Thursday 8 December 2016

ጸሎትና ጾም ለኢትዮጲያ



  ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስለረሃብ እንዲህ “ተቀኝቶ” ነበር፥
… ለኔ ብጤማ ትርጉሙ
የሁለት ድምጽ ነው፥ ʻራብʼ የሚሉት ከነስሙ
እንጂ የኔ ብጤውማ
የት አውቆት ጠባዩንማ፥
ብቻ ሲነገር ይሰማል
ይህንን ሁለት ፊደል ቃል፥ …
ቃሉማ ያው በዘልማድ፥ ይነገራል ይለፈፋል
ይተረካል ይዘከራል
ይደጋገማል ይተቻል
እንጂ እንኳን ጠባዩንና፥ የራብ እድሜውን የት ያውቃል? …
እና እምታውቁት ንገሩን፥ እውነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል? …
በጣር አፋፍ ላይ ያለህ ሰው፥ ራብ እንዴት ነው የሚያዛልቅ
ለስንት ቀን ቀን ይሰጣል፥ አንደበትክን ሳይሸመቅቅ
ሸረሪት በልሳንህ ላይ፥ የድር ትብትቡን ሳይሠራ
ቁራና ቀበሮ በቀን፥ ከቀየህ ድባብ ሳይደራ
ጥንብ አንሳ ሊጭር ሳይመጣ፥ ቅንቡርስ ከጐጆህ ጣራ
እንደፍካሬ ኢየሱስ ቃል፥ በጣር ምፅአትን ሳይጠራ …

አስከሬን ከየጥሻው፥ ተርፎ እንደሁ ሳይቀረቀር
ስንት ደቂቅ ስንት ፋታ፥ ቀጠሮው ስንት ትንፋሽ ነበር
ቆሽት አርሮ ሳይፈረፈር
ትናጋህ በድርቀት ንዳድ፥ ጉሮሮህ ሳይሰነጠር? … [1]
     በግማሽ ክፍለ ዘመን ያልታየ ረሃብ በ2008 ዓ.ም በአገራችን ተከስቷል፡፡ ከሕጻን እስከአረጋዊ ረግፈዋል፥ የምድሪቱ ጉስቁልና ራሱን ሳይሸሽግ አፍጥጦ ታይቷል፡፡ ሞትና ረሃብ የብዙ ወገናችንን ቤትና ደጅ በኃይል ሰብሮ ገብቷል፡፡ ከዚያኛው ዓመት ራብና ቸነፈር ሳናገግም፥ ዳግም ሌላ ራብና ቸነፈር በምድራችን ኢትዮጲያ ተደግኗል፡፡
     መጽሐፍ ቅዱስ፥ “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም፤” (መዝ.37፥25) እንዲል፥ እግዚአብሔር የሚወዱት ልጆቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም፤ እንጀራንም በመስጠት እንደሚመግባቸው፤ ደግፎም እንደሚይዛቸው ቃል የገባበትና ተስፋን የሰጠበት የመዝሙረኛው ክፍል ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑትንና የሚታዘዙትን ጻድቃን፥ ራብና ቸነፈር እንዲነካቸው አይተዋቸውም፡፡ በእርግጥም ተስፋው የጸና ነው፤ (ዘፍ.17፥7 ፤ 28፥15)፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ራብና ቸነፈር ያለመታዘዝ ውጤት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይናገራል፥ ለዚህም ሦስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ማንሳት እንችላለን፤
1.     ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል፡፡ በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ፡፡ እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል፡፡ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል፡፡ አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ፤” (ዘዳግ.28፥15-19)
     እግዚአብሔርን በሕጉ በፍጹም ፈቃደኝነት መታዘዝን ለሚታዘዙ ልጆቹ በረከትና እረፍት አለው፤ በመታዘዛቸውም ምክንያት “ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል”፡፡ መታዘዝ፥ በማናቸውም ነገር እግዚአብሔርን እሺ ብሎ ለፈቃዱ መገዛት ነው፤ ለማይታዘዙት ደግሞ በአለመታዘዝ ምክንያት የሚያገኛቸው ነገር ከባድና እጅግ አስፈሪ ነው፤ እግዚአብሔርን በመታዘዝ በረከቱ አገር ዓቀፍና ሁሉን የሚጎበኝ እንደሆነው ሁሉ ባለመታዘዝ ምክንያት የሚመጣውም መርገምም ከተማውን፣ እርሻውን፣ እንቅብና ቡሃቃውን፣ የማኅጸንና የምድር ፍሬ(አዝመራን ሁሉ) ከእርግማን በታች እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡
    እንዲያውም በመግባትና በመውጣት ሁሉ ርጉም ሊሆኑ እንዳለ በግልጥ አስቀምጧል፤ መውጣትና መግባት የየዕለት ተግባራችንን ሁኔታ መግለጫ ቃላት ናቸው፤ (2ዜና.16፥1)፡፡ እግዚአብሔር የሕይወት አረማመዳችንን ልብና ኩላሊትን በሚመረምር ባሕርይው ይመረምራል፤ ይህም ግለሰብን እንደግለሰብ አገርን እንደአገር ይመለከታል ማለት ነው፤ በመግባት መውጣታችን ስንቶች እንሆን ከእግዚአብሔር ጋር መንገዳችን የቀናው? አገራችን እንደአገር በእግዚአብሔር ፊት መንገዷ የቀና ነውን?
    መርገሙ በግልጥ እንደተቀመጠው ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፥ ምድሪቱንም ጭምር ሊመለከት እንደሚችል አመልካች ነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ውስጥ ብትሆን እንኳ፥ “ለሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል”(ቁ.20) እንደተባለው፥ ከመደናገርና ከተግሳጽ ባሻገር፥ እያደር መፈራረስ እንደማይቀርላትም ይናገራል፡፡ በሕዝቡም መካከል ሊመጣ ስላለው ነገር ሲናገር፥ “እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል፤”(ቁ.22) በዚህም እህሉ እንኳ በአረማሞና በዋግ በመመታቱ ምክንያት ፍሬ ቢስና የተገባውን ያህል የማያፈራ መሆኑን ይገልጣል፡፡ እንግዲህ የራብ መነሻ ምንጩ ከዚህ ሥፍራ ነው፡፡ ለምን ይሆን በመደጋገም በራብ ጠኔ የምንመታው?
   የእህል ጉልበት የሚሰበርብንና ሃይል አልባ የሚሆንብን ያለምንም መሸፋፈኛ ቃል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ባለመታዘዛችን ምክንያት፥ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት በአገራችን ከ9.8 ሚሊየን ሕዝብ በላይ እየተረዳ ነው፤ በአገሪቱ የአርብቶ አደር ክልሎች በአብዛኛው እጅግ አስከፊ ገጽታ እየተስተዋለ ነው፤ ምናልባትም የራቡ አደጋ ከዚህም በላይ ሊከፋ እንደሚችል ብዙ ማሳያዎች እየተከሰቱ ነው፤ ዛሬም ግን የንስሐ ፍሬ ለሚያፈራ መታዘዝ ከመታዘዝ የዘገየን፣ በቂምና በበቀል ታጅለን የተቀመጥን፣ በዘር በድንበርና በወንዝ ተካልለን ለመተያየትና ለመቀባበል የተጠያየፍን፣ ሕዝቡ በመንግሥት፤ መንግሥት ደግሞ በሕዝብ እየተመካከኘ ከይቅርታና ከብሔራዊ እርቅ ተገልሎ መቀመጥን መርጠናል፡፡
     የኢትዮጲያ በረከት መመለሻ መንገዱ የኢኮኖሚው መመንደግ አይደለም፤ እርሱ በራሱ ጊዜና በፈቃዱ የሚሆን ነው፡፡ የሚቀድመውና መርገማችንን የሚያስወግደው ብሔራዊ እርቅና ንስሐ ነው፤ በሕዝቦች መካከል መሳቂያ፣ መሳለቂያ፣ መዘባበቻ፣ መተያያ፣ መጠቋቆሚያና ከበዓለም መዝገበ ቃላት ከራብ ምሳሌነት ዛሬም ድረስ ያልተፋቅነው በመካከላችን ካለው ነውርና በዚህም ምክንያት ንስሐ ካለመግባታችን የተነሳ ብቻ ነው እንጂ፥ ተግተን ስላልሠራን ብቻ አይደለም፡፡
   ከንስሐና ከይቅርታ ስለዘገየን፥ በረከትና መትረፍረፍን አጥተናል፤ በምትኩ መርገም፣ አለመቻቻል፣ አለመቀባበል፣ አለመከባበር፣ በአንድ ቋንቋ እያወራን አለመግባባት… ከብቦናል፤ ምናልባትም ባለቅኔው እንዳለው፥ አንደበታችን ሳይሸመቅቅ፣ ሸረሪት በልሳናችን የድር ትብትቡን ሳይሠራ፣ ቁራና ቀበሮ በእኩለ ቀን በቀያችን ድባብ ሳይደራ፣ ጥንብ አንሳ ሊጭር፥ ቅንቡርስ ከጐጆዋችን ጣራ በጣር ምፅአትን ሳይጣራ … አስከሬን ከየጥሻው፥ ተርፎ እንደሁ ሳይቀረቀር፥ ቆሽት አርሮ ሳይፈረፈር፣ ትናጋችን በድርቀት ንዳድ፥ ጉሮሮአችን ደግሞ ሳይሰነጠር … በልቅሶና በዋይታ ንስሐና ብሔራዊ እርቅ ያስፈልገናል፤ አልያ ግን ምናልባት፥ “የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ፤” (መዝ.106፥15) እንደተባለው ምድራዊው ነገር ተትረፍርፎልን፥ በነፍሳችን ግን ክሳት እንዳይላክብን አሁን በደጅ ያለውን የጌታ ምሕረት መለማመን ይገባናል፡፡ ኢትዮጲያ ሆይ! እጆችሽን ወደእግዚአብሔር ዘርጊ!
አቤቱ ጌታችን ሆይ ማስተዋልን አብዛልን!
ይቀጥላል …




     [1]  ጸጋዬ ገብረ መድኅን(ሎሬት)፤ እሳት ወይ አበባ ፤ 1986 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.84-85

No comments:

Post a Comment