Wednesday 17 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፯)

Please read in PDF
  6.      እግዚአብሔርን መምሰል፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፣ የእነርሱ መልክ ከበግ ጋር የተቀራረበ የተኩላ መልክ ነው፤ በበጎች መካከል ኾነው ይጸልያሉ፤ ይማራሉ፤ ያስተምራሉ፤ የበግ ጠባይ የያዙ መስለው ይመላለሳሉ። ዓላማቸው በጉን ለራሳቸው መንጠቅና በእረኛው እንዳያርፍ ማባዘንና ማቅበዝበዝ ነው።

  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ሰዎች የጽድቅ ሥራ በመሥራታቸው ወደ መንግሥቱ እንደሚገቡ እርግጠኞች የኾኑ ሲመስላቸው፣ ዐመጸኞችና የማይታዘዙ፤ ፈቃዱንም የማያውቁ መኾናቸውን በግልጥ ተናግሮአል፤ (ማቴ. 7፥21-23፤ ሉቃ. 13፥24)። እግዚአብሔርን ከምናውቅበትና እርሱን እንድንመስል ከተጠራንበት እውነት አንዱ፣ ፈቃዱንና ዐሳቡን ለባዊት በኾነች ነፍሳችን እናውቀው ዘንድ ነው፤ ከዚህ እጅግ በሚልቀው ደግሞ፣ ክርስቶስ በመስቀል ተላልፎ ነፍሱን የሰጠልንና የሞተልን፣ “እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር” ነው፤ (1ጢሞ. 2፥1)።

   የስህተት መምህራን ራሳቸውን እንጂ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲመስሉ ፈጽሞ አያስተምሩም፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።” በማለት መንፈሳዊ ልጁን የመከረው፤ (1ጢሞ. 6፥3-5)።

  7.     የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን፦ የስህተት መምህራን ከማይደፍሯቸው ርእሶች ሌላው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣንን ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ማለት፣ የራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ማለት ነው። ይህም ማለት ቅዱሳት መጻሕፍት የራሱ የእግዚአብሔር ቃሎች መኾናቸውንና ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ተናጋሪነት መሰጠታቸውን፤ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ መኾኑን ማመንና መቀበል ማለት ነው። በአጭር ቃል ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ወይም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ (2ጢሞ. 3፥15)።

   እያንዳንዱ የቅዱሳት መጻሕፍት ቃላት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተሰጡ ናቸውና፣ “መጽሐፉ ሊሻር አይቻልም” (ዮሐ. 10፥35)። በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ወይም እስትንፋስነት የተጻፈና የማይሻር ቃል ነውና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሌላ መጽሐፍ ወይም ሌላ ቃል ፈጽሞ የለም። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም የሕይወታችን፣ የትምህርታችን፣ የአምልኮአችን፣ የልምምዳችን፣ የኑሮአችን … ኹሉ ገዢና መሪ፤ በኹሉ ነገራችንም ላይ ሥልጣን አለው።

  ነገር ግን የስህተት መምህራን ከዚህ በተቃራኒ የሚቆሙ ናቸው፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱ ቢኾኑም እንኳ፣ ሥልጣኑን አያከብሩም ወይም ቃሉ እንደሚለው ብቻ አይታዘዙም፤ ይልቁን የራሳቸውን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል ሰዎች እንዲቀበሉላቸው ደጋግመው በመናገር ይታወቃሉ፤ ለእነርሱ ብቻ፣ የተለየ መገለጥና ስጦታ እንዳላቸውም ደጋግመው ሲናገሩ እንሰማለን፤ ነገር ግን ከመንፈሱ የተወለድንና የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያዎች የኾንን ኹላችን፣ መንፈስ ቅዱስ በቃሉ አማካይነት እንደሚያስተምረን እናምናለን፤ እንታመናለንም። ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና ሥልጣኑን በማክበርና በመቀበል ለሕይወት መታዘዝ ይብዛልን፤ አሜን።

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment