Tuesday 20 September 2016

በዘመን መለወጫ የተቀማጠለው ንጉሥ (የመጨረሻ ክፍል)

  please read in PDF

ልንመርጥ የምንችለው አንድ መንገድ ብቻ ነው፤ ከኃጢአትና ከጽድቅ መንገድ አንዱን፡፡ ከሁለቱ አንዱን እንጂ ለሁለቱም ማመቻመች አንችልም፡፡ “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤” (ዕብ.12፥4) የሚለው ቃል በእውነት ላይ እስከመጨረሻ አለመጽናትንና አለመጨከንን የሚያሳይ ነው፡፡ ለእውነት ከቆምን እስከሞት ድረስ እንጂ ሁለቱን ለማደላደል መሞከር ከውርደት አያድነንም፡፡
    የሳሙኤልን መጽሐፍ የጻፈው ጸሐፊ፥ በንጉሥ ዳዊት ሕይወት የሆነውን ውድቀት ሁሉ ምንም ሳያዛንፍ ነው፡፡ አስቡ! የነቢዩ ሳሙኤልን ሕይወት፥ “እነሆኝ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ፡፡ እነርሱም፦ አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ፤” (1ሳሙ.12፥3-4) በማለት ገልጦታል፡፡ እንዲሁ የዳዊትን ደካማና ኃጢአተኛ ሕይወት ሳያቅማማ ነው የገለጠው፡፡

   ኃጢአትን በተመለከተ አሁን፤ አሁን እየተያዘ[የተያዘው] አቋም ኢ ክርስቲያናዊ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ስለኃጢአታችን ቤዛ አድርጐ መስጠቱን ቅዱሳት መጻሐፍት ደጋግመው ይመሰክራሉ፤ (ማቴ.26፥24 ፤ ዮሐ.1፥29 ፤ 1ቆሮ.15፥3 ፤ ገላ.1፥4 ፤ ዕብ.7፥25 ፤ 1ጴጥ.2፥24 ፤ 1ዮሐ.4፥10 ፤ ራእ.1፥4)፡፡ የኃጢአትን አስነዋሪነትና ከእግዚአብሔር ለዪነት በትክክል መናገር ካልቻልን ወደእግዚአብሔር መመለስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጥ ሊሆንልን ፈጽሞ አይችልም፡፡
    በበዓላት ወቅት ለምንሠራው ኃጢአት ብዙዎቻችን ዝንጉዎችና ግድ የለሾች ነን፤ እንዲያውም ድርጊታችን በአብዛኛው የተፈቀደ ያስመስለዋል ብንል ግነት የለበትም፡፡ ለምሳሌ፦ ዘፈንና ጭፈራ[በኮንሰርትና በየጭፈራ ቤቱ ሌሊቱን ሙሉ]፣ መጠጥና ልቅነት፣ ዝሙትና ርኩሰት፣ መዳራትና ሴሰኛነት የተከለከሉ እስከማይመስሉ ድረስ ይፈጸማሉ፡፡ ይህን ሁሉ እያደረግን አሁን ለደረስንበት መበላላትና ዘረኛነት በኃጢአታችን ምክንያት ነው ለማለት አንደፍርም፡፡ ዛሬም ጉልበታችን ሌላውን ለመኰነንና በሌላው ላይ ጣትን ቀስሮ ለመፍረድ እንጂ ወደራሳችን ለመመልከት አልታደልንም፡፡
    የማያስማማን የተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ስለሆንን አይደለም፤ በግልጥ ቃል ያልተስማማነው በኃጢአታችን ምክንያት ነው፡፡ ዳዊትን ከመንግሥቱ እስከመሰደድ ያደረሰው ነውር ትንሽ የተባለው የዝሙት መዘዝ ነው፡፡ በእኛ መካከል የገነነውን ኃጢአት ትተን በሃሳብና በፖለቲካ ፍትጊያ ብንፋተግ ሊሆን የሚችለው “ውኃ ቢመቱት እንቦጭ” እንደሚባለው ብቻ ነው፡፡ የሚቀድመውን ለማስቀደም ምንም ድርድር ውስጥ መግባት የለብንምና፡፡
   ዳዊት ከዚህ ሁሉ በደልና ኃጢአት በኋላ ምንም ሳያማርርና ሳያጉረመርም ምሕረትን ለመቀበልና ይቅርታን ለማግኘት “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም፤” (መዝ.51፥17) በማለት በጸጸትና በፍጹም ትህትና፥ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” እያለ ንስሐ ገባ፡፡ በኃጢአቱ ምክንያትም በመጣበት ነገር ሁሉ ምንም ሳያጉረመርም ቅጣቱን ሁሉ ተቀበለ፤ (16፥5 ፤ 24፥10)
    በክርስትና አስተምኅሮ ኀጢአትን ፈጽሞ አለመሥራት እጅግ የተሻለ ነው፤ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ፤” (1ዮሐ.2፥1-2) እንዲል፡፡ አስተውሉ! ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ይሟገትላቸው የነበረ ጠበቃቸው ነበር፤ በለዓም እስራኤል በድንኳኖቹ በውበት ተቀምጦ ሳለ በባላቅ ምክርና ብዙ ብር ሊራገም መጥቶ ነበር፤ እስራኤል በማያውቁበት ሰዓት እግዚአብሔር ከበለዓም ጋር ሲሟገት ነበር፡፡
    ይህንንም በለዓም በአንደበቱ፥ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔር ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደእኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን?” በማለት መስክሯል፤ (ዘኊል.24፥13)፡፡ በዚህ ክፍል ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ሙሉ ለሙሉ እግዚአብሔር ለኪዳኑ ሕዝቦች ተሟጋችና ጠበቃቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ኃጢአትን በሠሩ ጊዜ እንዲመለሱ ወዲያው ነቢያትን ይልክላቸው፤ ጠላት ሲነሳባቸው ደግሞ ይከራከርላቸው ነበር፡፡ ስለኢዮብ የተከራከረው ማን እንደሆነ አስቡ፤ (ኢዮ.1፥8)፤ ስለኢያሱ ማን እንደተከራከረ፤ እንደተካሰሰ አስተውሉ፤ (ዘካ.3፥2)፡፡
   በአዲስ ኪዳን ኃጢአትን እንዳንሠራ በጥብቅ ተነግሮናል፤ ነገር ግን ብንበድልና ኃጢአትን ብናደርግ፥ ቤዛችን ኢየሱስ የኃጢአታችን ማስተሥረያ ነውና በደሙ ፈጽሞ ይካሰስልናል፡፡ ምክንያቱም ስለኃጢአታችን ክርስቶስ የተቀጣ፣ ያለነውርና ዕድፍ ፍጹም ጻድቅ ሰውና አምላክ ሆኖ ተገኝቷልና ስለእኛ ሊካሰስ ይቻለዋል፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት በእኛ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ቁጣ ሁሉ በክርስቶስ ላይ ስላረፈ፥ የእግዚአብሔር ቁጣ በርዶ በልጁ ለምናምንና ቤዛነቱን ለምንቀበል በበዛ የምሕረቱ ዓይኖች ታይተናል፡፡
    እግዚአብሔር ዛሬም አልተለወጠም፤ ስለቅምጥልነታችንና በተላላነት ስለምንሠራው ኃጢአት ቸል አይለንም፡፡ ለሠራነውን ኃጢአት ምንም ዓይነት መሸፋፈኛና ምክንያትን አይቀበልም፡፡ “በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን በጌታ የምንገሰጸው”፤ (1ቆሮ.11፥32) አባት ልጁን እየቀጣ እንደሚያርም ሁሉ እኛም በነፍስ መዳን ያገኘን የእግዚአብሔር ልጆች በሠራነው ኃጢአት ንስሐ እንድንገባና በጸጋ እንድናድግ፤ በዘላለም ሞት እንዳንጐዳ ነው፤ (2ቆሮ.7፥10 ፤ ዕብ.12፥7 ፤ 2ጴጥ.3፥18)፡፡ ስለዚህም ጌታችን ትሁት በሆነና በተሰበረ ልብ ብንመለስና ንስሐ ብንገባ በድካማችን ይራራልናል፣ የሚረዳንን ጸጋ ይሰጠናል፤ (ዕብ.4፥16) ሊያድነንም ይችላል፤ (ዕብ.7፥25)፡፡ ስለዚህም በበዓላት አስባብ በምንሠራው በኃጢአታችን ሙታን እንዳንሆን አምላክ ወደሆነንና ወዳዳነንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊታችንን ዘወር ልናደርግ ይገባናል፡፡
   ንጉሥ ዳዊት እስከመጨረሻው በዚያው በክፋት መንገድ እንዳልዘለቀና እንደተመለሰ፤ ደግሞም ብዙ እንደተወደደና ምሕረትን እንዳገኘ አስተውሉ!!! “በዘመን መለወጫው” ቀን የት ናችሁ? ለሥጋ በሚለደልደውና በሚመቸው የኃጢአት መንገድ ላይ ናችሁ ወይስ የተሰጣችሁን ዘመን በቅድስና እንዲከናወኑላችሁ በመንፈሳዊው ሥፍራ በእግዚአብሔር ጽድቅ ከሰይጣንና ለእግዚአብሔር ከማይመች ማንነት ጋር  ከኢዮአብ፣ ከእርሱም ጋር እንዳሉት ኦርዮንና ባርያዎቹ በጽኑ እየተጋደላችሁ ይሆን?  ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

 ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment