Tuesday 2 August 2016

“27 አባቴ” የሚባል አባት የለንም!

Read in PDF

    አባት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው ሲፈቱት፥ “የግብርና የክብር የማዕረግ ስም፡፡ አባት መባል በብዙ ወገን ስለኾነ ከግዜር ዠምሮ ያባትነት ሥራ ለሚሠሩ ለመንፈሳውያን አባቶች ለቄስ ለመነኵሴ ለአእሩግና ለሊቃውንት ለመምህራን ኹሉ ይነገራል፡፡ … (ሐተታ) አብ በጥሬነቱ ዘርፍ ይዞ ሲቀጸል ምስጢሩ ካባትነትና ከጌትነት ከባለቤትነት አይወጣም፡፡” [1] በማለት በግልጥ አስቀምጠውታል፡፡
     የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም፥ “ የወለደ፥ በሥርዓት ኮትኩቶ ያሳደገ፥ በሥጋና በመንፈስ የአባትነትን የፈጸ ሁሉ አባት ይባላል፡፡ … ምእመናን ከእርሱ በመንፈስ ቅዱስ ስለተወለዱ “አባ አባት” ብለው ይጠሩታል ፤ ማቴ.6፥9 ፤ ዮሐ.1፥12 ፡ 13 ፤ ገላ.4፥6” በሌላ ሥፍራም፥ “አብ ፤ አባት ማለት ነው፡፡ ይህ ስም ከዘለዓለም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር አብ የሕላዌ(የአንዋንዋር) ስሙ ነው(ማቴ.28፥19 ፤ 1ጴጥ.1፥1-2)፡፡ ኢየሱስ ስለሰማያዊ አባት ሲናገር ብዙ ጊዜ አብ ብሎ ጠራው፡፡” በማለት ቄስ ኮሊን ይገልጡታል፡፡ [2]

     በሌላ ትርጉምም “አባት ፤ (አብ) ወላጅ አስገኝ ፤ አሳዳጊ ፤ ሞግዚት ፤ መነኵሴ፡፡ (የነገር አባት) ፣ ጠበቃ ነገረ ፈጅ፡፡ (ያገር አባት) ፤ ሽማግሌ መካር ዛሬ አንዱ ቤት ነገ እሌላ ቤት እያደረ የሚጦር፡፡ … (የድኻ አባት) ድኻ ሰብሳቢ፡፡ (የንጀራ አባት) ፤ የናት ባል እንጀራ እያበላ ያሳደገ፡፡ … ” [3] በማለትም አስፍተው መተርጉማን ያስቀምጡታል፡፡
    ከእነዚህ የፍቺ መዝገበ ቃላት የምናስተውለው ትልቅ ቁም ነገር አባትነት ከጽንሰት እስከ ልደት ፤ ከልደት እስከእውቀት በሁለንተናው ከተወላጅ ልጅ ጋር ፍጹም ሥጋዊ ፣ ነፍሳዊ ፣ ዕውቀታዊ … ትስስርን የሚያሳይ ትልቅ ምስጢርን ያዘለ ትርጉም መሆኑን ነው፡፡ 

    እኛ ግን ከሁሉ በላይ የሚሆን ፤ ፍጹም አባት አለን፡፡ እርሱ አባታችን የአባትነት ሁሉ መነሻና መድረሻ ፤ መጀመርያና መጨረሻ ነው፡፡ ከአባት ይልቅ አሳቢ ፣ “እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ.5፥45) እንደተባለ ፍጥረቱን ሁሉ በእኩል ዓይኖቹ የሚያይ ቅዱስ አባት እግዚአብሔር አብ አለን፡፡
   አዎን! “ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ” (ኤፌ.4፥6)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር አብን አባትነት እግዚአብሔር ወልድንና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ካነሣ በኋላ አጽንዖት ሰጥቶ ይናገራል፡፡ የመንፈስ አንድነትን በመያዝ አንድ ጽኑዕ ቤተሰብን ለመመሥረት የእግዚአብሔር አብ አባትነት የማይናወጥ መሠረት መሆኑን ይናገራል፡፡  “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” (ያዕ.1፥18) እንዲል፥  “በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ የሚሰየምበት እግዚአብሔር አብ ነው” (ኤፌ.3፥14) ብለን እናምናለን፡፡
     የእርሱ አባትነት የሕይወት ምንጭነትን የሚያሳይ ነው፡፡ እርሱ የሕልውናችን ጅማሬ ፤ የዘለዓለማችን ወጣኝና ፈጻሚ ፤ የአባትነቱም ፍቅር ለብቻው ዘለዓለም ማኖር የሚያስችል አቅምና ችሎታ ያለው ነው፡፡ አባታችን የሚያዩን ዓይኖቹ ርኅራኄን የተመሉ ፤ ፈቃድና ስሜትም ያሉት ነው፡፡
    አይሁድ የእግዚአብሔርን “አባትነት” የሚያውቁት በአስፈሪ መለኮትነቱና በአይቀረብነቴው ነው፡፡ የአብ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ ግን የአባቱን ነገር ሁሉ ተረከልን (ዮሐ.1፥18)፡፡ የተረከልን ብቻ አይደለም፥ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በልጁ የምናምን ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ልጆቹ ሆነን ከባሕርይ ልጁ ጋር የጸጋ ልጆች ሆነን ፤ ወራሽና የክብሩ ተካፋዮች ሆንን፡፡
    አስተውሉ! ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል ይመላለስ በነበረበት ዘመኑ “አባቴ አባቴ” እያለ ደጋግሞ በመጥራት፥ የፍቅር አባትና ከፍጥረቱ ያልራቀ የቅርብ አምላክ እንደሆነ ነገረን (ፊል.4፥5)፡፡ በእርግጥም አብ ከምንሰማው ጆሮዓችን ፤ ከራሳችንም ይልቅ ለእኛ ቅርብ ነው፡፡ እንዲያውም በሚበዛ ክብርና ልዕልና እንከብርና እንሾም ዘንድ ጌታና አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በጸጋ ልጆቹና ወንድሞቹ በእኛ መካከል በኵር ይሆንልን ዘንድ (ሮሜ.8፥29) እኛ “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበልን” (ሮሜ.8፥15)፡፡
    ስለዚህም እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ በመሆኑ ፣ መልካሙን ሁሉን በመስጠቱ ለሁሉ ፍጥረት ቸር አባት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በልጁ ማለትም በሞቱና በትንሣኤው ለሚያምኑ ብቻ የሚሆን አባትነት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በእርሱ ያላመኑትንና እጅግ ይቃወሙት ለነበሩት አይሁድ በግልጥ ቃል እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፡፡ እርሱ … ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና ” (ዮሐ.8፥44) አላቸው፡፡
     እግዚአብሔርን የሚሰማ ፣ ፈቃዱን የሚፈጽምና የሚታዘዝ ለእርሱ ብቻ እግዚአብሔር አባት ነው፡፡ አይሁድ በግልጥ ጌታን ሊገድሉ ይሹ ነበርና፥ “እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ” እንዳለው ሃሳባቸው መግደል ስለሆነ እግዚአብሔር አባታቸው ሊሆን አይችልም ፤ በዚህም ጌታ ኢየሱስ “እግዚአብሔር የሁሉ አባት” እንዳልሆነ በግልጥ ተናገረ፡፡ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ጨብጠን ወደርዕሳችን ስንመጣ ስህተቱ ጐልቶ ይታየናል፡፡ “27 አባቴ” ማለት ምን ማለት ነው? ምናልባት አንዳንድ የዋሐን ሰዎች 27 የሚለው “መድኃኒዓለም” ለማለት ነውና ምን “ማካበድ” ያስፈልጋል? ሊሉ ይችላሉ፡፡ አዎ! በቃሉ ላይ ለሚጨምሩና ከቃሉ ለሚያጐድሉ ምንም ላይመስልና ተራ ነገር ሊመስል ይችላል፡፡ ቃሉ ግን በግልጥ፦ “እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል” (ዘዳግ.12፥32) ፤ “እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር” (ምሳ.30፥6) እንዲል በቃሉ አንዳች መጨመር ወይም መቀነስ አይገባንም፡፡
    በተለይ እኒህ አዳዲስ የክህደት ጽሁፎች ብዙውን ጊዜ የሚተዋወቁት በመጓጓዣዎች (ታክሲና የተለያዩ የመጓዣዣ ቁሶች) ላይ በመለጠፍ ነው፡፡ “እግዚአብሔር አብ አባቴ” ወይም “እግዚአብሔር አባቴ” ማለት ሲገባ፥ “27” የሚለው በቦታው ለምን ይሆን የተተካው? ቀንን ለማምለክ ታስቦ ይሆንን? ከ“27” ውጪ እግዚአብሔር ፤ አባት ላይባል ነውን? እንግዲህ ሁሉን በቃሉ ልበ ሰፊነት በቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ሆነን መመዘን ተገቢ ነው፡፡
    ከጸሐይ መውጫ እስከመግቢያ ያለው አሥራ ሁለት ሰዓትም ሆነ ሌሊቱም ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጡራን ናቸው (ዘፍ.1፥5)፡፡ ቀንን ጨምሮ በጸሐይ ዙርያ ያሉ ፍጡራን ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር በድምጽ አልባ ንግግር ያወራሉ ፤ መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ” (መዝ.19፥1-4)፡፡
    ከዚህ የተነሳ እግዚአብሔር የእስራኤል ልጆች የሰማይንም ሆነ የምድርን የትኞቹንም አካላት እንዳያመለኩ አስጠነቀቀ፡፡ በተለይም ከርዕሳችን ጋር የሚሄደውን ክፍል ብናነሳ፥ “ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ፥ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ” (ዘዳግ.4፥19)፡፡
     ጸሐይ ፣ ጨረቃና ከዋክብት ለስፍረ ዘመናት ጥንትና ለቀንና ሌሊት መክፈያ መፈጠራቸውን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባንም(ዘፍ.1፥14)፡፡ ቀንን ማምለክ እኒህን ከማምለክ እኩል ነው፡፡ ስለዚህ አያድኑንምና ፈጽሞ ልናመልካቸው አይገባንም (ኢሳ.47፥13 ፤ ኤር.10፥1-3)፡፡ እንኪያስ አባታችን ቀን ወይም 27 አይደለም ፤ አባታችን በእንዲሁ ፍቅር የወደደንና ያፈቀረን ፤ አንድ አባት ሆኖ ልጆቼ ያለን ቅዱስ እግዚአብሔር ብቻ ነው! ከዚህ ውጪ ሌላ አባት የለንም፡፡ ቀንን ከሚያመልክ ፤ ፍጡርን በማየት ተስፋ ከሚያደርግ ከንቱነት ራቁ፡፡ መጽሐፍ፥ “ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” (1ዮሐ.5፥21) እንዲል፡፡
     ቅዱስ አብ አባታችን ሆይ! አባታችን ነህና በደስታ እንገዛለን ፤ እናመክልሃለን፡፡  አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ፡፡ አሜን፡፡


    [1] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ (ገጽ.194)
    [2]  ኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ 2002 ፤ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ (ገጽ.152)
     [3]  ደስታ ተክለ ወልድ ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ 1962 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡

2 comments:

  1. Eski YesafKewen Bedenb Anbebew, Bewenet Leka YEgeziabher Menfes karedan leka Tenshwan neger Enkwan Meredat Anchelem Wendeme b27 "Medanyalem" beye Sakeber kenu menu new yemakebrew? Yekenat balebet Geta engi yememesegenew ....geta bemasetewal Endetemelales Geta yerdah.

    ReplyDelete