Tuesday, 22 November 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ስምንት)

ታዲያ ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ምንድር ነው?
   የብሔርተኝነትን ትርጉም ይዘን ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነትን ስንተረጉመው፥ “ለአንድ ተመሳሳይ ወይም በአንድ ውስን ሥፍራ ወይም በአንድ መልክአ ምድራዊ  ክልል ውስጥ ለሚኖሩ፥ በሃይማኖታዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፥ በአንድ ቋንቋ መጠቀም[በሃይማኖት ጥላ መሰባበሰብ]፥ በጋራ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የወል ሥነ ልቦናዊ ገጽታዎችና በሃይማኖታዊ አመለካከቶች መያያዝን ያመለክታል ... ”  ብለን በአጭሩ መተርጐም ይቻለናል፡፡
    ምናልባትም ለሃይማኖታዊ “ብሔርተኝነት” ከዚህ የተሻለ ትርጉምን ልናመጣለትም አንችልም፡፡ [1] እንግዲህ የብሔርተኝነትን ትርጉም አንስተን ከሃይማኖት ጋር ለማሻረክ መሞከር፥ በራሱ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገሮችን እንድንፎርሽ ያደርገናል፡፡ በክርስቶስ የተመሠረተው ክርስትናችን ለጠቅላላው ዓለም[ሰው] መፍትሔ እንጂ “በሃይማኖት ወገንተኝነት” ላይ በማነጣጠር ወይም እንዲህ ባለው ነገር ላይ መሠረት በመጣል ፈጽሞ አይደለም፡፡
ስለዚህም፦
ü ክርስቶስ ቤዛነቱ ለሁሉም ዘር፤ ለሰው ፍጥረት ሁሉ ነው፡፡ ዓለም ኹሉ የወደቀው በቀደመው አዳም በደል ነው፤ እንዲሁ ደግሞ፥ “እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው ሳይሆን፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ቢሞቱም፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዝቶ” (ሮሜ.5፥15) ሁሉ በማመን ወደእርሱ ይለስ ዘንድ ነው፡፡
    ይህ እውነታ በምንም በምን አምኖ ከመቀበልና ከመገዛትም ውጪ ሊሸራረፍ አይችልም፡፡ መዳናችን እንኳ በእርሱ ምርጫና ውሳኔ ከሆነ፥ በእርሱ መሰባሰባችንም ለትምክህትና ሌላውን ለመናቅ ፈጽሞ ሊሆን አይገባውም፡፡ እንዲያውም የተቀበልነውን መዳናችንን ላልዳኑትና የጌታን ወንጌል ላልሰሙት እግራችንን በማስቸኰል ልንጓዝና የጸጋውን ወንጌል ልናበስራቸው ይገባናል፡፡ “ሃይማኖታዊ” ስያሜ ሰጥቶ በራስ ዙርያ መሰባሰብ ግን አደገኛ ጠባይ ነው፡፡ በነጻ ከተቀበልነውና ከተሰጠን መዳንም ጋር ተቃራኒ ባሕርይ ነው፡፡
ü ቤተ ክርስቲያንም ጥሪና ተልዕኰም ያላመኑትን፥ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” (ማቴ.28፥19) የሚል ፍጹምና ቅዱስ ጥሪን ማስተጋባት ወይም በፉጨት መጥራት ሲሆን ደግሞ ያመኑትን ማጽናትና ማጽናናት ነው፡፡
    በዚህ ሃሳብ ላይ ቆመን ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት የሚለውን ሃሳብ ብንመረምረው መንፈሳዊ ለዛ ላይኖረው እንደሚችል መገመት አያዳግተንም፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ አዲሷን ሕብረት ቤተ ክርስቲያንን ሲመሠርት በአንድ ሕዝብና ማህበረሰብ የነበረውን ኪዳን ሁሉ እንዲሳተፍበት አደረገው፡፡ ይህም የነበረውን ብሉያዊ ባህልና አስተምኅሮን ሙሉ ለሙሉ ለውጦት አይሁድነትን ከሳምራዊነት፤ ሕዝብን ከአሕዛብ ጋር አንድ አድርጐታል፡፡ እንኪያስ “የራስን አከባቢ፣ አገር ከተማ ... [ማኅበረሰብ] ማዕከል ማድረግ አለብን” የሚለውን አስተምኅሮ ከወዴት አገኘነው? ብልን እንድንሞግት ያስገድደናል፡፡ ምክንያቱም በግልጥ ቃል ብሔርተኝነት በማናቸውም አገላለጥ ውስጥ የመደብ አድልዎ፤ ሌላውን የማግለል ገሃድ ፉረሻ አለበትና፡፡
     ስለዚህም፦
1.     ምላካዊ መፍትሔ ማበጀት ይገባናል፦ ዛሬ ለሚነሱ ችግሮቻችን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሞት ከሁለት ሺህ አመት በፊት መለኮታዊ መፍትሔው ቀድሞ ተገኝቶለታል፡፡ ይህም ማለት ከችግራችን ፍጹም መፍትሔው ይቀድማል ማለት ነው፡፡ ችግሮቻንን አለማስተዋላችን ግን መፍትሔውን እንዳናስተውል አድርጎናል፡፡ የአምላካዊ መፍትሔ ምንጩ እግዚአብሔርን የሚፈራ ልብና በጸሎት ሕይወት ከተጋ ማንነት የሚፈልቅ ነው፡፡
    እውነት ለመናገር እኛም ጭምር የችግሩ አመንጪ አካላት ሆነናልና ንስሐ በመግባት መንገዳችንን ልናስተካክል ፤ ደሙን ከማክፋፋት አጅግ አስነዋሪ ኃጢአት ልንመለስ ይገባናል፡፡ በተለይም በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያለን “አገልጋዮችና መምህራን” በጉን የቀደመ የእረኝነት ተግባራችንን በሚገባ መወጣት ይገባናል፡፡ ምድራውያን መሪዎች ከሚሰጡት መፍትሔና ፖለቲካዊ ቅመራ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን በስብከት ብቻ ሳይሆን በሕይወት በመተርጎም ልታሳይ ይገባታል፡፡ እርሷም እንዲህ ካለ ነውር መራቅና መጠበቅ አለባት፡፡
     በአንድ ወቅት ሁለት የሃይማኖት አባቶች ተካሰው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ፥ ዳኛው እጅግ በማዘን “እኛ እናንተ ዘንድ  መፍትሔ ፍለጋ መምጣት ሲገባ፥ እናንተ ለክስ ወደእኛ!?” ብሎ በሃዘን እንደተናገረው፥ ዛሬ፤ ዛሬ እንዲህ ያለው ነገር በመካከላችን እጅግ ከመብዛቱም በላይ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ምናልባት እንዲህ ባለ ክፋት የሌሉትን አብያተ ክርስቲያናት ማግኘት እጅግ ሊጨንቅ ይችላል፡፡ የራሳችንን ነውር ሳንከድን የሌላውን መክደን አይቻለንም፡፡
     አምላካዊ መፍትሔን ማመልከት የሚቻለን እና በመጀመርያ በአምላካዊ ፈቃድና ምሪት መመላለስ ስንችል ብቻ ነው፡፡ ያለእርሱ ምሪት ፈቃድ የእርሱን ሥራና መንገድ ማመልከት አይቻልም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የሁላችንን ሰውነትና የእግዚአብሔር እኩል ፍጡራን መሆናችንን ያለጥርጥር በትክክል መቀበል መቻል አለብን፡፡ የእግዚአብሔር መልክና አምሳል በሁሉም ፍጥረት ላይ አለ፡፡ የሰውን ሰውነት መካድ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩንና ወደዚህ ምድር መምጣቱን መቃወም ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከሚገዛት ገዢ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በግልጥ ጠብ ውስጥ ለመግባት ካልፈለገች በቀር፥ ይህንን እውነት ከቃል በዘለለ በተግባር ልታሳይ፤ ያለምንም ማቅማማትም “የሰው ልጅን እኩልነትና ጸረ ዘራዊና ብሔር ነክ” አቋሟን “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”(ገላ.3፥29) በማለት ለዓለም ሁሉ ልትመሰክርና ልታውጅ ይገባታል፡፡
ጌታ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል....




  [1] ምናልባት ማኅበረ ቅዱሳን አባ ሰላማንና ተሰዓቱ ቅዱሳንን በመጠቀም  ለአገልግሎት የተሾሙት፣ ሥርዐተ ምንኩስናን ያስፋፉት፤ ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ያስተማሩት፣ ገዳማትን በየቦታው ያቋቋሙትና ያልተተረጎሙትን መጻሕፍት ወደ ግእዝ  ቋንቋ የተረጎሙት በሃይማኖት “ብሔርተኝነት”  ነው በማለት ሃሳቡን ያብራራል፡፡ ነገር ግን ይህን ሃሳብ ለመናገር “ብሔርተኝነት” የሚለውን ኢ- ክርስቲያናዊ ቃልን መጠቀም አስፈላጊ አልነበረም፡፡

No comments:

Post a Comment