Sunday, 26 June 2016

ቢረፍድም፥ ለወንጌሉ ደወል ለመደወልና ትውልዱን ለማንቃት አሁንም ዕድል አለን!!!

Please read in PDF


 የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስምዋ በባለቤትነት የምትመራውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሰሞኑ ከፍታልናለች፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩም፦
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” (ዮሐ.5፥24)፡፡
የሚለውን ቅዱስ ቃል በማንበብ መክፈቻዊ ንግግር በማድረግ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ወደር የለሽነትና የበላይነት ፍንትው አድርገው ሲናገሩ፥ ፍጥረታት ያለቅዱስ ቃሉ ሕያዋንና ነዋሪዎች መሆን እንደማይቻላቸው በአጽንዖት አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ለዛ ባለው ውብ ንግግራቸውም የቴሌቭዥን ሥርጭቱ መከፈቱን በመባረክ አብሥረዋል፡፡
     በመቀጠል ሊቃነ ጳጳሳትም አጫጭር ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ንግግር ካደረጉት መካከል ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ለዚህ ትልቅ ሥራ “ማርፈዳችንን” ምንም በማይሸነግል ንግግር ተናግረዋል፡፡ እውነታውን ላስተዋለው ካለን አማኝ ቁጥር ብዛትና ካለን አቅም አንጻር እጅግ በጣም ቢረፍድም፥ “ዘግይቶ መከፈቱ በራሱ” እጅግ ደስ የሚያሰኝና ለወንጌሉ ሥርጭት መልካም እድል እንደሆነ እናምናለን፡፡ 

    በእርግጥ አርፍደናል ፤ የወንጌሉን እውነት “ከአለሙ ቀድመን የተቀበልን ብንሆንም”፥ ለምስክርነቱ ከእኛ “እጅግ ዘግይተው የተነሱት በብዙ እጥፍ ቀድመውናል፡፡” እንዲያውም በብዙ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እህቶቻችን የተነቀፍንበት ነገር፥ እኛ ጐረቤታቸው ክርስትናን ተቀብለን ሳንመሰክርላቸው ዝም ብለን ተቀምጠን፥ ምዕራባውያን ግን ከሩቅ መጥተው እነርሱን መስበካቸውንና መውረሳቸውን በምሬት ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ አዎ! ቀድመን ወንጌልን ተቀብለን በምስክርነት ግን ለጐረቤት ሶማሊያና ጅቡቲ ፤ የመንና ሱዳን ፤ ለአፍሪካችን እንደሚገባው መድረስ አለመቻላችን እጅግ በጣም ማርፈዳችንን አድምቆ ያሳየዋል፡፡
     እንዲያውም ዲያስፖራው ኢትዮጲያዊ በሄደበት “ቤተ ክርስቲያን ሲያስተክል ወይም ነገሥታት ከነበራቸው ቅንነት የተነሣ ቤተ ክርስቲያንን ሲተክሉና ሲያስተክሉ” እናያለን እንጂ፥ እጅግ ለረዥም ጊዜ ዓላማ አድርገን መሥራታችንን ፤ መትከላችንን ማስታወስ ይቸግራል፡፡ ወንጌል እንደተቀበልንበት እድሜያችን ያደረግነው ሐዋርያዊ የወንጌል ጉዞ ለአብነት መጥቀስ እስኪቸግረን ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ስንቴ ይሆን ለኬንያና ለጅቡቲ ጐረቤቶቻችን ሐዋርያዊ የወንጌል ምስክርነት ልናደርግ የተጓዝነው? መች ይሆን ለሱዳንና ለሶማሊያና ለጅቡቲ ወንድሞቻችን ወንጌል ለማድረስ በፍቅር ወደእነርሱ የሄድነው? ኸረ ለመሆኑ፥ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ.28፥19-20) የሚለውን አምላካዊና ንጉሣዊ የታላቁ ተልዕኮ ሰጭ ጌታ ኢየሱስ ትእዛዝን እነማን ዘንድ ሄደን ይሆን የፈጸምነው?! ለገዛ ወገናችንስ በብዙ አድርገነው ይሆን?
      ደቀ መዛሙርት፥ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (ሐዋ.1፥8) የተባሉትን ቃል፥ “ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበትነው” (ሐዋ.8፥1) በመስበካቸው፥ [ጌታ መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ እስጢፋኖስ መሞት ነገሩን ለበጐ አድርጐ] “ ... አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ” (ሐዋ.13፥48-49) ተብሎ እንደተጻፈ፥ ቃሉን ሙሉ ለሙሉ እንደታዘዙት ፈጽመውታል፡፡ እኛ ወደየትኛው የአህዛብ መንገድ ሄደን ቃሉን ጮኸን አሰምተን ይሆን? ለመንግሥቱስ ምን ያህል ነፍሳትን ጨምረን ይሆን? በእርግጥ በዚህ ጉዳይ እጅግ በጣም አርፍደናል ብቻ ማለት ሳይሆን ብዙ ወንድሞቻችንና ጐረቤቶቻችንን ስለበጣም መዘግየታችን ይቅርታ መጠየቅ ጭምር የሚገባን ይመስለኛል፡፡
    እንግዲህ፥ የተከፈተው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የሆነው የቴሌቪዥን መስኮት ካለበት ሥራ ብዛት አንጻር በቂ ነው ባንልም ያለበት ኃላፊነትና ሸክም ግን ያለጥርጣሬ ታላቅ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በተለይም፦
1.     የቅዱስ ቃሉ ተቃዋሚዎች ፤ ወንጌሉን የሚሸቃቅጡና የቅዱስ ቃሉን ሥልጣን የሚጋፉና የሚክዱ መናፍቃን በበዙበት በዚህ ዘመን፥ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የጸጋውና የክብሩ ቅዱስ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ፍርሃት በመሆን ፤ ለቃሉ ሥልጣን በመሸነፍ የወንጌሉ ስብከትና ትምህርት ሰፊውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ጊዜ እንደሚሸፍን እናምናለን ፤
2.    በሥርጭቱም ላይ ዘመኑን የዋጀ የወንጌል መልእክት ፤ በተለይም ከወንጌሉ ጋር የሚስማማውን ሐዋርያውያን አበውና ከዚያ በኋላ የተነሡት የቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርትን ማዕከል ያደረገ መልእክት እንደሚቀርብ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 
3.     በመካከላችን ያለውን የጉበኝነትን ፣ የዘረኝነትን ፣ “ወንጌል ልጥፍ” ፖለቲከኛና ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደመዥገር ተጠግተው ደሟን የሚመጡትን ጥቅመኛ ቡድኖችንና ማኅበራትን በግልጥ በመውቀስና በመምከር ወደንስሐ እንዲመጡ እንደሚተጋ ፤ አልመለስ ሲሉም፥ በበቂ ማስረጃና ሚዛናዊነት ባልጐደለበት የዘገባ መንፈስ ያለአንዳች ፍርሃት ለእግዚአብሔር እውነትና ለቅዱስ ቃሉ ሥልጣን ብቻ በማድላት ፤ ስለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ለሌሎች ማሳወቅና ማጋለጥ እንዳለበት እናምናለን፡፡
4.    ቤተ ክርስቲያን እርሷን የማይወክሉ፥ ነገር ግን “በስሟ የታተሙትን” መጻሕፍትን ፣ መጽሔቶችን ፣ የስብከት ካሴትና ዝማሬዎችን ለልጆቿ ለማሳወቅ [ለሚከስሷትም ጭምር መልስ ለመስጠት] “ከፊት ይልቅ የተሻለ” ሰፊ በር ተከፍቶላታልና አንደበቷን አንደበቱ አድርጐ የሚሠራና የእውነትና የሐሠት ግልጥ መስመር የሚያበጅ እውነተኛ አገልጋይ (ሚል.3፥18) እናይበታለን ብለን እናምናለን፡፡
5.     ቅዱስ ወንጌል ከዘረኝነት መንፈስ በጸዳ ንጹሕ ሕሊናና አንደበት ሁሉም ማኅበረሰብ መስማት በሚችለው ቋንቋ መድረስ እንዳለበት እናምናለን፡፡ ስለዚህም በሌሎችም ቋንቋ ወንጌል እንደሚሰበክና እንደምንሰማ ተስፋ እናደርጋለን፡
6.    ከምንም ነገር በላይ ለዘመናት የተወቀስንበትን ታሪክ ለመሻርም የምንነሳበት እንዲሆንም እናስባለን፡፡ በተለይም ሶማሊያን ፣ ሁለቱን ሱዳንና ጅቡቲንና ሙሉ አፍሪካን የወንጌሉ ዓላማ አድርገን መሥራት ፤ እነርሱንም ማዕከል ያደረገ አፍሪካ ተኮር የቅዱስ ወንጌል ዝግጅት በቴሌቪዥኑ መስኮት ከመደረጉ ባሻገር፥ ሐዋርያዊ ጉዞ በጳጳሳትና በወንጌላውያን ሰባኪዎችና ዘማርያን ጭምር ጊዜ ሰጥቶ መሥራት እንደሚጀመር ተስፋ እናደርጋለን፡፡
7.    የቴሌቭዢኑ መስኮት መርሐ ግብር ብቻውን አይበቃም ፤ እንዲያውም በብዙ መንቀሳቀስና አብዝቶ መስበክ ፤ አብያተ ክርስቲያናትን [ምዕመናንን ወይም አማኞችን] መጐብኘት ያለብን ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ነው ብለን እናምናለን፡፡  አልያ እንደፖለቲከኛ መሪዎች ለቀረጻ ብቻ ሥፍራው ላይ እየተገኙ፥ ቀረጻው ሲያልቅ በሥፍራው ድርሽ አለማለት የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድና አሁን ካለው ይልቅ የባሰ ሊሆን ይችላል፡፡
    ቻናሉን ለመክፈት ቢረፍድብንም መክፈታችን በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ያለብንን የቤት ሥራ ግን አብዝተን ልንወጣ ይገባናል፡፡ ብዙ ኃይሉን እንዳጠራቀመ ሰው በቁጭት ወይም ከወይን ስካሩ እንደነቃ ጐልማሳ በብርታት መሥራት አለብን፡፡ በወንጌሉ ጉልበት በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ማስተዋል ከሠራን እውነት ስለእውነት አልረፈደብንም፡፡
   ጌታ ልባችንን ያስፋው ፤ ማስተዋልም ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment