣ በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲመለከት የሚገፋፋ” እንደሆነ ማርክሳዊ ሌኒኒናዊው መዝገበ ቃል ያትታል፡፡ ይህንኑ ሃሳብ “ሕዝቦችን በብሔር (ወይም በነገድ ፣ በጐሣ ፣ በወገን) በመከፋፈል የአንዱ ብሔር ሕዝብ ከሁሉ በላይ እንደሆነ በመቍጠር ሌሎችን ለመግዛት መብት አለው የሚል ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በአጭሩ “የእኔ ብሔር ከአንተ ብሔር ይሻላል” እንደማለት ነው፡፡” ይላል፡፡ [4]
       በጠቅላላው ዘረኛነት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ወይም መለያየትን ፤ ከሁሉ ይልቅ ራስን አለልክ በመውደድ ሌላውን ወግድ የማለት ፤ እኔና የእኔ ነገሮች ሁሉ ከሁሉም ይበልጣሉ ፤ በሁሉ ነገር ቅድሚያ ሊሰጠን የሚገባንና ልንደመጥ የሚገባን እኛን ብቻ ነው ፤ ከእኛ ውጪ እንደእኛ ሊኖር የሚገባ የለም የሚል ክፉና የጠለቀ የክፋት ትምህርትና ድርጊት ነው፡፡ አንዳንዶች ወገንንና ዘመድን ፤ የገዛ አገርን መውደድና ማክበርን ከዘረኝነት ጋር ደባልቀው ሊያቀርብ ይቋምጣሉ፡፡ ማንም ለወገኑ ፣ ለዘመዱ ፣ ለአገሩ ልዩ ስሜትና ፍቅር ሊኖረው ይችላል ፤ ይህንንም ተቃዋሚ የክርስትና ትምህርት የለም፡፡ የምንቃወመው ግን የሚበልጠውንና የሰፋውን የክርስትና ትምህርት በመቃወም ለራስ ወገንና አገር በማድላት ሌላውን እንደሁለተኛ የማየትና የመጠርጠር ስሜት ሲመጣ ነው፡፡
      በዓለማውያን መድረክ ምርጥ ከተባሉትም ይሁን ከድሆቹ(ከተናቁቱ) ብንወለድም ፤ ወደዚህ ዓለም ብንመጣም በክርስትና አስተምኅሮ ሁላችን የአንድ አባት ልጆች ነን፡፡ ማንም ከሌላው የሚበልጥበት  አንዳችም ነገር የለውም፡፡
ጌታ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል ...




     [1] የዘር መድልዎ የሚለውን ቃልም በዘር ላይ ተመስርቶ በሰዎች ላይ የሚደረግ አድልዎ፥ ተጽዕኖ” በማለት አስቀምጦታል፡፡ (ኣማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.437)
   [2] ዝኒ ከማሁ(ይህም እንደላይኛው ነው)
   [3] መስፍን ወልደ ማርያም ፤ መክሸፍ እንደኢትዮጲያ ታሪክ ፤ 2005 ፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚው ያልተጠቀሰ ፤ ገጽ.170-171
   [4] ምኒልክ አስፋው ፤ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ርእሰ ጉዳዮችና ተግዳሮቶች ፤ 1999 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ራእይ አሳታሚ፡፡

No comments:

Post a Comment