Friday 29 April 2016

“ፋሲካ”ውን በኃጢአት ልንፈስከው ቀን ቀጥረን ይሆን?


እንኳን ለብርሐነ ትንሣኤው መታሰቢያ በዓል በሠላም አደረሳችሁ፡፡
      የእስራኤል ልጆች የብሉይ ኪዳኑን ፋሲካ በተለያየ ዘመን እንዴት እንዳከበሩት ስናስተውል እንዲህ የሚመስሉ ቁም ነገሮችን እናገኝበታለን፦
ü በሙሴ ዘመን፦ የመጀመርያው ፋሲካ እንዲፈጸም የተሰጠው ለሙሴ ሲሆን ይህም በፈርዖን ቤት የበኵር ልጅ ሲገደል፥ በቤተ እስራኤል ይህ መቅሰፍት እንዳይደርስና እንዲያልፋቸው (ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነውና) ይህም የዘለዓለም ሥርዓት እንዲሆናቸው ተሰጣቸው፡፡ (ዘጸ.12፥14) ለፋሲካው የሚቀርበው ጠቦት በግ “ነውር የሌለበት”(ዘጸ.12፥5) ነው፡፡ ይህ በግ የሚበላው በመራራ ቅጠል እርሾ ከሌለበት ቂጣ እንዲሆን ታዘዋል፡፡ በእነዚህ የበዓል ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የሚበላ፦ “ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ” (ቁ.15) የሚል ግልጥ ማስጠንቀቂያ አለ፡፡ ስለዚህም ከዚህና ከሌሎችም ማስጠንቀቂያዎች የእስራኤል ልጆች ራሳቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ (ዘኍል.9፥6)

     ነውርና ዕድፍ የሌለበትን ጠቦት በጉን ለመመገብ እርሾ የሌለበት ቂጣ አብሮ መቅረብ እንዳለበት ተነገረ፡፡ ይህ ነገር ለአዲስ ኪዳኑ በግ በምሳሌነት (ዮሐ.1፥29) መነገሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እርሱ ነውርና እድፍ የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ አምላክና ሰው ነውና (1ጴጥ.1፥18-19)፡፡ ከእርሱ መዋጀትና መቤዠት የተነሳም ሞትና ሲዖል ደጅ ደጃችንን እያየ ሳይነካን አልፎናል፡፡ እርሱ ፋሲካችን ፤ ሞትን መሻገሪያ መርከብ ፤ ማለፊያ ታንኳችን ሆኖልናልና (1ቆሮ.5፥7)፡፡ ዋና ፋሲካችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ለማክበርና ለማምለክ ግን የኃጢአትና የመበስበስ ምሳሌ ከሆነው ከእርሾ ሕይወት መራቅና ኝስሐ በመግባት መመለስ አለብን፡፡ የኃጢአተኞች ምክር ፣ የክፉዎች ትምህርት እርሾ ፤ ኃጢአት ተብሎ ተጠርቷል (ማቴ.16፥6-12 ፤ ማር.8፥15 ፤ ሉቃ.12፥1 ፤ 1ቆሮ.5፥6-8)፡፡ ቅዱሱን ፋሲካ በቅዱስ ሕይወትና ኑሮ ልናከብረውና ልናመልከው ተጠርተናል፡፡
ü በኢያሱ ዘመን፦ የእስራኤል ልጆች የግብጽን ሸለፈት በጌልጌላ እንዲያስወግዱ ከተደረገ በኋላ፥ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ከነሸለፈታቸው ወይም ከነግብጽ ነውራቸው በዓሉን እንዲያከብሩ የፈቀደ አይመስልም፡፡ ስለዚህም ንጹሐን እንዲሆኑ ከዚያም በዓሉን እንዲያከብሩ ወደደ (ኢያ.5፥7-10)፡፡
     ሸለፈት የኃጢአትና የነውር ምሳሌ ሆኖ ተገልጧልና የእስራኤል ልጆች ወደተስፋይቱ ምድር ሳይገቡና የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው በፊት እንዲያስወግዱ ተነገራቸው፡፡ ከጾሙ በፊት በነበርበት ማንነት ከጾሙም በኋላ ብንገኝ፥ እጅግ በሚብስ ኃጢአት ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ የቀድሞውን ሳናውቅ ሊሆን ይችላል ፤ ከነሸለፈታችንና ከነነውር ኃጢአታችን እንመላለስ ይሆናል ፤ ከጾሙና ከጸሎቱ በኋላ በዚያው ኑሮ ብንመላላስ ግን አውቀን በድፍረት ኃጢአት ውስጥ እየተመላለስን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አመጸኞች መሆናችንን ያሳያል፡፡ ታዲያ ጽኑ ፍርድ ቢያገኘን ምን ይደንቃል? ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ü በኢዮስያስ ዘመን፦ የስምንት ዓመት ትንሹ ንጉሥ የልቡ ማስተዋል ትልቅ ነበር፡፡ የስሙ ትርጉም እንኳ “እግዚአብሔር ይደግፋል” ማለት ነው፡፡ አሥራ ስድስተኛው የይሁዳ ንጉሥ ሲሆን፥ ከዳዊት ቤት ከተነሡት መልካም ነገሥታት የመጨረሻውም ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር አምልኮ በመቅናቱም ምክንያት፦ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።”(1ነገ.13፥2) ተብሎ የተነገረውን ትንቢት በመፈጸም ከይሁዳ እስከገሊላ ምድር ድረስ ባዕድ አምልኮን ከምድሪቱ ሁሉ አጠፋ፡፡
     በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን የሆነው እጅግ ውብ ነገር፥ በሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ አማካይነት የጠፋው የሕጉ መጽሐፍ ተገኝቶ ነበር፡፡ መጽሐፉንም ካነበበው በኋላ ሕዝቡና እርሱ ያለበትን አስከፊ የኃጢአትና የውድቀት ሕይወት በመመልከት፥ ራሱን እጅግ በማዋረድ እግዚአብሔርን እጅግ ደስ አሰኘ፡፡ ከአምላኩ ጋር ያለውንም መንገድ ለማስተካከል “ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ” (1ነገ.22፥19 ፤ 2ነገ.23፥3) ይላል፡፡ እንዴት የሚደንቅ ውብ ነገር ነው! ከዚህ በኋላ እጅግ በሚታዘዝ መንፈስ እንደሕጉም መጽሐፍ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ፥ ታላቅ የፋሲካን በዓል አደረገ፡፡ “ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ” (2ነገ.23፥23)
     ንጉሥ ኢዮስያስ እጅግ የሚደንቅ ንጉሥ ነው፡፡ እንደስሙ ትርጉምም እግዚአብሔር በእርግጥ ደግፎታል፡፡ ገና ከማለዳ እግዚአብሔር መንገዱን ስላቀናለት በመንፈሳዊ ቅንአት ፍጹም ተመላ፡፡ ጣዖታትን ሁሉ ፤ ኃጢአትን ሁሉ ፍጹም ተጠየፈና አምላኩ የሚከብርበት መንገድ ፈለገ፡፡ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለማምለክ ጣዖታትን ማጥፋትና ኃጢአትን መጠየፍ በራሱ አይበቃም፡፡ ስለዚህም ኢዮስያስ ኃጢአትን ተጠይፎ በምትኩ እርሱና ሕዝቡ ፊታቸውን ወደአምላካቸው ፍጹም የሚመለሱትበን ለሕጉ መጽሐፍ ቃል ታማኞች ሆኑ፡፡ በሕይወታችን ሁሉ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና በአምልኮም ሁሉ እርሱን ደስ ልናሰኘው ኃጢአትን መጠየፍ ብቻ ሳይሆን እንደቃሉ ከሆነ በጐ ነገር ሁሉ ጋር ልንተባበር ይገባናል (ሮሜ.12፥9)፡፡
     የቀደመው ለጣዖታት የተገባውን ኪዳን ንጉሡ ሻረው፡፡ እንደሕጉ መጽሐፍ አዲስ ኪዳንን ፣ ሕይወትና ተሃድሶን ለሕዝቡ አደረገላቸው፡፡ በጨለማ ለሚኖረው ሕዝብ መሪ ብርሃን ቃሉን አመጣ ፤ እንዲነበብም አደረገው፡፡ ፋሲካውን ለእግዚአብሔር እንዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ ቀድሞ ይገዛን የነበረውን ጠላትና አስጨናቂ ፤ ተቃዋሚያችንንም “በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ ያስወገደልን አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድልም የነሳልን” (ቈላ.2፥14-15) ፤ መካከለኛም ሆኖ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን “የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰና በመስቀሉ የገደለ” (ኤፌ.2፥14-16) እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ የረሳነውንና የጣልነውን የአምላካችንን የሕግ መጽሐፍ መጥቶ ያስታወሰንና ዳግም በማስተማርና በመፈጸምም የሕግ ፍጻሜያችን የሆነልን እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው (ማቴ.5፥7 ፤ ሮሜ.10፥4 ፤ 13፥10)፡፡
   እርሱ የአዲሱ ኪዳን የመጨረሻው ፋሲካችን ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ ሌላ ምንም ፋሲካ ፤ ምንም በዓል ፤ ምንም ደስታ ፤ ምንም እርካታ ፤ ምንም ደስታና ተድላ የለንም፡፡ እርሱ በፋሲካነቱ አባቱን ብቻ ያያደለ እኛንም አርክቶናልና ለአንድ ቀን ብቻ ያይደለ ለዘወትር የምናከብረው ውዱ ፋሲካችን ነው!!! ለመሆኑ እኛ ፋሲካን ለእግዚአብሔር ነው የምንፈስከውን? በበዓሉ ቀን የወንጌሉ ቃል ይነበባል? ኃጢአተኞችን ሰብስበን የእንመለስ ጥሪና አዋጅ እናውጅ ይሆን? በሕይወታችን እግዚአብሔር አምላካችንን የማያከብረውን ነውርና እድፈት የምናስወግድበት ቀናችን ነውን? ራሳችንን እንመርምር!
ü በዕዝራ ዘመን፦ ፈጣኑ ጸሐፊ ዕዝራ፥ ፋሲካን ከሌዋውያን ካህናት ጋርና ከሕዝቡ ጋር ያከበረበትን ሁኔታ ታላቁ መጽሐፍ ሲገልጠው፦ “ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር ሁሉም ንጹሐን ነበሩ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ” (ዕዝ.6፥19-20)፡፡ ንጹሐን ነበሩ የሚለው ቃል ፍጹም በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ ገብተው ለእግዚአብሔር ሥራ ዝግጁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ እኛ ለእግዚአብሔር ሥራ ዝግጁ ሆነን ነው አሁን የቆምነው?
     ዕዝራ በምርኮ ምድር ብዙ ዘመኑን ቢኖርም ለእግዚአብሔር ሥራ ምቹ ፤ ጻድቅና ንጹሕ ነው፡፡ ሌሎችም እንደእርሱ የበረቱ እንዲሆኑ የሕጉን መጽሐፍ በፍጥነት በመጻፍ ያባዛዋል፡፡ የንጽሕና መሠረቱና ሚዛኑ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የፋሲካው በግ መሥዋዕቱና የሕጉ ቃል ነው፡፡ የእኛ ሚዛናችን ማን ነው? ቅዱስ ቃሉ ነው ወይስ የብዙሃን ድምጽ? ዕዝራ ንጹሐንን ለእግዚአብሔር ያጨው በቅዱሱ ሕግ ላይ ቆሞ ነው፡፡ ከእኛ ጋር እንዲሆኑ የምንወዳቸው ሰዎች ምን አይነት ሰዎች ናቸው? እንደቃሉ የሚኖሩ ወይስ የሚሸቃቅጡ?
    በክርስቶስ ኢየሱስ የጽድቅ ሚዛን ላይ ሳንቆም የቤተ ክርስቲያንን ቅድስናና ንጽሕናና የምንጠብቅ ከሆንን እጅግ ተታልለናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ሆና በክብር የምታጌጠው” ራሷን በሰጣትና በሞተላት ጌታ ፊት እንደቃሉ የተገባ ሆና ስትገኝ ብቻ ነው(ኤፌ.5፥27)፡፡
   የሕጉን ቃል ለሕይወታችን ፣ ለኑሮአችን ፣ ለመንፈሳዊነታችን ፣ ለትዳራችን ፣ ለፖለቲካችን ፣ ለትምህርታችን ፣ ለወጣትነታችን ፣ ለሽምግልናችን ፣ ለአገራችን ሰላምና ለሰው ልጅ ሁሉ እረፍትና መዳን መመርያ አድርገን እናስቀምጣለን? ከጾሙ በኋላ ስምምነታችን ከማን ጋር ነው? በእውኑ ከቃሉ ጋር ነው ወይስ ከዝሙትና ጭፈራው ጋር? በበዓሉ መታሰቢያ ማግስት ቀጠሮአችን የትና ከነማን ጋር ነው? ከጭፈራው ኮንሰርትና ዳንኪራው ፤ መጠጥ ቤቱና በየመሸታው ቤት አይደለምን? እኛ እኰ ወንጌል በየአባወራው ቤት ሲሰበክ የምንበሳጭ፥ በየጭፈራ ቤቱ ሄደን ስንረክስ ግን እንደጀብዱ የምናወራ ከፈሪሳውያን የባስን ግብዞች ነን፡፡ በጾሙ “ንጽሕናችንን” ጠበቅነው “ያቆየነው” በየጭፈራ ቤቱ ለመርከስ አልመሰለብን ይሆን?
      ከእነዚህ የብሉይ ኪዳን የፋሲካ መታሰቢያ በዓል ጥቂት ምንባባት የምናስተውለው እጅግ ብዙ የሆኑ ሃሳቦችን አሉ፡፡ ፋሲካችንን በእውኑ አውቀነዋልን? በፍሰካችን ፈስከን የምናከብረውና የምናመልከው ማንን ነው? ንዳለመታደል ዘፋኝነትና የዘፈን ኮንሰርት ፤ ዝሙትና ጭፈራ … ከክርስቲያናዊ በዓላት ጀርባ ያለማንምና ምንም ከልካይ ክርስቲያን ነን እያሉ አቧራ በሚያስነሱ ዘፋኞችና ዳንኪረኛ አማኞች የበዓሉ ምሽት መቅኖውን ያጣል፡፡ በእኛ እንደሚሆነው ብዙ ሕዝባዊና የሌላ ሃይማኖት በዓላት ሲከበሩ የሚጨፈረውን፥ በዝሙትና በኃጢአት ትውልድ የሚረግፈውንና በኃጢአት የሚረክሰውን ያህል በሌሎች በዓላት አይደረግም፡፡ ለምን? ሰይጣን ክርስትናን ለማሰደብ  “ክርስቲያኖችን” እንደተጠቀመባቸው ሳይ እጅግ አለቅሳለሁ፡፡ እጅግ የሚገርመው በዋናነት የዚህ ነውር አዘጋጆችና ተሳታፊዎች “ክርስቲያን ነን” ባዮችና ምናልባትም ለደንቡ ጿሚ የነበሩም ናቸው፡፡ አቤቱ ፍረድልን፡፡ አሜን፡፡
     መንፈሳዊነታችን ይታይ ቢባል በፋሲካው መታሰቢያ ቀን በዓል የት ነው መዋያችንና ማደሪያችን? በብሉይ ኪዳን የነበሩትና የጥላውንና የምሳሌውን ፋሲካ እንዲያ በብዙ ክብር ካከበሩት እኛ እንዴት በሚበዛ መንፈሳዊ ክብር ዘመናችንን በሙሉ ልናከብር ይገባን ይሆን? በመታሰቢያ ቀኑማ እንዴት ባለ ታላቅ አምልኮ ልናከብር ይገባ ይሆን? በእውኑ ከአሥራ ሁለት ሚሊየን ሕዝብ በላይ የተራበ ሕዝብ ባለባት አገር ላይ (በሠላሙ ተፈቅዷል የሚሉ እንዳይኖሩ ፈራሁ)  መአትና መቅሰፍት ለመጥራት ካልሆነ በቀር ጭፈራና ዳንኪራው ምንድር ነው? ያውም በተቀደሰው በዓል መታሰቢያ ቀን፡፡
የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል ፤የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?” (ዕብ.10፥28-29)

      የተመረጥንበትንና የዳንንበትን ቅዱሱን ፋሲካችንን ክርስቶስን እንድንዘብትበት አልተባለልንም፡፡ ፋሲካውን ክርስቶስን ደስ በሚያሰኝ ሕይወትና ኑሮ እናስደስተው፡፡ የእስከዛሬው ርኩሰትና በበዓላት ሰበብ ልክን አልፎ በመብልና መጠጥ በመቅበዝበዝ የኖርንበት ይብቃንና (1ጴጥ.4፥4) ከአምላካችን ጋር ኪዳናችንን የምናድስበት እንዲሆንልን ፤ የዕርቅ ቀን እንዲሆንልን ለኃጢአታችን ሞቶ ፤ ለጽድቅ እንድንኖር ከሙታን መካከል ወደተነሣልን ፋሲካችን ወደሆነው ጌታ ኢየሱስ ፊታችንን እናቅና፡፡ የኃጢአትን ቀጠሮ አፍርሰን የሕይወትን ኪዳን ቀጠሮ ከአዳኛችን ጋር እንግባባ፡፡

     ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡ 

1 comment:

  1. EGZABHER AMLAK ABZITO YIBARKH HULETEGNA AYIDEGIMEGNM!!!

    ReplyDelete