Wednesday 3 June 2020

ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ፣ ከኮሮና በፊት አልነበረምን?

Please read in PDF
    የትኛውንም የሕፃናት ሰቆቃ መስማት ያማል፤ ያስደንግጣል፤ ልብ ይሰብራል። በተለይም የቀኖቹ ክፋትና ዓመጽ፣ የምድሪቱን እርጅናና መወየብ አጉልቶ ከማሳየቱ ባሻገር፣ ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጭካኔና መራርነት እጅጉን አስፈሪ ኾኖአል። ግን እንዴት ችለን ይኾን የወለድናቸውን ሕፃናት፣ ቅርጥፍ አድርገን ስንበላ የጣፈጠን? እንዴት ቻለ አንጀታችን? የሰቈቃውን ስቃይ እየሰማን እንዴት አስቻለን? አውሬʼኮ የገዛ አውሬውን ስቃይ ይሰማል፤ ይራራልም፤ እንዴት እንዲህ ደበስን?!


   ከኮቪድ በኋላ፣ በዚህ ኹለት ወር ውስጥ፣ ከሦስት ሆስፒታሎች ብቻ የተገኘው መረጃ፣ 101 ሕጻናት በጥቅሉ መደፈራቸውን፣ 57 ወንዶች ደግሞ በሰዶማዊ ተግባር መደፈራቸውን ያሳያሉ ተብሏል፣ የአዲስ አበባ ሕጻናትና ሴቶች ቢሮ ኀላፊ፤ በዋልታ ቲቪ ቀርበው ሲናገሩ[https://www.youtube.com/watch?v=o9qmnHNDzzo]። ከሦስት ሆስፒታል ብቻ ይህን ያህል ርኩሰት ከተገኘ፣ ሌላውን ማስላት ምንም አይከብድም፤ በእውነት ያለነው፣ አስፈሪ ነገር ውስጥ ነው!!!

   በፕሮግራሙ ላይ የቀረቡት ሴቶች፣ ኹሉንም ነገር ወደ ሕግ አሰፈጻሚ አካላት አብዝተው መግፋታቸው፣ አግባብ አይመስለኝም። እኛም ያልሠራናቸው አያሌ የቤት ሥራዎች እንዳሉብን የዘነጉት ይመስለኛል። በተለይ ከኮሮና በፊት ያልሠራናቸው ወይም ለመንካት እንኳ የተጠየፍናቸው ተግባራት የመኖራቸው ውጤት እንደ ኾነ እንኳ እንዴት ሊያነሱ አልወደዱም?

  በአገራችን የወንዶችና የሴቶች ሕጻናት በግብረ ሰዶም መጠቃትና የሴት ሕጻናት መደፈር፣ የመበራከቱ መነሾ ምክንያት ኮቪድ 19 ኮሮና አይመስለኝም፤ እጅግ አባባሽ ጠንካራ ምክንያት ሊኾን ይችላል እንጂ። ነገር ግን ሚዲያዎች እንዲያ ሲዘግቡ መስማት፤ ባለሙያዎችም ኮሮናን በምክንያትነት ጠቅሰው መናገራቸው ትክክል ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል። ምክንያቱም፦

1.      ከዓመታት በፊት "በአገልጋዮች" ጭምር ይፈጸሙ ስለ ነበሩ የሰዶማዊነት ተግባራት፣ "የአገልጋዮች ገመና ለምን ተገለጠ?" በሚል የለበጣ ሙግት ከማቅረብ አልፈው፣ እጅግ ብዙዎች ሲራገሙ ነበር(ዙርያችን ያሉ አማኞችና አገልጋዮች ጭምር)፤ አንዳንዶች እንደውም የክርስትና ትምህርት ያልገባንና ፍቅር አልባ እንደ ኾንን በዘለፋ ቃል ሲናገሩ፣ ሲዝቱም ሰምተናል፣[ነውሩ እንዲህ አደባባይ ሲወጣ ምን ይሉ ይኾን?]
2.     ሰዶማውያን የፍርድ አመክሮ እንዲያገኙ ጭምር፣ በባለሥልጣናት ሴራ ሲጎነጎንና ረቂቅ ሲቀርብ በብዙዎች ዘንድ ረጅም ዝምታ እንጂ አይኾንም ያለ አካል አልሰማንም[ደግነቱ አልዘለቀም እንጂ]፣
3.     በሃይማኖት ካባ ተሸፍነው፣ ሰዶማውያን በሕፃናት ትምህርት ቤት ላይ አስነዋሪ ድርጊት ሲፈጽሙ ከአገር እንዲኮበልሉ፣ መዝገባቸው እንዲዘጋ፣ ከእስር እንዲወጡ ዋስትና ሲፈቀድላቸው አይተናል፣
4.     አኹን እንኳ በቅርቡ፣ ጋብቻን በተመለከተ፣ ከባልና ሚስት ውጭ በውክልና ጋብቻን የማፍረስ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል ደጉ የሰበር ችሎታችን ወስኖአል፤ እንግዲህ ይህንና ሌላውንም ጉዳይ፣ እንኳን ከክርስትና፤ ከነባሩ የማኅበረ ሰቡ “በሳል” ባህል ጋር በተቃራኒ ቆሞ እያየን፣ ድርጊቱ በዘመነ ኮሮና የጀመረ ይመስል ማቅረብ አመክንዮአዊነቱ አይታየኝም።

  የሕፃናቱ ጥቃት የነበረ፣ ዛሬ ያልጀመረ ነው፤ ያልዘራነው አልበቀለም፤ የበቀለው በገዛ እጃችን ተግተን የዘራነው ነው። ለክፋት ዕድል ሰጥተነው ነበር፤ ምቹ ጊዜ አገኘ፣ እናም በቫይረሱ ከሚማቅቀው ባሻገር፣ የሕፃናትንም ሰቈቃ በአንድነት እንሰማለን። በበሽታው ማመካኘት ተገቢ አይመስለኝም፤ አገርም እንደ አገር፤ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ቤተ ክርስቲያንነቷ ያልሠሯቸው አያሌ ተግባራት አሉ፤ የክፋት ዘር ዳግም እንዳያፈራ ከፈለግን፣ ምንጩን ማድረቅ እንጂ፣ የጐመራውን መከር አስፈሪነት መንሳቱ ብቻ በቂ አይመስለኝም።

   የፍትሕ አካላት ልልና ዝንጉ መኾናቸው፣ አንድ ምክንያት ነው፤ የኮሮና ጉዳይ አባባሽ ምክንያት ነው፤ የእኛ ኀጢአተኝነትን አለመጠየፍና ቅዱስ ኅብረትን አለመውደድ፣ በተገለጠ ነውር ለሚመላለሱ ደግሞ ሽፋን መስጠታችን፣ ዋናውና ቀዳሚው ምክንያት ነው። ዛሬም እንኳ ግብረ ሰዶማዊ አገልጋይ አጅበን የቆምን፣ አያሌ አማኝና አገልጋዮች አለን፤ ታዲያ የተዘራው ሲበቅል ምነው ደነገጥን? የኀጢአት ዘር በየትኛውም ዘመን፤ በየትኛውም ጊዜ ይበቅላል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ምሕረቱ እንዲበዛልን፤ በጐነቱ ከቊጣው እንዲሰውረን ንስሐ ብንገባ፣ ብንማልድ፣ ተግተን ብንጸልይ ይሻለናል፤ እንመለስ፣ ትዳራችንን የበደልን አገልጋዮች ትዳራችንን እንፈውስ፣ በርኩሰት የተያዝን ወጣቶች ከርኩሰታችን እንመለስ፤ ከልክ ባለፈ የምኞች ንሁለላ ውስጥ ያለን ጐልማሶች፣ ሰክነን እንመለስ፤ እናንባ፤ እንማልድ፤ ምናልባት የእስራኤል ቅዱስ፤ ታዳጊና መሐሪው ይቅር ይለን እንደኾን! አዎን! በዚህ በጐስቋላ ምድር ላይ የእግዚአብሔር ምሕረትና መጽናናት እንጂ፣ የቱም አያረካም፤ ምኑም አይጣፍጥም። ጌታ ሆይ፤ እባክህ እንደ በደላችን አይኹንብን! ማረን፤ እራራልን፤ አሜን።


1 comment: