Please read in PDF
እንኳን ለንስሐ የሚሆን ዘመን ተጨመረላችሁ!!!
ቅምጥልነትን፥ ቅዱስ ጳውሎስ “ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች
ናት” (1ጢሞ.5፥6) በማለት ይገልጠዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት መሞትን በሕይወት ቆሞ መሄድ አይተካውም፡፡ መንፈሳዊ ሞት ወደር
የለሽ እጅግ አስጨናቂ ሞት ነው፡፡ ቆሞ በመሄድ ማማር የለም፤ በቁም “በውጭ አምረው የሚታዩ” ሁሉ ደመ ግቡዎች አይደሉም፤ ውስጣቸው
“ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ሊመስሉ ይችላሉና”፤ (ማቴ.23፥27)፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች በሕይወት የሞቱና
ሕያውና የሚያድን ድምጽ መስማት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
ጌታችን “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን
መንግሥት ስበክ” (ሉቃ.9፥60) በማለት የተናገረው፥ በመንፈስ ሙት የሆኑ በሥጋ ሙት የሆኑትን ሊቀብሩ እንዳሉና በመንፈስ ሕያው
የሆነ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት በብርታት ማገልገልና መስበክ እንዳለበት አጽንቶ ሊናገር ወዶ ነው፡፡ አስተውሉ! ጥቂት ቅምጥልነት
ለምን አይነት መንፈሳዊ ሞት አሳልፎ ሊሰጠን እንደሚችል፡፡
ንጉሥ ዳዊት ሁሉንም “ጠላቶቹን” ቢያሸንፍም፥ አሞናውያንን [1]
ግን ገና አላሸነፈም ነበር፤ (2ሳሙ.10፥19)፡፡ እኒህ የቀሩ ጠላቶች ቢኖሩትም ግን፥ “እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት
ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ወደጦርነቱ ሰድዶ ለራሱ ግን በኢየሩሳሌም
ቆየ፤” (2ሳሙ.11፥1) አመሻሽ ላይ በዚያ ምቹና ተስማሚ ሰገነት ላይ (1ሳሙ.9፥25) ዳዊት ይመላለስ ነበር፡፡ በሌላ ንግግር
ወደዳዊት ሕይወት ቅምጥልነት ሰተት ብሎ ገባ ማለት ነው፡፡ “በልክ መዝናናት” አንድ ነገር ነው፤ ለሥጋዊ ተድላና ለቅምጥልነት ተዘልሎ
መቀመጥ ግን ራስን በወጥመድ ውስጥ የማስገባት ያህል እጅግ አደገኛ ነው፡፡
በመንፈሳዊ ዓለም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላት የሆኑትን አሞናውያንን ከመዋጋት
ይልቅ፥ ዳዊት ተዘናግቶ በምቹ ሥፍራ ሲዝናና ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ሕይወት በጌታ ትምህርት፥ “በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን
የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል፤” (ማቴ.13፥22) ያለውን ይመስላል፡፡
ለዘወትር በቃሉ አለመትጋትና በተጋድሎ አለመጽናት እንዲህ ያለ ተላላነትን እንድንለማመድ ያደርጋል፡፡
ዘመን መለወጫም ይሁን በሌሎች በዓል ቀናት በእኛ አገር ልማድ ለኃጢአት
የተፈታ ሆኖ መኖር ተለምዷል፤ ሥርም ሰዷል፤ ምናልባትም እንደልዩ የባሕል መገለጫም ጭምር ተቆጥሮ እናየዋለን፡፡ “የእግዚአብሔር
ሕዝቦች” ጭምር በዚህ ነውር ተጠላልፈው ሲወድቁ እናስተውላለን፡፡ የተሰጠንን ዕድሜና ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርና ለቅድስና ማዋል
ሲገባን፥ ነገር ግን የተሰጠንን ቀን ብቻ ለእግዚአብሔር ክብር መታሰቢያ እንዲሆኑ ለአምልኮ ይበልጥ ራሳችንን በምናዘጋጅበት ቀን
እንኳ ሳይቀር ራሳችንን በዚህ ዓለም ነገር አባክነን ስንኖር ይታያል፡፡
ከ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 11 እስከ ምዕራፍ 24 ላይ ያሉትን ምንባባት በሚገባ
በማስተዋል ብናጠና፥ በዳዊት ሕይወት ላይ የታየው እጅግ ከባድ መንፈሳዊ ውድቀት መነሻው ይኸው ቅምጥልነትን መውደድና በዚሁ ነገር
ተጠምዶ መባከነኑን በመጀመሩ ምክንያት ነው፡፡ ትንንሽ የሚመስሉ የኃጢአት ጅማሮዎች ለትልልቅ መንፈሳዊ ውድቀቶቻችን መነሻና መድረሻዎች
እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንዲያቦካ፥ ጥቂቱም ኃጢአት ብዙውን “በጐነታችንን” እንደሚያበላሸው
መርሳት የለብንም፤ (1ቆሮ.5፥6)፡፡
ለምሳሌ፦ ብዙዎች ወደዝሙት ዓለም ጭልጥ ብለው የገቡትና ዛሬም ድረስ መውጣት
ተስኗቸው በብዙ ራሳቸውን በስቃይ የሚወጉት፥ ጅማሬያቸው ዕርቃን ምስሎችን ከማየት፣ የዝሙት ወሬን ከማውራት፣ መሲባዊ ነክ የሆኑ
መጻሕፍትን ከማንበብ … ቀላል ከሚመስል ነገር ጀምረው ሊሆን ይችላል፤ ዛሬ ግን እንዲያ ቀላልና ወዲያው ሊተውት የሚቻላቸው አይደለም፡፡
ሰይጣን የሥጋ አምሮታችንን የሚቀሰቅሰውና ነፍሳችንን የሚያጠምደው ከማናስተውለው ጥቂት ስህተት ውስጥ ነው፡፡
ዳዊት ከ”ተጋድሎ“ ተዘናግቶ በሰገነቱ ሲመላለስ፥ “በሰገነቱ ሳለ አንዲት
ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች፤” ይለናል ታላቁ መጽሐፍ የዳዊትን የውድቀት መጀመርያ ሲነግረን፡፡ ኃጢአት፥
“ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው”(ምሳ.7፥26) ዳዊትም በእርስዋ ተወግቶ ወደቀ፡፡ ብዙ
ሚስቶች ያሉት ዳዊት የስርቆሽ ውኃ ጣፈጠው፤ ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ እድምተኞችዋም በሲኦል ጥልቀት እንዳለ አላወቀም፤
(ምሳ.9፥17-18)፡፡
ዳዊት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጠላቶች ከማሳደድ ይልቅ አንዲት ሴት ወደማሳደድ
ወረደ፤ ጠላት ትልቁን አስጥሎ ትንሹን የሚያስጨብጠን ሊያዋርደን እንጂ እንዲቀለን ፈልጐ አይደለም፡፡ የዳዊት የውድቀት ሕይወት እኛም
እንማርበት ዘንድ ነው የተጻፈው፤ ልክ የእስራኤል ልጆች ውድቀት “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን
ሊገሥጸን ተጻፈ፡፡” (1ቆሮ.10፥11) እንደተባለ፡፡ ዝሙት የዳዊትን ሕይወት ገዛው፤ ስለዚህም ስለሴቲቱ መመርመር ጀመረ፡፡ የኃጢአት
ሃሳቡን ከጫፍ ሊያደርስ እጅግ ቸኰለ፡፡
“ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፥
በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው፡፡ … ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም
የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ … እግዚአብሔርን እንዳትረሳ
ተጠንቀቅ፤” (ዘዳግ.6፥7 ፤ 11-12) የተባለውን የሕጉን ቃል ፈጽሞ ዘነጋ፡፡ እንዲያውም አባቱ በረሳው ጊዜ ያስታወሰውንና ለንግሥና
የመረጠውን ጌታ ፈጽሞ ዘነጋው፡፡ ብዙ
ጊዜ በኃጢአት የምንጨማለቀውና እንደታናሽ ነገር ቆጥረን ኃጢአትን እንደውኃ ጭልጥ አድርገን ለመጠጣት የምንቸኩለው፥ የተደረገልንን
ፈጽሞ ስንዘነጋ ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የተገረገልንን የመስቀል ላይ ውለታ በትክክል ብናስብ፥ እንኳን ለክፉ ነገር መልካም የሆነውን
ለመሥራት ጊዜው ባልበቃን!!!
ዳዊትን እግዚአብሔር ሲመርጠው በሳሙኤል አንደበት ምን እንዳለው አስተውሉ!
“እግዚአብሔር
እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤” (1ሳሙ.13፥14) እንደእግዚአብሔር ልብ ቅን የነበረው ሰው በኃጢአት ምክንያት ተመረዘ፡፡ እንዳይወድቅ
መጠንቀቅ ሲገባው፥ (1ቆሮ.10፥12) እግዚአብሔርንና ቃሉን በማቃለሉ ፍጹም ተሰናከለ፡፡ ዳዊት በመጀመርያ አታመንዝር የሚለውን
ኃጢአት ተላለፈ፤ ቀጥሎ ኃጢአቱን ለመሸፈን ከመዋሸቱም በላይ ኦርዮንን [2]
ኢላማው አደረገ፡፡ ስለዚህም ወደሦስተኛው ኃጢአት ተሸጋገረ፤ አትግደል የሚለውን ወደመተላለፉ፡፡
ከብዙ ሠራዊት ጋር እንዲዋጋ የተጠራው ንጉሥ፥ ከአንድ “አንዲት በግ ካለው
ድኃ” (2ሳሙ.12፥3) ጋር ውጊያ ጀመረ፡፡ እንግዲህ ኃጢአት ሲያዋርደን የሚያዋርደን እስከመጨረሻው ነው፡፡ የኃጢአት መንገድ ፈጥነው
በንስሐ ካለቆሙት ከቁልቁለት መንገድ ይልቅ ወደጥፋት ያንደረድራል፡፡
ከኃጢአት መንገዳችን ብንመለስ እንኳ፣ የእግዚአብሔርን ይቅርታና ምሕረት
ብናገኝም በኃጢአታችን ከሚያመጣብን መዘዝ(ቅጣት) ከመቀበል ግን ፈጽሞ አናመልጥም፡፡ በዳዊትም የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ዳዊትን ለመቅጣት ምንም መሸፋፈኛን አልሰጠም፤ ኃጢአቱንም በመሸፈን ሊራራለት አልወደደም፡፡ ጸሐፊውም ምንም ሳይራራ በደልና ነውሩን
ግልጥልጥ አድርጐ በመጻፍ ለኃጢአት ያለውን ግልጥ አቋሙን ያሳየናል፡፡
ብዙዎቻችን ለኃጢአት ያለን አቋም ጠማማ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል
ያልተደገፈ ልምሾ ነው፡፡ አንድ ሰው በግልጥ ኃጢአት ቢያዝና ለብዙዎች መሰናክል ምክንያት ቢሆን፥ በግልጥ ንስሐ እንዲገባ ከመምከርና
በግልጥ ከመቃወም ይልቅ ተለሳልሰን ዝምታን እንመርጣለን፡፡ እንዲያው አንድ ሰው ከመካከላችን በርትቶ ቢቃወምና ቢገስጽ በዚያ ሰው
ላይ ተቃውሞአችንና ጥላቻችን የጸና ይሆናል፡፡ ለኃጢአት ምንም አይነት ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው ከመጀመርያዎቹ ሰዎች ከአዳምና
ከሔዋን መረዳት እንችላለን፡፡
አዎን! እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ጭካኔና ፍርድ
በልጁ ላይ ከተደረገበት ከዚያ የመስቀል መከራ መረዳት እንችላለን፡፡ ስለኃጢአታችን ሥርየት ልጁን እንዲያ እንዲዋረድ ፈቅዷል፤ በእውኑ
አሁን በሚሆነው ኃጢአት ተስማምቶ ዝም ያለ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እንድንመለስ ስለሚፈልግ ብቻ ነው፡፡ ዘመን የሚጨመርልን እንድንመለስ፤
መንገዳችንን በፊቱ እንድናቀና ብቻ ነው እንጂ በቅምጥልነት እንድንጸና አይደለም፡፡ አልያ ግን፥ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ
ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ
ያለው የእሳት ብርታት አለ፤” (ዕብ.10፥26-27) እንደተባለ ባንመለስ የሚጠብቀን ፍርድ አስፈሪ ነው፡፡ እንኪያስ በልጁ አምነን
ሕይወት ይሆንልን ዘንድ ከዓመጻችን እንመለስ፡፡
ጌታ አብ ሆይ! በልጅህ ቤዛነት ማስተዋልን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
[1] አሞን ሎጥ ከትንሿ ሴት ልጁ የወለደው ልጅ ሲሆን፥ እርሱም የአሞናውያን ሁሉ አባት ነው፤ (ዘፍ.19፥38)፡፡ እኒህም
ብዙ ጊዜ እስራኤልን የሚቃወሙ ነበሩ፤ (መሳ.3፥13 ፤ 10፥6 ፤ ነህ.2፥10)፡፡ በተለይም የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት
ወደአገራቸው ሲመለሱ በመንገድ ሳሉ ሊራገሟቸው ካሰቡ ሕዝቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሞናውያንና ሞዓባውያን “በመስጴጦምያ ካለው
ከፋቱራ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግምህ ዘንድ አምጥተውብሃልና አሞናዊና ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤
እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ለዘላለም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፡፡” (ዘዳግ.23፥3) የሚል ክልከላ ተጥሎባቸዋል፡፡ ዳዊት
ይህን አምላካዊ ቃል ነበር በመናቅ ስለቅምጥልነቱ የተላለፈው፤ የረሳውም፡፡
ተባረክ
ReplyDeleteበርታ
ReplyDelete