Saturday 26 September 2020

መስቀሉን የማያውቅ መስቀል

 Please read in PDF

መግቢያ

  በአገራችን በኢትዮጲያ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ከደመራ ጋር ተያይዞ የሚከበረው በዓል  ነው፤ በዓሉ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እንጨቱ መስቀል፣ ለዓመታት ከተቀበረበት ቦታ መውጣቱን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው። በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን፣ ይህ የመስቀል በዓል በአያሌ የአገራችን ሕዝብ ባህሎች ውስጥ የተለያየ መልክና ቅርጽ ይዞ ሲከበር እንመለከታለን። ሃይማኖታዊው ትውፊት መስቀሉ ከተቀበረበት መውጣቱን በማሰብ ሲያከብር፣ አያሌ ባህሎች ደግሞ ከዘመን መለወጫ ጋር በማያያዝ በዓሉን ያከብሩታል።

ሃይማኖታዊ መልክ ያለው የመስቀል በዓል አከባበር ግን ማዕከሉ እንጨቱ እንጂ የክርስቶስ ሕማም፣ ሞትና ትንሣኤ አይደለም። ይን ለማስተዋል በአከባቢያችን ያለውን የመስቀል ወይም የደመራ በዓል መመልከት ብቻውን በቂ ነው።

የመስቀሉ ትርጉም

    መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መስቀሉ ሲናገር በዋናነት እንጨቱን ማዕከል አያደርግም፤ የክርስቶስ የድኅነት ሥራ እንጂ፣ “ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ. 2፥16) ሲል፣ ጥል የተገደለበት መስቀል የክርስቶስ የጽድቅ ሥራና መሥዋዕታዊ ሞቱ እንጂ እንጨት የኾነው መስቀሉ አይደለም። ኹለቱን ወገኖች(አይሁድንና አሕዛብን) አንድ ያደረገው የእንጨቱ መስቀል አይደለም፤ በእንጨቱ መስቀል ላይ የሞተው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንጂ።

በክርስቶስ የመስቀል ሞት ሥራ ወይም ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ምክንያት፣ በሰው ልጆች መካከል የነበረው ኹለንተናዊ ልዩነት ተወግዶአል ወይም ተደምስሶአል፤ የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት በሰው ልጆች መካከል በኀጢአት ምክንያት የነበረውን ጠላትነት ኹሉ አፍርሶአል። ስለዚህ መስቀል ስንል፣ የክርስቶስ ሕማም፣ ሞት፣ መከራ፣ መሥዋዕታዊ መሰጠቱ እንዲሁም በሞቱ በሠራው ሥራ በትንሣኤው ያስገኘልንን ድል ኹሉ (ቈላ. 1፥19-20) የሚያካትት ታላቅ መለኮታዊ የማዳን ሥራ ነው።

   በሌላ የቅዱስ ጳውሎስ እይታ፣ መስቀሉ የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል የታየበት ድንቅ ሥራ መኾኑን እናስተውላለን፤ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።” (1ቆሮ. 1፥18) መስቀሉ ላላመኑበት አይሁድ ሞኝነት ነው፤ እንዲህ ባለ ታላቅ የሕይወት ውርደት መሲሑ ሰውን ያድናል ማለት ለአይሁድ እጅግ ሞኝነት ነውና፣ ለአሕዛብ ደግሞ ማሰናከያ ነው፣ ምክንያቱም እጅግ በምድር ላይ መልካም የኾነ ሰው እንዴት እንዲህ ያለ ታላቅ ውርደት ሊደርስበት ይችላል? የሚል ጽኑ ሙግት በማንሳት ይሰናከሉበታልና።

የመስቀሉ ሥራ ወይም ትርጉም ግን የእግዚአብሔር ኀይል የተገለጠበት ዕጹብ ድንቅ ሥራ ነው፤ እግዚአብሔር ልጁን የገለጠው በመስቀል መንገድ ነው ስንል፣ ማንም ይኾናል ብሎ በማይገምተው እጅግ ታላቅ በኾነ በውርደት መንገድ መግለጡን የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ የተዋረደው በመስቀል ላይ ሳይኾን፣ ከቅድስት ድንግል በተፀነሰ ጊዜ ነው፤ ምክንያቱም የተዋረደውንና የፍጡሩን ሥጋ በመልበስ ፈጽሞ ክብረትን አላገኘምና። ስለዚህም ስለ መስቀል ስናወራ ክርስቶስ ያለፈበትን እጅግ አስደናቂውን መንገድ ኹሉ ማለታችን እንጂ እንጨቱን እንዳልኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው።

መስቀል አልባው መስቀል

ደመራን ማዕከል አድርጎ በአገራችንና በብዙ የአገራችን ባህልና ሕዝብ መካከል የሚከበረው የመስቀል በዓል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወራው መስቀል የራቀ ብቻ ሳይኾን፣ ለእውነተኛው ክርስትና መስቀል ባዳና እንግዳ ነው። ጌታችን ኢየሱስ “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ. 10፥38) ብሎ ሲናገር፣ እያንዳንዱ ሰው የሚያልፍበት የመስቀል መንገድ እንዳለና እንደሚቀበል አመልካች እንጂ እያንዳንዱ ሰው የራሱን መስቀል ሠርቶ ይከተለኝ የሚል ትምህርት የለውም፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ስለ መስቀሉ ወይም ሕማምና ሞት ወይም መከራ እያወራ የነበረው ከመሰቀሉ በፊት ነውና።

ትምህርቱን ይሰሙ የነበሩት አይሁድ፣ መስቀል የሚለውን ቃል የተረዱት መከራ፤ ጸዋትዉ፣ ሕማም፣ ተጋድሎ በሚለው እንጂ የተመሳቀለ እንጨትን እንዳልኾነ ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አይስተውም። ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ማንም ስለ እንጨቱ መስቀል ማስተዋል አይችልምና። እንግዲህ ዛሬ ላይ የምናየው የመስቀል በዓል እውነተኛውን የመስቀል ትርጉም የማያውቅ ባዳና እንግዳ ነው። መስቀሉን ማስቀመጥና መቀበል ያለብን በመስቀሉ ትክክለኛ ትርጉም ውስጥ ኾነን እንጂ ከትርጉሙ ርቀንና ስተን አይደለም።

 ማጠቃለያ

   ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ልትረሳው የማይገባት እውነት፣ በመስቀሉ ክርስቶስ ስለ እርሷ ሲል የተቀበለውን መከራና ሕማም፤ የሠራላትን የጽድቅ ሥራ ነው፤ ይህን ዘወትር ልትዘነጋው አይገባትም፤ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ የምንናገረው ዋናው ርእሳችን ሞትና ሕማሙ ነው፤ እንጨቱ ሥራ ተሠራበት እንጂ በራሱ ሥራችን፣ ዋጋችን፣ ጽድቃችን፣ ቤዛችን፣ ኀይላችን፣ ትምክህታችን፣ ማስተስረያችን አይደለም፤ በአንድ ወቅት ሙሴ በዓላማ ላይ እባቡን በነሐስ ሰቅሎ እስራኤል ከተፈረደባቸው የእውነተኛው እባብ መርዝ ዳኑ፣ ነገር ግን እስራኤል ያንን የነሐስ እባብ ወደ መቅደሱ አስገብተው አመለኩት፣ አጠኑለት፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ ግን የቤተ መቅደሱን ተሐድሶ ሲያደርግ የነሐሱን እባብ፣ “ነሑሽታን” አለው፤ ነሐስ ብቻ! በማለት፤ ምክንያቱም ዋናውን ያሕዌ ይህ የነሐስ መስቀል ጋርዶት ነበርና፤ እንግዲህ የዛሬውም የደመራ በዓል እንደ ነሐሱ እባብ ተሰቅሎ ያዳነንን እውነተኛ አዳኝ ክርስቶስን ጋርዶአልና፣ እንጨቱን “ነሑሽታን” ወይም ሕዝቅያስ ነሐስ ብቻ እንዳለው “እንጨት ብቻ” ልንል በቅዱስ ቃሉ መሠረትነት እንደፍራለን፤ ምክንያቱም፣ ደግሜ እላለሁ፤ እንጨቱ ቤዛውን፣ አዳኙን፣ ቤዛችንን ጋርዶአልና፤ አማናዊውን መስቀል የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ትንሣኤ በማስተዋል ደግሞም እርሱን በእውነት በመከተል ሕይወትና ሰላም ይኹንልን፤ አሜን።

 


2 comments:

  1. እባክ መስቀሉን የሚያውቅ መስቀል ወይንም ሰዎቹ እንዴት እንደሚያከብሩ ብትነግረን ? ቤተክርስቲያኒቱ 360 ቀን እኮ የምታከብረው በአል አላት ለዛ ደሞ 8አመት ሙሉ በመቃወም አልጨረስከውም። እስኪ ደሞ ወንጌል ላይ ያለውን ክርስቶስን የሚያሳይ አከባበር ብታሳየን? ብሉግህ ላይ ያለው ስእል የቤተክርስቲያኒቱ ያሳሳል ዘዪ ነው ለምን ለጠፍክ መፃፍ ቅዱስ ስለሚደግፍህ ነው?

    ReplyDelete
  2. ጥሩ እይታ

    ReplyDelete