Wednesday 1 November 2023

ነገረ ሥላሴን የምናጠናበት ምክንያት (ክፍል ፭)

Please read in PDF

ካለፈው ቀጠለ …

 4. ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ስናጠና ልናስተውላቸው የሚገቡ ቃላት

ቃላትን በትክክል መረዳት ወይም ትክክለኛ ትርጕማቸውን ማወቅ ወደ እውነተኛ ዕውቀት ያደርሳል። በተለይ ደግሞ ትምህርተ ሥላሴን ስናጠና፣ በጥንቃቄ ልናጠናቸው የሚገቡ ቃላት አሉ። እኒህም፦

4.1. ሥላሴ፦ በአጭር ቃል፣ “ሥላሴ” የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ምንባባት ውስጥ የለም። ነገር ግን ለቃሉ ሳይኾን ለትምህርቱ ፍጹም ዕውቅናን እንሰጣለን። ምክንያቱም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሥላሴ ትምህርትና መገለጥ በስፋት አለና።

“በግእዝ ቋንቋ ቃሉ “ሦስትነት” ማለት ነውና በትምህርተ መለኮት ጥቅም ላይ ሲውል በአንዱ በእግዚአብሔር ሦስት አካላት እንዳሉ ያሳስባል። በ2ኛው መቶ ዓመት የአንጾኪያ ጳጳስ የነበረው ቴዎፍሎስ[1] በግሪክ ቋንቋ “ትሪአስ” እና ተርቱሊያን[2] በላቲን ቋንቋ “ትርንታስ” (በእንግሊዘኛ TRINITY) ስለ እግዚአብሔር ሲያስተምሩ፥ አካላት ሦስትነትን ለማመልከት ተጠቀሙባቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምረው የቤተ ክርስቲያን አባቶች በእነዚህ ቃላት እየተጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለማብራራትና ለመወሰን ሰፊ ጥረት አደረጉ።”[3]

አንዳንድ ሰዎች፣ ““ሥላሴ” የሚለው ቃል፣ ቃል በቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለምና ትምህርቱም ሐሰት ነው” ይላሉ። ነገር ግን አንድ ሰው “ሥላሴ” የሚለውን ቃል፣ በግሉ አልቀበልም ማለት ይችላል። ኾኖም “ሥላሴ” የሚለው ቃል የሚወክለው፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ከኾነ፣ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ደግሞ የሚወክለው በመላው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ ያለ ነው። ስለዚህ ቃሉ ትምህርቱን እጅግ የሚያጐላ እንጂ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወይም እውነት ላይ አንዳች የሚጨምረው እንግዳ ትምህርት ወይም እውነት የለም።

“ሥላሴ የሚለው ቃል የሚወክለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ክዶ የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ወይም የዘላለም ሕይወት አለኝ የሚል አስተሳሰብ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም።”[1]

“የሥላሴ ትምህርት በክርስትና እምነት መሠረታዊ ነው። ያለ ሥላሴ የእምነት መሠረትነት ክርስትና የሚባል እምነት የለም። የስህተት ትምህርት የመጀመሪያውና ዋናው የችግር ምልክቱ ስለ ሥላሴ ያለው አስተምህሮ የተሳሳተ ወይም የተዛባ ኾኖ መገኘቱ ነው።”[2]

“ትምህርተ ሥላሴ በክርስትና እምነት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከኾኑት አስተምህሮዎች አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥላሴ የሚያስተምረውን ማጥናት እግዚአብሔርን ስለ መሻት ለምናነሣቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች ትልቅ አብርሆት ይሰጠናል።”[3]

“ሥላሴ” የሚለው ቃል ሦስትነትን እንጂ አንድነትን የሚያመለክት ቃል አይደለም። ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ሥላሴ የሚለውን ቃል በውስጡ አንድነትንም መያዙንም ለማመልከት፣ “ሥሉስ ቅዱስ ወይም ቅድስት ሥላሴ” ማለትም “ልዩ ሦስትነት” በማለት ይጠቅሳሉ። በእርግጥም ሥላሴ በውስጡ ሦስትነትን ብቻ ሳይኾንም አንድነትንም በውስጡ የያዘ ነው። “ቅድስት ሥላሴ” ሲባል ደግሞ፣ አንዳንዶች ደግሞ የሥላሴን እናታዊነት[4] ጠባይ ማለት ርኅራኄነት ለማመልከት ነው ይላሉ።

ከዚህ ጋር አያይዘን ማንሳት የሚገባን ሌላው ነገር፣ ሥላሴን ስንጠራ “ሥላሴዎች” ብሎ መጥራት እጅግ የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም ሥላሴ የሚለው ቃል ራሱ ሦስትነትን የሚያመለክት ነው፤ “ሥላሴዎች” ከተባለ ደግሞ “ሦስቶች” የሚለውን ትርጕም ይይዛል። ይህም ወደ ዘጠኝ ሊያድግ ይችላልና።

“ሥላሴ” ማለት “ሦስትነት” ማለት እንጂ፣ “ሦስት” ወይም “ሦስቶች” ማለት አይደለም። ስለዚህ፣ ሦስትነት በብዙ ቍጥርም ኾነ በአንቱታ አትጠራም፤ የብዙ ቍጥር የሚያስፈልገው የሥላሴ ስም እንጂ፣ ሥላሴ አይደለችም። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን እንጂ፣ ሥላሴንስ በብዙ ቍጥር መጥራት ስሕተት ነው፤ ሦስትነትን በብዙ ቍጥር መጥራት ይኾናል። እንኳን በብዙ ቍጥር በወንድ ጾታም መጥራት ልክ አይደለም። የቀድሞ አባቶች ትክክሉን ምስጢር ተረድተው ለሥላሴ (ለሦስትነት) “ቅድስት” የሚል የአንስታይ ጾታ ቅጽል ሰጥተዋታል … ቅድስት ሦስትነት ሲሉ “ቅድስት ሥላሴ” ብለዋል። የኛ ዘመን አባቶች ግን፣ “ለሥላሴ የአንስታይ ጾታ ቅጽል የተሰጣቸው ማለት፣ ‘ቅዱስ ሥላሴ” ወይም ‘ቅዱሳን ሥላሴ’ በማለት ፈንታ ‘ቅድስት ሥላሴ’ የተባሉት እንደ እናት ዓለምን ስለ አስገኙ ነው” ይላሉ። እንዲህ የሚያስተምሩ መምህራን የአባቶችን ትምህርት በትክክል አልተረዱትም።[5]

እናም ስለ ሥላሴ ስንናገር እንዲህ እንላለን፣ እግዚአብሔር በኅላዌው በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አካልነት ይኖራል፤ ኾኖም፣ አንድ አምላክ ነው። በሌላ አገላለጥ፣ እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም በሦስት አካላት ማለትም በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ይኖራል፤ እያንዳንዱ አካል ፍጹም አምላክ ነው፤ ኾኖም አምላክ ነው። ስለዚህም ሥላሴ የሚለው ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለመኖሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አያስተምርም ማለት አይደለም።

“እግዚአብሔር በዘላለማዊ ባሕርዩ አንድ ነው፤ ነገር ግን በዚህ ባሕርዩ ሦስት አካላት አሉ፤ እነርሱም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ናቸው። እነዚህ ሦስቱ አካላት እንደ ሦስት ነጠላ ሰዎች የተነጣጠለ ሦስትነት የላቸውም። ነገር ግን አንዱ የመለኮት ባሕርይየሚገለጥባቸው ናቸው።”[6]

እንግዲህ “ሥላሴ” የሚለው ቃል፣ ከእነዚህ ኹለቱ አባቶች በኋላ፣ አያሌ አባቶች በተለይም ባስልዮስና ኹለቱ ጎርጎርዮሶች (ጎርጎርዮስ ዘቀጰዶቅና ዘእንዚናዙ) በምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ እስኪፈጥር ድረስ ትምህርቱን በጥልቀት አብራርተዋል።

 

ይቀጥላል …



[1] ተስፋዬ ሮበሌ፤ የአስተምህሮተ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት፤ ገጽ 11

[2] መልሳቸው መስፍን(ዶ/ር)፤ እግዚአብሔር መለኮት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ Cornelius Van Til, An Introduction to Systematic Theology, January 1, 1974, Philipsburg: Presbyterian & Reformed Pub Co. p. 223

[3] ዋይኔ ግሩደም፤ ሥልታዊ ነገረ መለኮት፤ ገጽ 244

[4] በግዕዝና በሌሎችም አንዳንድ ቋንቋዎች ቃላት በጾታ ተራ የሚመደቡት በሚያመለክቱት ከሦስቱ በአንዱ ምክንያት ነው፤ (1) የሕያው ፍጡር ተፈጥሮው ወንድ ወይም ሴት ሲኾን፣ (2) የነገሩ መጠን፣ ትልቅ ወይም ትንሽ ሲኾን፣ (3) የቃሉ ዓይነት ወይም አፈጣጠር፤ እነዚህ ሦስቱ ቃሉን በጾታ ያስመድባሉ።

… በቃሉ አፈጣጠር ጾታው ይወሰናል፤ ለምሳሌ፣ “ሥላሴ” በቃሉ ዓይነት ምክንያት ከአንስታይ ጾታ ከሚመደቡ ቃላት አንዱ ነው። የቃሉ አፈጣጠር እንደ “ውዳሴ”፣ “ቅዳሴ”፣ “ስያሜ”፣ “ምጣኔ”፣ “ሥጋዌ”፣ “ቡራኬ” መኾኑን ልብ እንበል። እነዚህ ስሞች ለማይዳሰስ፣ ለማይታይ፣ ነገር ስም ለማውጣት በተፈጠረ ዘዴ የተገኙ ናቸው። ጾታቸው የተፈጥሮ ሳይኾን፣ የሚጠቀምባቸው ሰው ለእነዚህ ዓይነት ቃላት የሰጣቸው ነው። በአማርኛ ቢኾን ተጠቃሚው ኅብረተ ሰብ የመሰለውን ጾታ ይሰጣል። ለምሳሌ፣ “ቡራኬ” በግዕዝ አንስታይ ስትኾን፣ በአማርኛ ተባዕታይ ሊኾን ይችላል። (ጌታቸው ኀይሌ(ፕሮፌሰር)፤ ከግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ፤58-59።)

[5] ጌታቸው ኀይሌ(ፕሮፌሰር)፤ ከግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ፤58።

[6] ሉውስ በርከኾፍ(ፕሮፌሰር)፤ የትምህርተ መለኮት ጥናት፤  1989 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ 66

1 comment:

  1. አብ + ወልድ + መንፈስቅዱስ = እግዚአብሔር = ሥላሴ

    ሥላሴ ወይም Trinity የሚለው፣ቃል በቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ባይገኝም በትርጉም ግን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ለማመልከት የምንጠቀምበት ቃል ነው።
    የይሖዋ ምስክሮች ይህንን አገላለጽ ስለማይቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃሉ አለመገኘቱን አንድ መከራከሪያቸው ያደርጉታል። በብዙ የክርስትና ተከታይ ግን ከላይ በሂሳብ መልክ የቀረበውን ይቀበላሉ።

    ReplyDelete