Monday 6 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (የመጨረሻው ክፍል)


  

 “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። … በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? … ” (ያዕ.3፥16 ፤ 4፥1-2)

     እንደማንኛውም ሰው ስናስብ፥ በአስተዳደር ጉዳይ መጣላት ሊኖር ይችላል፡፡ መጋጨት ስላለም ሁከት ፣ ጦርና ጠብ ውጭ ለሚያየው መገለጫ ሆነው ይታያሉ፡፡ ለመንፈሳዊ ሰው ግን የጦርና ጠብ መነሾ ዋና ምክንያቱን ቅዱስ ያዕቆብ እንደነገረን ስናስተውል፥ በብልቶቻችን ውስጥ ከሚዋጉ ምቾቶቻችን እንደሆነ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ምቾት ብርቱ ስሜት ፤ ጠንካራ ውጊያ ፤ አደገኛ ምኞት ፤ ክፉ ቅንአትንም ጭምር ያሳያል፡፡ የዚህም መነሾው ሥፍራው ልብ ነው እንጂ የትም አይደለም፡፡ በልብ ብርቱ ሰልፍ አለ ፤ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ ሮሜ.7
   በዚህ ሳምንት በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀለል አድርጐ ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን ያለ ምስክር አይተውምና (ሐዋ.14፥17)፥ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ እውነታውን በማንሳት መምከርና መገሰጽ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ልብንና የመንገድን ቅንነት እንጂ ዕድሜን ወይም ታላቅ መሆንን ብቻ እንደማያይ ታላቁ ባለበት አቤልን ፣ ዮሴፍን ፣ ኤፍሬምን መምረጡን ፤ በእድሜ የሸመገሉቱ ዔሊና ሌሎች ካህናት ባሉበት ሕጻኑን ሳሙኤልን ፣ እንዲሁም [ወጣቱን] ሕጻኑን ኤርምያስን እንደመረጠው መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ይነግረናል፡፡ 

      እርግጥ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ዲያቆን ስለትህትና፥ ካህን ኤጲስ ቆጶስን መቆጣትም ሆነ መገሰጽም እንደማይቻለው ቢናገርም፥ ግልጥ ስህተት በተሠራ ጊዜ ግን ቀኖናው ሳያመነታ፥ “… ሰዎችን ሊያሳዝናቸውና ፈርተው እንዲገዙለት ፈልጎ በማይገባ ቢያሥር ቢያወግዝ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታሠረ የተወገዘ ይሁን፡፡ ካህናትም በእውነት ይቋቋሙት” (ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.184) ይላል፡፡ ቅዱስ ቃሉም፦ “እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው” (1ሳሙ.16፥7) ፤ “እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም” (ገላ.2፥6) “ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ” (ያዕ.2፥1) ይለናል፡፡
    ከቃሉ በተቃራኒ የቆመውን ማናቸውም ሰው ወይም ማኅበር እንደቃሉ አንዳች ሳናደላና ፊትን ሳናይ፥ ለእግዚአብሔር ብቻ በማድላት ልንናገረው ፤ ልንመክረው ፤ ልንስጸው ይገባናል፡፡ ይህንኑ አብነት አድርገን ኤጲስ ቆጶሳቱን እንደቀረበላቸው ሚዛን ስንመዝናቸው፦
1.    የማይነቀፍ፦ በግሪክ ቋንቋ “አኔጲመፕቶስ” ማለት ቃል በቃል ሲተረጎም፥ “በደል የሌለበት” የሚል ሲሆን፥ ኤጲስ ቆጶስ የሚለውን ደግሞ  ነቀፋ በደል የማይቀርብበት ሰው ብለን መተርጐም ይቻለናል፡፡ የማይነቀፈው ከግል ብቃቱና ቅድስናው ሳይሆን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ በደሙ ቤዛነት  ከሆነው ሕይወት የተካፈለና ክርስቶሳዊ የጽድቅ መርሆዎችን ሁሉ ስለሚከተልና ስለሚኖርበት ነው፡፡ ይህም ማለት ታማኝ ፣ ሐቀኛ ፣ ንጹህ ፣ እጅግ ታማኝ ፣ ከነቀፋ ሁሉ የጸዳ ነው ማለታችን ነው፡፡
    መነቀፍ ሁሉ ትክክል አይደለም ፤ ስለመልካም ሥራቸው የተነቀፉ ቅዱሳንም ነበሩና፡፡ በገዛ ሥራችን ወይም በሚያስነቅፍ ሥራችን መነቀፍ ግን የጠራንን መናቅ ወይም እልኸኝነት ነው፡፡ ከነቀፋ የጸዳ መንገድን አለመምረጥ ፈሪሃ እግዚአብሔርን መጣልና የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት መናቅና ችላ ማለት ነው፡፡
2.     ራሱን የሚገዛ፦ ራስን መግዛት የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላ.5፥22)፡፡ ኤጲስ ቆጶሳዊ ራስን መግዛት ከተፈተነ ጠባይ ፣ እግዚአብሔርን በመፍራት በሥራ ከሚካብት ልምድ ፣ ከላቀ አስተዳደር ችሎታ  የሚመነጭ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ራስን አለመግዛት ለብዙ ነገር የሚያጋልጥ ነው፡፡
    ራስን መግዛት በመጠን ከመኖር ጋርና ከወይን ጠጅ ስካር ጋር በንጽጽር ቀርቧል (1ተሰ.5፥6)፡፡ በወይን ጠጅ የሰከረ ሰው ራሱን መቆጣጠር የማይችለውን ያህል ፤ ከወይን ስካር ውጪ በሆነ ጊዜ ግን ራሱን እንደሚቆጣጠር እንዲሁ ራሱን የማይገዛ ሰው የማይገቡ ንግግሮችንና ድርጊቶችን ከማንጸባረቅ አይመለስም ማለት ነው፡፡ ሌላውን በቁጣና በኃይለ ቃል የመናገር መነሾው ራስን አለመግዛት ነው፡፡ ራሱን የሚገዛ ሰው ምንን ለማን እንደሚናገር በሚገባ ያስተውላል፡፡
3.     በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል፦ ለኤጲስ ቆጶስ መልካምነት ምስክርነት ከምዕመናን መካከል የሚያስፈልገውን ያህል የቤተ ክርስቲያን አባላት ካልሆኑትም መካከል ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ኤጲስ ቆጶስ ያለምንም ነቀፌታ በሁሉ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችለዋል፡፡
4.     ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ፦ ኃጢአት አንድ ሌላ ትርጉሙ አለመታዘዝ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ አለመታዘዝ እንቢተኛ ጠባይን የሚያሳይ ነው ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በምሳሌው፥ አባታቸው ስላዘዛቸው ስለሁለቱ ልጆች ሲናገር የታዘዘው ልጅ ብቻ የአባቱን ፈቃድ እንደፈጸመ በትክክል ተናግሯል (ማቴ.21፥28-31) በተለይም ደግሞ ጳጳሳት ለፓትያርክ ፣ ቀሳውስት ለጳጳሳት ፣ ዲያቆናት ለቀሳውስት መታዘዝ እንዳለባው የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በግልጥ መታዘዝ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡
      ተለይም ደግሞ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን፥ “እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር” (ፊል.2፥3) እንደሚለው፥ ስለመታዘዝ ስናነሳ በፍቅር እርስ በእርስ “ልንተዛዘዝ” እንደሚገባን መዘንጋት የለብንም፡፡
5.     የማይቆጣስለመልካም ነገር መቆጣት ይገባን ይሆናል፡፡ ለመቆጣት ግን መሄድ ያለብን መንገድ የተሟጠጠና የተጠናቀቀ መሆን አለበት፡፡ ብንቆጣም ዲያብሎስ ፈንታ እንዲያገኝ እድል ልንሰጠው አይገባም (ኤፌ.4፥27)፡፡
6.    የማይጨቃጨቅ፦ ጭቅጭቅ አንዱ የቁጣ መገለጫ፡፡ ጭቅጭቅም ፤ ክርክርም የሥጋ ፍሬዎች ናቸው (ገላ.5፥20)፡፡ ስለዚህም፥ ቍጡ ሰው ክርክርን ያነሣሣል” (ምሳ.29፥22)፡፡ የእስራኤል ልጆች በክርክር ውኃ እግዚአብሔርን አስቆጡት (መዝ.106፥32) ፤ ለክርክር የሚጾሙትንም አብዝቶ ወቀሳቸው (ኢሳ.58፥4)፡፡
      የሚጎመጅ ሰው ደግሞ ክርክርን ያስነሳልና፥ (ምሳ.28፥25) እንዲህ ካለ ሰው እጅግ መራቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም “ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል” (ምሳ.20፥3)፡፡ ታዲያ ቃሉ እንዲህ የሚል ከሆነ ሲኖዶሳችን ረጅም ሰዓታት በአንድ ጉዳይ ለምን ሲከራከር ይቆያል? ለእውነት መወያየት ፤ ረጅም ሰዓት መነጋገር ባልከፋ ፤ በእውነት ላይ ግን በክርክር መንፈስ ውሎ ሲታደር እንደመጽሐፉ ቃል መመርመር እጅግ መልካም ነው፡፡ ቃሉ እውነትን እንኳ በፍቅር እንድንገልጥ እንጂ የክርክርን መንፈስ በፍጹም አያበረታታም፡፡ ታዲያ ሲኖዶሳችን በተለይም ጥቂቶቹ ጳጳሳት ይህን መንፈስ ከወዴት አመጡት?
እናንት “የምትከራከሩ” ጥቂት ጳጳሳት ሆይ!
       እንዲህ የሚያስነቅፍ ነገር ውስጥ ምነው ዘው ብላችሁ መግባታችሁ? ዓርዓያነታችሁን ምነው ሳታሳዩን?
       ራስን ያለመግዛት መገለጫ የሆነው ክርክር ፣ ቁጣ ፣ ያለመታዘዝን መንፈስ ከወዴት በመካከላችሁ ተሰማ? በእውኑ የእናንተ ክርክር የጳውሎስና የበርናባስ አይነት ነውን? (ሐዋ.15፥2)
       “ለጎረቤቶቻችን ክርክር አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም በላያችን ተሣለቁብን” (መዝ.80፥6) የሚለውን የዳዊትን ቃል፥ ምነው በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲሆን አልተሰማችሁ? የአመጽ ክፍፍልና የመንፈስ አንድነት ምነው ከመካከላችሁ ተወገደ?
   በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጉልበትና በቅዱስ ቃሉ መነጽርነት ሁል ጊዜ ጠንቃቃ መሆንን መለማመድ መቻል አለብን፡፡ ጥንቃቄ ይጠብቀናል ማስተዋልም ከጥፋት ይጋርደናልና፡፡ ከሰሞኑ ግን በሲኖዶሳውኑ አባቶቻችን መካከል የከረረ ነገር መኖሩን ሰምተናል፡፡ ቁጣ ፣ ክርክር ፣ አለመስማማት ፣ አለመከባበር ፣ አለመቀባበል ፣ በጥላቻ ጐራ መሰላለፍ ይህ ሁሉ የሆነው ሚዛን የሆነው የእግዚአብሔር ቃል መሳቱና ከሚዛኑ ፈቀቅ ማለታችን ነው፡፡ “እኛና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል” ለማለት እኮ፥ መንገድ ከማሳየት ፣ በጸሎት ከመርዳት ውጪ እጅን ከሚያስገባና የሚያዋርድ ተግባርን ከመፈጸም የትኛውም መንግሥታዊ ፣ ቤተ ክርስቲያን ነክ ማኅበርም ሆነ ግለሰብ እጁን መሰብሰብና “ሃሳቡን ከመሰንዘር” መከልከል እንደሚገባው እናምናለን፡፡
    ለዚህ ደግሞ ጳጳሳትም ሆኑ የሲኖዶስ አባላት በእግዚአብሔር ቃል እውነት  ታጥቀው መቆም መቻል አለባቸው፡፡ ኸረ ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ስንከራከር ስንት ትውልድ አመለጠን ይሆን? እባካችሁ አባቶቻችን ለክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ሥራ እንጂ ለሌላ ነገር እንዳንጨክን ልባችንን እናበርታ፡፡
አልያ፥
    እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ።እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።” (ሕዝ.34፥7-12) የሚለው ቃል ዛሬም ሕያውና የሚሠራ ነው፡፡ ጌታ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

1 comment:

  1. ሌላውን ለመምከር ከመነሳትህ በፊት ራስህን መጀመሪያ ብትመክር እንዴት ጥሩ ነበር። ቢያንስ ላመንክበት ነገር ትቆም ነበር። ቢያንስ ዲያቆን የሚል ማዕረግ አንጠልጥለህ አታስመስልም ነበር።

    ReplyDelete